Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በዝቅተኛው እርከን እስከ 30 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ የተደረገበት የኤሌክትሪክ  ኃይል አቅርቦት በመጪው ወር ተግባራዊ ሊደረግ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለመጪዎቹ አራት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚሆን የሚጠበቀው አዲሱ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የዋጋ ታሪፍ፣ በዝቅተኛው ደረጃ እስከ 30 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበት መዘጋጀቱ ታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የወርኃዊ ፍጆታቸው ከ50 ኪሎ ዋት (በሰዓት) ጀምሮ እስከ 500 ኪሎ ዋትና ከዚያ በላይ ኃይል በሚጠቀሙ ደንበኞች ላይ የታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት ዝቅተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ 50 ኪሎ ዋት በሰዓት ከታሪፍ ጭማሪው ነፃ ሲደረግ፣ ከ500 ኪሎ ዋት በሰዓት እስከ 500 ኪሎ ዋት በሰዓት፣ እንዲሁም ከ500 ኪሎ ዋት በሰዓትና ከዚያ በላይ በሚጠቀሙት ላይ የተደረገው ማስተካከያ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ይፋ ያደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ለአብነት ወርኃዊ ፍጆታቸው 100 ኪሎ ዋት በሰዓት የሆኑ ደንበኞች በነባሩ ታሪፍ መሠረት 35.64 ብር (ይህም ማለት በሰዓት ለአንድ ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ 0.3564 ብር) ሲከፈልበት የቆየው፣ በዚህ ዓመት በሚተገበረው ማሻሻያ መሠረት ወደ 45.91 ብር (100 ኪሎ ዋት በ0.4591 ብር በኪሎ ዋት በሰዓት ታሳቢነት) በማደጉ፣ የ10.27 ብር ወይም የ28.8 በመቶ ጭማሪ መደረጉን ይጠቁማል፡፡ ይህ ጭማሪ በመጪው ዓመት ወደ 57 በመቶ ያድግና በ2013 ዓ.ም. ወደ 46 በመቶ፣ እንዲሁም በ2014 ዓ.ም. መልሶ ወደ 54 በመቶ ከፍ እንደሚል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያስቀመጠው አዲስ ታሪፍ ያሳያል፡፡

በተመሳሳይ የወርኃዊ ፍጆታቸው 200 ኪሎ ዋት በሰዓት የሆኑ ደንበኞችም በአሁኑ ወቅት የሚከፍሉት የ99.93 ብር ሒሳብ የ56.28 ብር ጭማሪ ታክሎበት ወደ 156 ብር ከፍ ብሏል፡፡  በመሆኑም የ36 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህ ጭማሪ በ2012 ዓ.ም. ወደ 212.57 ብር ሲያድግ በነባሩ ታሪፍ ላይ የ112 ብር ጭማሪ ወይም የ53 በመቶ ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ወደ 325 ብር ከፍ ሲል በአሁኑ ወቅት እየተተገበረ ከሚገኘው ታሪፍ አኳያ የ225 ብር ጭማሪ አለው፡፡

እንዲህ ባለው አኳኋን ከ100 ኪሎ ዋት (በሰዓት) እስከ 500 ኪሎ ዋትና ከዚያ በላይ የአሌክትሪክ ኃይል የሚጠቀሙ ደንበኞች ላይ ወሳኝ ሊባል የሚችል ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ጭማሪ ጉዳይ የወቅቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላን ሪፖርተር ለማነጋገርና ምላሻቸውን ለማካተት ባይችልም፣ በቅርቡ ለሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች በሰጡት መግለጫ መሠረት በአገሪቱ እስካሁን እየተከፈለበት የቆየው ታሪፍ በዓለም ዝቅተኛውና የግል ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ያደረገ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ላለፉት 12 ዓመታት ምንም ማስተካከያ ሳይደረግበት የቆየ በመሆኑና በየጊዜው እያደገ ከመጣው የፍጆታ ጭማሪ፣ ብሎም ከጥራት አቅርቦት አኳያ ማስተካከያው ማስፈለጉን አስረድተው ነበር፡፡

