Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዶላር ያጣች አገር ከቅንጦት ትታቀብ  

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀና ማለት ተስኖታል፡፡ ያልተፈቱ በርካታ ችግሮች አሁንም አሉ፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ በሚፈልገው ደረጃና አቅሙ እየሠራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ሥር የሰደደውና የተወሳሰበው ቢሮክራሲ አሁንም አልከሰመም፡፡ ፖለቲካዊ ግጭቶችም ኢኮኖሚው ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ፣ ነገሩ በቶሎ መፈታት ይኖርበታል፡፡ ሕገወጥ ተግባራትን በቅጡ የመቆጣጠርና የሕግ የበላይነትን የማስፈን ተግባርም ለወቅቱ ወሳኝ ሥራ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ኢኮኖሚውን የሚያነቃቁ ምክንያቶች እየታዩ ነው፡፡ ለኢኮኖሚው ማነቆ ከተባሉ ጉልህ ችግሮች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲሆን፣ በተወሰነ ደረጃ ተስፋ የሚሰጡ ለውጦች እንዳሉ እየተነገረን ነው፡፡

ቀስ በቀስ እየመጣ ያለው ብድርና ዕርዳታ ለውጭ ምንዛሪ ገቢ ብሎም ለአገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት አበርክቶውና ጠቀሜታው ቀላል አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ ከመጡ ወዲህ በዕርዳታም ሆነ በብድር እንደተገኘ የተገለጸው ገንዘብ፣ የኢትዮጵያን የተራቆተ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በጥቂቱም ቢሆን እንደሚያሻሽለው አይጠረጠርም፡፡ ትልልቅ የውጭ ኩባንያዎች እዚህ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል መግባታቸውም ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም ያለውን ሥር የሰደደ የውጭ ምንዛሪ ችግር በተወሰነ ደረጃ እንደሚቀርፈው ይታመናል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሰማነው፣ መንግሥት ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከቀደመው ዓመት አኳያ ከ300 በመቶ በላይ ጨምሯል፡፡ ይህም የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ላይ እፎይታ ባይሰጥም ከሥጋት ቀለበት ሊያወጣ የሚያስችል ጊዜያዊ ለውጥ እንዳለ የሚጠቁም ነው፡፡

የዓለም ባንክ በዕርዳታና በብድር ያቀረበው ገንዘብ ሊሠራበት የታቀደውን ሥራ ወይም የታሰበለትን ዓላማ ከማሳካት በላይ ለውጭ ምንዛሪ ችግራችን ማቃለያ ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመታደግ የሚያግዙ ዕደሎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ዳያስፖራውም የማይናቅ የመፍትሔው አካል ነው፡፡

ዳያስፖራው በኢንቨስትመንትና በሌሎችም ዘርፎች አገሩ ላይ እንዲሠራ መኖሪያ ጎጆ እንዲቀልስ፣ ሌሎችም ሥራዎችን እንዲያስፋፋ የፋይናንስ አገልግሎት ተመቻችቶለት ወደ አገር ቤት የሚልከውን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ለማድረግ አንዳንድ ባንኮች የጀመሩት እንቅስቃሴም ቢሆን በአግባቡ ከተተገበረ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ አጋዥ አማራጮች ሰፊ ስለመሆናቸው ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ‹‹ደመወዛችሁን ስጡን አንላችሁም፡፡ ከማኪያቶ አንድ ዶላር ቀንሳችሁ እንድትሰጡን እንለምናችኋለን፤›› ሲሉ ሰምተናል፡፡ ይህ ንግግራቸው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ኤርትራውያኑ ዳያስፖራዎች የነበራቸውን አስተዋፅኦ ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ የኤርትራ መንግሥት ለሰብዓዊ ጉዳዮች እንዲያውለው ሳይሆን፣ ለጦር መሣሪያ ግዥ የሚያውለው 140 ሚሊዮን ዶላር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሚኖሩበት አገርና አካባቢ አሰባስበው ገቢ ማድረጋቸውን የውጭ ጸሐፍትና ጋዜጠኞች ዘክረውታል፡፡ ከተማሪ እስከ ጡረተኛ ሳይቀር ለአገሪቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከአንድ ወር ደመወዛቸው እስከ ምግብ ወጪያቸው በመቀነስ ያዋጡ፣ የምግብ ራሽናቸውን በመቀነስ፣ የቤት እንስሳት ምግብ እስከመመገብ የደረሱና ለምግብ የሚያወጡትን ወጪ ለአገራቸው ድጋፍ ይውል ዘንድ ያዋጡ ኤርትራውያን ገድላቸው ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን ከተረፋቸውና እንዳልባሌ ከሚያወጡት ነገር ላይ እዚህ ግባ የማይባል መዋጮ እንዲያደርጉ ተለምነዋል፡፡

ምንም እንኳ እንዲህ ያለው በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ድጋፍ መኖሩ ባይጠላም፣ ዘላቂነቱ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ የወጪ ንግዳችን ባለበት እየተረገጠ ስለሚገኝ፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝቱ የሚረዱ ሥራዎች መስፋፋት እንዳለባቸው ግልጽ ነው፡፡ ለማንኛውም ከጥቂት ወራት ወዲህ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ከፍ ሊያደርግ የሚችል፣ በተግባርም ለውጡን የሚያመላክቱ እውነታዎች ተስተውለዋል፡፡ እነዚህን አጠናክሮ ግለታቸውን ጨምሮ፣ ወኔያቸውን ቀስቅሶ የምንዛሪ ምንጩ እየጎለበተ እንዲሄድ ማድረጉ የመንግሥት የሰርክ ተግባር መሆን አለበት፡፡

የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን የሚመጥን አቅርቦት ባይኖርም፣ ጅምሩ ላይ ለውጥ እየታየ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በብዙ ድካምና ልመና ጭምር  የተገኘው የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አመዳደቡ ምን ይመስላል የሚለው ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

በእጅ ያለውንም ሆነ ነገ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን የውጭ ገንዘብ በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ካልተቻለ ትርፉ ኪሳራ ይሆናል፡፡ እስካሁን እንጓዝበት በነበረው የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥና ፈቃድ መሠረት መጓዝ እንደማያዋጣን መቼም ነጋሪ አያሻውም፡፡ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥና ፈቃድ ላይ ከዚህ ቀደም ይነሱ የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙ አሠራሩ ላይ ቆቅ መሆን ይጠበቅብናል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ በተለያየ አቅጣጫ እንዲመጣ መደረጉና ክምችቱ መጨመሩ ብቻ ግብ እንዳልሆነ በማወቅ፣ የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እስኪኖር ድረስ ቆንጠጥ ያለ መተግበሪያም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጉዳይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፣ የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ ነው፡፡ የዜጎች ቅንነትና አገር ወዳድነት ይጠይቃል፡፡ የአገርን ችግር ተገንዝቦ ቅድሚያ ለሚሰጠው ትብብር ማድረጉ፣ ለሚያስፈልገው ብቻ መረባረቡ የውዴታ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ እስኪያልፍ መልፋት የሁላችን ግብ መሆን ይኖርበታል፡፡  

መድኃኒት ጠፋ እየተባለ የቅንጦት ዕቃዎችን ለማምጣት የባንክ ቤት ደጃፍ የሚያጣብቡ ከተበራከቱ ነገሩ ሁሉ የእንቧይ ካብ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ዶላር የለም እየተባለ ለቢራ ፋብሪካዎች ግን የውጭ ምንዛሪው በገፍ ተሰጣቸው ታዝበናል፡፡ ስንዴ ለመግዛት የውጭ ምንዛሪ የለም እየተባለ ለቅንጡ ተሽከርካሪዎች፣ ለከረሜላና ማስቲካ የውጭ ምንዛሪ ሲፈቀድ ማየት ያማል፡፡

ስለዚህም ያገኘነውን የውጭ ምንዛሪ ለሚረባውም ለማይረባው ከማዋል ተቆጥበን ቅድሚያ ለሚሰጠው፣ ለአገር ፋይዳ ላለው፣ ሕዝብ ለሚፈልገው ተግባር በማዋል በአግባቡ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ ማድረግ ነው መንግሥትን መንግሥት የሚያሰኘው፡፡ በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙ የሚፈቀድላቸው ምርቶች እዚሁ በቀላሉ የሚገኙ ከሆነ ለእነዚህ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ የሚፈቀድበት ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ የውጭ ምንዛሪ አሰጣጡ ግልጽና ምክንያታዊነት የሰፈነበት እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት