ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ በርካታ ደረቅ ቼኮችን በተደጋጋሚ በመፈረም ተጠርጥረው ጉዳያቸው በሌላ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን መዝገብ ወደ ተመደቡበት ችሎት በማዘዋወር፣ ተጠርጣሪዎቹን በዋስትና የለቀቁ አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ፓርላማው ከዳኝነት እንዲያሰናብት ተጠየቀ።
የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ዳኞችን ለሚሾመውና ለሚያነሳው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላከው የውሳኔ ሐሳብ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ተመድበው እየሠሩ የሚገኙት አቶ አየለ ዲቦ ስሜ ሆነ ብለው በፈጸሙት የዲስፕሊንና የሕግ ስህተት እንዲሰናበቱ መወሰኑንና ከጥቅምት 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከሥራቸው ማገዱን በመግለጽ ምክር ቤቱ ውሳኔውን እንዲያፀድቅለት ጠይቋል።
ተጠርጣሪዎቹ አቶ አዲሱ አማኑኤል፣ ፓስተር አማንና በዛብህ ሲሳይ በተለያዩ ጊዜዎች ፈርመው የቆረጧቸው ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ቼኮች በባንኮቻቸው ስንቅ የሌላቸው (ደረቅ ቼክ) መሆናቸው በመረጋገጡ፣ የተከፈተባቸውን የወንጀል ክስ ለሚመለከተው የከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ችሎት የዋስትና ጥያቄ አቅርበው ውድቅ መደረጉን ጉባዔው የላከው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል።
በዚህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ያቀረቡትን ይግባኝም ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመልክቶ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን እንዳጸና ይገልጻል። በመቀጠልም ተጠርጣሪዎቹ በጠበቃቸው አማካይነት ለአራዳ ምድብ ችሎት መዝገቡ ወደ አቃቂ ቃሊቲ አንደኛ ወንጀል ችሎት እንዲዘዋወርላቸው በአቤቱታ አመልክተው ችሎቱ ውድቅ እንዳደረገው ያትታል።
ነገር ግን ዳኛ አየለ ዲቦ በአራዳ ምድብ ችሎት የተከፈተውን መዝገብ ለመመርመር በሚል ዳኛ ሆነው ወደሚያስችሉበት አቃቂ ቃሊቲ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት በትዕዛዝ አስመጥተው መዝገቡን በማጣመር፣ ተጠርጣሪዎች በገንዘብ ዋስትና በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ መወሰናቸውን ያስረዳል።
የክሱ ወደ ሌላ ችሎት ይዘዋወርልኝ አቤቱታ አግባብነት የሚኖረው የክሱ ጭብጥ ከመሰማቱ በፊት የቀረበ እንደሆነና አቤቱታውም ለቀጣይ እርከን ፍርድ ቤት ቀርቦ ተገቢነት ያለው መሆኑ ከተረጋገጠ ብቻ መሆኑ በሥነ ሥርዓት ሕጉ ተደንግጎ ሳለ፣ ይኼንን በመጣስ እንዲሁም ጉዳዩን የያዘው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በጉዳዩ ላይ ተጠርቶ አስተያየት ሳይሰጥበት የወሰኑት በመሆኑ፣ ዳኛው ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ሆን ብለው የሕግና የዲስፕሊን ጥሰት መፈጸማቸውን የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለፓርላማው አመልክቷል።
ፓርላማው በቀረበው ጥያቄ ላይ በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የውሳኔ ሐሳቡንና የዳኛውን ምላሽ መርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል።