Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበአገራችን የለውጥ ሒደት የሚታዩ ፈተናዎችና መፍትሔዎች

በአገራችን የለውጥ ሒደት የሚታዩ ፈተናዎችና መፍትሔዎች

ቀን:

በበረራ ቢያ

የሕዝቦች የትግል ውጤት የሆነ ለውጥ በአገራችን እየታየ ነው፡፡ ይህን ሕዝባዊ ለውጥ የሕይወት መስዋዕትነትን ሊያስከፍል በሚችል ሁኔታ የመሩትና የመጀመሪያውን ምዕራፍ እንዲጠናቀቅ ላደረጉት የቲም ለማ ቡድን ያለኝን አድናቆትና ክብር ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ስለሆነም ይህን ብዙዎች የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የመጣውን ወርቃማና በአፍሪካ አኅጉር የማይታሰብ ዕድል እንዳያመልጠን፣ እያንዳንዳችን እንደ ዜጋ ምን ይጠበቅብናል በሚል ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት ተነሳሳሁ፡፡ እንደ አገር በታሪካችን ከዚህ በፊት የገጠሙንን ለውጦች በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላችን ዕድሎች አምልጠውናል፡፡ ለአብነት የ1953 ዓ.ም. በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይና ገርማሜ ንዋይ የተመራ መፈንቅለ መንግሥት፣ የ1966 ዓ.ም. አብዮት፣ የ1983 ዓ.ም. የደርግ መውደቅና የ1997 ዓ.ም. ምርጫ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በአሁኑ ጊዜ ሊታረቁ የማይችሉ ጫፍ የረገጡ አቋሞች ናቸው ሲራመዱ የምናየው፡፡ በመሀል እነዚህን በማስማማት አስታራቂ ሐሳብ ሊያቀርቡ የሚችሉ በአቋም መሀል ላይ ያሉ ድምፆች ብዙ አልተሰሙም፡፡  እንደዚህ ዓይነት ድምፆች ናቸው በአሁኑ የአገራችን ሁኔታ መበራከት ያለባቸው የሚል እምነት አለኝ፡፡

- Advertisement -

ሥጋቶችን ወደ መልካም ዕድል በሚለወጥ መልኩ ያሉትን ጥንካሬና ዕድሎችን በመጠቀም፣ የሚታዩትን ፈተናዎችና ሥጋቶችን እንዴት ወደ መልካምና ዕድገት በመለወጥ ልጆቻችንና ተከታታይ ቀጣይ ትውልዶች ሰላም የሰፈነባት፣ አንድነቷ የተጠበቀና ኢትዮጵያን ለመገንባት ይቻላል በሚሉት ዙሪያ ነው ሐሳቦቼ የሚያጠነጥኑት፡፡ በዚህ ሒደት ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ፣ አንድ ጠጠር የማቀበል ዓይነት የዜግነት ግዴታን ለመወጣት በአዎንታዊነትና ይቻላል የሚል መንፈስን በሰነቀ መንገድ አዎንታዊ አስታራቂ አማራጭ ሐሳቦች ለማንሸራሸር የቀረብኩ በመሆኑ፣ ጽሑፌን በፅሞና በማንበብ ሐሳቦቼን በማጠናከርም ሆነ በማሻሻል ሌሎችም አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እጠይቃለሁ፡፡

አገራችን ካለችበት የዕድገት ደረጃ የዳበረ ካፒታሊዝም ውጤት ወደ ሆነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማሸጋገር ከተቻለ፣ ትልቅ ልምድና አርዓያነት ያለውን ተሞክሮ በተለይ ለታዳጊ ዓለም ሕዝቦች የምታበረክት በመሆኑ ይህንን የአገራችንን ገጽታ ወደ ላይ የሚሰቅለውን ተግባር በስኬታማነት ለማጠናቀቅ ተገቢውን ሥራ በቅንጅት ማከናወን ይጠበቅብናል፡፡

 በዚህ ረገድ በአብዛኛው የማያግባቡ ሐሳቦችን የሚወክሉና ለሚታሰበው ውጤት ብዙም የማይጠቅሙ የማኅበራዊ ሚዲያ የድብቅ ጀግኖችና አንዳንድ የብዙኃን መገናኛ፣ የቴሌቪዥንና ሬድዮ ጣቢያዎች ወደ ኅሊናቸው በመመለስ ከሚከፋፍሉንና ከሚበታትኑን ከሁለቱ ጫፎች ወደ መካከለኛ በመምጣት ከእልህና የእኔ ብቻ ትክክል አስተሳሰብ በመላቀቅ ወደ ብሔራዊ መግባባት ወደሚያመጡን ጉዳዮች እንግባ የሚል ተማፅኖ ማቅረብም እወዳለሁ፡፡ ጽሑፌ በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው በማንነትና በፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር ጉዳይ፣ ሁለተኛው በዴሞክራሲ ሥርዓት አተገባበር የሚታዩ ውዥንብሮችና መፍትሔዎቹ በማለት ይሆናል፡፡

በአገራችን የሚታዩ ድክመቶችና ሥጋቶች

በአገራችን ምንም እንኳ በአንዳንድ ጉዳዮች የብሔራዊ መግባባቱ እየመጣ የሚገኝ ቢሆንም፣ ያሉትን ዕድሎች እንዳንጠቀም ሊያደርጉን የሚችሉ ሥጋቶች አሉ፡፡ እነዚህ ብሔራዊ መግባባት ላይ ያልተደረሱ የቆዩ ልዩነቶችና ሌሎች በቅርቡ የሚታዩ ክፍተቶች ናቸው፡፡

በሚከተሉት አገራዊ ጉዳዮች ላይ በቂ ሁኔታ ብሔራዊ መግባባት ላይ አልተደረሰም

1. በማንነትና የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀርና በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ፣

