የጠቅላይ ሚኒስትር የፕሬስ ሴክሬተሪ (ቃል አቀባይ) ሆነው መሾማቸው ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በይፋ የተገለጸው ወ/ሪት ቢልለኔ ሥዩም ሹመት ጥያቄ አስነሳ፡፡
ወ/ሪት ቢልለኔ እ.ኤ.አ. በ2014 በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Transformative Spaces” በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ፣ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም ዜግነታቸው ግን ካናዳዊ እንደሆነ ገልጸው ነበር፡፡
የመጀመርያዋ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቃል አቀባይ ሆነው የተሾሙት ወ/ሪት ቢልለኔ፣ በካናዳዊ ዜግነት ምክንያት ሹመታቸው የሕግ ጥሰት እንዳለበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዋጅ ቁጥር 270/1994፣ ‹‹የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ዜጎች በትውልድ አገራቸው የሚኖራቸውን መብት ተጠቃሚነት ለመወሰን በወጣው ሕግ መሠረት፣ ማንኛውም የውጭ ዜግነት ያለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ በማናቸውም የአገር መከላከያ፣ የአገር ደኅንነት ወይም በውጭ ጉዳይና መሰል የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በመደበኝነት ተቀጥሮ መሥራት እንደማይችል ተደንግጓል፤›› ይላል፡፡
በዚህም አዋጅ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም እንደ አንድ ወሳኝ የፖለቲካ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መቀጠር እንደማይችሉ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
‹‹ይህ ጉዳይ መንግሥት ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ነው፡፡ ምክንያቱም ዜጎች ለየትኛው ፖስፖርት ነው ታማኝነታቸው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል፤›› ሲሉ አንድ የሕግ ባለሙያ ተናግረዋል፡፡
ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ እንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ መቀመጥ ካለባቸው፣ የያዙትን የውጭ አገር ዜግነት መመለስ ይገባቸዋል ሲሉ እኚሁ የሕግ ባለሙያ ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሪፖርተር ቃል አቀባይዋን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም መልስ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ሪፖርተር ለቃል አቀባይዋ በስልክ የጥሪና የጽሑፍ መልዕክት፣ እንዲሁም በትዊተር ገጻቸው መልዕክት ቢልክም መልስ ማግኘት አልቻለም፡፡ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተደርገው የተሾሙትን አቶ ሽመልስ አብዲሳን ለማግኘት የተደረገው ሙከራም አልተሳካም፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱት ወ/ሪት ቢልለኔ በልጅነታቸው በዚምባብዌ ሐራሬ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ያሳለፉ ሲሆን፣ የከፍተኛ ትምህርታቸው ወደ አዲስ አበባ የንግድ ኮሌጅ በማቅናት የሁለት ዓመት ቆይታ አድርገው በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ ካናዳ በመሄድ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከብሪትሽ ኮሎምቢያ መያዛቸውን፣ ከኢትዮጵያ የሴቶች ነጋዴዎች ማኅበር ድረ ገጽ ላይ የሰፈረው የግል ማኅደራቸው ያሳያል፡፡
በብርታታቸው የሚታወቁት ወ/ሪት ቢልለኔ ማስተርሳቸውን በፆታና በሰላም ግንባታ የትምህርት ዘርፍ ኮስታሪካ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዩኒቨርሲቲ፣ በመቀጠልም ሁለተኛ ማስተርሳቸውን በሰላምና በደኅንነት ትምህርት ዘርፍ ከኦስትሪያ ኢንስበርክ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ በተለያዩ ዘርፎች ማገልገላቸው ታውቋል፡፡
ከሁለት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማኅበር የቦርድ አባልና ፕሬዚዳንት በመሆን አገልግለዋል፡፡ በተጨማሪም በቅርቡ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተደርገው የተሾሙት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በመሥራችነት የተሳተፉበትን እናት ባንክ አክሲዮን ማኅበር በምሥረታው ወቅት በማስተባበር ተሳትፈዋል፡፡ ወ/ሪት ቢልለኔ ለሴቶች መብት መከበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችም ሲያደርጉ ይታወቃሉ፡፡
በተለይ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ተደርገው ከተሰየሙ በኋላ ወ/ሪት ቢልለኔ ሰዊት ኃይለ ሥላሴ ከተባሉ ግለሰብ ጋር በመሆን በሚያዝያ 2010 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሴቶች ፍትሕ ለማግኘት የሚያደርጉትን ተጋድሎ ዕውቅና እንዲሰጡ ጠይቀው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያዋቅሩት ካቢኔ ውስጥ የሴቶች ድርሻ እኩል ወይም (50/50) እንዲሆን፣ ይህም በወንዶች ሥር የነበሩ የኃላፊነት ቦታዎች ማለትም የውጭ ጉዳይ፣ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የገንዘብና የመከላከያ የመሳሰሉት ለሴቶች እንዲሰጡ በደብዳቤያቸው ጠይቀው ነበር፡፡
በተያያዘ ዜና ከሹመታቸው ጋር ተያይዞ ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን መግለጫ የሰጡት ወ/ሪት ቢልለኔ፣ ከዚህ በኋላ እሳቸው የሚመሩት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ከዚህ ቀደም የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይሠራቸው የነበሩትን ተክቶ እንደሚሠራና ለሕዝቡ በግልጽኝነት መረጃዎችን እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት በቀጣይ ሁለት ዓመታት ትኩረት የሚሰጥባቸው የተለያዩ ነጥቦችን የያዘ ባለ አንድ ገጽ የዕቅድ ሰሌዳ አስተዋውቀዋል፡፡ ሰሌዳው መንግሥት በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ያከናውናቸዋል የተባሉ 11 የትኩረት መስኮችን ይዟል፡፡