የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች በመዋጮ ላይ አልተስማሙም
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አስተዳደራዊ የሆኑ ብልሹ አሠራሮችንና ሌብነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ መሆን እንደሚገባው፣ በአነስተኛ ሴት ነጋዴዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሠራ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ሰኞ ጥቅምት 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በንግድ ምክር ቤቱ ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በመገኘት ሊተገብራቸው የሚገቡ በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ገልጸው፣ በተለይ ብልሹ አሠራርንና ሌብነትን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ራሱን በማፅዳትና ንቁ ተሳታፊ በመሆን መሥራት እንደሚጠበቅበት ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የግል ባለሀብቱ ምልክት መሆኑን በመጥቀስም፣ ለዘላቂ አገራዊ ዕድገት ተወዳዳሪነቱን ማጠናከር እንደሚገባውም አስታውቀዋል፡፡
አነስተኛ ሴት ነጋዴዎች ላይ ንግድ ምክር ቤቱ መሥራት እንደሚኖርበት በመጠቆም፣ በተለይ በገጠር አካባቢ የንግድ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ሴቶች በመሆናቸው እነሱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚኖርበት መግለጻቸውን፣ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔው ዓመታዊ የሥራ ክንውን በተመለከተ ንግግር ያደረጉት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ፣ የንግዱን ኅብረተሰብ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡ ምክር ቤታቸው በአንድ ዓመት ውስጥ የሠራቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ በዕለቱ የመተዳደሪያ ደንብና የምርጫ አፈጻጸም መመርያን ለማሻሻል በቀረበው አጀንዳ ላይ በመወያየት አፅድቋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ አመራር በመተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ለ32 አንቀጾች ማሻሻያዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ እነዚህ ማሻሻያ ይደረግባቸው ተብለው የቀረቡ አንቀጾች በአብላጫ ድምፅ እንዲሻሻሉ ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ማሻሻያ ይደረግባቸው ተብለው ከቀረቡት የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች ውስጥ የአባላት መብትና ግዴታን በተመለከተ፣ ቀድሞ ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል በምክር ቤቱ ጉባዔ የተወሰነው መዋጮ በወቅቱ መክፈል አለበት የሚለው አንዱ ነው፡፡ ይህ አንቀጽ ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የአባልነት መዋጮንና የአገልግሎት ክፍያን ጉባዔውን አካሂዶ የኦዲት ሪፖርቱን ባፀደቀ በሦስት ወራት ውስጥ መፈጸም አለበት ተብሎ እንዲሻሻል ተወስኗል፡፡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትን ኃላፊነት በተመለከተም ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲሰጥ ተደርጎ ተሻሽሏል፡፡ በዚህ መሠረት ፕሬዚዳንቱ በውጭ ጉብኝት የንግድ ልዑካን ቡድኖችን ይመራል፣ ይቀበላል፣ ተገቢውን ሪፖርት ያዘጋጃል ወይም እንዲዘጋጅ ያደርጋል የሚል ተጨማሪ ሐሳብ ተካትቶ ፀድቋል፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባን በተመከተም ከዚህ ቀደም በአንድ ሦስተኛ አባላት ጥያቄ ከቀረበ አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል የሚለውን፣ ብዛታቸው አንድ ሦስተኛ በሆኑ አባላት ጥያቄ ከቀረበ አስቸኳይ ስብሰባ በፕሬዚዳንት ወይም በምክትል ፕሬዚዳንት ሊጠራ ይችላል በሚል ተሻሽሎ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡
ይሁን እንጂ ሥራ ላይ ያለውን ደንብ ለማሻሻል ከተለዩ 32 አንቀጾች ውስጥ፣ የአባል ምክር ቤቶች መዋጮን የተመለከተውን አንቀጽ ለማሻሻል የቀረበው ሐሳብ አሟጋች ሆኗል፡፡ ቀድሞ ማንኛውም አባል ምክር ቤት በአዲስ አባላቱ ልክ የመመዝገቢያ ሦስት ብር፣ ማንኛውም አባል ምክር ቤት በነባር አባላቱ ልክ ዓመታዊ የአባልነት መዋጮ ክፍያ አምስት ብር፣ ማንኛውም አባል ምክር ቤት ከስፖንሰርሺፕ ክፍያ፣ ከዕርዳታና ከትብብር ድጋፎች ከአባላቱ የመመዝገቢያ ክፍያና በስተቀር ከሌሎች ዘርፎች ከሚያገኛቸው ገቢዎች ላይ ከወጪ ቀሪ ተሰልቶ በተገኘው ገንዘብ ላይ አሥር በመቶ፣ ለአገራዊ ምክር ቤቱ ገቢ ያደርጋል የሚለው መለወጥ የለበትም የሚል ነው፡፡
ይህ አንቀጽ በጥቅል በአባላት አምስትና ሦስት ብር የሚለው ቀርቶ ከጠቅላላ ከሚገኝ ገቢ አሥር በመቶ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ይከፈል የሚለውን ማሻሻያ፣ በተለይ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በፅኑ ተቃውሞታል፡፡
ይህ አንቀጽ መፅደቅ የለበትም የሚለውን አቋም የያዘው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት፣ ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የሚከፈለው ዓመታዊ መዋጮ እንደ አዲስ በተሻሻለው አንቀጽ የሚከፈል ከሆነ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል በሚል ነው፡፡
እስካሁን ባለው አሠራር የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በዓመት በአባላቱ ቁጥር በአምስትና በሦስት ብር ተሰልቶ የሚከፈለው ክፍያ ከ85 ሺሕ ብር ያልበለጠ ነበር፡፡
በዚሁ ጉዳይ ብዙ ክርክር ተደርጎ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አንቀጹን በመቃወም በልዩነት ሲወጣ፣ ከ130 በላይ በሚሆኑ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በመደገፉ አንቀጹ ፀድቋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ግን ይህንን አላደርግም በሚለው አቋሙ ቢፀናም፣ አንቀጹን ለማሻሻል የቀረበውን ሐሳብ ሰባት አባላት ብቻ ድምፀ ተዓቅቦ አድርገው በ130 ድምፅ ፀድቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ176 መቀመጫዎች 18 አባል ምክር ቤቶችን በአባልነት የያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የአራት ክልል ንግድ ምክር ቤቶች ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡
በዚህ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ያልቻሉት የጋምቤላ፣ የድሬዳዋ፣ የአፋርና የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የንግድ ምክር ቤቶች ያልተሳተፉት በንግድ ምክር ቤቱ አሠራር ላይ ተቃውሞ ስላላቸው ነው፡፡
የተቃውሞ መነሻቸውም በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለዓመታት የሚወከሉት በአንድ ድምፅ በመሆኑ፣ ውክልናቸው ከፍ እንዲል ያቀረቡት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ መላኩ ጥያቄው ተደጋግሞ የሚቀርብ መሆኑ ገልጸው፣ ሆኖም የውክልናው ቁጥር የሚወሰነው ባላቸው የአባላት መጠን ነው፡፡ ስለዚህ ከአንድ በላይ ውክልና እንዲኖራቸው የግድ የአባላት ቁጥር ማደግ ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ አዋጁን ተንተርሶ የተሠራ ነው፡፡ ስለዚህ ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው የንግድ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ሲሻሻል በዚያ እንዲካተት ማድረግ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