2. በዴሞክራሲ ሥርዓት አተገባበርና በርዕዮተ ዓለም፣

3. በመሬት ይዞታና በሌሎች የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣

4. በታሪክ ጉዳዮች፣

5. በብሔራዊ ቋንቋዎች ምርጫ፣

6. በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ፣

ሌሎች የሚታዩ ክፍተቶች

  1. ለውጡን የሚቃወሙ ኃይሎች በጥፋታቸው ተፀፅተው ሕዝቦችን የማሳመጽ ተግባራቸውን፣
  2. ማቆም ያለ መፈለጋቸው ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትግራይ ሕወሓት ከለውጡ ራሱን የማግለል አዝማሚያ መታየት፣
  3. በአገሪቷ ሲፈጠሩ በነበሩ የፀጥታ መታወክ የዜጐች ሞት መፈናቀልና የንብረት ውድመት ከበስተጀርባ በመምራት ተጠያቂ ሊሆኑ በሚችሉ ኃይሎች ላይ ተገቢ ዕርምጃ አለመወሰድና ዕርምጃዎች ይዘገያሉ የሚሉ ቅሬታዎች መደመጥ፣
  4. በአንዳንድ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ሌሎች ጥርጣሬና ፍርኃት መኖር፣
  5.  በየወቅቱ በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በሕዝብ ውስጥ እንዲናፈሱ የሚፈበረኩ ሕዝቦችን ለመከፋፈልና የለውጡን ሒደት ለማደናቀፍም የሚሠሩ ሥራዎችን እውነታውን ለሕዝቡ ማብራሪያ የመስጠትና የማጋለጥ ሥራ በአግባቡ አይከናወንም የሚሉም ቅሬታዎች መሰማታቸው፣
  6. አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙኃን የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጐት ለማስፈጸም ሕዝቡን የመከፋፈል ድርጊት የሚያካሄዱ መሆን፣
  7.  በታችኛዎቹ እርከን የሚገኘው በቀበሌ፣ በወረዳና በመሳሰሉት የሕዝብ አደረጃጀት ሕዝቡን በሚያረካ መንገድ ለውጥ ባለመደረጉ ኅብረተሰቡን ለመንጋ ፍርድና ሥርዓተ አልበኝነት መዳረጉ፣
  8.  ድህነቱና ሥራ አጥ ጉዳዮች የወደፊቱ የአገራችን ትልቅ ፈተና መሆን፣
  9.  ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖርና በኢንቨስትመንትና በሥራ መስፋፋት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር መሆኑ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በተወሰኑት ላይ ሐሳቦቼን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

በማንነት ጉዳዮችና በፌዴራል መንግሥት አወቃቀር መግባባት ላይ ያለመደረስ

ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ ከኢሕአዴግ ሥልጣን መያዝ ጀምሮ የፖለቲካ ልሂቃን የልዩነት አጀንዳ ሆኖ ሲያወዛግብና ሲያከራክር የቆየ፣ በተለይ የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ተቀራርበው እንዳይሠሩ እንቅፋት ሆኖ የቆየ አጀንዳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ማንነትን በተመለከተ የብሔር ማንነት ሳይሆን የዜግነትና የኢትዮጵያዊነት ማንነት ላይ ነው መመሥረት ያለብን የሚለው የልሂቃን ቡድን፣ ለብሔር ማንነት ነው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት፣ የብሔሩ ማንነት ዕውቅና ካገኘ የኢትዮጵያ ማንነት በዚሁ ውስጥ የሚታወቅና የሚገለጽ ነው የሚለው የልሂቃን ቡድን በሌላ ጫፍ ቆሞ፣ በዚህ ጉዳይ ላለፉት ረዘም ያሉ ዓመታት መግባባት ላይ ሳይደርስ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዓመት መስከረም 6 ቀን 2011 ዓ.ም. በአቶ ዳዊድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ወደ አገር መግባትና ቀደም ሲል ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አገር ቤት ከገባው ከግንቦት 7 አርበኞች ግንባር ጋር ተያይዞ በባንዲራ ልዩነት ጭምር የተነሳው ውዝግብ፣ በኋላም በቡራዩና በአዲስ አበባ ለደረሰው የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ መቁሰልና የንብረት መውደም ለማቀጣጠያነት ምክንያት የሆነውም ይኸው ጉዳይ መሆኑም የታወቀ ነው፡፡

የዜግነትና የኢትዮጵያዊነት ማንነት ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት አደረጃጀት ለአስተዳደር አመቺነት ያለውና ብሔርን መሠረት የማያደርግ በመሆኑ፣ የመከፋፈልና ከክልሌ ውጣ የሚለውን ሥጋት ይቀንሳል፡፡ ለመገንጠል የማስፈራራት ሁኔታንም  ያስወግዳል፡፡ በራስ ማንነት ላይ የሚውጠነጠንን ሥጋት ያስወግዳል የሚል መከራከሪያ ከዚህ ሐሳብ አራማጆች ይቀርባል፡፡ የሚቀርበውም ሐሳብ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ ይህን ሐሳብ የሚያራምደው የሕዝብ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ተቃዋሚዎች የነበሩ አሁን ተፎካካሪ የሆኑ የፖለቲካ ድርጅቶችና ቱባ ቱባ ግለሰቦች በርካቶች ናቸው፡፡

ይህን የዜግነት ማንነት ሐሳብ በይበልጥ ሲያራምዱ የቆዩት የአማራ ልሂቃንና የብሔር ቅይጥ ያላቸው ወገኖች ናቸው፡፡  በእርግጥ ከሌሎችም የተወሰኑት ሐሳቡን የሚደግፉ ይኖራሉ፡፡ ግን ይህ ጉዳይ አላዋጣም በሚል የአማራ ልሂቃንም በአብዛኛው የአማራ ሕዝብን መብት የሚያስጠብቅ ብሔራዊ የአማራ ክልል ሕዝብ ላይ የተመሠረተ የአማራ ብሔራዊ ንቅነቄ (አብን) በሚል ድርጅት መመሥረቱም ይታወቃል፡፡

በሌላው ወገን ለብሔር ማንነት ነው ቅድሚያ የምንሰጠው፡፡ ስለሆነም የፌዴራል ሥርዓት አወቃቀሩ በቋንቋና በሥነ ልቦናዊ አንድነት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ለብዙ ዓመታት በጭቆና ተገዝተናል፣ ባህላችንና ማንነታችን ተሸርሽሯል፣ ተጐድቷል፣ የሥነ ልቦና ጥቃት ተፈጽሞብናል፡፡ ስለዚህ በባህላችን፣ በሥነ ልቦናችንና በቋንቋችን ያለምንም መሸማቀቅና ተፅዕኖ መጠቀም አለብን የሚለው ቡድንና በግንባር ቀደምትነት የሚመራው በኦሮሞ ልሂቃን ነው፡፡

ይኼንን አቋም የሚደግፉትና የሚያራምዱት ከኦሮሚያ ውጪ በርካታ ሌሎች ብሔርና ብሔረሰብ ሕዝቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ የትግራይ፣ የሶማሌ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ የመሳሰሉ ልሂቃንም እዚሁ ቡድን ውስጥ የሚካተቱ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም ይኼ ቡድን በርካታ ደጋፊዎች አሉት፡፡ የዚህ ዓይነት አደረጃጀት የብሔርና ብሔረሰብ ጥያቄዎችን የመለሰና ለአገራዊ አንድነት መፍትሔ ያመጣ ነው ብለው የሚከራከሩም ብዙ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አሁን ሥልጣን ላይ ያለው ኢሕአዴግም ይህን ሐሳብ ነው የሚያራምደው፡፡ በሕገ መንግሥቱም የተቀመጠው ይኸው በብሔር ላይ የተመሠረተው ማንነትና የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር በመሆኑ፣ ይኼንኑ ሐሳብ የሚቃወሙ ኃይሎች በሌላ በኩል የለውጥ ኃይሉን መቃወምና በመታየት ላይ የሚገኘውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል መጋረድ ይሆናል የሚለው ሌላው ሥጋት ነው፡፡