ምንም እንኳ ኃላፊው ይህንን ይበሉ እንጂ በመላው አገሪቱ ካለው የአገልግሎት አቅርቦት ችግር ባሻገር፣ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎችም ከተሞች የሚታየው ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የረጅም ጊዜ የሕዝብ ብሶት ነው፡፡ የታሪፍ ማሻሻያ  ከተሰማበት ዕለት ጀምሮም በርካቶች ቅሬታቸውንና ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ የታሪፍ ማሻሻያ እንደሚደረግ፣ ሆኖም ጭማሪው የታችኛውን ተጠቃሚ እንደማይነካ ከኃላፊነታቸው ከመሰናበታቸው ቀደም ብለው ተናግረው ነበር፡፡ መንግሥት ለኃይል ማመንጫ የሚያወጣው ወጪ በሰዓት በኪሎ ዋት 0.9 የአሜሪካ ሳንቲም (አሁን ባለው የምንዛሪ ዋጋ ቢሰላ 25 ብር ገደማ) እንደነበረና በድጎማ ለሕዝቡ የሚያስከፍለው ግን 0.6 የአሜሪካ ሳንቲም እንደሆነ ማብራሪያ የሰጡት፣ ከአንድ ዓመት በፊት የዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት አካል በሆነውና ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተሊጀንስ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነበር፡፡ ይህንን የማምረቻ ወጪ ለማቻቻል የሚደረገው ጭማሪ ወደ 0.9 የአሜሪካ ሳንቲም ከፍ ሊል እንደሚችል በመግለጽ በሰጡት ማብራሪያ ለሪፖርተር ባረጋገጡት መሠረት፣ በተሠራው ዘገባ ላይ ተቃውሞ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ሪፖርተር ባቀረበው ዘገባ የ50 በመቶ ጭማሪ ሊደረግ እንደሚችል ያሳየ ቢሆንም የተባለው ‹‹ጭማሪ ስህተትና ያልተባለ ነው፤›› በማለት መቃወማቸው አይዘነጋም፡፡ ይሁንና በመጪው ወር ተግባራዊ የሚደረገው ጭማሪ ግን በዝቅተኛ ደረጃ የ30 በመቶ ጭማሪ ከፍ ሲልም እስከ 60 በመቶ የሚጠጋ የታሪፍ ጭማሪ፣ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ጭማሪው የዋጋ ንረት ብቻም ሳይሆን በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተጠቃሚዎችን ይጎዳል የሚል ቅሬታ በተደጋጋሚ ቢነሳም፣ ይህንኑ በመፍራት ይመስላል መንግሥት ፈራ ተባ ሲልበት የቆየውንና ጭማሪው ብዙም ተፅዕኖ አያመጣም በማለት ሲሟገት ቢቆይም የታሪፍ ማሻሻያው ከሰሞኑ በመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነት ፕሮጀክቶች ይፋ መደረግ ጋር እንዲገጣጠም ተደርጓል፡፡ በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የሚገነቡ 13 የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጀክቶች ይፋ መደረጋቸውን በማስመልከት ሪፖርተር ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች በውጭ አልሚዎች የለማ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለመንግሥት በመሸጥ፣ ወደ ዋናው የኤሌክትሪክ ኃይል ቋት ማስገባትን ያካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ኩባንያዎች መንግሥት የታሪፍ ጭማሪ እንዲያደርግ ሲወተውቱ መቆየታቸው የሚታወስ ነው፡፡

ሦስት ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ የኤሌትሪክ ኃይል ደንበኞች ያሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ከእነዚህ ውስጥ 83 በመቶ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ ይህም ሆኖ የተደረገው ጭማሪ በአብዛኛው የድርጅት ተጠቃሚዎች ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ከመግለጽ አልቦዘነም፡፡ እንደ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ያሉ ዘርፎች ከዚህ ቀደም ሊደረግ ስለታሰበው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ታሪፍ ቅሬታ ማሰማታቸው አይዘነጋም፡፡

የተደረገውን ጭማሪ በሚመለከት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎች ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ማብራሪያ ለመስጠት ቀጠሮ መያዛቸው ታውቋል፡፡

       ሰንጠረዥ 1 የመጀመሪያ ሁለት ተከታታይ ዓመት ማስተካከያ

 

ንዑስ መደብ

 

ወርኃዊ ፍጆታ (ኪዋሰ/Kwh)

 

ነባር ታሪፍ

   የተስተካከለ ታሪፍ

ከታኅሳስ 2011 ጀምሮ በኪዋሰ (በብር)

ከታኅሳስ 2012 ጀምሮ በኪዋሰ (በብር)

1ኛ ብሎክ

እስከ 50

0.2730

0.2730

0.2730

2ኛ ብሎክ

እስከ 100

0.3564

0.4591

0.5617

3ኛ ብሎክ

እስከ 200

0.4993

0.7807

1.0622

4ኛ ብሎክ

እስከ 300

0.5500

0.9125

1.2750

5ኛ ብሎክ

እስከ 400

0.5666

0.9750

1.3833

6ኛ ብሎክ

እስከ 500

0.5880

1.0423

1.4965

7ኛ ብሎክ

ከ500 በላይ

0.6943

1.1410

1.5870

 

  ሰንጠረዥ 2 የመጨረሻ ሁለት ተከታታይ ዓመታት ማስተካከያ

ንዑስ መደብ

ወርኃዊ ፍጆታ (ኪዋሰ/Kwh)

የተስተካከለ ታሪፍ

ከታኅሳስ 2013 ጀምሮ በኪዋሰ (በብር)

ከታኅሳስ 2014 ጀምሮ በኪዋሰ (በብር)

1ኛ ብሎክ

እስከ 50

0.2730

0.2730

2ኛ ብሎክ

እስከ 100

0.6644

0.7670

3ኛ ብሎክ

እስከ 200

1.3436

1.6250

4ኛ ብሎክ

እስከ 300

1.6375

2.0000

5ኛ ብሎክ

እስከ 400

1.7917

2.2000

6ኛ ብሎክ

እስከ 500

1.9508

2.4050

7ኛ ብሎክ

ከ500 በላይ

2.0343

2.4810

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች