በጋዜጣው ሪፖርተር
በኦሮሞ ባህል ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የኦዳ ዛፍን የሽልማቱ ስያሜ ያደረገው የኦዳ የኪነ ጥበብ ሽልማት በአምስት ዘርፎች እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
ሽልማቱን ያዘጋጀው በሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በመጪው ታኅሣሥ ወር የሚካሄደው ሽልማት በ2010 ዓ.ም. በአፋን ኦሮሞ በተሠሩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችና በባለሙያዎቻቸው ላይ ያተኩራል፡፡
ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው መርሐ ግብር የተካተቱት የሽልማት ዘርፎች ሙዚቃ፣ ፊልም፣ ቴአትር፣ መጽሐፍና የቴሌቪዥን ድራማ ሲሆኑ የሕይወት ዘመን ተሸላሚም ይኖራል፡፡ በአምስቱ የኪነ ጥበብ ዓይነቶች ውስጥ በተካተቱ 18 ዘርፎች የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና ይሰጣል፡፡
የውድድሩ ዳኞች በየዘርፉ አንቱ የተባሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራን ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ በአጭር የጽሑፍ መልዕክትና በድረ ገጽ ከመጨረሻ ዕጩዎች ውስጥ አሸናፊውን ለመለየት የሚሰጠው ድምፅ 30 በመቶ የሚይዝ ሲሆን፣ ውድድሩ በሚካሄድበት ቀን ከዳኞች ውጤት ጋር በመደመር አሸናፊው ይለያል፡፡
ዓምና በተዘጋጀው የመጀመርያው የኦዳ ሽልማት በፊልም፣ በሙዚቃና በቴሌቪዥን ድራማ ውስጥ በተካተቱ 15 የሽልማት ዓይነቶች ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ዕውቅናና የዋንጫ ሽልማት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡
ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የሚዘጋጀው የኦዳ ሽልማት እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም የሚካሄደው በኦሮሞ ባህል ማዕከል መሆኑ ታውቋል፡፡