ማንነቱ በዜግነት ላይ ይመሥረት የሚለው ቡድን ጠባብ ብሔርተኛ፣ የጐሳ ፖለቲካ፣ የዘር ፖለቲካ፣ ወዘተ በሚል ሌላውን የሚያሸማቅቅና የሚያንኳስስ የእርግማን ዓይነት ነው፡፡ ሌላውን ወገን የማያሳምን እኔ ነኝ የማውቅልህ ዓይነት ከሚል ፕሮፓጋንዳ ወጣ ያለ፣ በሁለቱም ጥቅምና ጉዳት ላይ በሳይንሳዊ ትንታኔ የተመሠረተ ማብራሪያ እንኳን ሲሰጥ አይደመጥም፡፡ በዚህ ሰበብ ሌላውን ወገን ለማሳመንም አልተሠራም፡፡ በአጠቃላይ በሁለቱም ቡድን ተቀራርቦ በመከባበርና መቻቻል መወያየት አልተቻለም፡፡ ሁለቱም በአሜሪካ ተመሥርተው ወደ አገር ቤት የገቡና በመግባት ላይ የሚገኙ ወካይ የቴሌቪዥን ጣቢያም አላቸው፡፡ በቴሌቪዥናቸውም ሕዝቦችን ከማቀራረብና ወደ አንድነት ከማምጣት ይልቅ የአንዱ ሐሳብ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በሚያደርጉት ፉክክር፣ ሕዝቦችን ወደ መለያየትና መከፋፈል ይወስድ ይሆን የሚልም ሥጋት አለ፡፡ ምልክቶችም ታይተዋል፡፡ በብሔር ማንነት የሚያጠነጥነውም እንደ ቀድሞው በኢትዮጵያ አንድነት ስም በጭቆና ሊገዛን የሚሻ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች ናቸው በሚል በሩቁ የሚኮንን እንጂ፣ ስለዚሁ አደረጃጀት ጥቅም የሚያስረዳበት መድረክ አልተመቻቸም፡፡

ይህ የማንነት ጉዳይ ወደ ኋላ ከዳግማዊ ምኒልክ የኢትዮጵያ የአሁኑ አገራዊ ቅርፅ ምሥረታ ሒደት የኦሮሞን ሕዝብ በአገዛዝ ሥርዓታቸው በማጠቃለል የገዳ ሥርዓቱ እየተዳከመ መምጣት ጋር ይያያዛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ አንድ ለማድረግ ሲሠሩ የነበሩት ሥራዎች በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥትም ተጠናክረው መቀጠላቸውና ይህ የኦሮሞን ሕዝብ ማንነትን የሚቀይር፣ ባህሉን የሚጐዳ ተብሎ በመወሰዱ በመሆኑ የተማረው የኦሮሞ ኃይል እየጨመረ ሲመጣ፣ በአካሄዱ ላይ ተቃውሞ የመስፋፋት ውጤት የመጣው ነው፡፡

መስከረም 29 ቀን 2011 ዓ.ም ምሽት ዋልታ ቴሌቪዥን ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ ውስጥ አቶ ዳውድ እናትና አባቱ ያወጡላቸው ስም መገርሳ መሆኑን፣ ትምህርት ቤት ሲገቡ “ፍሬው” ተብለው እንዲጠሩ ትምህርት ቤት ማድረጉን ሲገልጹ በማንነትህ እንድታፍር ስምህ ሁሉ ወደ አማርኛ ይቀየራል የሚል አንድምታ ያለው ሐሳብ ነው የሰነዘሩት፡፡ የሌሎችንም ብዙ ኦሮሞዎች ስም ወይም የአባት ስም ትምህርት ቤት ሲገባ ወደ አማርኛ እንዲቀየርም ተደርጓል፡፡ አማርኛን አስተካክሎ ባለመናገር በብዙ ኦሮሞዎች ላይ የማሾፍና የመሳለቅ በደሎች ደርሰዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኦሮሞነታቸውን ለመደበቅም የተገደዱ ብዙዎች ነበሩ፡፡

በዚህ ምክንያት በ1950ዎቹ የባሌ ኦሮሞ በጄኔራል ዋቆ የሚመራው የብሔር ጥያቄ፣ በ1960ዎቹ የኦሮሞ ልሂቃን ትግል በፊውዳል ሥርዓቱ ላይ የመደብ ትግል ማካሄድ ብቻ ሳይሆን የማንነት ጥያቄ ትግልም ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የተመሠረተው፡፡ በዚያን ጊዜና ከዚያ በፊት የነበረው በደል ለዚህ ዓይነት ድርጅት መመሥረት ተገቢነት እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ሊታሰብ አይገባም ብሎ መከራከር አያስችልም፡፡ በወቅቱ ሌላው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ የኦሮሞ ሕዝብ የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት በሶሻሊስት ሥርዓት በመደብ ትግል ለመፍታት፣ የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) የሁሉንም ብሔርና ብሔረሰብ አባላትን የያዘ ማለት ይቻላል የፖለቲካ ድርጅት መሥርቶ፣ ከደርግ ጋር በመሥራት ሕዝቡን በማንቃት በውስጠ ትግል ለውጥ ማምጣት ይቻላል በሚል ያደረጉት ትግልም ሊሳካ ባለመቻሉ የብሔርተኝነት ትግሉ የበለጠ እንዲገፋበት ተደርጓል፡፡

በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ጭቁኖች አንድነት ትግል (ኢጭአት) የሚል በዋነኛነት በኦሮሞ ልሂቃን የሚመሩትና የሲዳማ፣ የጋሞ፣ የሌሎች የደቡብ ብሔረሰቦች ልሂቃን የተሳተፉበት ድርጅትም ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነት ግንባታ የሌሎች ብሔረሰቦችንም የሚነካ ስለነበር የሌሎች ብሔረሰቦች ልሂቃንም የዚሁ የተቃውሞ አካል ነበሩ፡፡ የዚህ ድርጅት አባላት የነበሩት የኦሮሞ ልሂቃን በኋላ ወደ ኦነግ የተቀየሩ ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ምክንያት ነው ደርግ መውደቂያ ላይ በርካታ የታጠቁ የብሔረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩ የሚባለው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ሲይዝ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ነው በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓት እንዲዘረጋ ያደረገው የሚባለው፡፡ ስለዚህ ለድርጊቱ መከናወን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በገዛ ፍላጐታቸው ሆን ብለው ሕዝቦችን በመከፋፈል አገሪቷን በብሔር ማንነት ጠፍጥፈው እንደሠሩ የሚደረገው ፕሮፓጋንዳ ትክክል አይደለም፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች በዞን ደረጃ ብቻ መደራጀት የሚገባቸውን በክልል ደረጃ ማሳደጉ አስፈላጊ አልነበረም የሚሉ አሉ፡፡  ከአገራዊ አንድነት ይልቅ ብሔራዊ ጉዳዮች ከሚፈለገው በላይ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል የሚሉ ትችቶች መሬት የሚወድቁ አይደሉም፡፡ ድርጊቱም ለከፋፍለህ ግዛም አግዞ ሊሆን ይችላል፡፡

ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩት እንደ ኦነግና ሌሎች አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሕወሓት፣ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር፣ የሲዳማ አርነት ግንባር፣ የጋምቤላ፣ የቤንሻንጉል፣ የአፋርና ሌሎችም ጥያቄዎችን ጨፍልቆ በኢትዮጵያዊነት ማንነት ሥር በጂኦግራፊ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት የሚቻል አልነበረም፡፡ ይህን ለማድረግ ቢሞከር አገሪቱ የመበታተን ዕጣ ነበር የሚገጥማት፡፡ በወቅቱ እነ መለስ አማራጭ ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በእርግጥ የፌዴራል ሥርዓት ያለ ዴሞክራሲ ውጤታማ መሆን ስለማይችል፣ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነውና የአግላይነት ባህርይ የነበረው በጠንካራ ማዕከላዊነት ላይ የተመሠረተው አገዛዝ ለሌላ አመፅ ሕዝቡን አነሳስቷል፡፡ በሶቭየት ኅብረትና በዩጎዝላቪያ ብሔር ተኮር ፌዴራል መፈራረስና የአገሮች መበታተንም ውጤት፣ በማዕከላዊነት በአንድ ፓርቲ አመራር ሥር መውደቅና የዴሞክራሲ መገደብ ነው ተብሎ ይነገራል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ማንነት ተደጋጋፊ ወይስ ተገዳዳሪ?›› በሚል ርዕስ ሪፖርተር ጋዜጣ ቅጽ 24 ቁጥር 1922 መስከረም 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ለወጣው በእንግሊዝ ኬል (Keele) የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና በኢትዮጵያ አካባቢ የሕግና የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያዊነትና የብሔር ማንነትን በተመለከተ የምርምራቸውን ግኝት ካቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ተቀነባብሮ የተወሰደው፣ ‹‹ኢትዮጵያዊነትና የኦሮሞ ማንነት ከመደጋገፍ ይልቅ ተገዳዳሪ የሆኑት፣ ኢትዮጵያዊነት ራሱን ከሁሉ የበላይ የሆነ አድርጐ በመቅረፁና ይኼንንም በተለያዩ ግዙፍ ታሪካዊ ዳራዎች በማስደገፍ በፖለቲካ ላይ ብቸኛ የበላይ በመሆኑ፣ በተቃራኒው ደግሞ ኦሮሙማ (ኦሮሞነት) ጨቋኝና የበላይ ነው ብሎ የተገነዘበውን ኢትዮጵያዊ ማንነት በመቃረን ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ምክንያት ነው፤›› ሲሉ ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ማንነት ብቸኛ የበላይ ሆኖ ራሱን የሚገልጽ ስለመሆኑ ሦስት ማሳያዎችን አወል ቃሲም አሎ ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያዊ ማንነት ራሱን የሚገልጸው በኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች መሆኑንና ኢትዮጵያዊነት ነፃ (Liberal)፣ የሠለጠነ (Civilized)፣ የመከባበርና የእኩልነት ምልክት የሞራል ልዕልና ያለው ቢሆንም፣ ጠባብ ብሔርተኛ ኃይሎች ሊፈታተኑት የሚሞክሩት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊነት ሌሎች ማንነቶች ራሳቸውን በአማራጭነት እንዲገልጹ የመጫን ባህሪው ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው (Universal) አድርጐ ራሱን በመግለጽ፣ በሥልታዊ መንገድ ሌሎችን የሚያገልጽ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የዚህ ማንነት መገለጫ የሆነውን ቋንቋ መናገር፣ የኢትዮጵያዊነት ሞራል ደረጃዎችን በሚገባ መጠቀምን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሁሉን አቃፊ መሆኑን የሚገልጽ ነገር ግን አግላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ኢትዮጵያዊነት የእውነት መገለጫ፣ ከፖለቲካና ሥልጣን ገለልተኛ የሆነና ራሱን ችሎ የሚቆም እውነት እንደሆነ አድርጐ ራሱን የሚገልጽ ማንነት መሆኑን፣ በዚህም ውስጥ ሁሉንም እንደሚወክል የሚያምን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያዊነት ብቸኛ የበላይ እንደሆነ የሚያምንና በሁሉም ተቀባይነት ያለው አድርጐ ራሱን የሚገልጽ ቢሆንም፣ ውስን የሆነ ብሔረሰብና ማንነትን እንደሚወክል የጠቀሱት ምሁሩ በአመዛኙ የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል (የአማራና የትግራይ) ባህል፣ ትውፊት፣ ፊደልና የአኗኗር ዘይቤ በማስፋፋት ወካይ ማንነት (Ethiopinization) ማድረግ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በሌላ በኩል ኦሮሞነት የኢትዮጵያዊነት ተፅዕኖ ሰለባ፣ ማንነቱና ተደማጭነቱ ኢፍትሐዊ በሆነ ጥቃት የተነጠቀ አድርጐ የሚያምን፣ ይኼንንም ታሪካዊ ኢፍትሐዊነት በእምቢተኝነት ለመቀየር የተነሳ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ኦሮሞ የኢትዮጵያ ማኅበራዊና አገራዊ ድንበር አካል ቢሆንም፣ በተግባር ግን የኢትዮጵያ አካል የሆነ ነገር ግን እንደ ቡድን ተቆጥሬያለሁ፣ ድምፅ ያለው ድምፅ አልባ ሆኛለሁ ብሎ የሚያምን፣ የተጠቂነት ስሜት የተጫነው መሆኑንና የኦሮሙማ (የኦሮሞነት) ማዕከላዊ ችግር ኢትዮጵያዊነትን የማይቀበል ሆኖ፣ በራሱ ልሂቃን እየተገለጸ ያለ ማንነት ነው፤›› ሲሉም ዶ/ር አወል አስረድተዋል፡፡

በዚህ ዜግነትን መሠረት ያደረገውን ማንነት የሚያራምዱ ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ አንድነት የማቀንቀን ሐሳብን ትርጉም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔርን መሠረት ያደረገውን ማንነት ወርውረው ሙሉ በሙሉ ወደ እነርሱ ሐሳብ እንደመጡ የወሰዱ ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር ዓብይ የመጡት ከየት ነው? በአሁኑ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብሔራዊ ማንነትን በመተው የት ላይ ቆመው ነው ዜግነትን መሠረት ያደረገ ማንነት ብቻ የሚያራምዱት? በዚህም በቂ የፖለቲካ ትንተና ያለማድረጋቸውና በስሜት ራሳቸውን ብቻ በማዳመጥ ብሔርን መሠረት የሚያደርገው ማንነት ኢትዮጵያን እንደሚከፋፍልና የሚበታትን እንደሆነ፣ የዜግነት ማንነቱ ብቻ ለአገራችን ብቸኛ ፍቱን መፍትሔ አድርገው  መቁጠራቸው የዜግነት ማንነት አራማጆች ሌለኛው ስህተት ይመስለኛል፡፡

ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ በ1966 ዓ.ም. አብዮት ወቅት ከኦሮሞ ብሔርተኞች ጋር በትግል ታክቲክ ልዩነት ቅራኔ ፈጥረው እንደነበር ይነገራል፡፡ የቅራኔውም ምንጭ የኦሮሞ ጥያቄ በኢትዮጵያ አንድነት በዜግነት ማንነት ይፈታል የሚለው አቋማቸው፣ በሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኝነት በሚያራምዱ እንደ ኦነግ በመሳሰሉት ተቀባይነት ያለማግኘቱ ነበር፡፡ ዶ/ር ዓብይ ምንም እንኳ ከዶ/ር ኃይሌ ፊዳ የሚያመሳስሏቸው ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ በዚህ አገራዊ ጉዳይ እንደ ዶ/ር ኃይሌ ፊዳ መደበቂያ ወይም መሸሸጊያ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ምሽግ ያፈርሳሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ይህን ምሽግ እንዲያፈርሱም ግፊት መፍጠሩ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ቢያንስ በአንድ እግራቸው በምሽጉ ውስጥ ሆነው ቢሠሩ ነው ለሁሉም ተመራጭነት ያለው፡፡ በዚህ ምክንያት ይሆናል አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶችና አቶ ዳዊድ ኢብሳ በዚህ በመደመር የዶ/ር ዓብይ የፍልስፍና ሐሳብ ላይ ጥርጣሬ የፈጠሩት፡፡ የአዲስ አበባ የአስተዳደር የባለቤትነት ጉዳይን በተመለከተ ሲነሱ የነበሩ ውዝግቦችም ከዚሁ ከማንነቱ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡

የአዲስ ከተማ አስተዳደር ባለቤትነት ጉዳይና ስያሜ ያስከተለው ልዩነት

የአዲስ አበባ ከተማ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት እንብርት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት ዋና ከተማና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥትም መቀመጫ ዋና ከተማ ናት፡፡ በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ስትስፋፋ ነባር ነዋሪ ተፈናቅሏል፡፡ ሕዝቡ በቂ ካሳ አላገኘም፡፡ ለድህነት ተዳርጓል፣ ተታሏል፣ ተጭበርብሯል የሚሉ ቅሬታዎች ከሕዝቡና ከኦሮሞ አክቲቪስቶች ሲሰማ ነበር፡፡ የኦሮሞን ወጣቶች (ቄሮዎች) ለአመፅ መነሳሳትና ለዚህ ለውጥ መምጣት መነሻ ምክንያት የሆነው የአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም፣ በ2008 ዓ.ም የተጀመረው አመፅ ከዚሁ ከአዲስ አበባ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነው፡፡

ሁለተኛ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ ሲቀየር፣ በኦሮሞ ልሂቃን በተለይም በመጫና ቱለማ ማኅበር ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳበትና ብዙዎች የታሰሩበት፣ ከአገር የተሰደዱበት ጉዳይ ነበር፡፡ይኸው ጉዳይ አሳሳቢ ሆኖ በመገኘቱ በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ኢሕአዴግ በደረሰበት የፖለቲካ ቀውስ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ የሆነው የአዲስ አበባ ዋና ከተማ፣ በኢሕአዴግ ተቀባይነት አግኝቶ ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) መቀየሩም የዚሁ ጥያቄ አካል ነው፡፡ ሦስተኛ በ27 ዓመታት የኢሕአዴግ አስተዳደር የአዲስ አበባን ከተማ በከንቲባነት ሲያስተዳድሩት የቆዩት አብዛኞቹ ከንቲባዎች የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑበትም የፖለቲካ አንድምታ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን በአቶ ዳዊድ ኢብሳ በሚመራው የኦነግ አዲስ አበባ መግባትና ትልቅ የድጋፍ ሠልፍ ከተደረገና በቡራዩና አዲስ አበባ ከተከሰተው የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል ጉዳት መድረስና የንብረት ውድመት ጋር በተያያዘ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የተቃውሞ ሰላማዊ ሠልፍ ሠልፈኞች ይዘዋቸው የወጡት መፈክሮች በቅርቡ የተሾሙት የኦሮሞ ተወላጅ ምክትል ከንቲባው ሥልጣን እንዲለቁ፣ የኦሮሚያ መሥሪያ ቤቶች ከአዲስ አበባ እንዲወጡ፣ የሽግግር መንግሥት መቋቋም እንዳለበት፣ ወዘተ የመሳሰሉት የኦሮሞን ሕዝብ ክብር የሚነኩ ነበሩ፡፡

 አንዳንድ የግል የብዙኃን መገናኛ አውታሮችም ይህን ጉዳይ ማውገዝ ሲገባቸው ተባባሪ የመሆንና የማባባስ ሁኔታዎች ውስጥ መግባታቸው የኦሮሞ ልሂቃንን አበሳጭቷቸዋል፡፡ በእርግጥ ኤርትራ ቆይቶ የነበረው ኦነግ አዲስ አበባ ከመግባቱ ጋር ተያይዞ ከኦሮሞ ውጪ በሆኑት በአንዳንዶች ፍርኃትና ሥጋት ይንፀባረቃል፡፡ ይህ ለአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችና ለሌሎች ጥርጣሬና ፍርኃት ምክንያት የሆነው ደግሞ፣ ኢሕአዴግ በኦነግ ላይ ያካሄደበት የማጥላላት ፕሮፓጋንዳ ያስከተለው ውጤት ነው፡፡ አንድ አዲስ አበባ ያደገች 40 ዓመት አካባቢ ዕድሜ ያላት ሴት ለዚያውም የኦሮሞ ተወላጅ የሆነች፣ ስለኦነግ ስትገልጽልኝ፣ “እኔ እኮ ኦነግ የሚባለው የተንጨፋረረው ጥፍሩ ትልልቅ የሆነ፣ ቀንድ ያለው፣ የሚቧጭርና ሰውን የሚበላ ጭራቅ ዓይነት ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካስ እንደ እኛው መልክ ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው፤›› ያለችኝ አቶ ዳውድ ሲገቡ በአውሮፕላን ማረፊያ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫና አብዮት አደባባይ በሕዝባዊ አቀባበል ያደረጉትን ንግግር ካዳመጠች በኋላ፡፡

ይህ የሚያሳየው ግንባሩ ለሌሎች ሕዝቦች በተለይ በወጣትነት ዕድሜ ክልል ላሉት እንዴት እንደተሳለ ነው፡፡ ይህ በኢሕአዴግ የተፈጸመው ኦነግን የማጥላላት ዘመቻ የኦሮሞ ሕዝብ ቀድሞውን ተረድቶ ስለነበር ትክክል አለመሆኑን በመገንዘቡ ለግንባሩ የነበረው ድጋፍ አልቀነሰም፡፡ በግንባሩ ባንዲራ ሥር ነበር በቅርቡ የቄሮና የቀሬ ትግልም ሲካሄድ የነበረው፡፡ እነ ክቡር ዶ/ር ዓብይና ለማም ኦነግ ይዞት የተነሳውን የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ ነው ሲታገሉ የቆዩት፡፡ ልዩነት ይኖራል ቢባል እነ ዶ/ር ዓብይ የሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በኢትዮጵያ አንድነት ሥር በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዝርጋታ ነው ሲሉ፣ ኦነግ የኦሮሞን ሕዝብ ዕድል የሚወስነው ሕዝቡ ራሱ ነው የሚለው እስካሁን የታየው የሕዝቡ ፍላጐት ደግሞ ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት መኖር እንጂ፣ ለብቻ መሆን ምልክት ያሳየበት ሁኔታ ስለሌለ  በሁለቱ መካከል የሚታይ ልዩነት የለም ማለት ይቻላል፡፡ የኦነግ አመራርም በ1983 የሽግግር መንግሥት ቻርተር ፈርሞ ከኢሕአዴግ ጋር ለመሥራት ሲገባም ሆነ አሁንም የገባው በዚሁ በኢትዮጵያ አንድነት ሥር ከሌሎቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት እንጂ ከዚያ ውጪ ለመሄድም ሆነ የኦሮሞ ሕዝብ እንዲከፋፈል ይደርጋል የሚል እምነት የለም፡፡ ይህንን ዓይነቱን ክፍፍል ሕዝቡም ዕድል አይሰጥም የሚልም እምነት በመኖሩ፣ ሌላው ሕዝብ  የሚሠጋበት ሁኔታ ሊኖር አይገባም፡፡

በአዲስ አበባ መስከረም 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተካሄደው ሰላማዊ ሠልፍ የአጀንዳው ባለቤቶች ግልጽ ባልሆኑበት፣ ይህን ጉዳይ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች  ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሰላምና መረጋጋት የሥራዎች ላይ ማተኮር ሲገባቸው፣ በከተማው ሕዝብ መከፋፈልና ጥርጣሬን የሚያመጣ ጉዳይ ላይ መግለጫ መስጠታቸው ትክክል አልነበረም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጥያቄውን ማንሳቱ መብት ሆኖ የአንዳንድ አክቲቪስቶች ግፊት ቢኖርም፣ ይህ አጀንዳ በአሁኑ ጊዜ የቅድሚያ መነጋገሪያ እንዲሆን ማድረግ አይገባም የሚለው አባባል ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ዶ/ር አወል ቃሲም አሎ እንዳሉት የኦሮሞ ልሂቃን በተለይ ለረዥም ዓመታት በትጥቅ ትግል የቆዩት ስንትና ስንት ጓዶቻቸውን የቀበሩትና ለዚህ ጉዳይ ፍዳ ያዩት፣ በስሜት መጐዳት ውስጥ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚህ ሳቢያ ቶሎ ብሶት ቢሰማቸው አይገርምም፡፡

ዜግነትን፣ ማንነትንና ብሔርን መሠረት በማድረግ ላለፉት 27 ዓመታት በኦሮሚያና በአማራ ሕዝቦች ልሂቃን መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ልዩነት ወደ አንድነት በመምጣት፣ በጋራ የዴሞክራሲ ሥርዓት በማስፈን በኩል ደንቃራ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በውጭ በሚኖሩ ዳያስፖራዎች ጭምር የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን በዚህ ምክንያት ተግባብተው መሥራት ባለመቻላቸው ድንበር አብጅተው ተራርቀው ሲሠሩ ነው የቆዩት፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የኦሮሞ ወጣት ተወካዮች ጣና የኛም ነው (ጣና ኬኛ) በማለት ሐይቁን ከእንቦጭ ለመታደግ እኛም ድጋፍ ማድረግ አለብን በሚል ወደ ባህር ዳር መጓዛቸው፣ ቀጥሎም በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት መሪዎች የተማራው የኦሮሞ አባገዳዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎችን ያቀፈ ቡድን ወደ ባህር ዳር በማቅናት የአማራ ብሔራዊ ክልል መሪዎችና ሕዝቡም ከፍተኛ አቀባበል አድርጐላቸው፣ በሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃን መካከል የነበሩት ልዩነቶችና የእርስ በርስ መጠራጠርን የቀነሰ ትልቅ ሥራ መከናወኑ የሚታወስ ነው፡፡

ይህም በኢሕአዴግ ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ ውጤታማ በማድረግ በኩል፣ በተለይ በኢሕአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ላይ ወሳኝ ሚና የነበረው በመሆኑ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የኦሮሞና የአማራ ጥምር መንግሥት ዓይነት እንዲሆን አድርጐታል፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃን የተፈጠረው መግባባት ወደ ሕዝቡ ዘልቆ የሕዝቡን አንድነትና ኅብረት የበለጠ ያጠናከረ በመሆኑ፣ ለአገሪቱ አንድነት፣ ሰላምና ብልፅግና ትልቅ ሚና የሚኖረው ነው ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር በተገናኘ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች የአማራ ሕዝብ በቁጥር ከኦሮሞ በእጥፍ ይበልጣል፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ አስተዳደር ሥር ከሆነች ኦሮሚያ ትገነጠላለች፣ ኦሮሞ ያልሆነው ሕዝብ በሁለተኛ ዜግነት ነው የሚታየው፣ ይህ ከሚሆን የሕይወት መስዋዕትነት እከፍላለሁ የሚሉ ሁለቱን ሕዝቦች የሚያጋጩ የትኛውን ወገን እንደሚወክሉ የማይታወቁ ፍላጐታቸውን በሕዝብ ላይ በመጫን እንደ ጋዜጠኝነት ከሚሠሩ፣ ከጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር ያፈነገጡ የአክቲቪስት ሚናን በጋዜጠኝነት ስም የሚያካሂዱ አንዳንድ ጋዜጠኞች ቴሌቪዥናቸውንና ሬድዮናቸውን ለዚህ ተግባር ከአሜሪካ በማሠራጨት፣ ይህንን የሁለቱን ሕዝቦች አንድነትና ትብብር ሲፈታተኑ ነበር፡፡ ሌሎች የከተማው ነዋሪዎችም በሁለተኛ ዜግነት ለምንድነው የሚኖሩት? አሁን እየኖሩ ካሉት ምን ልዩነት ይመጣል? ይህ ከሆነ እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ በአዳማ ከተማና በሌሎች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የሚኖሩት ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች በሁለተኛ ዜግነት እየኖሩ ነው ማለት ነውን?

ይህ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ሕዝቦችን፣ በተለይ በስንት ጥበብ የተቀራረበውን የአማራና የኦሮሞ ልሂቃን ዳግም ለማጋጨት የሚከናወነውን ሥራ ለሁለቱ ሕዝቦች የግጭት መነሻ በፍጹም ሊሆን አይገባም፡፡ እስቲ ሁኔታዎችን በፅሞና እንይ፡፡ የከተማው ከንቲባ ኦሮሞ ቢሆን የሚያስከትለው ጉዳት ምንድነው? መቼም ሕንፃዎቹ፣ ድርጅቶቹ፣ መኖሪያ ቤቶቹ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት የሚወሰዱ አይሆንም፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ ባለፉት ዓመታትና በአሁኑም ጊዜ ከተማው በኦሮሞ ተወላጆች ከምትተዳደረው በምን ይለያል? ይህ በነፃነት እየኖረ ያለውና የሚኖር ሕዝብ ይቅርና የኦሮሞ ሕዝብ በጦርነት ያሸነፈውን ምርኮኛ እንኳን በሞጋፈቻ ሥርዓት የራሱ ሕዝብ አካል አድርጐ ደግፎት የሚያኖር ባህል ያለው፣  በቅኝ ገዥነት ሌላውን ሕዝብ በሁለተኛ ዜግነት የሚያኖር ታሪክም ሆነ ተሞክሮ የለውም፡፡ እነዚህ የቀረቡት ሥጋቶች አግባብነት የሌላቸው መሆኑን ለማንሳት እንጂ፣ ጉዳዩን ለክርክር ለመጋበዝ አይደለም፡፡ ጉዳዩ የሥጋትና የልዩነትም ምንጭ ከቶውኑ ሊሆን አይገባም፡፡ ይህ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ ቅድሚያ የሚሰጠው አጣዳፊ ጉዳይ ባለመሆኑና ከሕገ መንግሥት ማሻሻል ጋርም የተያያዘ ስለሆነ፣ የከተማው የልማት ሥራ ሳይስተጓጎል ጊዜ ተሰጥቶት በተረጋጋ ሁኔታ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታን ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ጋር በተገናዘበ መንገድ ውይይትና ድርድር ተደርጐበት መፈታት ያለበት ነው፡፡

ይህ የማንነት ጉዳይና ተያያዥነት ያለው የፌዴራል አወቃቀር ሥርዓት  አንደኛው ወገን ሌላውን ማሳመን የማይቻል ሆኖ በክርክር ላይ ይገኛል፡፡ በእርግጥ በዚህ ረገድ በሁለት ጫፍ የረገጡ ማለት አንድ አገር አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ባህል የሚመስል የአሀዳዊ ሥርዓት ዓይነት አመለካከት ፍላጐቱም ሊኖር ቢችልም ጐልቶ በመድረክ ሲወጣ አይታይም፡፡ ወደ መገንጠል ዓይነት የሚሄድ የብሔርተኝነት ስሜትም በአገራችን አሁን አይታይም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱንም የሚቃወም ፊት ለፊት የወጣ አስተሳሰብም የለም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በቋንቋ ሳይሆን በጂኦግራፊ ይሁን ከማለት ውጪ፡፡  በዚህ ሁኔታ ለውጡን በማስቀጠል የዚህን አገር አንድነትና ህልውና ለማቆየት ከተፈለገ፣ ላለመስማማቱ መስማማትም ይሁን አንድ መፍትሔ ላይ መደረስ ግን ያስፈልጋል፡፡

የመፍትሔ ሐሳቦች

በዚህ የማንነት ጉዳይ ሁላችንም ልንነጋገር ይገባል፡፡ በእኔ አስተያየት ችግሮቹን መረዳት የመፍትሔው ግማሽ መንገድ በመሆኑ፣ በመጀመሪያ በችግሮቹ መነሻ ላይ መግባባት ያሻል፡፡ ሁለተኛው የአሁኑን የአገራችንን ሁኔታ ገምግሞ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ክፍት በሆነና በመረጃ በበለፀገ አዕምሮ ውይይቶች ማካሄድ ነው፡፡ ይህ ሒደት ረዥም ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ ይኸው እስከሚደረግ በአሁኑ ጊዜ ባለው ሕገ መንግሥት ለመሄድ መስማማት ነው መፍትሔ ሊሆን የሚችለው፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ በቋንቋ በብሔር ማንነት ላይ መመሥረቱ የራሱ ችግር እንዳለው፣ አንዳንዶች ጥፋት ፈጽመው የሕዝባቸውን ሰብዓዊ መብት ረግጠውና ወንጀል ሠርተው በብሔራቸው ውስጥ እንደሚደበቁና ለዚህ ተግባራቸው ተጠያቂ እንዳይሆኑ ብሔራቸውን በማነሳሳት ግጭት እንዲፈጠር እንደሚያስደርጉ፣ በዚሁ በአገራችን በቅርቡ ዓይተናል፡፡ የተደበቁበትንም ብሔር ከሌላው ሕዝብ በመነጠል ሕዝባቸውን እንደፈለጉ ለመግዛት እንዲያመቻቸውም ጥረት ማድረጋቸውም ተስተውሏል፡፡

የዚህ ዓይነት አደረጃጀት በርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሠረተ ምርጫ በማካሄድ ረገድ የራሱ አሉታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዕሙን ነው፡፡ እንደሚሰማው በአንዳንድ በተለይ ታዳጊ ክልሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ከፍተኛ እንደሆነ፣ የሕግ የበላይነት መከበር በችግር ላይ የሚገኝና ሙስና (ሌብነቱ) ከፍተኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ለጊዜውም ቢሆን በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥቱ እነዚህን ሁኔታዎች እንዲያስተካክል ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 16፣ “በማንኛውም ክልል ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱና ክልሉ ድርጊቱን ማቆም ሳይቻል ሲቀር፣ በራሱ አነሳሽነትና ያለ ክልሉ ፈቃድ ተገቢው ዕርምጃ እንዲወሰድ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ጥያቄ ያቀርባል፣ በተደረሰበት ውሳኔ መሠረት ለክልሉ ምክር ቤት መመርያ ይሰጣል፤” ይላል፡፡ የክልል መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የመሳሰሉት ጥፋቶች ፈጽመው በማስረጃ ከተረጋገጠ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማለትም የክልል መንግሥት ጥያቄ ወይም ያለመከሰስ መብት መነሳት መመዘኛ ጣልቃ ገብቶ ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብ የሚያስችል ሁኔታን መፍጠርንም ያካተተ የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ለወደፊቱ በማድረግ፣ የፌዴራል መንግሥትን የበለጠ ማጠናከርና የክልል መንግሥታትን በበጀት አጠቃቀም፣ በሰብዓዊ መብት አጠባበቅ፣ በሕግ የበላይነትና በዴሞክራሲ ሥርዓት፣ ወዘተ በመሳሰሉት አተገባበር ላይ ክትትል ማድረግንም ይጠይቃል፡፡

በብሔር ማንነት የሚኖረውን አደረጃጀት የሚታዩትን ሥጋቶች በዚህ ዓይነት በመቀነስና ለወደፊቱ ሁኔታዎችን በመገምገም፣ ሕዝቦች መብታቸውን ካጣጣሙና ምናልባት የዚህ የብሔር አደረጃጀት ከጊዜ በኋላ ወደ ዜግነትና በርዕዮተ ዓለም ላይ ወደ ተመሠረተ የፖለቲካ አደረጃጀት መምጣት የሚቻል ከሆነ በጊዜ ሒደት ማየት እንጂ፣ አሁን በአገራችን ካለው ተጨባጭ ሁኔታና ከብሔር ብሔረሰቦች ፍላጐትና ሥነ ልቦና ዝግጅት አንፃር ይህን በብሔራቸው የመደራጀት መብታቸውን ማክበሩ አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩን ከሥር መሠረቱ በማጥናት ወደ መፍትሔ መሄድ ነው የሚሻለው እንጂ፣ ቀድሞ ኢሕአዴግን ለችግሩ መፈጠር ተጠያቂ አድርጐ ማቅረብና ችግሩን እነ ዶ/ር ዓብይ የኢትዮጵያን ስም ደጋግመው ስለሚያነሱ፣ በኢትዮጵያዊነት ወይም በዜግነት ማንነት ብቻ ይፈታሉ ብሎ መጠበቅ አይቻልም፡፡ በዚህ ሒደት አንዱ ወገን በሌላው ላይ የፖለቲካ የበላይነት ለማግኘት ወይም አሸናፊ በሚሆን መንገድ ሳይሆን በሠለጠነ መንገድ በመመካከር፣ በመደራደርና በመተሳሰብ የሁሉንም ፍላጐት በእኩልነት የሚያሟላ ሁሉም አሸናፊ በሚሆንበት ነው ችግሮች መፈታት ያለባቸው፡፡

ልዩነቱ ሳይራገብ አንደኛው ሐሳብ ሳይሞት በጠረጴዛ ላይ ቆይቶና አስፈላጊ ከሆነም መረጋጋት ተፈጥሮ፣ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ መስመር ከያዘና አገሪቱ ተረጋግታ ሰላም ሰፍኖ  ሥራ አጥነትና ድህነት ላይ የሚደረገው ትግል ፍሬያማ ከሆነ በኋላ፣ እንደገና ተነስቶ ውይይት ቢደረግበትና መግባባትም ካልቻለ በሕዝብ ውሳኔ ከፍፃሜ የሚደረስበት ቢሆን ይመረጣል፡፡ ለጊዜው አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አብዛኛው ብሔርና ብሔረሰቦች የተቀበሉትን ብሔርን መሠረት ያደረገው የዜግነት መብትን ባካተተ መንገድ ተቀብሎ መቀጠል የተሻለ መፍትሔ ነው፡፡ ዜግነትን መሠረት ያደረገው የኢትዮጵያዊነት አቋም የሚያራምደው ወገን በዚሁ መሠረት ሐሳብ የሌሎችን መብት ሳይነካ የጐሳ ፖለቲካ፣ የዘር ፖለቲካ የሚል ማጣጣያ የትንኮሳ ቃላትን አስወግዶ፣ ደጋፊዎቹ በቂ ግንዛቤ ኖሮዋቸው ችግር ሳይፈጠር በዴሞክራሲው ምርጫ ተወዳድሮ ሁሉም የሚያገኘውን ድምፅ ተቀብሎ፣ በፓርላማው የራሱን ሐሳብ የሚያንፀባርቅበት ዕድል ሊኖረው በሚችልበት መንገድ ቢሠራ መልካም ይሆናል፡፡ የብሔርተኝነት አራማጆችም በሃይማኖቶች ልዩነት መከባበር እንደተቻለው ሁሉ፣ የሕግ የበላይነትን መሠረት ባደረገና በመከባበር ሁሉም የፖለቲካ እምነቱን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ መብቱ በመሆኑ ይህን መብታቸውን ማክበር የሚያግባባ ይሆናል፡፡

በዶ/ር አወል ቃሲም አሎ አመለካከት አማራጭ መፍትሔ የሚሆነው ከጠንካራ የልዩነት ምሰሶዎች ይልቅ፣ እስከ ዛሬ ትኩረት ያላገኙ የላሉ የልዩነት ገመዶችን ማጥበቅ ተመራጭ ናቸው፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲስ ፍልስፍና የሆነው የመደመር መርህ ግልጽ የሆነ ትርጉምና ዝርዝር ማዕቀፍ ወጥቶለት መተግበር እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል በመተዋወቅና በመግባባት ላይ የተመሠረተ ትብብራዊ አንድነት (Solidarity) መገንባት እንደሚያስፈልግ፣ የዚህ ዓላማ መሠረቱ መታረቅ ሳይሆን የማይታረቁ ፍላጐቶችን የያዘ ማኅበረሰብ መሆንን አምኖ ነገር ግን አንድ የሚያደርጉና የሚያስተሳስሩትን በማስቀደም፣ ተደጋግፎ መኖርን ለመለማመድ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም ያልተማከለ እውነተኛ ዴሞክራሲ የፖለቲካ ሥርዓትን ማስፈንን በምክረ ሐሳብነት አቅርበዋል፡፡

ስለዚህ ስለኢትዮጵያ አንድነት የምንጨነቅ በሥነ ልቦና ተጐድቶ የነበረውን የኦሮሞ ሕዝብ ልሂቃን በማስታመም መጠገን፣ ወይም ማደስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡ የተጐዳ ሰው ብዙ ጩኸት አይፈልግም፡፡ ፍላጐቱ ሁሉ ይሟሉለታል፡፡ መድኃኒትም እንዲቀርብለት ይደረጋል፡፡ መድኃኒቱ ክኒን ወይም መርፌ ሳይሆን የሥነ ልቦና ሕክምና ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ዓይነት ግንዛቤ በመተሳሰብና መቻቻል ነገሮችን በማቅለል መጓዙ ተመራጭ ነው፡፡ በአንድነት የሚኖሩ ባልና ሚስት በዘለቄታ አብሮ ለመኖር የግል ፍላጐቶቻቸውንና ስሜቶቻቸውን በመቀነስ፣ ወይም በመተው ወደሚያስማማ የጋራ ፍላጐትና ባህርይ መምጣት የግድ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ፍቺ ነው ውጤቱ፡፡ እንደ አገርም ሲታሰብ በጋራ ለመኖርና የጋራ አገር ለመገንባት የአንደኛው ወገን የሌለኛውን ወገን ስሜት በማድመጥና ፍላጐቱን ለማሟላት በሚያስችል ሁኔታ በጋራ አሸናፊነት፣ ሁሉም ወገኖች የመመራት አስፈላጊነት አያጠራጥርም፡፡ ጊዜ በሒደት የሚፈታቸው ጉዳዮች ይመጣሉ፡፡ ትዕግሥት፣ መቻቻልና መደማመጥ ብቻ ነው አሁን የሚፈለገው፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...