Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትዕድሜ ማጭበርበር የአትሌቲክሱ ሌላው ‹‹ዶፒንግ››

ዕድሜ ማጭበርበር የአትሌቲክሱ ሌላው ‹‹ዶፒንግ››

ቀን:

ክለቦች በጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ እንዲኖራቸው በኦሮሚያ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 22ኛ መደበኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ግዮን ሆቴል ጥቅምት 24 ቀን 2011 ዓ.ም አከናውኗል፡፡ ክልሎች፣ ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም ማኅበራትና የክለብ ተወካዮች ባካተተው ዓመታዊ ጉባዔ የአትሌቲክሱ ሁለንተናዊ ቁመና ስፖርቱ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ አኳያ ተመጣጣኝና ተዓማኒነት ያለው መዋቅር ሊኖረው እንደሚገባ፣ በተለይም በአትሌቶች የዕድሜ ተገቢነትና ክለቦች በጠቅላላ ጉባዔ ድምፅ ‹‹ይኑራቸው አይኑራቸው›› በሚለው አጀንዳ ላይ ክርክር አድርጓል፡፡

በክብር እንግድነት ተገኝተው ጉባዔውን ያስጀመሩት መንግሥት በቅርቡ ይፋ ባደረገው አዲሱ ካቢኔ መሠረት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ነበሩ፡፡ አቶ ሀብታሙ በንግግራቸው መግቢያ ዘመናዊ አትሌቲክስ በኢትዮጵያ መታየት የጀመረው ‹‹በ1958 ዓ.ም.›› መሆኑን ተናግረው፣ አትሌቲክሱን ጨምሮ በሁሉም የስፖርት ተቋማት አሁን ላይ ከአደረጃጀትና ከአሠራር አኳያ የሚስተዋሉ ክፍተቶች በተለይም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ውዝግቦችና ሁከቶችን ማስተካከልና ማረም እንደሚያስፈልግ፣ በተለይ አትሌቲክሱ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የሚወክል እንደመሆኑ መጠን መንግሥት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ለወትሮው ሁለት ቀን ይፈጅ የነበረው የአትሌቲክሱ ጉባዔ ፌዴሬሽኑ ለ2011 ዓ.ም. የውድድር ዓመት ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ማለትም በሰንዳፋ ቤኬ ለዓመታት አገልግሎት ሳይሰጥ በቆየውንና ወደ መሬት ባንክ የገባውን ቦታ ከኦሮሚያ ክልል ጋር የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ግብረ ኃይል በማቋቋምና ጠንከር ያለ ክትትል በማድረግ ችግሩን ፈትቶ ግንባታ እንደሚያስጀምር፣ በየደረጃው የሚገኙ የማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በመጠገን የሥልጠና አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርና በመደጋገፍ ጥቅም ላይ እንዲውሉ እንደሚያደርግ፣ አራቱን የሥልጠና ማዕከላት በሰው ኃይል፣ በግብዓትና በሙያ፣ እንዲሁም የተጀመረውን ተተኪ የማፍራት ሥራ ውጤታማ ማድረግ፣ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ተገቢውን ጊዜና በጀት በመመደብ ለአትሌቶች ውጤት ሊያስመዘግብ የሚችል ሥልጠና መስጠት፣ በአትሌቶች የሚስተዋለውን የዕድሜ ተገቢነትና የፀረ አበረታች ቅመሞች ላይ ተገቢው ክትትልና ምርመራ ማድረግና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ በማመላከት ፌዴሬሽኑ ለጉባዔው ዕቅዱን ይፋ አድርጓል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በ2010 ዓ.ም. የውድድር ዓመት በተለይ ከውጤት ጋር ተያይዞ ያስመዘገበው ውጤት እንደሚናገረው ሳይሆን፣ ካለፉት ዓመታት የተሻለ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ይሁንና ጉባዔው የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በቅርቡ በፈረንሣይ ሞናኮ በሚያከናውነው የ2018 ዓ.ም. የዓመቱ ምርጥ አትሌት ምርጫ ላይ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አለመካተታቸውን በመጥቀስ የአትሌቲክሱ ውጤት በሪፖርቱ እንዳቀረበው ሳይሆን፣ አንገት የሚያስደፋ ስለመሆኑ ከአንዳንድ ክልሎችና በተለይ ከኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበር ተወካዮች ጠንካራ ትችቶች ተሰንዝሯል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በበኩሉ፣ ‹‹ውጤቱ ወድቋል አልወደቀም›› የሚለውን በተጨባጭ ማመላከት የሚቻለው በቁጥር የተደገፈ ማስረጃ ማቅረብ ሲቻል እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ይሁን እንጂ የአትሌቲክስ አሠልጣኞች ማኅበርን ጨምሮ ከኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እነሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ያቀረቡትን መከራከሪያ እንደማይስማሙበት አመላክተዋል፡፡

