ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት ተፈቀደባቸው
የቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ሌሎች ባለሥልጣናት፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ልዩ የፖሊስ ኃይል በማሰማራት ከ200 በላይ ሰዎችን አስገድለው በጅምላ እንዲቀበሩ ማድረጋቸውን፣ የፌዴራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረዳ፡፡
ባለሥልጣናቱ ልዩ የፖሊስ ኃይሉን ሲቪል በማስለበስ ግድያውን እንዲፈጽሙ ማድረጋቸውን በማስረጃ ያረጋገጠ መሆኑን መርማሪ ቡድኑ ገልጾ፣ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል የመቀበልና በጅምላ የተቀበሩትን የመለየት ሥራ እንደሚቀረው አስታውቋል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ለልዩ ፖሊስ ኃይሉ ትዕዛዝ በመስጠትና በማሰማራት በክልሉ በፊቅ ዞን 83 ሰዎችን፣ በጀረር ዞን ጉኖጉዱ ወረዳ 24 ሰዎች፣ በፋፈን ዞን 18 ሰዎችና በቀላፎ ዞን 63 ሰዎችን ማስገደላቸውንና ተጨማሪ የምርመራ ሥራ እንደሚቀረው ለፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑ አስረድቷል፡፡
የፌዴራል ፖሊስ የምርመራ ቡድኑ የሠራውንና የቀረውን የምርመራ ሥራ ለፍርድ ቤቱ ያስታወቀው፣ ከጥቅምት 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በፊት በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የሠራውንና ይቀረኛል ያለውን ተጨማሪ የምርመራ ሥራ በችሎት ሲናገር ነው፡፡
መርማሪ ቡድኑ በአቶ አብዲ መሐመድ፣ በወ/ሮ ራሂማ መሐመድ፣ በአቶ አብዱራዛቅ ሳሜና በኮሚሽነር ፈሪሃን ጣሂር ላይ በተሰጠው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በትዕዛዝ የተገደሉ ሰዎችን በመረጃ መለየቱን፣ በወቅቱ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት ከዕቅዱ እስከ ፍፃሜው የሚያውቁ አራት ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉን አስረድቷል፡፡ በሁከቱና ብጥብጡ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን 11 ሰዎች የምስክርነት ቃል መቀበሉን፣ ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን የ37 ሰዎች የሕክምና ማስረጃ ከሆስፒታል ማምጣቱንም ቡድኑ ተናግሯል፡፡
በሁከቱና በብጥብጡ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ 62 ግለሰቦችን ማስረጃ ማስተርጎሙን፣ ብጥብጡን ሲመሩና ሲያስተባብሩ ለነበሩ ለ‹‹ሄጎ›› አባላት ገንዘብ ወጪ የተደረገበት 96 ገጽ የሰነድ ማስረጃ ማስተርጎሙን፣ ከመረጃና መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የሞባይሎች፣ የላፕቶፕና የኮምፒዩተር የቴክኒክ ምርመራ ውጤት መቀበሉን፣ ለ‹‹ሄጎ›› አባላት ገንዘብ ወጪ የተደረገበት 16 ገጽ የኦዲት ሪፖርት ሰነድ መቀበሉን፣ በክልሉ የተፈጠረውን ሁከትና ብጥብጥን መቆጣጠር እንዳይቻል የኤሌክትሪክ ኃይል በማቋረጥ እንዲባባስ የተደረገ መሆኑን የሚገልጽ ሁለት ገጽ የሰነድ ማስረጃ መሰብሰቡንም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ በተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት የሚገልጽ 35 ገጽ የሰነድ ማስረጃ ከክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ማምጣቱንም አክሏል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ቀሪ የምስክሮችን ቃል መቀበል፣ የ37 ሰዎችን የጉዳት መጠን የሚገልጽ ሰነድ ትርጉም መቀበል፣ አስከሬናቸው ከጉድጓድ የወጡ ሰዎችን የሞት ምክንያትና ማንነት ማረጋገጥ፣ ግብረ አበሮችን ተከታትሎ መያዝ፣ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የጦር መሣሪያዎችና ገንዘብ መያዝ እንደሚቀረው በማስረዳት፣ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ያቀረበውን የምርመራ ግኝት፣ ይቀረኛል ያለውን የምርመራ ዓይነትና የጠየቀውን ተጨማሪ 14 ቀናት ተቃውመዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ላለፉት ሰባት የጊዜ ቀጠሮ ቀናት የሚያቀርበው የምርመራ ውጤትና ቀረኝ የሚለው የምርመራ ሥራ፣ ተመሳሳይ መሆኑንና የሕግ መሠረት የሌለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ስንት ምስክሮች፣ በማን ላይ ምን ያህል፣ ምን ያህል ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ከመንግሥት ተቋማት ማስረጃ ለማምጣት ደንበኞቻቸውን ማሰሩ ተገቢ እንዳልሆነም አመልክተዋል፡፡ ምን ያህል ገጽ እንደሚያስተረጉም፣ ምን ያህል ገንዘብና የጦር መሣሪያ መያዝ እንደሚቀረው ግልጽ አለማድረጉንና በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ምክንያት በመሆኑ፣ የጠየቀው ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድ እንደማይገባ ተከራክረዋል፡፡ ተጨማሪ ጊዜ የሚሰጥባቸው ምክንያቶች መኖራቸውንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19 (4) ላይ ተደንግጎ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸውና በዋስ እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑም ዋስትናውን ተቃውሞ በድጋሚ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ያከናወነውን የምርመራ ሥራ ከምርመራ መዝገቡ መመልከት እንደሚቻል በመግለጽ፣ ከላይ የጠቀሳቸውን ቀሪ የምርመራ ሥራዎች በማስታወስ የጠየቀው ተጨማሪ ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማና የመርማሪ ቡድኑን መዝገብ ወስዶ ከተመለከተ በኋላ፣ መርማሪ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የቻለውን መሥራቱን እንደተገነዘበ ገልጿል፡፡ በመሆኑም የምርመራ ቡድኑ ቀረኝ ለሚለው የምርመራ ሥራ 14 ቀናት በመፍቀድ ለኅዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