Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ባዮቴክኖሎጂ የጥጥ የስንዴና የበቆሎ ጉዳይ ብቻ አይደለም›› ኃይሉ ዳዲ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር

ቴክኖሎጂ በነገሠበት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአገሮች ልማት የባዮቴክኖሎጂ ዘርፍ ወሳኝ ሚናዎችን ይጫወታል፡፡ ይህ የምርምርና የሳይንስ ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች ሩቅ ነበር፡፡ የምርምር ውጤቶችን ኢኮኖሚያቸውን በባዮቴክኖሎጂ ምርምሮችና ምርቶች ካቀኑ ምዕራባውያንና ሌሎች የዓለም አገሮች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገባት ብቸኛው አማራጭ ነበር፡፡ ዘግይቶም ቢሆን የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ወደ ኢትዮጵያም ጎራ ማለት ችሏል፡፡ በዩንቨርሲቲዎችና በተለያዩ የምርምር ተቋማት ልዩ ልዩ ሥራዎች መሠራት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ የተጀመረውን የዕድገት እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ምትክ የሌለው ሆኖ በመገኘቱም እነዚህን የምርምር ሥራዎች በበላይነት እንዲቆጣጠርና ድጋፍ እንዲያደርግ የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሁለት ዓመት በፊት ራሱን ችሎ ተቋቁሟል፡፡ በኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴና በኢትዮጵያ በምርምር ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን ኃይሉ ዳዲን (ዶ/ር) አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ሌሎች ተቋማት የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ በዚህ ረገድ የእናንተ ድርጅት የተለየ የሚሠራው ነገር ምንድነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በአገሪቱ ውስጥ በየዩንቨርሲቲዎችና በተለያዩ ተቋማት ሥር የምርምር ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን በተበጣጠሰ መልኩ ነው የሚሠሩት፡፡ እነዚህ ሥራዎች  አስፈላጊውን ድጋፍም አያገኙም፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂ የምርምር ሥራ በጣም ውድ ነው፡፡ ሠፊ የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል፡፡ እንደግብዓት የሚውሉ ከሚካሎችና የላቦራቶሪ መሠረተ ልማቶችም በጣም ውድ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን በተበጣጠስ መልኩ የሚሠሩ ምርምሮችን አንድ ላይ ማምጣት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን እንዲያስተባብርም ነው ኢንስቲትዩቱ የተቋቋመው፡፡ ብዙ ሰው ባዮ ቴክኖሎጂን እንደ አንድ ዘርፍ ብቻ ነው የሚያየው፡፡ የአብዛኛኞቹ ሰዎች አረዳድ ባዮ ቴክኖሎጂን እንደ ግብርና ብቻ ነው፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂ ከግብርና በላይ ነው፡፡ ሆለታ ላይ የሚሠራው የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ነው፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የእንስሳት ዝርያን፣ ምርትና ምርታማነትን የመጨመር ሥራ ይሠራል፡፡ በሌሎች የምርምር ተቋማትም በእንስሳት ላይ ተመሳሳይ የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ይሠራል፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሰብልን ምርታማነት መጨመር ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ኢንዱስትሪያል ባዮ ቴክኖሎጂ የሚባል ዘርፍ አለ፡፡ በአገራችን የሌዘር፣ የጨርቃጨርቅ፣ የምግብ ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ባዮ ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ፡፡ ዳቦ ለማምረት እርሾ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የተለያዩ እርሾዎችን ማምረት የባዮ ቴክኖሎጂ ሥራ ነው፡፡ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ ኢንዛይሞችን ማምረትም የባዮ ቴክኖሎጂ ድርሻ ነው፡፡ መድኃኒትንም ብንወስድ የባዮቴክኖሎጂ ሥራ ነው፡፡ በአራት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ነው የምንሠራው፡፡ የመጀመሪያው ግብርና ነው፡፡ በግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ ረገድ በተለያዩ ተቋማት በአገሪቱ ላይ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎችን የማስተባበር፣ የመምራት፣ የማደራጀት፣ አቅም የመገንባት ሥራ እንሠራለን፡፡ በኢንዱስትሪያል ባዮ ቴክኖሎጂ  ዘርፍም የተበጣጠሱትን የምርምር ሥራዎች የማስተባበር ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ ግብርናን በተመለከተ ደግሞ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር እንሠራለን፡፡ ሦስተኛው የጤና ባዮ ቴክኖሎጂ ዘርፍ  ነው፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኛው መድኃኒት የባዮ ቴክኒሎጂ ውጤት ነው፡፡ የሕዝባችን የጤና ሁኔታ እንዲሻሻል መድኃኒቶች ላይ ምርምሮች መሠራት አለበት፡፡ መድኃኒቶችን፣ ክትባቶችን በምርምር መሥራት አለብን፡፡ እኛ ብዙ ባህላዊ መድኃኒቶች አሉን፡፡ ባህላዊ መድኃኒቶች በባዮ ቴክኖሎጂ ከተደገፉ የተሻለ ውጤት ያመጣሉ፡፡ ስለዚህ ባዮ ቴክኖሎጂ በጤናው ዘርፍ የሚሠራቸውን ሥራዎች እናስተባብራለን፣ ድጋፍም እንሰጣለን፡፡ የሰው ኃይል በማሠልጠን አስፈላጊውን ላብራቶሪ በመገንባትና በማደራጀት፣ የተመረጡ የምርምር ፕሮግራሞችን በገንዘብ በመደገፍ ነው ኃላፊነታችንን የምንወጣው፡፡ አራተኛው የምናስተባብረው ዘርፍ ኢንቫይሮሜንታል ባዮቴክኖሎጂን ነው፡፡ በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ልማት እየተፋጠነ ነው፡፡ የኢንዱስትሪ መበልፀግ ካለ ደግሞ የአካባቢ ብክለት የሚጠብቅ ነው፡፡ ይህንን በማስተካከል ረገድ ባዮ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ከኢንዱስትሪ በሚወጣው ፍሳሽ ወንዞች እየተበከሉ ነው፡፡ የአየር ብክለትም ይኖራል፡፡ አፈርም እየተበከለ ነው፡፡ ለምሳሌ አፈር በፕላስቲክ እየተበከለ ነው፡፡ ፕላስቲክ አፈር ውስጥ ገብቶ ለዘለዓለም አይበሰብስም፡፡ መበስበስ የሚችል ፕላስቲክ በመሥራት ይህንን ችግር እንዴት በምርምር መቅረፍ ይችላል? የተበከሉ ውኃማ አካላትን በባዮቴክኖሎጂ በመታገዝ እንዴት ንፁህ ማድረግ፣ ለመጠጥ እንዲውል ማድረግ ይቻላል የሚሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በምርምር እንመልሳለን፡፡ ይህንንም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ነው የምንሠራው፡፡ በአጠቃላይ በየዘርፉ ካሉ ከተለያዩ መሥሪያቤቶች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- በየመስኩ የሚካሄዱ ምርምሮችን ከማከናወን ባሻገር በራሳችሁ ምርምር የምታካሂዱበት አግባብ አለ?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ባዮ ቴክኖሎጂ ለአገራችን አዲስ ነው፡፡ ቀደም ብሎ አለ ቢባል እንኳ ቀድሞ የተጀመረው የግብርናው ሴክተር ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ባዮ ቴክኖሎጂን አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ላይ በትንሹ ጀምር አለ፡፡ ጎንደር ላይም እንዲሁ በሙከራ ላይ ነው፡፡ በሌሎች ዩንቨርሲቲዎች ግን መሣሪያም ሆነ ራሱን የቻለ ላብራቶሪ ስለሌለ በተግባር የሚታይ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቱ ከማስተባበሩ ጎን ለጎን የምርምር ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ምክንያቱም ላስተባበር ብቻ ብሎ ቢቀመጥ በሒደት ላይ ያሉ ምርምሮች በጣም ውስን ስለሆኑ ያስቸግራል፡፡ አሁን ገና አንድ ብለን ሥራ እየጀመርን ነው፡፡ እንደ ግብርና ምርምሮች በየክልሉ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የሉንም፡፡ ወደፊት ግን እንደዛ ማድረጋችን አይቀርም፡፡ ለጊዜው ግን ባለን አቅም ከማስተባበሩ ጎን ለጎን ትልልቅና ነጥረው የሚወጡ የምርምር ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ምርምር እንድናደርግም ሥልጣናችን ይፈቅድልናል፡፡ ሁሉንም እኛ እንሥራው ለማለት ሳይሆን ብዙ የሚሠራ አካል ስለሌለ ለመስራት ስለምንገደድ ነው፡፡ እኛ ምርምር የማድረግ አቅማችንን ከገነባን ታች ወርዶ ቁጥጥር ለማድረግ እንዲሁም ላብራቶሪዎችን ለመገንባት አቅም ይኖረናል፡፡

ሪፖርተር፡-  የተሰጣችሁ የሥራ ድርሻ ሰፊ ነው፡፡ ኃላፊነታችሁን ለመወጣት ጠንካራ በጀት እንደሚያስፈልጋችሁ ግልጽ ነው፡፡ የበጀታችሁ ምንጭ መንግሥት ነው? ወይስ ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በአገራችን ያሉ የምርምር ተቋማት የሚደግፉት በመንግሥት ነው፡፡ ሌላው ዓለም ላይ ግን መንግሥት የሚሰጠው ድጋፍ ትንሽ ነው፡፡ ትልቁን ወጪ የሚሸፍነው የኢንዱስትሪው ዘርፍ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ እንዲህ ያለችግር አለብኝ ብሎ ለተመራማሪዎች ይሰጣል፡፡ በምርምር ችግሩ ይፈታል፡፡ ችግሩን ሲያቀርብ ግን ከእነገንዘቡ ነው፡፡ በእኛ አገር ግን እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንምና መንግሥት ነው ሁሉንም ድጋፍ የሚያደርገው፡፡ ከውጭ አግኝተን የምንሠራቸው የተወሰኑ ጥቃቅን ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ካለው አንፃር ሲታይ ኢምንት ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የተመራማሪዎችን ደመወዝ፣ የምርምር መሣሪያዎች ምንገዛበትን ሁሉንም የሚችለው መንግሥት ነው፡፡ የትኛውም አገር ላይ መሰል ተቋማትን መጀመሪያ የሚያደራጀውም መንግሥት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዓመታዊ በጀታችሁ ምን ያህል ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ገና ጀማሪዎች ነን፡፡ በጀት ለሁለተኛ ጊዜ ሲመደብልን ነው፡፡ የዘንድሮ በጀታችን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ነገር ግን ለሰው ኃይል ሥልጠና፣ አቅም ለመገንባት፣ በ6 ክላስተሮች ላብራቶሪዎች ለመገንባት ብለን የያዝነው ለየት ያለ ወደ አንድ ቢሊዮን የሚደርስ በጀት አለ፡፡ የምንገነባቸው ላብራቶሪዎች በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንዲያገለግሉ ነው፡፡ ለየምርምር ተቋማቱ፣ ለየዩንቨርሲቲዎቹ መሣሪያ ገዝቶ ከመስጠት አንድ ማዕከላዊ ቦታ ላይ ላብራቶሪ ብንገነባ በዙሪያው ላሉ ሁሉ ጥቅም ይሰጣል የሚለውን ተሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ወደፊት እንግዲ አቅማችንን ከገነባን በየተቋማቱ ለመሥራት እንችል ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- የምርምር ላብራቶሪዎችን ማቋቋም አቅም የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ እያንዳንዱ የላብራቶሪ ግብዓቶች በውድ ዋጋ እንደሚገዙ ይታወቃል፡፡ እናንተ ደግሞ 6 ላብራቶሪዎችን ለማቋቋም አንድ ቢሊዮን ብር የማይሞላ በጀት መድበናል እያላችሁ ነው፡፡ ምን ያህል በቂ ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- እሱስ አይበቃም፡፡ ነገር ግን በክፍል በክፍል ለመገንባት ያቀድን ስለሆነ አሁን የተባለው አንድ ቢሊዮን ብር ለመጀመሪያ የግንባታ ክፍል ነው የምናውለው፡፡ መንግሥትም ተነስቶ በአንዴ 20 ቢሊዮን ብር ቢሰጠን ችግር ነው፡፡ የተደራጀ የሰው ኃይል ሳይኖረን ዕቃውን ገዝተን ብንከምር ምን ዋጋ አለው፡፡ በሒደት የምንሠራው