Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የትራንስፖርት ባለሥልጣንና በቴክኖሎጂ አገልግሎት በሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል ውዝግቡ ቀጥሏል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሰሞኑን በንግድ አገልግሎት ዘርፍ በተለይም በኪራይ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ካስታወቁና በጥሪና በአፕልኬሽን በመጠቀም በቴክኖሎጂ ትራንስፖርት ዘርፉን በሚያግዙ ተቋማት ላይ ዘመቻ ከፍቷል፡፡

ይህንኑ በማስመልከት የተቋሙ ኃላፊዎች ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ዘለቀ ከምክትላቸው አቶ ምሥጋን ከበደ ጋር በመሆን በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ በኮድ 03 የአውቶሞቢል ታርጋ አውጥተው ነገር ግን ከታክሲ አገልግሎት ጋር ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ ግለሰቦች ‹‹ሕገወጦች›› በመሆናቸው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ መመርያ አስተላልፈዋል፡፡

ሰፊ መነጋገሪያ ሆነ የሰነበተው የኮድ 03 ተሽከርካሪዎችና የባለሥልጣኑ ፍጥጫ መነሻው ሕግና ሥርዓት አልተገበረም የሚል እንደሆነ ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡ ፈቃድ ባለወጡበትና ዕውቅና ባላገኙበት የሥራ ምድብ አገልግሎት ሰጥተዋል የተባሉት የኮድ 03 ተሽከርካሪ ባለንብረቶች በየመንገዱ እየታደኑ እንደሚያዙ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ አቶ ዳዊትም ሆኑ አቶ ምሥጋን እነዚህ አካላት ሕገወጥ ብቻም ሳይሆን፣ ለተሳፋሪው ደኅንነት ሥጋት የሆነ፣ የሚያስከፍሉት ዋጋ የተጋነነ፣ የሚያገኙት ገቢ ምን ያህል እንደሆነና ሌሎችም መሠረታዊ ጉዳዮች እንደማይታወቁ የገለጹት አቶ ዳዊት፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚሰጡት አገልግሎት ይብሱን ከከተማው የትራንስፖርት ፍላጎት ስፋት አኳያ እዚህ ግባ የማይባል እንደሆነ የጠቀሱትም፣ ከከተማው አራት ሚሊዮን የሕዝብ ትራንስፖርት ፈላጊ ውስጥ በሜትር ታክሲዎችና በሰማያዊና ነጭ (ላዳ) ታክሲዎች የሚሸፈነው ከ0.5 በመቶ በታች እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ኃላፊዎቹ ሕገወጥ ያሏቸው የኮድ 03 ትራንስፖርት አቅራቢ አውቶሞቢሎችን ብቻ አልነበረም፡፡ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎቹን ከተጠቃሚው ጋር በማገናኘት የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሲሰጡ የቆዩ፣ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችም ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያው ተላልፎላቸዋል፡፡

የኪራይ አገልግሎት መስጠት በንግድ ሥራ ለተመዘገቡት ኮድ 03 ተሽከርካሪዎች መፈቀዱን የሚያምኑት አቶ ምሥጋን በበኩላቸው፣ የኮድ 03 አውቶሞቢሎች በተለይም ቶዮታ ያሪስ፣ ቶዮታ ቪትዝ፣ ቶዮታ ኮሮላ፣ ሊፋን 530 እንዲሁም ሊፋን 520 ተሽከርካሪዎች የኪራይ አገልግሎት ለመስጠት የሚሰጣቸው የኮድ 03 ታርጋ፣ በሕጉ መሠረት ለተጠቃሚው ጨረታ አውጥተው የኪራይ አገልግሎት መስጠት ሲጠበቅባቸው፣ በየመንገዱ የመደበኛ ታክሲ ሥራ መሥራታቸው ሕገወጥ ነው ብለዋል፡፡  

የዚህ ሁሉ መነሻው በከተማው አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙትና ዘጠኝ ያህል የቴክኖሎጂ ድጋፍ በማቅረብ ከሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች መካከል ራይድ የተሰኘውና በዚሁ መተግበሪያ አማካይነት በርካታ የኮድ 03 አውቶሞቢሎች የትራንስፖርት ሥራው ላይ እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ በርካቶችም በዚሁ ተነሳስተው የኮድ 02 የቤት አውቶሞቢላቸውን ወደ ኮድ 03 በማዞር በትራንስፖርት አገልግሎት ንግድ ሥራ ለመሠማራት የታርጋ ቁጥር ለውጥ ጥያቄዎች መበራከታቸው ለባለሥልጣኑ ዕርምጃ መነሻ እንደሆነ ሲገለጽ ከርሟል፡፡

ይህ ይባል እንጂ ባለሥልጣኑ ኮድ 03 ተሽከርካሪዎች ከትራንስፖርት አገልግሎት እንዲታገዱ የተፈለገበት ዋናው ምክንያት የታክሲ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ የተሰጣቸውና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ተሰጧቸው እስከ 1,000 መኪኖችን ከውጭ በማስገባት እየሠሩ የሚገኙ ማኅበራትና አባሎቻቸው ያነሱት ቅሬታ እንደሆነ አቶ ዳዊት መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡    

እነዚህ ከቀረጥ ነፃ ዕድል የተሰጣቸውና ቀድሞውንም በተጋነነ ዋጋ የታክሲ አገልግሎት በኮንትራንት ሲሰጡ የሚታዩት ኮድ 01 ተሽከርካሪዎች በሁለት ወገን ቅሬታ ይቀርብባቸዋል፡፡ የዋጋቸው መወደድና መጋነን እንዲሁም መንግሥት ለሜትር ታክሲዎች ያስቀመጠውን የታሪፍ ዋጋ አለማክበር ዋና ዋናዎቹ የተገልጋዩ ቅሬታ ምንጮች ናቸው፡፡ እነዚህ ታክሲዎች የመንግሥት ዕውቅና ስላላቸው፣ በመንግሥት ድጋፍና ዕገዛ ከማግኘታቸው ባሻገር የወጣላቸው ሕግና ደንብ በአብዛኛው ሳያከብሩ፣ በአብዛኛው ተጠቃሚ ዘንድ ተፈላጊነትን ያተረፈውና በቴክኖሎጂ የታገዘው የኮድ 03 ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ‹‹ሕገወጥ›› መባሉ መንግሥትን አድሏዊ አያሰኘውም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ጨምሮ ‹‹መንግሥት የመደብ መጨቆኛ መሣሪያ ነው›› የሚል ቅሬታ ስለማስነሳቱም በጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ባለሥልጣኑ የቁጥጥር ሥራውን በማኑዋል የሚያከናውን በመሆኑ ክፍተቶችና ውሱንነቶች እንዳሉበት ያመኑት አቶ ዳዊት፣ ይህም ሆኖ ኮድ 03ም ሆነ እንደነ ራይድ ያሉ ቴክሎጂዎች በትራንስፖርት ንግድ ዘርፍ ለመሠማራት የሚያስችላቸውን መሥፈርት አላሟሉም፡፡ ሕገወጦች ናቸው ብለዋቸዋል፡፡ ይህን ቢሉም ተቋሙ ለማንኛውም በታክሲ  ወይም በትራንስፖርት ዘርፍ አገልግሎት መስጠት የሚፈልግ አካል ተቋሙ የሚያስተናግድበት አግባብ እንዳለውና ለማንም በሩ ክፍት ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳ ባለሥልጣኑ ይህን ይበል እንጂ የኮድ 03 ተሽከርካሪ ባለንብረቶችም ሆኑ የቴክኖሎጂ አገልግሎት ያቀረቡት ድርጅቶች ሕገወጥ መባላቸውን አይቀበሉትም፡፡ ይልቁንም ፍትሐዊ ትራንስፖርትን በተቀላጠፈና አስተማማኝነቱ በተረጋገጠ አኳኋን አገልግሎት ማቅረባቸውን ይናገራሉ፡፡ ለአብነትም የራይድ ማስተግበሪያን በስልካቸው አውርደው ከሚጠቀሙ ግለሰቦች ሪፖርተር እንደተገነዘበው ከዋጋው ቅናሽነት ባሻገር፣ የሾፌሩ ስምና የመኪናው ታርጋ ቁጥር ከእነ ሞባይል ስልክ ቁጥሩ፣ የሚጓዝበት ርቀትና ቦታ ከሚያስከፍለው የገንዘብ መጠን ጋር አብሮ ለተጠቃሚው በጽሑፍ መልዕክት ይደርሰዋል፡፡

ለዚህ አገልግሎት ራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ከትራንስፖርት አቅራቢው ላይ ከሚያስከፍለው 17 በመቶ ኮሚሽን ሒሳብ ውስጥ ለመንግሥት የሁለት በመቶ የተቀናሽ ሒሳብ ታክስ (ዊዝሆልዲንግ) ለመንግሥት ገቢ ያደርጋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በቂ ሆኖ አልተገኘም፡፡

በመሆኑም ባለሥልጣኑ ዘመን አመጣሽ ቴክሎጂዎች የትራንስፖርት አገልግሎቱን ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ አለማድረጋቸውን በማጥናት፣ እውነትም ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ተገቢውን አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ ስለማቅረባቸው ማረጋገጥ ሲገባ፣ ሕግ ባይፈቅድላቸው እንኳ ሕጉ እንዲያካትታቸው ማድረግ ሲገባ ሕገወጦች ተብለው የመታገዳቸው አግባብነትም በጥያቄ ተነስቷል፡፡

አቶ ዳዊትም ሆኑ አቶ ምሥጋን ስለኮድ 03 የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም ሆነ ስለቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹ በሚባለው አይስማሙም፡፡ ተሳፋሪው መንግሥት ካስቀመጠው የሜትር ታክሲዎች ታሪፍ አኳያም የተጋነነ እንደሆነ፣ ቴክኖሎጂውም ቢሆን መንግሥት ከሚፈልገው ደረጃና አገልግሎት አኳያ ብዙ የሚቀረው በመሆኑ በየሚዲያው እንደሚባለው አይደለም በማለት ሞግተዋል፡፡

አስገራሚው ጉዳይ ግን ባለሥልጣኑ ዕገዳ ያወጣው በሚዲያ በኩል እንጂ የቴክኖሎጂ አቅራቢዎቹን አነጋግሮ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡ በደብዳቤ ለቀረበለት የእንነጋገር ጥያቄም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ አቶ ዳዊትም ሆነ አቶ ምሥጋን እንዳረጋገጡት፣ በተለይ ከራይድ በቀረበው ጥያቄ ላይ መነጋገር ያላስፈለገው ቀድሞውኑ በንግድ ሚኒስቴር የተሰጠው ፈቃድ ሶፍትዌር ዲዛይን የማድረግና የማበልጸግ ሥራ ላይ በመሆኑ ከትራንስፖርት ጋር የተገናኘ ሥራ እንዲሠራ ፈቃድ አልተሰጠውም የሚል መከራከሪያ በማቅረብ ማነጋገሩ እንዳላስፈለገ ጠቅሰዋል፡፡ የራይድ ትራንስፖርት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ በበኩሏ ቴክኖሎጂው ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎትም ሆነ ስምሪት እንደማይሰጥ፣ ይልቁንም ተጠቃሚዎች በሚያቀርቡት ጥሪ መሠረት ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር ማገናኘት እንደሆነና ለዚህ ሥራ የተለየ የንግድ ፈቃድም ሆነ የትራንስፖርት ሰጪነት ፈቃድ እንደማያስፈልገው ትገልጻለች፡፡ ይሁንና አገልግሎቱ ስለሚሰጥበት መንገድ ለማብራራትና እንዲያውቁት ለማድረግ ለባለሥልጣኑ የቀረበው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ ማጣቱንም አስታውቃለች፡፡ ባለሥልጣኑ በየሚዲያው መግለጫ እየሰጠና ዕግድ እያወጣ ማነጋገር ምርጫው መሆኑም እንደሚያስገርማት ሳትጠቅስ አላለፈችም፡፡

‹‹በተሰጠው ሊብሬ ከተፈቀደለት የንግድ ሥራ ውጭ የሚሠራ ኮንትሮባንድ ነው፡፡ ኮድ 03 ተሽከርካሪዎች የሚሠሩበት አግባብ ከእኛ አሠራር ጋር ይጋጫል፤›› በማለት አቶ ምሥጋን ሲገልጹ፣ አቶ ዳዊት በበኩላቸው ኮድ 03 ተሽከርካሪዎች ‹‹ከሚሰጡት ጥቅም ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል›› ብለዋቸዋል፡፡ አስተካክለው ይግቡ የተባሉት ኮድ 03 ተሽከርካሪዎች ወደ ኮድ 01 የታክሲ አገልግሎት ሰጪነት እንዲገቡ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

በከተማው 13 ሺሕ ኮድ 01 እና 03 ታርጋ ያላቸው ሚኒባስ ታክሲዎች፣ 900 አውቶቡሶች በየቀኑ አራት ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ሲኖሩ በምልልስ እንደሚያጓጓዙ የባለሥልጣኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ቁጥር 1,000 ያህል የሜትር ታክሲዎችን ሳይጨምር ነው፡፡ ከመጪው ሳምንት ጀምሮም አዳዲስ 700 አውቶቡሶችን ወደ መስመር የማስገባት ሥራ እንደሚጀመር አቶ ዳዊት ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ አገልግሎት የሚሰጥበት የኡበር አምሳያው የጥሪና የአጭር ጽሑፍ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ በአፍሪካ በተለይም በኬንያና በኡጋንዳ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ኡበር የግል አውቶ ሞቢሎች ያሏቸውን በሥሩ በማካተት የሚያስተናግድበት የቴክኖሎጂ ማስተግበሪያ በዓመት እስከ ሰባት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ያስገኝለታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች