Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራ ክልል በአንድ ቀን ብቻ 13 ሰዎች ሞቱ

በአማራ ክልል በአንድ ቀን ብቻ 13 ሰዎች ሞቱ

ቀን:

በአማራ ክልል በተለያዩ ከተሞች በአንድ ቀን ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች 13 ሰዎች ሲሞቱ፣ ዘጠኝ ያህሉ ደግሞ የተለያዩ የአካል ጉዳቶች እንደደረሰባቸው ታወቀ፡፡

በዋናነት በግለሰቦች መካከል ተነሳ በተባለ ግጭትና በቦምብ ፍንዳታ ምክንያት፣ የሰዎች ሕይወት ሲጠፋ የአካል መጉደል አጋጥሟል፡፡

ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በደባርቅ ወረዳ አደባባይ ጽዮን በተባለ የገጠር ቀበሌ በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ኤፍዋን ቦምብ ፈንድቶ አራት ግለሰቦች ወዲያውኑ ሲሞቱ፣ ሁለቱ ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በደባርቅ ከተማ ሆስፒታል ሕክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

‹‹ኤፍዋን ቦምቡ በግለሰብ መያዝ የሌለበትና ሕገወጥ ነው፤›› ሲሉ የወረዳው የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ እሸቱ ፀሐይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ግለሰቦቹ ለድግስ በተሰባሰቡበት ሥፍራ ይሠራል ወይስ አይሠራም በማለት ለማረጋገጥ ሙከራ ሲያደርጉ ቦምቡ እጃቸው ላይ ፈንድቶ፣ አራት ሰዎች መሞታቸውን አቶ እሸቱ አስታውቀዋል፡፡

ሌላው የሰው ሕይወት መጥፋት አደጋ ያጋጠመው በላሊበላ ከተማ ነው፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በግለሰቦች መካከል በተነሳ ግጭት፣ አንድ ግለሰብ ከፈተው በተባለ ተኩስ ዘጠኝ ግለሰቦች ወዲያው ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ግጭቱም በታሪካዊው ላሊበላ ከተማ ልዩ ስሙ ሮሃ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራ ሥፍራ በተጠቀሰው ቀን ከምሽቱ ሁለት ሰዓት መከሰቱ ታውቋል፡፡

በእነዚህና በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ከክልሉ ባለሥልጣናት ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

የቀድሞው የክልሉ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አሁን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የባህልና ቱሪዝም ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁንን፣ በተደጋጋሚ ለማግኘት የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡

በቅርቡ ተሰብስቦ በነበረው የክልሉ ምክር ቤት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር በስፋት መስተዋሉን፣ በዚህም ምክንያት በዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እክል መፍጠሩን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከዚህም ጋር በተያያዘ የክልሉን የፀጥታ ኃይሎች የማዘመንና የማሠልጠን ሥራ እየተከናወነ ነው ሲሉ አቶ ገዱ ተናግረው ነበር፡፡ ከፀጥታ ኃይሎች ሥልጠና ጋር በተያያዘም በክልል፣ በወረዳና በቀበሌዎች የተከፋፈለ ሥልጠና፣ ለታጠቁ የመንግሥት አመራሮች ጭምር እየተሰጠ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚህም በዋናነት በክልል ደረጃ በሦስት ክላስተሮች ተከፋፍሎ ለፀጥታ አካላት ሥልጠና መስጠቱን የሪፖርተር ምንጮች ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በወረዳ ደረጃ በ178 ወረዳዎች የሚገኙ ሚሊሻዎችና የታጠቁ አመራሮች ለማሠልጠን ታቅዶ የ129 ወረዳዎች መጠናቀቁን፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በዋናነት ሥልጠናው የሚሊሻዎችን አቅም ለመገንባትና የአቅም ግንባታውም በፖለቲካ ትምህርት ጭምር የታገዘ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ሥልጠናው በቀበሌ ደረጃም እንደሚቀጥል፣ በዋናነት የሥልጠናው ዓላማ የፀጥታ ኃይሉን የክልሉን ሰላም እንዲያስከብርና ሥርዓተ አልበኝነትን እንዲቀርፍ ነው ሲሉ ኃላፊው አክለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና በክልሉ በምዕራብ ጎንደር ዞን ግጭቶች እንደነበሩ፣ በዚህም ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱ ተሰምቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...