ሥራ ነው መሆን ያለበት፡፡ እንደተባለው አንድ ቢሊዮን ብር ምንም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በሁለትና በሦስት ዓመት ውስጥ ግብዓቶች ገዝተንበት ብናስገባ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዚያ ላይ የምርምር መሣሪያዎች እንደ ሞባይል ቀፎ በየጊዜው አዳዲስ ስለሚወጡ አንዴ ገዝተን ከምንቀመጥ ገበያ ላይ ያለውን ዘመናዊ መሣሪያ ባለን ጊዜ ውስጥ እየገዛን ብናስገባ ይመረጣል፡፡ መሠረተ ልማቱን ስንገነባ የሰው ኃይሉንም ጎን ለጎን እየገነባን መሆን ስላለበት ግዢውን የምንፈፅመው በሒደት ነው፡፡ አንድ ቢሊዮን ብር የተባለውም በሐሳብ ደረጃ የቀረበ እንጂ ገና አልፀደቀም፡፡

ሪፖርተር፡- በምርምር ዘርፉ ላይ አሉ ከሚባሉ ተግዳሮቶች አንደኛው የተማረ የሰው ኃይል ፍልሰት ነው፡፡ ይህ በተለይ በምርምሩ ዘርፍ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከባድ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ይህ በኛ ኢንስቲትዩት ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ችግር ነው፡፡ እኔ ራሴ ምርምር ውስጥ ስለቆየሁ ችግሩ እንዳለ አውቃለሁ፡፡ መንግሥት የተሻለ ደመወዝ ለተመራማሪው ይከፍላል፡፡ እንዲያም ሆኖ ተመራማሪዎቹን ማቆየት አልተቻለም፡፡ የተሻለ የሚከፍላቸው ሲያገኙ ይሄዳሉ፡፡ አገሪቱ ባላት አቅም የተሻለ ለመክፈል ጥረት ይደረጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ምርምር የሚያደርጉበት ጥሩ ሁኔታ ከተመቻቸ ለረዥም ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ቢሮክራሲ ያልበዛበት፣ የመልካም አስተዳደር ሥራ የሰፈነበት አሠራር ቢዘረጋ የሚሄዱትን በመጠኑም ቢሆን ማቆየት ይቻላል፡፡ አንዳንድ በሳል ባለሙያዎችን ማጣት ከባድ ነው፡፡ የዶክትሬት ዲግሪ ኖሮት በሥራ ላይ ልምድ ያለው ሰው ለመተካት 10 ዓመት ይፈጃል፡፡ ይህንን መንግሥትም የሚያውቀው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተማሪዎች ከስር ጀምሮ ስለባዮቴክኖሎጂ አውቀው እንዲወጡ ከማድረግ አኳያ ምን እየሰራችሁ ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- የባዮ ቴክኖሎጂ አዘጋጅተናል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የሚማሩበትን ጭምር ነው ያዘጋጀነው፡፡ የሌሎቹን አገሮች ልምድ ሥናይ ባዮቴክኖሎጂን በተመለከተ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ ይሠራሉ፡፡ እነሱ ወደ ዩንቨርሲቲ ሲገቡ ሥለ ባዮ ቴክኖሎጂ መነሻ ሐሳብ ይዘው ነው፡፡ ካሪኩለሙ የባዮ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ ምን መማር አለባቸው የሚለውን ማኑዋል (መመሪያ)፣ ምን ምን ዓይነት የላብራቶሪ ሥራዎችን መሥራት አለባቸው የሚለውን ያካተተ ነው፡፡ የቢ ኤስሲ፣ የኤም ኤስሲና የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን በተመለከተም በካሪኩለሙ ተካቷል፡፡ መጽሐፎቹም ተዘጋጅተው አልቀዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ካሪኩለም ማዘጋጀት ያስፈለገው በየዩንቨርሲቲው ያለው የትምህርት አሰጣጥ ወጥ እንዲሆን ታስቦ ነው፡፡ ምክንያቱም ከነባር ዩንቨርሲቲዎች የሚወጡና ከአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ አቅማቸው እኩል አይደለም፡፡ እንደ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ካሉ ነባር ተቋማት የሚወጡት የተሻለ አቅም አላቸው፡፡ ለዚህም ነው ስታንዳርድ ማዘጋጀት ያስፈለገው፡፡ የቻሉ ከተቀመጠው ስታንዳርድ በላይ ያድርጉ ከስታንዳርዱ በታች መሆን ግን አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኒቨርሲቲዎችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የባዮቴክኖሎጂ ላቦራቶሪዎችን መሠረተ ልማት ለማሟላት ምን ታደርጋላችሁ?

ዶ/ር ኃይሉ፡- በሌላው ዓለም ላይ ከታች ጀምሮ ነው ላብራቶሪ ተደራሽ የሚደረገው፡፡ በእኛ አገር ግን በዩንቨርሲቲዎች ደረጃ ከተሠራ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዕድገት ደረጃችን ግን ወደዚያ ሊወስደን ይችላል፡፡ የአቅም ጉዳይ እንጂ ሁሉም ያስፈልጋቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የተደራጀ ላብራቶሪ ያላቸው ዩኒቨርሲቲዎች የትኞቹ ናቸው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- እንደ የዩንቨርሲቲው ይለያያል፡፡ ጠንካራም ባይሆን እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉ ጥሩ ጅምሮች አሉ፡፡ በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በመቀሌና በመሳሰሉት ዩኒቨርሲቲዎችም እንደዚሁ የተጠናከረ ባይሆንም ላቦራቶሪዎች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህም ብዙ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ላቦራቶሪ የተሟላላቸው አይደሉም፡፡ የሰው ኃይልም በበቂ የላቸውም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንስቲትዩቱ በራሱ የጀመራቸው የምርምር ስራዎች ምን ያህል ይሆናሉ? ትኩረቱን የሚያደርገውስ በምን ላይ ነው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- ኢትዮጵያ በግብርና መስክ በቀዳሚነት የሚያስገልጓት ምርምሮች ምንድናቸው የሚሉትን ለይተን ቅድሚያ በመስጠት እንሠራለን፡፡ ለምሳሌ ጥጥ ለእኛ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አብዛኛውን ምርት የምናስገባው ከውጭ ነው፡፡ እዚሁ አምርተን፣ እዚሁ ሸምነን መላክ እንጂ ከውጭ ማስገባት የለብንም፡፡ ቡናም እንዲሁ  ወሳኝ ነው፡፡ የምግብ ሰብል ላይም በተመሳሳይ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻልና ሌሎች የአገሪቱ ፍላጎት ማርካት የሚችሉ የምርምር ፕሮጀክቶችን እየመረጥን ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ የአገሪቱ አንገብጋቢ ችግር በሆኑ እንደ እምቦጭ ያሉ ችግሮች ላይ የሚሠሩ ምርምሮችን ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ባሻገርም ኢንስቲትዩቱ 25 የሚሆኑ የምርምር ፕሮጀክቶችን በራሱ እያካሄደ ነው፡፡ ከሚሠራቸው ምርምሮች መካከል በምግብ ስብል ረገድ የስንዴን ምርታማነት ማሻሻል ላይ ያተኮረው አንደኛው ነው፡፡ በእንስሳት ጤና መስክም የተለያዩ ክትባቶችን ለማውጣት ምርምር በማድረግ ላይ እንገኛለን፡፡ ከስኳር ፋብሪካ የሚወጡ ተረፈ ምርቶች አካባቢን ሳይበክሉ ወደ ሌላ ምርት የሚቀየሩበት የምርምር ሥራም ከ25ቱ ፕሮጀክቶች መካከል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰቡ ስለ ባዮቴክኖሎጂ ምን ያህል ግንዛቤ አለው?

ዶ/ር ኃይሉ፡- አንድ ነገር አዲስ ሆኖ ሲገባ ማኅበረሰቡ ግንዛቤው እስኪጨምር ቁንፅል አረዳድ ነው የሚኖረው፡፡ ባዮ ቴክኖሎጂ ሲባል ብዙዎች የዘረመል ምሕንድስና (ጄሞ) ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ባዮ ቴክኖሎጂ ሰፊ ዘርፍ ነው፡፡ በሕክምና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአካባቢና በግብርና ዘርፎች የተለያዩ ምርምሮች ይሠሩበታል፡፡ ባዮቴክኖሎጂ በሺዎች የሚቆጠሩ የግብርና ምርምር ምርቶች ላይ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ጄሞ ከዚያ ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ባዮቴክኖሎጂ የጥጥ፣ የስንዴና  የበቆሎ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ባዮቴክኖሎጂ ሁሉንም ሕይወት፣ ሁሉንም ዘርፍ የሚነካካ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን የአረዳድ ችግር ለመቅረፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንሠራለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከ ግለሰቦች የሚደርሰው ወገን ፈንድ

ወገን ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሕጋዊ ዕውቅና በማግኘት ከኢትዮጵያና ከተለያዩ አገሮች ልገሳን ለማሰባሰብ ‹‹ወገን ፈንድ›› የሚባል የበይነ መረብ (ኦንላይን) የድጋፍ ማሰባሰቢያ ድረ...

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...