Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርጅግጅጋ ብትጮህም ሰሚ ጆሮ ያገኘች ግን አይመስልም!

ጅግጅጋ ብትጮህም ሰሚ ጆሮ ያገኘች ግን አይመስልም!

ቀን:

በሀብታሙ ግርማ

ኢትዮጵያዊያን የዓመቱን 13 ወራት በልዩ መገለጫቸው ማንሳታቸው የተለምዶ ነው፡፡ ለምሳሌ በደገኛው ነዋሪ ዘንድ የሐምሌ ወር በነጎድጓድ በታጀቡ ጥቁር ደመናማ ቀናት ይታወሳል፡፡ ይህ ግን ለምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል፣ በተለይ ለሶማሌ ምድር አይሠራም። ሶማሌዎች ‹‹Heeg Heeg›› ብለው የሚጠሩት ባለአሸባሪ ድምፅ ያለው ነጎድጓድና ሐምሌ ወር ትውውቃቸው እምብዛም ነው። ያሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር የመጨረሻ ሦስት ቀናት ግን ባልተለመደ ሁኔታ መላው የሶማሌ ክልል በአስገምጋሚ ነጎድጓድ ተመታ፣ ነጎድጓዱ የተፈጥሮ አልነበረም፣ ራሱን Heego (ነጎድጓዶቹ)  ብሎ የሰየመው የተደራጀ ቡድን የጎሰመው የእልቂት ነጋሪት እንጂ።

ከሐምሌ 28 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የዘለቀው ይህ ሰው ሠራሽ ነጎድጓድ የበርካታ ንፁኃንን ሕይወት በልቷል፡፡ የታዳጊ ልጃገረዶች፣ ወጣት ሴቶችና እናቶችን የሴትነት ክብር ደፍሯል፡፡ የግለሰቦችንና የመንግሥትን ንብረት አውድሟል። በአጥፊዎቹ ላይ ክስ የመሠረተው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ባሰማው የክስ ጭብጥ የጥፋት ኃይሎቹ ድግስ የብሔርና የሃይማኖት ግጭት በማስነሳት እልቂት ማምጣት ነበር፡፡ ነገር ግን በፈጣሪ መልካም ፈቃድና ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ይዘን በቆየነው መንፈሳዊና ማኅበራዊ እሴቶቻችን ሊከሰት ይችል የነበረው ከባድ ጥፋት ቀንሷል።

የዚህ መጣጥፍ ዓላማ የደረሰውን ውድመት እያስታወሱ ለማላዘን፣ ወይም በአዋሽ ማዶዎቹ አፍ ‹ሒራር ለመጥራት› አይደለም፡፡ ችግሩ ከተከሰተ ከዘጠና ቀናት በኋላ ያ ጥቁር ቀን ጥሎት ያለፈውን ጠባሳ ለመሻር የተደረጉ እንቅስቃሴዎችን መገምገም፣ እንዲሁም ጉዳቱን ለመቀነስ ፈጣን እልባት የሚያሻቸውን ጉዳዮች ነቅሶ የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ እንዲሰጡ ለማሳሰብ ነው። 

መንግሥታዊ ማፈናቀል በሶማሌ ክልል አልተጀመረም!

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም በጽሑፎቻቸው ደጋግመው እንዳስነበቡንና እኔም አጥብቄ እንደምደግፈው የተለያዩ ብሔር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊያን ከልዩነቶቻቸው ጋር በአንድ አገር ልጅነት የቆዩት ሦስት ሺሕ ዓመታትን ከተሻገረው መንፈሳዊ ሥልጣኔያቸው በወረሱዋቸው እሴቶቻቸው ነው። ኢትዮጵያዊያን የጥበብ መጀመሪያ ተብሎ በቅዱሳን መጻሕፍት የምናገኘው ትልቅ ሀብት የሆነውን ፈሪኃ እግዚአብሔር መታደላቸው፣ በነቢብም ሆነ በገቢር የምናስተውለው ሀቅ ነው። የዚህ መገለጫ አንዱ ኢትዮጵያዊያን በችግሮቻቸው ወቅት አብሮ የመቆም የቆየ ታሪክ ወይም ማንነት ባለቤት መሆናቸው ነው። በእርግጥም ችግርን በጋራ መጋፈጥ የኢትዮጵያዊነት ልቡ ነው።

ነገር ግን ይህ ዕንቁ ኢትዮጵያዊ ሀብት ባለፉት 25 ዓመታት ያውም መንግሥት ነኝ በሚል አካል በተደጋጋሚ ጥቃት ተሰንዝሮበታል።

በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን ታሪክ መንግሥታዊ ማፈናቀል ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመው በ1990 ዓ.ም ገደማ በኤርትራዊያን ወገኖች ላይ ነበር። በወቅቱአንድን ቡድን ለይቶ ማጥቃትና ማፈናቀል ዘርን ለይቶ ማጥራት (Ethnic Cleansing) ነው፣ መዘዙም ትውልድ የሚተላለፍ የተስቦ ያህል ነው ብለው የሞገቱ በርካታ ምሁራንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሰሚ ጆሮ አላገኙም ነበር።

የሚገርመው ነገር መንግሥታዊ ማፈናቀሉ ከተፈጸመ ሰባት ዓመት እንኳ ሳይሞላ (በ1997 ዓ.ም. የምርጫ ዋዜማ ወቅት) ኢሕአዴግ ዓይኑን በጨው አጥቦ ተበዳይ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዳኘኝ አለ፡፡ የአዞ ዕንባውን እያፈሰሰ የክስ ጭብጡን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሰማ እንዲህ ሲል፣ ‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ፍረድ፣ ጽንፈኛ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ቡድኖች ስብስብ የሆነው ቅንጅት ለአንድትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ‹ትግሬ ወደ መቀሌ› የሚል በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ዘመቻ እየደሰኮረ ነው፣ የአብሮነትህ መሠረት የሆነውን እሴትህን ለፖለቲካ ቁማር አውሎታል።

ለኢሕአዴግ ክስ ምላሽ እንዲሆን ቅንጅት ይህን ብሎ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ አሸናፊ ሐሳብ ስላልነበረውና ምርጫውን ለማሸነፍ የግድ ክስ ማብዛት ነበረበት፡፡ እናም  የኢትዮጵያዊያንን የሥነ ልቦና መሠረት እንደሆነ በሚያውቀውና ሕዝቡ በማይደራደርበት ጉዳይ ላይ የሐሰት ክስ ለማቅረብ ተገደደ።

ፍርዱን ለጊዜው እንተወውና ኢሕአዴግ ከሳሽ ሆኖ በቀረበበት ወቅት፣ የሚመራው መንግሥት በኤርትራዊ ወንድሞች ላይ ለፈጸመው በደል ይቅርታ አልጠየቀም ነበር፡፡ እናም ክስ ለመሰንዘር የሞራል መሠረት አልነበረውም፡፡ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት እንኳ መንግሥታዊ ማፈናቀሉ መልኩን ቀይሮ ቀጥሏል።

የሶማሌ ወንድሞቻችን ዕገዛ አይረሳም!

በ2010 ዓ.ም በሶማሌ ክልል ሁለት ብሔር ተኮር መንግሥታዊ ጥቃቶችና ማፈናቀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በሁለቱም አስቀያሚ ቀናት የማፈናቀሉ ዕዝ የነበረችው ጅግጅጋ ከተማ ነበርኩ። የመጀመሪያው መስከረም 2 ቀን 2010 ዓ.ም በኦሮሚኛ ቋንቋ ተናጋሪ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ላይ የተቃጣ ነበር፡፡ ሁለተኛው ብሔር ተኮር መንግሥታዊ ጥቃት ከሐምሌ 28 እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የዘለቀው  ነው።

አምባገነን በሆነ ሥርዓት ሕዝብ መንግሥትን የመውቀስም ሆነ የመተቸት፣ በሰላማዊ መንገድ መብቶቹን መጠየቅ አይችልም፡፡ ለምን ወገኖቻችን ይፈናቀላሉ ብሎ በተደራጀ ሁኔታ ቢጠይቅ ቅጣቱ የከፋ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን የማንነታቸው እሴት የሆነውን አብሮታቸውን የሚንድ ድርጊት የአምባገነኖች አርጩሜ ሳያስበረግጋቸው ተቃውመዋል። ለአብነት በኦሮሞ ወገን መፈናቀል ወቅት ተቃውሞ ያሰማ አንድ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ኢትዮጵያዊ፣ ለ11 ወራት በጅግጅጋ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ የስቃይ አምባ ያለ ምንም ክስ ሆነ ፍርድ ማቋል።

ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. የሶማሌ ወገኖቻችን የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቦና ዳግም የተገለጠበት ቀን ነበር። በዚያ ጥቁር ቀን ወንድም የሶማሌ ሕዝብ የአብዲ መሐሙድ ዑመር መንግሥት ጡንቻ ሳያንበረክከው ጥቃቱ ለተሰነዘረባቸው ወገኖቹ መሸሸጊያ ሆኗል። የሶማሌ ወንድሞቻችን ዕገዛ በእውነቱ እጅግ ትልቅ፣ ግን ብዙ ያልተባለለት ነው። የዚህ መጣጥፍ አዘጋጅን ጨምሮ ጎረቤቶቹን፣ የሥራ ባልደረቦቹንም ሆነ የቅርብ ጓደኞቹን ከአጥፊዎች የታደጉት ሶማሌ ወገኖች ናቸው። በግሌ የሶማሌ ግቢ ተከራይቶ የሚኖር ወይም ከሶማሌ ኢትዮጵያውያን ተጎራብቶ እየኖረ የተዘረፈም ሆነ ሌላ ጥቃት የደረሰበት አልሰማሁም።

በሕዝቡ ዘንድ ተደጋግሞ እንደተነገረው የጥፋት ድግሱ ዓላማ የተፈጸመው አሥር በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው፡፡ ታዲያ ዕልቂቱ በ90 በመቶ ቀነሰ ከተባለ ምክንያቱ (የፈጣሪ ዕገዛ ሳይዘነጋ) በታላቁ የሶማሌ ሕዝብ በጎነት ነበር ማለት ይቻላል።

ለሙስጠፌ መሐሙድ ዑመር አስተዳደር ተገቢው ድጋፍ ይደረግ!

ሙስጠፌ መሐሙድ ዑመር የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ከተሾሙ ሁለት ወራት ብቻ ነው፡፡ ከቀደመው አስተዳደር የተረከቡት የፋይናንስ፣ የሰው ኃይልም ሆነ የቢሮክራሲ መዋቅር አልነበረም፡፡ መንግሥት የማዋቀር ሥራ እንደ አዲስ ነው እየሠሩ ያሉት። የሶማሌ ክልል ጂኦፖለቲካዊ ሁነቶች፣ የቀደመው የክልሉ አስተዳደር ባህሪያትና የደረሰው ጥፋት እጅግ ከፍተኛ መሆን፣ እንዲሁም ችግሮቹ በአፋጣኝ ምላሽ የሚሹ መሆናቸው ተዳምረው የክልሉን አስተዳደር እጅግ የሚፈትኑ ናቸው። ስለሆነም የፌደራል መንግሥት ለአዲሱ የክልሉ አስተዳደር ድጋፍ ማድረግ አለበት። ነገር ግን እስካሁን ባለው ሁኔታ የፌዴራል መንግሥት ዕገዛ እያደረገ ስለመሆኑ ፍንጭ የሚሆኑ ተጨባጭ ተግባራትን አላስተዋልኩም፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱ የተጎዳው ሕዝብ ጉዳይ ጉዳዩ ቢሆን ኖሮ፣

  • ዛሬ ከሦስት ወራት በኋላ እንኳ ንብረት የተዘረፉ ግለሰቦች ካሳ ጉዳይ እልባት ያገኝ ነበር።
  • የተበዳይ ማኅበረሰብ ክፍል በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ የፀጥታ መደፍረሶች መነሻ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል የሰፋ መሆኑን ተገንዝቦ መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች በመንቀስ ምላሽ ይሰጥ ነበር። ከዚህ አንፃር የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ ተከታታይ የሕዝብ ለሕዝብ የሰላምና የዕርቅ ውይይቶችን ከክልል እስከ ቀበሌ ባለ መዋቅር እንዲካሄድ ይሠራ ነበር፡፡ የተቃጠሉ ቤተ ክርስቲያናት በፍጥነት እንዲጠገኑ ለሚመለከተው የመንግሥትም ሆነ የሃይማኖት አካላት አቅጣጫ ይሰጥ ነበር፡፡
  • ከሁሉም በላይ  ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት አደጋ የሆኑት እነዚህ ሰፋፊ ቀዳዳዎች ለማጥበብ ሳይሠራ የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች (ከጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ) ትምህርት እንዲጀምሩ ባልተወሰነ ነበር።

በመጨረሻም

የአዋሽ ማዶ ሰው ነገር ማብረድ መለያው ባይሆን ኖሮ፣ ጠንካራ የመረዳዳት ማኅበራዊ እሴት (Social Capital) ጥሪት ሆኖት የደረሰበትን ሰብዓዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እንዲሁም ቁሳዊ ጥቃት እንዲቋቋም ባያግዘው ከደረሰው አደጋ አንፃር ከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ይከሰት እንደነበር አዕምሮ ያለው ሁሉ የሚያገናዝበው ነው።

ከሁሉ በላይ ደግሞ የወንድም ሶማሌ ወገኖቻችን በችግሩ ወቅት ከተጎጂ ወገኖች ጎን መሆናቸው የመንፈስ ብርታት ሆነውታል። የሶማሌ ወገኖች የክፉ ቀን አለኝታ መሆናቸው በተጎጂዎች ዘንድ የተጠቂ ሥነ ልቦና (Victimhood Mentality) እንዳይኖር፣ በዚህም በዕለት ተዕለት እንቅሰቃሴዎች ስሜታዊነትና ጥላቻ ቦታ እንዳይኖራቸውና ሕዝቡ በአስተውሎት እንዲጓዝ ያደረጉ ናቸው። ለዚህም ነው ተጎጂ ወገኖቻችን በደላቸውን ችለው የመንግሥትን ምላሽ በትዕግሥት እየተጠባበቁ የሚገኙት።

ነገር ግን ማኅበረሰቡ በራሱ ተነሳሽነት እያደረገ ያለው ነገር የማብረድ ጥረት ከመንግሥት ድጋፍ ካልተቸረው መዘዙ ብዙ ይሆናል። ከመንግሥት በኩል እያንዳንዷ ቀን ለተጎጂ ወገኖች የሞት የሽረት መሆኑ ግንዛቤ የተወሰደ ስለመሆኑ ብርቱ ጥርጣሬ አለኝ። ችግሩ መልኩን ቀይሮ በኋላ ለመፍታት እጅግ አስቸጋሪ ከመሆኑ በፊት፣ ተጎጂዎቾን በፍጥነት መካስ (የካሳ ክፍያው ከፌዴራልም ሆነ ከክልሉ በጀት ታሳቢ ተደርጎ የሚለው ጉዳይ ሳይደረግ) ለነገ የማይባል የቤት ሥራ ነው፡፡ የቤተ እምነቶች ዕድሳት ጉዳይም እንዲሁ። ፈጣሪ ቸር ወሬ ያሰማን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻው [email protected]  ማግኘት ይቻላል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...