ፓርላማው ዛሬ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ልዩ ስብሰባ፣ አዲስ ለተቋቋሙት አሥር ቋሚ ኮሚቴዎች ያቀረባቸውን ሁለት ዕጩዎች በከፍተኛ ድምፅ ውድቅ አደረገ፡፡
ፓርላማው ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀቱን ከሃያ ወደ አሥር ዝቅ እንዲል አድርጎ ካፀደቀ በኋላ፣ በሰብሳቢዎቹ ላይ ሳይስማማ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱ በነበረው ስብሰባ ከፍተኛ ተቃውሞ የቀረበባቸው አቶ ሞቱማ መቃሳና አቶ አማኑኤል አብርሃም ሲሆኑ፣ አቶ አማኑኤል ከዕጩነት ራሳቸውን አግልለው ነበር፡፡
ይሁንና ዛሬ በተካሄደው ስብሰባ ምክር ቤቱ አቶ ሞቱማ መቃሳን በ152 ድምፅ ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ አቶ አፅበሀ አረጋዊን ደግሞ በ157 ድምፅ ውድቅ አድርጓል፡፡
የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ በዕጩነት የቀረቡት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመሩ ነበር፡፡ አቶ አፅበሀ ደግሞ የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመሩ ነበር የታጩት፡፡
በዛሬው ዕለት በተካሄደው ስብሰባ ራሳቸውን ባገለሉት አቶ አማኑኤል ምትክ ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ለሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው ታጭተው በአብላጫ ድምፅ አልፈዋል፡፡ ለቀሪዎቹ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢነት የቀረቡ ዕጩዎች በሙሉ ድምፅ አልፈዋል፡፡