Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ 938 ሚሊዮን ብር በማትረፍ የትልልቆቹን ጎራ ተቀላቅሏል

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከወለድ አልባ አገልግሎት የሦስት ቢሊዮን ብር ተቀማጭ አሰባስቧል

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ሥራ በጀመረ አሥረኛ ዓመቱ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት በ2010 ዓ.ም. ያስመዘገበው የትርፍ ምጣኔ ዕድገት በ140 በመቶ ጨምሮ ወደ 938 ሚሊዮን ብር ማደጉን ያሳያል፡፡ ከታክስ በኋላ የተመዘገበው የባንኩ የተጣራ ትርፍም 724 ሚሊዮን ብር እንደሆነ ታውቋል፡፡

ባንኩ በ2009 ዓ.ም. ካስመዘገበው የ391 ሚሊዮን ብር ትርፍ አንፃር ሲታይ፣ በ2010 ዓ.ም. ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን በ547 ሚሊዮን ብር ጭማሪ የተመዘገበበት ነው፡፡ የተጣራ ትርፉም 727.7 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪው በዚህ ደረጃ ብርሃን ባንክ ቀደም ብሎ ዓመታዊ ትርፉን በ170 በመቶ ማሳደግ ችሎ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ባንክ የ2010 ዓ.ም. ትርፍ የ140 በመቶ ዕድገት በማስመዝገቡ ሁለተኛው የግል ባንክ ለመሆን አስችሎታል፡፡

የኦሮሚያ ባንክ የ2010 ዓ.ም. የትርፍ ምጣኔ በዚህ ደረጃ ማደግ የቻለው በተለያዩ የባንክ አገልግሎት መስኮች ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረጉ እንደሆነ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቢ ሳኖ አስታውቀዋል፡፡

ከባንኩ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለውም፣ ባንኩ ከሌሎች ቀድሞ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ከመጀመሩ አኳያም የዚህ ዘርፍ ማደግና እንቅስቃሴ እየሰፋ መምጣት ከወለድ አልባ ዘርፍ ብቻ የሚያገኘውን የትርፍ መጠን ከፍ ማድረጉ ለባንኩ አጠቃላይ የትርፍ መጠን ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ በ2010 ዓ.ም. ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ብቻ 194.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ከ2009 ዓ.ም. አኳያ በ46 በመቶ ወይም በ61.5 ሚሊዮን ብር ብልጫ የታየበት ሆኗል፡፡ ባንኩ በ2010 ዓ.ም. ካገኘው ጠቅላላ ትርፍ ውስጥ ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የተገኘው ትርፍ 20.8 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ ባንኩ በ2009 ዓ.ም. ከወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን 133.2 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ከግል ባንኮች በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ይህን ያህል ትርፍ ያስመዘገበ ባለመኖሩም ባንኩን በዘርፉ ቀዳሚ አድርጎታል ተብሏል፡፡

እንደ ባንኩ ዓመታዊ የሒሳብ ሪፖርት ከሆነም፣ በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ብቻ ያሰባሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ሦስት ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከ2009 ዓ.ም. አኳያም ከግማሽ ቢሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡

በመደበኛው የባንክ አገልግሎት መስክም ባንኩ በ2010 ዓ.ም. የሰጠው የብድር መጠን በ73 በመቶ ጨምሮ ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ካቻምና ያበደረው 8.2 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ የተበዳሪዎችን ቁጥርም ወደ 8,240 አሳድጓል፡፡

ለብድር ካዋለው ገንዘብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ለአገር ውስጥ ንግድና ለአገልግሎት ዘርፍ የተሰጠው ነው፡፡ የወጪ ንግድና ኢንዱስትሪ በሁለተኛ በሦስተኛ ደረጃ የሚመደበውን ብድር ያገኙ ዘርፎች ናቸው፡፡

ባንኩ ዓመታዊ ገቢውን ወደ 2.47 ቢሊዮን ብር ማሳደግ የቻለ ሲሆን፣ ከቀደመው ዓመት የ65 በመቶ ብልጫ ያለው ገቢ እንዳገኘ ለማወቅ ተችሏል፡፡  በአንፃሩ የ2010 ሒሳብ ዓመት ጠቅላላ ወጪው በ38 በመቶ አድጎ 1.53 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ ረገድ ያስመዘገበውን በተመለከተ በ2009 ሒሳብ ዓመት 13.4 ቢሊዮን ብር የነበረውን የተቀማጭ የገንዘብ መጠን በ2010 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ 19.9 ቢሊዮን ብር አድርሷል፡፡ ይህም የተቀማጭ ገንዘቡን በ15 በመቶ ማሳደጉን ያመላከተ ነው፡፡

ባንኩ በ2010 ሒሳብ ዓመት የባንኩን የአስቀማጮች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ማሻገር የቻለበት ነው፡፡ በ2008 ሒሳብ ዓመት የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር 537,960 የነበሩ ሲሆን፣ በ2009 ሒሳብ ዓመት ደግሞ 806,739 አድርሶ ነበር፡፡ በ2010 ሒሳብ ዓመት ግን ይህንን የአስቀማጮች ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ በማሳደግ አጠቃላይ የአስቀማጮች ቁጥር 1.14 ሚሊዮን አድርሷል፡፡ ይህም ከግል ባንኮች የአስቀማጮቻቸውን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ማድረስ ከቻሉ ጥቂት ባንኮች አንዱ መሆን ችሏል፡፡

የሀብት መጠኑን በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 23.8 ቢሊዮን ብር ያደረሰ ሲሆን፣ ይህም ከካቻምናው በሰባት በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 2.59 ቢሊዮን ብር የደረሰና ዘጠኝ ሺሕ ባለአክሲዮኖች የሚያስተዳድሩት የግል ባንክ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች