Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበሐዋሳ ከተማ ሕገወጥ ግንባታ ብሶበታል

በሐዋሳ ከተማ ሕገወጥ ግንባታ ብሶበታል

ቀን:

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ የሆነችው ሐዋሳ ከተመሠረተች ከ60 ዓመት በላይ ሆኗታል፡፡ የከተማዋ ማስተር ፕላን በተለይ የመንገዶቹ ፕላን በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ከተሞች በአንፃራዊነት ጥሩ ደረጃ ያላት ከተማ ያሰኛታል፡፡ ሆኖም በካርታ ላይ ያለው የከተማዋ ማስተር ፕላን በአግባቡ ባለመተግበሩ ምክንያት በመንገዶች አሠራር ላይ በርካታ ግድፈቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡

በሐዋሳ ከተማ ውስጥ በርካታ የንግድ ድርጅቶች ከሕጋዊ ይዞታቸው ውጪ ለተሽከርካሪ ማቆሚያ የተተዉ ቦታዎችን በሕገወጥ መንገድ ወደ መንገድ ዳርቻ በመግፋትና አስፋፍተው በመያዛቸው የከተማዋ መንገዶች እየጠበቡና የትራፊክ መጨናነቅም እያስከተሉ ነው፡፡ ለማስረጃ ያህል ታይም ካፌ፣ ፍሪላንድ ካፌ፣ ዊነርስ ካፌ፣ አሜ ካፌ፣ ሎጊታ ካፌ፣ የቀድሞ ኢንጆሪ ኬክ ቤት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በከተማዋ ጎልቶ የሚታየው ሌላው የፕላን ግድፈት ከዋርካ ሆቴል አደባባይ ተነስቶ ወደ ጉድጓዳ ሠፈር የሚወስደው መንገድ፣ መንታ መንገድ በመሆኑ ለእግረኛም ለተሽከርካሪም አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ ከዚሁ አደባባይ ወደ ዓረብ ሠፈር የሚወስደው መንገድም በፕላኑ መሠረት መንታ መሆን ሲገባው ነጠላ መንገድ በመሆኑ በተለይ በገበያ ቀናት ማለትም ሰኞና ሐሙስ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይታይበታል፡፡

ሌላው አስገራሚ ጉዳይ እግረኞች በዚህ አካባቢ የሚጓዙት ዋናው የተሽከርካሪ መንገድ ውስጥ እየገቡ መሆኑ ነው፡፡ በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ባለፈው ሰኔ ወር በተከሰተው ግርግር አጋጣሚውን ተጠቅመው በተንቀሳቀሱ ሰዎች አማካይነት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የመሬት ወረራ እየተካሄደ ነው፡፡ ማንነታቸው የማይታወቁ ወጣቶች ለአረንጓዴ ልማት የተከለሉትን ቦታዎች በማጠር ለሽያጭ እያዘጋጁ ይገኛሉ፡፡ በሐዋሳ ከተማ ዙሪያ በተለይ በአላሙራ፣ በዳቶ፣ በአሊቶና በኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ ከ20 ሺሕ በላይ ሕገወጥ ቤቶች ተገንብተው ይታያሉ፡፡ ለእነዚህ ሕገወጥ ቤቶች ግንባታ ለአካባቢው የቀበሌ አመራሮች ለአንድ ቤት እስከ 30 ሺሕ ብር ጉቦ እየተሰጠ በመሆኑ የከተማዋ ገጽታ እንዲበላሽ አስተዋጾ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የከተማው አስተዳደር ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከመንግሥት በተመደበ በጀት 20 ማኅበራትን በማደራጀት ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ከጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ጎን ለእያንዳንዱ ማኅበር 360 ሺሕ ብር ተመድቦ የዋናውን መንገድ በከፊል በመውሰድ በቂ ጥናት ሳይደረግ የከተማውን ገጽታ ያበላሹ የጭቃ ቤቶች ተሠርተው የመኪና እጥበት ሥራውም ሳይጀመር ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ባክኗል፡፡ በዚሁ ምክንያት የመንገዱ ፕላን በመጥበቡ የአካባቢው ፋብሪካዎች በወቅቱ ለከተማው አስተዳደር ከፋብሪካዎች ምርት ለማጓጓዝም ሆነ ጥሬ ዕቃ ለማስገባት የመንገዱ መጥበብ ችግር እንደሚፈጥርባቸው ቅሬታቸውን ለከተማው አስተዳደር ቢገልጹም በቂ ምላሽ አልተሰጣቸውም፡፡

 የሐዋሳ ከተማ ማስተር ፕላን ምንም እንኳ ለከተማዋ ዘመናዊ ቢሆንም፣ በአተገባበር ረገድ በርካታ ግድፈቶች እየታዩበት በመሆኑ ጉዳዩ ከመባባሱ በፊት ትኩረት ካልተሰጠውና ዕርማት ካልተደረገበት፣ ወደፊት ሐዋሳን እንደ አዲስ አበባ ወደ መልሶ ማልማት ሥራ በማስገባት ከፍተኛ የመንግሥት ሀብት ከማባከኑም በተጨማሪ፣ ከተማዋን ለነዋሪው ሕዝብ እንዳትመች ያደርጋታል፡፡ በመሆኑም የሐዋሳ ከተማ ማስተር ፕላን አተገባበር በፌዴራል የከተማ ልማት ባለሙያዎች ኦዲት መደረግ ይኖርበታል፡፡

(ማቴዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...