Monday, July 22, 2024

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄና አንድምታው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጉባዔ ከተወያየባቸው አጀንዳዎች መካከል፣ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ትኩረትን ስቦ ቆይቷል፡፡ ምክር ቤቱ ባደረገው ጉባዔ የቀረበለትን የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ እንደተቀበለም ተገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ይህንን ጥያቄ ከተቀበለ በኋላ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲፈጸም አቅጣጫ ያስቀመጠ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ የክልልነት ጥያቄ ላቀረበው ብሔረሰብ ሕዝበ ውሳኔ ያደራጃል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47 መሠረት ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት አለው፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ይህ መብት ተግባራዊ የሚሆነው የክልል መመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ወይም ሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልል ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበለት ምክር ቤት ጥያቄውን በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ሲደገፍና የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣኑን ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሲያስረክብ እንደሆነና ይህ አዲሱ ክልል የፌዴራል መንግሥቱ አባል እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

ይሁንና አገሪቱ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራል ሥርዓትን ተከትላ ክልሎችንና የከተማ አስተዳደሮችን ካዋቀረች ወዲህ፣ በአገሪቱ ክልል መሥርቶ ተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት አባል የሆነ ብሔር፣ ብሔረሰብም ሆነ ሕዝብ የለም፡፡ ነገር ግን በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. ውስጥ የተሰበሰበው የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ የዞኑን የክልልነት ጥያቄ በመደገፍ ያፀደቀ ሲሆን፣ ይህም ሕጉን ተከትሎ ለክልል ምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ በዚህም ምክንያት ፌዴሬሽኑ ከተመሠረተ ለመጀመሪያ ጊዜ ክልል ሆኖ የወጣ የመጀመሪያው ክልል በመሆን በታሪክ ይመዘገባል፡፡

ነገር ግን የሲዳማን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚቃወም ባይኖርም፣ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ተግባር እንቅስቃሴ መገባቱ የሚኖረው አንድምታ ላይ ጥያቄዎች የሚያነሱ በርካቶች ናቸው፡፡

በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚቀርቡ ትችቶች

የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ከፍተኛ ትችቶች ሲያቀርቡበት የቆየ ሲሆን፣ በአንድ ወገን የብሔር ብሔረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ይሰጣቸዋል የሚሉ ደጋፊዎች ሲኖሩ፣ ይህ በአገሪቱ ግጭትን በማባባስ አገሪቱን ሊበታትናት ይችላል የሚሉ ተቺዎች ያማቋረጥ ሲከራከሩበት ቆይተዋል፡፡

ያም ሆነ ይህ ተፈጻሚነት አግኝቶ በተግባር ሕገ መንግሥታዊ ድጋፍ ኖሮት እየተተገበረ ያለው የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም፣ በተለይ በደቡብ ክልል አወቃቀር ላይ ከፍተኛ ትችት ይቀርብበታል፡፡ ይህም ብሔርን መሠረት ያደረገ አወቃቀር የተከተለ ክልላዊ ሥርዓት ያለው ፌዴራሊዝም ተተግብሮ እያለና የሐረሪ ክልል አነስተኛ ቁጥር ያለው የሕዝብ ብዛት ኖሮት ሳለ፣ 56 ብሔር ብሔረሰቦችን በአቅጣጫ መትሮ አንድ ላይ በክልልነት ማቀፉ አግባብ አይደለም ከሚል መነሾ የሚመነጭ ነው፡፡

ከደቡብና ከጋምቤላ ክልሎች በስተቀር ሁሉም ክልሎች ስያሜያቸው ሳይቀር አብላጫ ቁጥር ባለው ብሔር የተሰየሙ ሲሆን፣ በዚህ አግባብ ከተሄደ ሕገ መንግሥቱም ስለሚፈቅድ በኢትዮጵያ ከ80 ያላነሱ ክልሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አሰፋ ፍሰሐ (ዶ/ር)፣ ባዘጋጁት የማስተማሪያ ጽሑፍ ላይ አመልክተዋል፡፡

እንደሳቸው ምልከታ በክልል ደረጃ በፖለቲካ ሥልጣን ሽሚያ ተገፍቻለሁ ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የራሳቸውን ክልል የመመሥረት ግፊቶችን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

ፕሮፌሰሩ አክለውም በ2001 ዓ.ም. ባቀረቡት ትንታኔ፣ 56 ብሔር ብሔረሰቦች ያሉትን የደቡብ ክልል እንደገና በተለያዩ ክልሎች ማደራጀት ከተጀመረ ማብቂያው የት ነው ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህም የፓንዶራ ሳጥን መክፈት ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡

ፓንዶራ በግሪክ አፈ ታሪክ የነበረች ገጸ ባህርይ ስም ሲሆን፣ ከገነት እሳት የሰረቀውን ፐሮሜቲየስን ለመቅጣት ሲል የአማልክት ንጉሡ ዚየስ የላካት ሴት ነች፡፡ ይህችም ሴት በድንገት ያገኘችውን በሽታን፣ ሞትንና በርካታ ክፉ ዕጣ ፈንታዎችን የያዘውን አቁማዳ ሳታስበው ትከፍታለች፡፡ አቁማዳውን በፍጥነት ብትከድነውም፣ በውስጡ ተስፋ ታፍኖ ሲኞር ሌሎቹ ክፉ ዕጣ ፈንታዎች ሁሉ ወጥተው ነበርና ከፍተኛ ጉዳትን አስከተሉ፡፡

ይህም በጊዜ ሒደት አቁማዳው ወደ ሳጥን ተቀይሮ እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ አባባሉም ብዙ ያልተተነበዩ ችግሮችን የሚያስከትል ጉዳይን መነካካት በሚል ትርጉሙ ጥቅም ላይ ይውላል፡፡

የደቡብ ክልልም የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም የፓንዶራ ሳጥን እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡

ሲንከባለል የቆየው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ላለፉት ከ20 በላይ ዓመታት ሲንከባለል የመጣ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ አልፎ አልፎም የግጭቶች መነሻና የተቃውሞዎች መጀመሪያ ሲሆን ተስተውሏል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ የክልልነት ጥያቄ ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ ለክልሉ ምክር ቤት ሊቀርብ ባለመቻሉ እስካሁን ምላሽ ሳይሰጠው ዘልቋል፡፡ የዚህ መነሻ የፓርቲው (ደኢሕዴን/ኢሕአዴግ) ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች የሚጠቅሱ ሲሆን፣ ጥያቄው ወደ ምክር ቤትና ወደ ሕዝብ ከመሄዱ በፊት በፓርቲው ውስጥ ውይይቶች ተደርገውበት እዚያው ይቀር እንደነበር ያትታሉ፡፡ ይህ ለክልልነት ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን፣ በፓርቲው ውስጥ በውይይት ያላለፈ ጉዳይ በምንም ሁኔታ ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ሆኖም ከኢሕአዴግ ጉባዔ ቀደም ብሎ አሥረኛ ጉባዔውን ያጠናቀቀው ደኢሕዴን በክልሉ የተከሰቱ ግጭቶችንና የፀጥታ ሁኔታዎችን ከገመገመ በኋላ በክልሉ የሚነሱ ማናቸውም ዓይነት የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ሲል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ የሲዳማ ጥያቄ ወደ ምክር ቤቶች ሄዶ ድምፅ ሊሰጥበትና ተቀባይነትን ሊያገኝ ችሏል፡፡

የሲዳማ ዞን ምክር ቤት በሐምሌ ወር ጥያቄውን ለክልል ምክር ቤት ያቀረበ ቢሆንም፣ በክልሉ በነበረ የፀጥታ ችግር ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት አባላት መሰብሰብ ሳይችሉ መቅረታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ለሪፖርተር በስልክ አስታውቀዋል፡፡ የክልሉ ሕገ መንግሥት የክልሉ ምክር ቤት ቢያንስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባዔ እንዲያደርግ ይደነግጋል፡፡

‹‹የምክር ቤት አባላት ጥያቄው በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየ በመሆኑና በድርጅቱ ጉባዔ ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ያግኙ የሚል አቋም በመያዙ፣ ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ መንገዱን ተከትሎ ምላሽ ያግኝ በሚል ጥያቄውን ተቀብሎታል፤›› ያሉት አቶ ሚሊዮን፣ ‹‹ሪፈረንደም ለማካሄድ ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራትም፣ ከዞኑ ጋር በመሆን ሪፈረንደም እንዲካሄድ ነው ውሳኔ የሰጠው፤›› ብለዋል፡፡

በሲዳማ ዞን ኢጀቶ የሚባል በኦሮሚያ ክልል በሰፊው እንደሚታወቀው ያለ የወጣቶች ቡድን ያለ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ በሐዋሳ ከተማ በተከሰቱ ግጭቶች ወቅትም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ይህንን የሲዳማ ክልልነት ጥያቄን ሲያነሳ እንደነበር በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲጠቀስ የቆየ ነው፡፡ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ በተከሰተ ብሔር ተኮር ግጭት ምክንያት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ውይይት ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተሰብሳቢዎቹ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ሕዝቡ ተወያይቶ ጉዳትና ጥቅሙን እንዲለይ አሳስበው ነበር፡፡

የሲዳማ ጥያቄ ይዟቸው የሚመጡ በርካታ ጥያቄዎች

ምንም እንኳን በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄን ለክልሉ ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ ይካሄድልኝ በማለት ጥያቄ ያቀረበው የሲዳማ ዞን ብቻ ቢሆንም፣ በሌሎቹ የክልሉ ዞኖች ተመሳሳይ ጥያቄዎችና ፍላጎቶች ስለሌሉ ነው ለማለት ግን አይቻልም፡፡ እንዲያውም የሲዳማ ክልል ተቀባይነት ማግኘትና የአፈጻጸም አቅጣጫው በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ለነበሩ የክልሉ የተለያዩ ዞኖች ሕዝቦች ማንቂያ ደወል ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

ለምሳሌ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ አንድ የወላይታ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንደሚሉት፣ የወላይታ ክልልነት በወላይታ ዞን ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ያለው ጥያቄ ነው፡፡ የዞኑ ምክር ቤት ዝምታና ማጓተት ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንደማይገባቸውና ይህም በርካቶችን ግራ እንደሚያጋባ አክለዋል፡፡

በተመሳሳይ በፓርቲው ጉባዔ ላይ በሲዳማ ጉዳይ ውይይት ሲደረግ ሌሎቹም ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገጸዋል፡፡ በዋናነት ጥያቄውን ያቀረቡት ካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ዞኖች እንደሆኑም ምንጮች አክለዋል፡፡

ከሪፖርተር ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን፣ በዋናነት እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚያስነሱት የልማትና የዕድገት ተጠቃሚነት እንደሆኑ በማስታወቅ፣ ሁሉም ዞኖች የክልልነት ጥያቄ ቢያነሱና ምላሽ ቢያገኙ ለማስተዳደር እንደሚያስቸግር ገልጸዋል፡፡

ስለዚህም የክልሉ መንግሥት ሁሉም ዞኖች ከክልሉ ልማት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችለኛል ያለውን ጥናት እያካሄደ እንደሆነ አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሁሉም ይበታተን ቢባል የሚጠበቀው ውጤት ያመጣል ለማለትም አይቻልም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ይሁንና በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው መብት ምንም የማያወላዳና ማንኛውም ብሔር በፈለገው ጊዜ ክልል የመመሥረት መብቱን ያስጠበቀ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ምንም እንኳን የልማት ተጠቃሚነት የሚያስገኝ ጥናት ተደርጎ ተግባራዊ ሆኗል ቢባልም፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ሊያስቆም እንደማይችል አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡

የሐዋሳ ከተማ ጥያቄና የንብረት ክፍፍል ጉዳይ

የዛሬ 20 ዓመት ገደማ ሐዋሳ ከተማን የጎበኘ አንድ ሰው አሁን ከ20 ዓመታት ቆይታ በኋላ ለጉብኝት ቢሄድ ሌላ ከተማ የገባ እንጂ፣ በፊት ‹‹ሐዋሳ ላንጋኖ ለሽር ሽር ሄጄ . . .›› እየተባለ የተዘፈነላት የጥንቷ ሐዋሳ ነች ለማለት አይደፍርም፡፡ ሐዋሳ በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉ ከተሞችና የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷ ሆናለች፡፡

የሐዋሳ ዕድገት ለአዲስ አበባ ባላት ቀረቤታና በመሬት አቀማመጧ እንደሆነና በዚህም ምክንያት በርካታ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ መቻሏን የሚገልጹ ቢኖሩም፣ ደቡብ ክልል የተገነባችው በደቡብ ክልል ሥር ባሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀብት ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡ የክልሉ ነዋሪዎችና ምሁራን በርካቶች ናቸው፡፡ በመሠረቱ የክልል መቀመጫን ለማልማት ከክልሉ ዞኖች የሚደረግ ድጎማ አለ፡፡

በዚህም ምክንያት ከሲዳማ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተነሳው አንዱ ጉዳይ በጋራ የለማችው ሐዋሳ ምን ትሁን የሚል እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ሐዋሳ የፌዴራል ከተማ እንድትሆን ጥሪ ሲያቀርቡ ተስተውለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን፣ ‹‹የሐዋሳ ከተማ በሲዳማ ዞን ውስጥ ስለምትገኝ የሐዋሳ ጉዳይ ከሲዳማ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የክልሉ መቀመጫ ከሐዋሳ የሚነሳ ከሆነ ሌላ ከተማ ለደቡብ ክልል መቀመጫ ይሆናል፡፡ አቶ ሚሊዮን በዕጩነት የተያዙ ከተሞች እንደሌሉ አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በአገሪቱ ተመሳሳይ ክስተት አጋጥሞ ስለማይታወቅ የሀብት ክፍፍል ሕግ እስከ ዛሬ ባለመሠራቱ፣ ሲዳማ ክልል ሆኖ ሲወጣ እንዴት ከደቡብ ክልል ጋር ያለውን ንብረት ሊከፋፈል ይችላል ሲሉ የሚጠይቁ ትንሽ አይደሉም፡፡ ይህም ሕግ ሳይኖር እንዴት ሊተገበር እንደሚችል ግራ ያጋባል ሲሉም አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹ልክ ነው ይህንን የሚገዛ ሕግ በአገሪቱ የለም፡፡ ነገር ግን ካሁን በፊት በክልሉ የዞንና የወረዳ አደረጃጀት ስንሠራ በነበረን ልምድ ተጠቅመን ኮሚሽን በማቋቋም እናከናውናለን፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ይህ አሠራር በአንድ አስተዳደራዊ ክልል ስለሆነ ቀላል እንደሚሆን፣ ብሎም የሚከፋፈሉት ንብረት ከተሽከርካሪዎችና ከቢሮ መገንቢያ ገንዘብ ያለፈ ስለማይሆን ብዙም ውዝግብ እንደማያስነሳ በክልሉ የሚሠሩ አንድ ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ክፍተት ወይ በአፋጣኝ እንደተለመደው ሕግ ሊወጣበት አልያም የጥያቄውን መመለስ ሊያዘገየው የሚችል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የደኢሕዴን ዕጣ ፈንታ

የሲዳማ ክልል ከደቡብ ክልል ሲወጣ የደቡብ ክልልን ከሚመራው ደኢሕዴን ሌላ የራሱን የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሠርት ስለሆነ፣ ደኢሕዴን የቀረውን ክልል በመምራት እንደሚቀጥል የፓርቲ ፖለቲካ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ይሁንና የሲዳማ ክልል ፓርቲ ምን ዓይነት ቅርፅ ሊኖረው እንደሚችል፣ በምን አግባብ (በአጋርነት ወይስ ቀድሞ አባል ከነበረ ፓርቲ ስለወጡ በአባልነት) ከኢሕአዴግ ጋር ያላቸውን መስተጋብር ይቀጥላሉ የሚሉናና ተያያዥ ጥያቄዎች ያሉበት ጉዳይ ነው፡፡

የደቡብ ክልል ዞኖች በቀጣይ የሲዳማን ፈለግ የሚከተሉ ከሆነ፣ ደኢሕዴን በፓርቲነት መቀጠሉም አጠራጣሪ ሊሆን እንደሚችል የሚገምቱ አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -