Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹የጎዳና ሩጫ ለማዘጋጀት መመዘኛ መስፈርት መቀመጥ አለበት›› አቶ ኤርሚያስ አየለ፣ የታላቁ ሩጫ...

‹‹የጎዳና ሩጫ ለማዘጋጀት መመዘኛ መስፈርት መቀመጥ አለበት›› አቶ ኤርሚያስ አየለ፣ የታላቁ ሩጫ ዋና ሥራ አስኪያጅ

ቀን:

ከአራተኛው አገር አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫ ጊዜ ጀምሮ ቀደም ሲል ሲሠራበት የነበረበትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትቶ ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያን ተቀላቀለ፡፡ እ.ኤ.አ. በመስከረም 1998 ዓ.ም.  የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅ ከሆነ በኋላ በ1997 ዓ.ም. በማንችስተር ከተማ የአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ ኃይሌ ገብረሥላሴ መወዳደሩን ተከትሎ ወደ ሥፍራው የማቅናት ዕድል አገኘ፡፡ በውድድሩ ላይም ዕውቅናን ካተረፉ የውድድር አዘጋጆች ጋር ልምድ መቅሰም ቻለ፡፡ በእንግሊዙ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ በስፖርትና መዝናኛ ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡ ከሁለት ዓመታት የማርኬቲንግ ሥራ አስኪያጅነት ሥራ በኋላ የቀድሞ የታላቁ ሩጫ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሪቻርድሰን መልቀቅን ተከትሎ አቶ ኤርምያስ አየለ 2003 ዓ.ም. ኃላፊነት ተቀብሎ በዋና ሥራ አስኪያጅነት እየመራ ይገኛል፡፡ ከ44 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች የሚካፈሉበት 18ተኛው የታላቁ ሩጫ ኅዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም. መነሻና መድረሻውን ስድስት ኪሎ በማድረግ ይከናወናል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች አስቸኳይ ስብሰባን ተከትሎ ከመስቀል አደባባይ ወደ ስድስት ኪሎ መነሻና መድረሻውን ያደረገው ታላቁ ሩጫ የቦታ ለውጥ ማድረጉን ተከትሎ ብዙ ክርክሮችን አስተናግዷል፡፡ ስለ ዘንድሮ ታላቁ ሩጫ የውድድር ዝግጅትና የቦታ ለውጥ ድርድሮቹን በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ ከአቶ ኤርምያስ አየለ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 18ተኛ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ የዘንድሮ ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ ኤርምያስ፡- የዘንድሮውን ሩጫ 2011 ዓ.ም. ቶታል ታላቁ ሩጫ ብለን ነው የምንጠራው፡፡ እንደሚታወቀው ዓለም አቀፍ የጎዳና ላይ ሩጫዎች የራሳቸው ስያሜዎች አላቸው፡፡ በዚህም መሠረት ከእኛ ጋር ሦስቱን ዓመታት ያሳለፈው ቶታል ዘንድሮም ከዚህ በፊት የነበረውን ውል አጠናቆ አዲስ ውል በመፈራረምና ስያሜውን በመያዝ አብሮን ይቀጥላል፡፡ በአጠቃላይ 44 ሺሕ ተመዝጋቢዎች በዘንድሮ ውድድር ላይ ይገኛሉ፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባና ታላቁ ሩጫ ፕሮግራም ቀን ተመሳሳይ በመሆኑ መነሻና መድረሻውን ስድስት ኪሎ አድርጎ ይካሄዳል፡፡ የተሳታፊ ቁጥር አልጨመርንም፡፡ ከ44 ሺው በተጨማሪ 10 ሺሕ ተሳታፊዎች የመሳተፍ ፍላጎት ቢኖራቸውም የውድድሩን ጥራት ማሻሻል ስለምንፈልግ መልሰናቸዋል፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሒደት እየተለመደ በመምጣቱ የተሳታፊው ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፤ በዚህ ጉዳይ ምን ለማድረግ ታቅዷል?

አቶ ኤርምያስ፡- የተሳታፊ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎና የተካፋዮችን ፍላጎት ለማርካት የተለያዩ ዘዴዎችን ስንቀይስ ቆይተናል፡፡ ይህም የአረንጓዴና የቀይ ማዕበል የማስጀመር ሒደት ነው፡፡ ምክንያቱም ደግሞ ሁሉንም በአንዴ መልቀቅ ስለማያስችል ነው፡፡ በዘንድሮው ውድድር ላይ 10 ኪሎ ሜትሩን ከአንድ ሰዓት በፊት የሚጨርሱት ሰባት ሺሕ ተሳታፊዎች በመለየት ቀደም አድርገን እናስጀምራለን፡፡ ቀሪዎቹን 37 ሺሕ ተወዳዳሪዎች ደግሞ የተወሰነ ጊዜ በመስጠት እንዲከተሉ ይደረጋል፡፡ በዓለም ላይ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ በአሜሪካ ውስጥ የሚካሄደው ፒችትሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ የጎዳና ላይ ሩጫ 57 ሺሕ ተሳታፊዎች ይካፈላሉ፡፡ የ10 ኪሎ ሜትር ሩጫው ላይ የሚካፈሉትን ተሳታፊዎች በአግባቡ ለማከናወን ሲባል ከ30 እስከ 40 የሚደርስ ማዕበል አላቸው፡፡ የእኛ ግን በአረንጓዴና በቀይ ቀለም ተከፍሎ ሁለት ማዕበል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ቀስ በቀስ ያንን ሒደት እስክንለምድ ቁጥሩን ባለበት ማስኬድን መርጠናል፡፡ ወደ ፊት ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉት የጎዳና ላይ ሩጫ እኩል መጓዝ ስላለብን የተሻሻለ መንገድ መቀየስ እንዳለብን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- በታላቁ ሩጫ ከሚሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች ባሻገር አዳዲስ አትሌቶች ስማቸውን የሚያሰፍሩበት መድረክ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከውጭ አገርም ተጋብዘው የሚሳተፉ ነበሩ፡፡ በዘንድሮው ላይ የአትሌቶች ተሳትፎ ምን ይመስላል?

አቶ ኤርምያስ፡- ከብዙኃኑ ተሳታፊዎች ባሻገር የአትሌቶች ፉክክር ሌላኛው የውድድር ድምቀት ነው፡፡ 300 ወንድና 200 ሴት አትሌቶች ከክልል፣ ከክለብ፣ ከከተማ አስተዳደሮችና በግል የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ ከዚህ ቀደም በብዛት የኬንያ አትሌቶች ይሳተፉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ከኤርትራ የሚመጡ አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ እንደዚሁም ከዑጋንዳ ቦትስዋናም አትሌቶች ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በዘንድሮ የጎዳና ላይ ሩጫ አዲስ ነገር ምን አለ?

አቶ ኤርምያስ፡- ታላቁ ሩጫ በየዓመቱ አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ይመጣል፡፡ ዘንድሮ ጥራቱን የጠበቀ ቲሸርት ከውጭ አገር አስመጥተናል፡፡ አዲሱ ቲሸርት ጥራቱን የጠበቀና በሙቀት የሚከሰተውን ላብ ቶሎ ማትነን የሚያስችልና ቀለል ያለ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሙሉ ከለር ያለው ቲሸርት ተጠቅመን አናውቅም፡፡ በፊት ቲሸርት የምናሳትመው የኢትዮጵያ ባንዲራን ተከትለን ሲሆን ዘንድሮ ግን ነጭ ቲሸርት በአረንጓዴ እንዲሁም በቀይ ስትራይፕ ያለውን አሳትመናል፡፡ ሌላው የታላቁ ሩጫ ተሳታፊዎች አባላት ምዝገባን ጀምረናል፡፡ በውድድር ላይ ለመሳተፍ በቂ ቅድመ ዝግጀት ሳያደርጉ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች ላይ በልብ ድካም ችግር አደጋ ይከሰታል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ እንዲረዳቸው የልምምድ ትምህርቶች እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡ የጤና ባለሙያዎችም በውድድሩ 500 ሜትር ርቀት ላይ ቀይ መስቀል የመጀመሪያ ዕርዳታ እንዲሰጡ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ በተጨማሪም የሻወር ዕጥረት እንዳለ ቅሬታ ይቀርብ ነበር፡፡ ዘንድሮ ሦስት ቦታ ይኖረናል፡፡

ሪፖርተር፡- በአፍሪካ መሪዎች አስቸኳይ ስብሰባ ምክንያት የቀን ቅያሪ ማድረግ እንዳለባችሁ ከመንግሥት በኩል ቀርቦ ነበር፡፡ ከተወያያችሁ በኋላ ቦታ እንድትቀይሩ ተወስኗል፡፡ ድርድሩ እንዴት ነበር?

አቶ ኤርምያስ፡- ታላቁ ሩጫ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሕዝቡ ዘንድ ተወዳጅ ያደረገው ቀኑን ጠብቆ መከናወኑ፣ ጠንክረን መሥራታችን፣ ታዋቂ አትሌቶችን ማሳተፍ መቻሉና፣ በየዓመቱ ማሻሻያዎች ማድረጉ ነው፡፡ እነዚህን ማድረግ መቻላችን በዓለም አቀፍ ደረጃ የራሱ የውድድር ቀን በመያዝ በዓለም አቀፉ ማኅበር ሊመዘገብ ችሏል፡፡ ባለቀ ሰዓት የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ቀን ከእኛ ጋር በመደረቡ ምክንያት የቦታ ለውጥ ለማድረግ ተስማምተናል፡፡ እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ቀኑን ከመቀየር ቦታ ለመቀየር ተወስኗል፡፡ የውድድር ቀኑን መቀየር ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና የውጭ አገር ተሳታፊዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረን ያደርጋል፡፡ ይኼ ውድድር ከውድድር በላይ ለአገራችን በጎ ገጽታ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ ለ17 ዓመት የቀን ቅያሬ ሳናደርግ ቆይተን አሁን ቀኑን ብንቀይር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን ዕውቅና ይቀንሳል፡፡ ለእኛ በቀላሉ ከመስቀል አደባባይ ወደ ሌላ ቦታ ውድድር መቀየር እንደ አዘጋጅ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንድ ዓመት የተዘጋጀንበት በሳምንት ውስጥ መቀየር ከባድ ነው፡፡ ችግሩ የሚጀምረው የውድድሩን መንገድ መለካትና የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን የፕሮግራም መሰናዶ ማዛባት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ እንደ አገር ስህተቶችን መማር አለብን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ዝግጅቶች እንደ መስቀል በዓል ለቱሪዝሙ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን አገሪቷ ያለችበትን የለውጥ ሒደትና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በመሆኗ ቦታውን በመቀየር አጋርነታችንን አሳይተናል፡፡ ምክንያቱም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚመጡት መሪዎች ደኅንነት ቀዳሚ ስለሆነ፡፡

ሪፖርተር፡-  የውድድሩን ቀን መለወጥ ይኖርባችኋል የሚለው ሐሳብ ሲቀርብ የተወሰኑ ክርክሮች  እንዳደረጋችሁ ተገልጿል፡፡ በዚህም ታላቁ ሩጫ ውሳኔውን የተቀበለበት ሒደት እንዴት ነው?

አቶ ኤርምያስ፡- ይኼን ጉዳይ እንደሰማን ቀጥታ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር ነበር ግንኙነት ያደረግነው፡፡ እነሱም ጉዳዩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተያዘ አሳወቁን፡፡ በዚህም ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ ቱሪዝም አብሮን ሲሠራ ስለነበረና የከተማ አስተዳደሩም ፈቃድ ሰጪ አካል ስለሆነ ውይይት ጀመርን፡፡ በውይይቱም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባት ከስምምነት ላይ ደረስን፡፡ ኢትዮጵያ ለውጥ ላይ መሆኗን ተከትሎ ይኼንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ነበረብን፡፡ ስለዚህ በውይይቱ እኛ መቀየር የምንችላቸውን ጉዳዮች ጠቀስን፡፡ የታላቁ ሩጫ አንደኛው መንገድ ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ባለበት መንገድ በመሆኑ አንድ መሪ ልውጣ ቢል አስቸጋሪ ሁኔታ ሊከሰት ስለሚችል ቦታውን መቀየር አስፈልጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች እንደ መስቀል አደባባይ ዓይነት ታሪካዊ  ቦታዎችን ለመነሻና መድረሻ ተመራጭ ሲያደርጓቸው ይስተዋላል፡፡ እንደዚህ  ተደራራቢ ችግሮች እንዳይከሰቱ እንደ አገር ምን ዓይነት መንገድን መከተል ይገባል?

