Friday, December 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የተሽመደመዱ ተቋማት በተመሰከረላቸው አመራሮች ነፍስ ይዘራባቸው!

ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ መንግሥታዊ ተቋማት በደመነፍስ የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በአዋጅ ተቋቁመው ሥልጣንና ኃላፊነታቸው በግልጽ ቢደነገግም፣ ብዙዎቹ በመፈክሮች ከማጌጥ ውጪ እዚህ ግባ የሚባል አፈጻጸም የላቸውም፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ መሥፈርት ብቻ ተሹመው የሚመሯቸው ግለሰቦችም በአንድ በኩል ከፍተኛ በሆነ የአቅም ማነስ፣ በሌላ በኩል የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ሲያባርሩ ስለሚውሉ ተቋማቱ ውርጭ እንደመታው የስንዴ ቡቃያ ጠውልገዋል፡፡ ሹመት፣ ዕድገት፣ ዝውውር፣ ስኮላርሺፕና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚገኙት በትውውቅና በኔትወርክ በመሆኑም፣ አንገታቸውን ደፍተው ሥራቸውን የሚያከናውኑ ንፁኃን እንደ አሮጌ ዕቃ ተጥለዋል፡፡ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎችም ጥለዋቸው ጠፍተዋል፡፡ የፓርቲ አባልነትና የቡድን መሳሳብ የበረታባቸው ብዙዎቹ ተቋማት በባለሙያዎች ድርቅ የተመቱ ስለሆኑ፣ እንኳን ለኃላፊነት ለምንም ነገር ብቁ ያልሆኑ ግለሰቦች መጫወቻ ሆነዋል፡፡ በዚህና በመሰል ምክንያቶች የተሽመደመዱ ተቋማት በብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች ተደራጅተው በፍጥነት ቅርፃቸውንና ይዘታቸውን ካልለወጡ፣ በነበሩበት መቀጠል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የተቋማቱን አጠቃላይ ገጽታ ለመቀየር ግን የተለመደው አካሄድ አያዋጣም፡፡ ‹ከሰው መርጦ ለሹመት ከእንጨት መርጦ ለታቦት› የሚባለው ዕድሜ ጠገብ አባባል በተግባር ይታይ፡፡ ለብቃት ልዩ ትኩረት ይሰጥ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ተቋማትን እንዲመሩ አዳዲስ ፊቶች እየታዩ ነው፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸው፣ በልምዳቸውና በምግባራቸው አንቱታ የተቸራቸው ሰዎች ወደ ኃላፊነት መምጣታቸው መልካም ጅምር ነው፡፡ ነገር ግን እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር ተደባልቆ መዘናጋት እንዳይፈጠር ደግሞ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ለዓመታት የተበላሹ ተቋማትን ለማፅዳት መሠረታዊ ለውጥ ሲደረግ፣ ለውጡ የተሻለ ነገር ማምጫ እንጂ በብልጦች እንዳይጠለፍ ማድረግ ይገባል፡፡ የዘመናት የአገር ችግርን ለማቃለል በሚደረገው ጥረት አሁንም ከብሔር፣ ከእምነትና ከፆታ በላይ ለብቃት ትልቅ ትኩረት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ተቋማት ትልቁ ችግር እጅና እግራቸውን ተይዘው መሥራት አለመቻላቸው ነው፡፡ ብቃት ያላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ሲገኙ ደግሞ፣ እንዴት ውጤታማ ሆነው መሥራት እንደሚችሉ መፍትሔ ይገኛል፡፡ የሕግ ማዕቀፎች፣ የሥራ አካባቢ ሁኔታ፣ የሰው ኃይል ሥምሪት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ትልቅ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ተቋማቱን በሥርዓት መምራትና ማዘመን የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡

የመንግሥታዊ ተቋማት ተጠናክሮ መውጣት አገርን በሥርዓት ለመምራት፣ የመንግሥት ሥልጣንን በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ለማከናወን፣ የሕግ የበላይነት ለማስፈን፣ የሕዝቡን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ለመፍጠር፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር፣ ሕገወጥነትን ለማስወገድ፣ ወዘተ ይጠቅማል፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተማምነው የአገር ግንባታው መቀጠል የሚችለው የተቋማት የተበላሸ ገጽታ ሲለወጥ ብቻ ነው፡፡ ገጽታቸውን ለመለወጥ ደግሞ በአመራርነት የሚመደቡ ግለሰቦች በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ የትምህርት ዝግጅቱና ልምዱ እንዳለ ሆኖ፣ በሥነ ምግባር ጥራታቸው ምርጥ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ከያሉበት ማፈላለግ ተገቢ ነው፡፡ ራሳቸውን ችለው የማይቆሙ፣ ብሔርን፣ ፆታን፣ እምነትን ወይም ሌላ መሥፈርትን ብቻ የሚታከኩ ተሿሚዎች ለአገር ያላቸው ፋይዳ እምብዛም ነው፡፡ ተሿሚዎች ከሌብነት የፀዱ፣ ካላስፈላጊ ድርጊቶች ራሳቸውን ያቀቡና በራሳቸው የሚተማመኑ ከሆኑ ተቋማቱም ያን መንፈስ ይላበሳሉ፡፡ በአስመሳዮችና በአድርባዮች የሚመሩ ተቋማት ግን ዘቅጠው ይቀራሉ፡፡