ሻለቃ ኃይሌን ጨምሮ ሌሎችም የፌዴሬሽኑ አመራሮችና ሙያተኞች ለአትሌቲክሱ ውጤት መውደቅ በማሳያነት የተጠቀሰው በዓለም አቀፉ ተቋም ለውድድር ዓመቱ ካቀረባቸው አሥር ምርጥ አትሌቶች ዝርዝር መካተት አለመካተታቸው መከራከሪያ እንደማይሆን፣ ከዚህ ይልቅ በዓለም ላይ የሚደረጉ ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ወደ ተለያዩ አውሮፓና ሌሎችም አገሮች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ የሚጓዙ የአትሌቶችን ቁጥር መመልከትና በእያንዳንዱ ውድድር ላይ የሚመዘገበውን ውጤት በማስላት ኢትዮጵያ በአትሌቲክሱ ዓለም ላይ ያላትን ውጤት በማየት መናገር እንደሚቻል በቁጥር የተደገፉ መረጃዎችን በማሳየት ጭምር ይከራከራሉ፡፡

ከዕድሜ ማጭበርበር ጋር በተገናኘ በጉባዔው ከተነሱ አከራካሪ ጉዳዮች በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለጊዜያዊ ውጤት ሲባል ብቻ ተገቢ ያልሆኑ አትሌቶችን በማሠለፍ ውጤታማ ነኝ እንደሚል፣ በጉባዔው በተለይ የአማራና የኦሮሚያ ተወካዮች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የጉባዔው ተሳታፊዎች በአብዛኛው ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ያለው የፌዴሬሽኑ አሠራር መስተካከል እንዳለበት እንደሚያምኑ ሲናገሩ ሪፖርተር ታዝቧል፡፡

በአፍሪካ የመጀመርያ እንደሆነ የተነገረለትና ባለፈው ዓርብ ጥቅምት 23 ቀን በአዲስ አበባ ስታዲዮም ተተክሎ አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩ የተነገረለት የአየር ብክለት መለኪያ መሣሪያ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከታደሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ ተወካዩ ቅዳሜ ጥቅምት 24 ቀን በተደረገው 22ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገኝተው፣ ጉባዔው እንደ ክፍተት ሲያቀርበው የነበረውንና ከአትሌቶች የዕድሜ ተገቢነት ጋር ተያይዞ፣ ‹‹አትሌቲክስ ለኢትዮጵያውያን ትልቁ ስጦታ ብቻ ሳይሆን ገፀ በረከትም ነው፡፡ ይህን በሚገባ ተንከባክቦ መያዝ ደግሞ ለነገ ሊባል የማይገባ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም በተለይም በአሁኑ ወቅት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስበት የአበረታች ቅመሞች ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በዋናነት የችግሩ ተጠቂ ተብለው ከተዘረዘሩ አምስት የዓለም አገሮች አንዷ እንደነበረች፣ ይሁንና የዓለም አቀፉን መመርያና ማስጠንቀቂያ ተቀብለው ተግባር ላይ ካዋሉ አገሮች አንዷ እንደመሆኗ መጠን አሁን ላይ ችግሩን መቆጣጠር በሚያስችል ደረጃ ላይ ትገኛለች፤›› ብለው የዓለም አቀፉ ተቋም የመረጃ ቋት እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ከዕድሜ ተገቢነት ጋር ትልቅ ችግር ያለው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይ ነው ከማለት አልተመለሱም፡፡

ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2011 ዓ.ም. የውድድር ዓመት እተገብራቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው ዕቅዶች የዕድሜ ተገቢነትን ጉዳይ እንደሚሠራበት ጠቅሷል፡፡ እስካሁን በነበረው ግን ችግሩ የፌዴሬሽኑ ብቻ እንዳልሆነ በዋናነት ክልሎችንና ክለቦችን ጭምር እንደሚመለከት ለቀረበው ቅሬታ ምላሽ የሰጠው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ነበር፡፡

እንደ ኃይሌ ከሆነ፣ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየትኛውም ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ባሳተፋቸው ብሔራዊ አትሌቶች ከዕድሜ ተገቢነት ጋር የተያያዘ የቀረበለት ቅሬታም ሆነ ማስጠንቀቂያ የለም፡፡ ይህ ማለት ግን ፌዴሬሽኑ ችግሩ እንደ ችግር መታየት የለበትም እያልኩኝ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ችግርን ለማስወገድ ጥረት ያደርጋል፤›› ብሎ አገር ውስጥ ለሚደረጉ ውድድሮች በተለይ ክልሎች ለተሳትፎ የሚልኳቸው አትሌቶች የዕድሜ ችግር ያለባቸውን አትሌቶች እንዲያስተካክሉ መመርያ በሚወጣበት ወቅት ከፍተኛው ተቃውሞ የሚጀምረው በዋናነት ከክልሎች ስለመሆኑም ተናግሯል፡፡

ከአትሌቶች ቤተሰቦች ጀምሮ ክልሎች የአትሌቶቹን ዕድሜ በተመለከተ ፌዴሬሽኑ እንዳላዋለደ በመግለጽ፣ የተቋሙ መመርያና ደንብ ተቀባይነት የማያገኝበት ጊዜ እንደሚበዛ ያስረዳው ኃይሌ፣ አሁንም ጣት ከመቀሳሰር ችግሩን የጋራ አድርጎ ለመፍትሔው መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፡፡

በጉባዔው ሌላው የተነሳው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአትሌቶችና ከአሠልጣኞች ማኅበር ጋር በጋራ አይሠራም የሚለው ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያ አሠልጣኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ፣ ‹‹አሠልጣኞች ለአትሌቲክሱ ውጤት ትልቁን ድርሻ የሚወስዱ ናቸው፡፡ ይሁንና ማኅበሩ  ሕጋዊ ሰውነት ኖሮት የሚንቀሳቀስ መሆኑ ታውቆ ከፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር እንዲሠራና የማማከር አገልግሎት እንዲሰጥ ዕድል አያገኝም፡፡ የማኅበሩ ግልጋሎት የሚፈለገው በጉባዔ ያለውን ድምፅ ለመጠቀም ሲባል ብቻ ነው፤›› በማለት በቀጣይ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከማኅበሩ ጋር ተቀራርቦ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ የአትሌቶች ማኅበርም ተመሳሳይ ችግር እንዳለበት የማኅበሩ  ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆነው ማርቆስ ገነቴ ተናግሯል፡፡

ለቅሬታው መልስ የሰጠው ሻለቃ ኃይሌ፣ ‹‹ብሐራዊ ፌዴሬሽኑ ሁለቱን ተቋማት ያገለለ ሥራ ልሥራ ቢል እንኳን መሥራት አይችልም፡፡ ምክንያቱም የአትሌቲክሱ ውጤት ሆነ ተቋሙ መሠረቱ  አሠልጣኞችና አትሌቶች ናቸው፤›› ብሎ በጋራ ካልሆነ በተናጠል የሚሠራ አንዳች ነገር እንደሌለ ተናግሯል፡፡

በመጨረሻም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደ አንድ አጀንዳ አድርጎ ለጉባዔ ባያቀርበውም፣ በዋናነት በኦሮሚያና በአማራ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች አማካይነት ክለቦች በጉባዔው ድምፅ ሊኖራቸው ይገባል የሚለው ነበር፡፡ የኦሮሚያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የክለብ አሠልጣኞችና ሙያተኞች ክለቦች በጉባዔ ድምፅ እንዲኖራቸው ጠይቀዋል፡፡ በሌላ በኩል የታዳጊ ክልሎች አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተወካዮች በበኩላቸው፣ ክለቦች ድምፅ እንዲኖራቸው በኦሮሚያ የቀረበው አጀንዳ የታዳጊ ክልሎችን ድምፅ ለማፈን ካልሆነ በስተቀር የነበረው እንዲቀጥል ተከራክረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች፣ ‹‹ክለቦች ድምፅ ይኑራቸው አይኑራቸው?›› የሚለው ክርክር ለአትሌቲክሱ ዕድገት እስከ ሆነ ድረስ ክለቦች በጉባዔው የባለቤትነት ዕድል እንዲኖራቸው በድምፅ ቢሳተፉ ክፋት እንደሌለው ነው፡፡ ምክንያቱን አስመልክቶ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በቆየው የጠቅላላ ጉባዔ ጥንቅር ምንም ዓይነት ክለብ የሌላቸው ክልሎች አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን በሚያስተዳድሩ ክልሎችና የክለብ አመራሮች ህልውና ላይ እንዲወስኑ ማድረግ በተለይ ክለብ ለመመሥረት ፍላጎቱ ያላቸውን ወገኖች ለስፖርቱ ትኩረት እንዳይሰጡ ያደርጋል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ክለቦች ‹‹በድምፅ ይሳተፉ›› የሚለው ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጥያቄው ትክክለኛ መልስ ሳይሰጠው ሲንከባለል የቆየ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ በዘንድሮ ጉባዔም በተመሳሳይ መልኩ ቀርቧል፡፡ ከፌዴሬሽኑ የተሰጠው መልስ አጀንዳው ተይዞ ለሚቀጥለው ጥናት ተደርጎበት እንዲቀርብ ይደረጋል የሚል ሆኗል፡፡ አጀንዳው አሁኑኑ ውሳኔ እንዲያገኝ አጥብቆ የተከራከረው የኦሮሚያ ክልል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ የተቀበለው አይመስልም፡፡ ምክንያቱም እንደወትሮ ሁሉ ፌዴሬሽኑ በጉባዔው ማጠናቀቂያ ላይ ለክልሎችና ክለቦች የሚሰጠውን ማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ሳይቀበል ቀርቷል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ከሁሉም ክልሎች የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል በሚል ሽልማቱ 240 ሺሕ ብር እንደነበርም ታውቋል፡፡ ሁለተኛውና ሦስተኛ በመሆን 180 ሺሕና 140 ሺሕ ብር የተሸለሙት አማራና አዲስ አበባ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...