አቶ ኤርምያስ፡- በዓለም ትልልቅ የጎዳና ሩጫዎች ታሪካዊ ቦታዎችን መነሻ በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ለንደን ማራቶን፣ ኒዮርክንና በርሊን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ አገሮች በታሪካዊ መነሻ ቦታዎች ከተማቸውን ያስተዋውቁበታል፡፡ ስለዚህ በእኛም ዘንድ ይሄን መንገድ መከተል ይኖርብናል፡፡ ጃንሜዳን መነሻ በማድረግ ከተማዋን ማስተዋወቅ አይቻልም፡፡ ያደጉት አገሮች ለእንደዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች አማራጭ መንገዶች አላቸው፡፡ እኛ እዚያ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ስለዚህ ከዚህ ትምህርት ወስደን ዝግጅቱ ሲመጣ መቅደም ያለበት ማስቀደም አለብን፡፡ ተሰብሳቢዎችም ወደ ውድድሩ መጥተው በኢትዮጵያ ትልቁን የጎዳና ላይ ሩጫ መመልከት እንዲችሉ ግብዣ ቢደረግ ለስብሰባው በመጡት የሚዲያ ባለሙያዎች አገሪቷን ማስጎብኘት ይቻላል፡፡ ወደፊት ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ እኛም በዕቅዳችን ውስጥ እናካትተዋለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በጎዳና ላይ ሩጫ ቀዳሚ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ አዘጋጆች በራሳቸው መርሐ ግብር ውድድር ሲያዘጋጁ ይስተዋላል፡፡ እናንተ እንዴት ተመለከታችሁት?

አቶ ኤርምያስ፡- ውድድር ማዘጋጀት ሚስጥሩ ልምድ ነው፡፡ እኛ ልምድና ጥሩ ቡድን ስላለን ስኬታማ 17 ዓመታትን ማሳለፍ ችለናል፡፡ ስለዚህ ሰው መጥቶ ውድድር አዘጋጃለሁ ሲል ማየት ነው፡፡ እስካሁን ትልልቅ ውድድሮች በሰፊው ተዋውቀው እንዴት እንደተዘጋጁ መታዘብ ችለናል፡፡ ውድድር ለማዘጋጀት ታታሪና ዝግጁ የሆነ ሰው ይፈልጋል፡፡ ስኬት አንደኛው መለኪያ ነው፡፡ ስኬት እንዴት ይለካል? ውድድሩ ቀጣይነት ይኖረዋል ወይ? ቲሸርት ስለተሸጠ ብቻ በስኬት ይጠናቀቃል ማለት አይቻልም፡፡ ዋናው ነገር ሰው እንዳይጉላላ የሚለው ቀዳሚ ነገር ነው፡፡ ልምድ በሌለው ሰው መንገድ ተዘግቶ ሰው ባይጉላላ መልካም ነው፡፡ ፈቃድ ለሚሰጠው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መመዘኛ ይውጣ እያልን ነው፡፡ ስለዚህ ውድድር ለማዘጋጀት የአቅም መመዘኛ መስፈርት መቀመጥ አለበት፡፡ ሁለት ሺሕ ሰው ማስተናገድ የማይችል ሰው 10 ሺሕ ሰው ማስተናገድ ይችላል የሚለው ቅድሚያ መታየት አለበት፡፡ በሌሎች አገሮች ብዙ መስፈርቶች ከደኅንነትና ከተለያዩ ችግሮች አኳያ ኃላፊነት መውሰድ ይችላሉ ወይስ አይችሉም የሚለው ተመዝኖና ልምድ ታይቶ ነው ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ ልምድ እንጂ ፉክክር መኖሩ አይከፋም፡፡ እየተዋወቁ ያሉ ውድድሮች አሉ፡፡ በሳምንት ልዩነት ውስጥ ይደረጋሉ፡፡ ይሄ ደግሞ በተቀራራቢ ቀናት መደረጉ እኛ ላይ ጥላ የሚያጠላው ነገር ይኖራል፡፡ ስለዚህ አዘጋጁ በአግባቡ መገምገም ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በአገር ውስጥና በአፍሪካ ውድድሮችን እያስተናገደ ቆይቷል፡፡ በቀጣይ ያለው መርሐ ግብር ምን ይመስላል?

አቶ ኤርምያስ፡- በአገር ውስጥ ውድድሮች ዓምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 75ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአምስት ክልሎች ውድድሮችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ በአገሪቱ በነበሩት አለመረጋጋት ግን ኦሮሚያ ውስጥ አላደርግንም፡፡ በዋነኛነት ግን በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች ዕርዳታ ለማሰባሰብ አትሌቶች ዝግጅት ያደርጉ ስለነበር የእነሱን መርሐ ግብር መጋፋት ስላልፈለግን አላከናወንም፡፡ ከዚህ በኋላ በየዓመቱ የሚከናወኑት የክልል የጎዳና ላይ ሩጫዎች በቀዳሚነት ይኖሩናል፡፡ በባህር ዳር፣ መቐለ እንዲሁም አዳማ ላይ በቀጣይነት ለማከናወን የአምስት ዓመት ዕቅድ ይዘናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...