ለዓመታት የዴሞክራቲክ ተቋማት ተብለው የሚታወቁት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ ተቋምና ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተቋማት መካከል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየዓመቱ በሚያቀርባቸው ምሥጉን ሪፖርቶቹ ምክንያት በሕዝብ ዘንድ የተሻለ አመኔታ ያገኘ ሲሆን፣ የሌሎቹ ግን እንዲያው ተከድኖ ይብሰል ከማለት ውጪ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ በተለይ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተነፈገው የሕዝብ አመኔታና የሌሎቹ እንደሌሉ መቆጠር በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ የሕግና የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነት ተጥሶ የአስፈጻሚው መንግሥት ተላላኪ መሆኑ፣ በአገር ላይ ያደረሰው በደል ተዘርዝሮ አያልቅልም፡፡ ፍርድ ቤቶች ከክብራቸውና ከማዕረጋቸው መውረዳቸው፣ ማረሚያ ቤቶች የሥቃይ ማዕከል መደረጋቸው፣ ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ያልተገባ ድርጊት ውስጥ መገኘታቸው የሕዝብ ብሶት እንዲፈነዳ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሌሎች የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ደግሞ በቡድን የተደራጁ ሌቦችና ዘራፊዎች መጫወቻ መሆናቸው የሕዝብንም የአገርንም ጉዳት ያመላክታሉ፡፡ እነዚህን ለማፅዳት ነው ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው፡፡ ጠንካራና ብቁ አመራሮችም የሚያስፈልጉት፡፡

በፖለቲካው መስክ የደረሰውን ጥፋት በወፍ በረር ስንቃኝ የተቋማት ጎዶሎነት ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ትልቅ ጎዶሎ የሚታየው የመንግሥትና የፓርቲ መቀላቀል ነው፡፡ በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ለመለየት እስኪያስቸግር ድረስ በመቀላቀላቸው ግለሰቦች ከሕግ በላይ ሆነዋል፡፡ ሕግን የመሰለ የሰው ልጆች ከለላና አለኝታ የግለሰቦችና የቡድኖች ማጥቂያ መሣሪያ የተደረገው፣ ፓርቲና መንግሥት በመደበላለቃቸው ነው፡፡ ይህ መደበላለቅ ደግሞ እያንዳንዱ ተቋም ውስጥ ዘልቋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ገለልተኛ መሆን ይገባቸው የነበሩ የዴሞክራቲክ ተቋማትን፣ የፀጥታ መዋቅሮችን፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራትን፣ ወዘተ በማዳከም እንደ ግል ንብረት የተጠቀመባቸው ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ገንብቶ እንዳሻው ለመሆን ነበር፡፡ ይህም ለተወሰነ ጊዜ ተሳክቶ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምኅዳሩ ተባረዋል፡፡ መንግሥትና ፓርቲ ዳር ድንበራቸው እስከማይታወቅ ድረስ ተቋማት የካድሬ መጫወቻ ሆነዋል፡፡ ግለሰቦች ከሕግ በላይ እየሆኑ እንዳሻቸው በሥልጣን ባልገዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ተቀልብሶ ተቋማቱ ነፃ መውጣት አለባቸው፡፡ ነፃ የሚወጡት ደግሞ ጠንካራ ሰብዕና ባላቸው ብቁ አመራሮችና ባለሙያዎች እንደሆነ መታመን አለበት፡፡

ማንኛውም ሥርዓት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ሲንጠላጠል ተስፋ አይኖረውም፡፡ ሥርዓት አስተማማኝና ዘለቄታዊ መሆን የሚችለው ተቋማዊ ሲሆን ነው፡፡ ተቋማዊ መሆን ማለት በሕግ ብቻ የሚመራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያገለግሉ ተቋማትን ማደራጀት ነው፡፡ ተቋማቱ መደራጀት ያለባቸው አገራቸውን በሚወዱ አመራሮችና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን፣ በአገልጋይነት መንፈስ የተሰጣቸውን ሥራ በኃላፊነት በሚያከናውኑ ሠራተኞች ጭምር ነው፡፡ ተቋማቱ በዚህ መንገድ ሲደራጁ የመንግሥት ሥራ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት ይከናወናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን መብታቸውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ግዴታቸውንም ይረዳሉ፡፡ ሌብነትና አጭበርባሪነት አስነዋሪ ይሆናሉ፡፡ አገርን ለማገልገል ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ይሆናል፡፡ የብሔር፣ የእምነት፣ የፖለቲካ ወይም መሰል ልዩነቶች የቅራኔ ምንጭ አይሆኑም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዕውቀቱና በጉልበቱ አገሩን ለመገንባት ዝግጁ ይሆናል፡፡ ለዚህም ሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እርስ በርስ እየተናበቡና ቁጥጥር እያደረጉ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ተቋማት በጠንካራና በብቁ አመራሮች ሳይደራጁ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነጋገር አይቻልም፡፡ አገር ከምንም ነገር በላይ በመሆኗ ለተቋማት ግንባታ ትኩረት ይሰጥ፡፡ የተሽመደመዱ ተቋማት በተመሰከረላቸው አመራሮች ነፍስ ይዘራባቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...