Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየማንነት ጥያቄ አንስታችኋል ተብለው ከቀዬአቸው የተባረሩ 180 ግለሶቦች በፖሊስ በመታገታቸው ለፍርድ ቤት...

የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል ተብለው ከቀዬአቸው የተባረሩ 180 ግለሶቦች በፖሊስ በመታገታቸው ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቀረበ

ቀን:

‹‹ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል እያቀረቡና ጥበቃ እየተደረገላቸው ነው››

አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን

መኖሪያቸውና የትውልድ ቦታቸው ወልቃይት ጠገዴ ተብሎ በሚታወቀው ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሑመራና ቃፍታ ወረዳዎች የሆኑ 180 ግለሰቦች፣ ‹‹የአማራ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል›› ተብለው ከቀዬአቸው ተባረው አዲስ አበባ ከተማ የመጡ ቢሆንም፣ መንቀሳቀስ እንዳይችሉ በፖሊስ መታገታቸው ተገልጾ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቀረበ፡፡

አቤቱታው የቀረበው ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሲሆን፣ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5(10)፣ 14(1) እና  በፍትሐ ብሔር ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 177 (1) ድንጋጌ መሠረት፣ ፍርድ ቤት ሳይወስንባቸው ወይም ሳይፈርድባቸው ሥልጣን ባለው ወይም በሌላ ሰው ተገደው እንዳይዘዋወሩ ተከልለው የተያዙ ሰዎችን አካል ነፃ ማውጣት እንደሚቻል የሚፈቅደውን ሕግ መሠረት በማድረግ መሆኑን አቤቱታው ያስረዳል፡፡ በጠበቃና የሕግ አማካሪ በሆኑት አቶ አለልኝ ምሕረቱ የቀረበው አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ ግለሰቦቹ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል ተብለው በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ከቀዬአቸው ተባረዋል፡፡ ከትውልድ ቄዬአቸው በመባረራቸው ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታና ዕገዛ እንዲደረግላቸው ለማመልከት፣ ጥቅምት 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ከተማ መምጣታቸውን አቤቱታው ያብራራል፡፡

ግለሰቦቹ አዲስ አበባ ከተማ ሲገቡ ስለመሸባቸውና ማደሪያ በማጣታቸው፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በተባለ የፖለቲካ ድርጅት የተከራየው ቢሮ ግቢ ውስጥ እንዲያድሩ ተፈቅዶላቸው እንደገቡ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊሶች፣ ግለሰቦቹ በገቡበት አጥር ዙሪያ በመቆም ወደ የትኛውም ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ያገዷቸው መሆኑንና ዘጠኝ ቀናት (እስከ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ) እንደሆናቸውም ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል፡፡

ግለሰቦቹ አቤቱታቸውን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ለማቅረብ ካለመቻላቸውም በተጨማሪ፣ በከፍተኛ ረሃብና ብርድ እየተሰቃዩ መሆኑን ጠበቃው በአቤቱታቸው አስረድተዋል፡፡ አካባቢውም ሽታ ያለበት በመሆኑ ለበሽታ እየተጋለጡና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብታቸው የተጣሰ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ግለሰቦቹ አቤቱታቸውን ለመንግሥት እንዳያቀርቡና ሕዝብ ዓይቷቸው ዕርዳታ እንዳያገኙ በፖሊስ መገደባቸውን ጠቁመው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 ተደንግጎ የሚገኘው የመዘዋወር መብታቸው መገደቡንም አስረድተዋል፡፡ አቤቱታውን የተመለከተው ፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ሁለቱ ተቋማት ሐሙስ ጥቅምት 29 ቀን 2011 ዓ.ም. አምስት ሰዓት ላይ ቀርበው እንዲያስረዱ፣ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ መስጠቱን ሪፖርተር ለማወቅ ችሏል፡፡

የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸው ከቀዬአቸው ስለተባረሩ፣ የፌዴራል መንግሥት ዕርዳታ ለመጠየቅና ወደ ቀዬአቸው እንዲመልሳቸው አቤቱታ ለማቅረብ ወደ አዲስ አበባ የመጡትን የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች፣ ፖሊስ ለምን እንዳገታቸው ወይም እንዳይንቀሳቀሱ እንደገደባቸው ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ፣ ሁሉም በአንድ ላይ ሆነው በሠልፍ መንቀሳቀስ የለባቸውም ብለዋል፡፡ ነገር ግን በተወካይ ከአምስት እስከ 20 እየሆኑ ለሚመለከተው አካል ጥያቄያቸውን እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ግለሰቦቹ እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ሳይሆን ፖሊስ ለእነሱም ደኅንነት ጥበቃ ማድረግ ስላለበት፣ ጥበቃ እያደረገላቸው እንጂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳልሆነ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ ሁሉም በሠልፍ ሆነው ሁከት እንዳይፈጥሩ እንጂ ሌላ ምንም እንዳልሆነ ሜጀር ጄኔራል ደግፌ አስረድተዋል፡፡ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በግዳጅ መባረራቸውን ግለሰቦቹ መናገራቸውን በሚመለከት፣ ሪፖርተር ከትግራይ ክልል የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...