Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በቀደም ዕለት አውቶቡስ መሳፈሪያ አጠገብ ያለ ቢል ቦርድ መሳይ ሰሌዳ ላይ የዕርቃን ያህል የተገላለጠች ወጣት ሴት ያለችበት የፊልም ማስታወቂያ እያየሁ በሐሳብ እንደነጎድኩ አንድ ዕድሜ የጠገቡ አዛውንት ጠጋ ብለውኝ፣ ‹‹ሰማህ ወዳጄ?›› አሉኝ፡፡ እኔም በአክብሮት፣ ‹‹አቤት አባቴ?›› አልኳቸው፡፡ ‹‹ለመሆኑ እዚህ አገር ሕግ የለም እንዴ?›› በማለት ጥያቄ አቀረቡልኝ፡ ‹‹ሕግማ መኖር አለ፡፡ ነገር ግን ከሕጉ በፊት እኮ ሞራልና ሥነ ምግባር ቢቀድሙ ጥሩ ነበር፤›› ስላቸው፣ ‹‹አሁን ገና ቁም ነገሩን አመጣኸው፡፡ አየህ ሞራልና ሥነ ምግባር የአንድ አገር ምሰሶ መሆን ሲገባቸው፣ እንዲህ ያለ ጋጠወጥነት አገር ያጠፋል፤›› ብለውኝ እሳቸውም በሐሳብ ጭልጥ አሉ፡፡ እኔም ተከትያቸው ነጎድኩ፡፡

ሁለታችንም ከነበርንበት የሩቅ ዓለም ስንመለስ እንደገና ዓይን ለዓይን ተያየን፡፡ ‹‹አባቴ ለምን ሻይ ቡና እያልን ትንሽ አናወራም?›› ብያቸው ከተስማሙ በኋላ ካፌ ጎራ ብለን ቡናችንን እየጠጣን ወግ ጀመርን፡፡ ‹‹የእኔ ልጅ ከእኔ ከአባትህ ጋር ለመወያየት በመፈለግህ አመሠግንሃለሁ፡፡ እኔም አንተን የሚያክሉ ለወግ ለማዕረግ የደረሱ ሦስት ልጆች አሉኝ፡፡ እንግዲህ እንደ አባትና ልጅ እናውጋ፤›› ብለውኝ ማውራት ጀመርን፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ዝቅጠት የደረሰበትን ደረጃ ካብራሩልኝ በኋላ፣ ችግሩ የትውልዱ ብቻ ሳይሆን ይኼንን ትውልድ አበላሽቶ ያሳደገው ጭምር መሆኑን ነገሩኝ፡፡ ‹‹ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይ ጫትና ሺሻ የሚነግደው ማን ነው? እኛ! ትምህርት ቤት አካባቢ አልቤርጎ ሠርቶ ለተማሪዎች ድሪያ የሚያዘጋጀው ማነው? እኛ! ለአቅመ አዳምና ሔዋን ላልደረሱ ልጆች ቢራና አረቄ የሚሸጠው ማን ነው? እኛ! ወጣቶችን ውሸት የሚያስተምረው ማን ነው? እኛ!..›› እያሉ ዘርዝረው ቀዳሚውና አዲሱ ትውልድ እየተቀባበሉ ያሉት ለአገር የማይበጅ መሆኑን አስረዱኝ፡፡ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣና በመጽሔት ለሕፃናት ዕድገት የማይበጁ እሳቸው ‹‹መርዛማ›› ያሉዋቸው ነገሮች ትውልዱን እንዴት እያጠፉት እንደሆነ ተነተኑልኝ፡፡

‹‹የእኔ ልጅ ድሮ በሲኒማ ሲሳሳሙ የምናውቀው ፈረንጆችን ነው፡፡ ልብ ብለህ እንደሆነ የህንድ ፊልም ውስጥ መሳሳም የሚባል ነገር የለም፡፡ እዚህ አገር ጡትና ጭን በግላጭ እየተዳበሰ ከሕዝባችን ባህል ውጪ ሲላላሱ ማየት ምን ይባላል? አንድ ቀን ከልጅ ልጆቼ ጋር ተቀምጬ በአገር ሰላም አንዱን አስቂኝ ብጤ ፊልም ስናይ መሳሳም ሲጀመር ሪሞት ኮንትሮሉን አንስቼ እስካጠፋው ድረስ ሕፃናቱ ፐ…ፐ…ፐ… ሲሉ የምገባበት ጠፋኝ፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ የዚህን አገር ፊልም ማየት ትቼ የፈረንጅ ካራቴና ጦርነት እያየሁ ነው፡፡ ያለ ፍላጎቴ በስተርጅና ስደት ማለት ይኼም አይደል?›› ብለው ተከዙ፡፡

- Advertisement -

እኔንና እኚህን አዛውንት እንዲህ አገናኝቶ ጉድ ያሰኘን የአንድ ፊልም ማስታወቂያ ነው፡፡ አዛውንቱ በመመሰጥ ውስጥ ሆነው፣ ‹‹አየህ! አሁን ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ ደረስን፡፡ ካልጠፋ አጀንዳ እንዲህ ዓይነት ፊልም ይወጣል? የፈለገውን ያህል ለውጥ ለውጥ ቢባል እንዲህ ዓይነት መራቆት ለምን ያስፈልጋል? ለውጥ አገር የሚያሳድግና ትውልድ የሚቀርፅ መሆን አለበት፡፡ አይደል እንዴ?…›› እያሉ ተብከነከኑ፡፡ ‹‹ይኼው እንዲህ ዓይነት ፊልም ከተሠራ ነገ ደግሞ ይለይላችሁ ተብሎ የአደባባይ ወሲብ ላለመምጣቱ ምን ዋስትና አለ? ከእንዲህ ዓይነቱ ነገር ማን ነው የሚማረው? የፈለገውን ዓይነት ይዘት ይኑረው ይኼ በተለይ ለሚያድጉ ሕፃናት ጥሩ አይደለም፡፡ እኛስ የዘራነውን እያጨድን ነው፡፡ ያለ ኃጥያቱ የጥፋት ሰለባ የሚሆነው ትውልድ አያሳዝንም?›› ብለውኝ በትካዜ አዩኝ፡፡ እኔም በትካዜ ውስጥ ሆኜ እያየሁዋቸው የልጆቼ ዕጣ ፈንታ አሳሰበኝ፡፡

(ዮሴፍ መገርሳ፣ ከአያት)

***

ጊዜው በአገራችን ኢትዮጵያ የመስቀል ዋዜማ የደመራ በዓል ዕለት ነበር፡፡ ሁኔታዎች ተገጣጠሙና በዕለቱ ሥራ አልነበረኝምና ዕድሜ ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ከኢንተርኔት የጠለፍኩትን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ከዋናው የቲቪ መስኮት በማገናኘት፣ ይህን ድንቅ በዓል ስከታተል የበሬ ደውል አቃጨለ፡፡ የሕንፃ ሙያ ባለቤት የሆነው ፊንላንዳዊ ጎረቤቴ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡና በተለይም የይርጋ ዓለም ቡና ነፍሱ ነው፡፡ እናም አንዳንዴ እሱም እረፍት የሆነ ቀን ጎራ እያለ አሳምሬ የማፈላትን የአገሬን ቡና እየላፈ፣ ጥሎበት የኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ በተለይ የደቡብን ትርዒት ከእኔ ጋር ማየት ይወዳል፡፡

ዛሬ ደግሞ ልዩ ቀን ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህል ማዕከል ልዩ ዕውቅና የሰጠው የመስቀል በዓል ዋዜማ የደመራ ቀን የተለመደውን ቡናችንን አፈላልተን ስናበቃ፣ ከዚህ ውብ ፕሮግራም ላይ ተጥደን ቀሳውስቱ፣ ካህናቱ፣ ዲያቆናቱ ከምዕመናን ጋር ታጅበው የሚያስደምጡት ያሬዳዊ ማህሌት፣ ቅኔው፣ ዝማሬው፣ ወረቡ፣ የከበሮው ምት፣ የሕዝቡ ኅብረ ቀለም አልባሳት ፍሰሐውና እርካታው ልዩ ቢሆንም፣ ለእኔ ብቸኝነትና ባዶነት በአንፃሩ ምነው በወገኔ ዘንድ አብሬ በነበርኩ ሌላ የቁጭት ቁስል ነው፡፡ ፊንላንዳዊ ጎረቤቴ ግን በተደጋጋሚ ወደ አገር ቤት ጎራ በማለቱ ይኼንን ክብረ በዓል በገሃድ በማየቱ በተመስጦ ነበር የሚመለከተው፡፡

ይኼንን የሳምንት ገጠመኝ መጫር አለብኝ ያልኩት በዚህ ጉዳይ ነበር፡፡ የዚህ ድንቅ የደመራ በዓል የመጨረሻ መዚጊያ የደመራ በዓል ግዙፍ ችቦ፣ በብፁዕ አባታችን አቡነ ማትያስ ፀሎትና ቡራኬ ከተለኮሰ በኋላ የተከተለው የርችት ተኩስ ያን ፊንላንዳዊ ጎረቤቴን ፊቱን አጨለመ፣ ከእሱ በከፋ ፊቴ በንዴት ጠቆረ፡፡ ዓለም ውብ ድንቅ በዓል ብሎ በክብር የሰቀለን እኮ ዳር እስከዳር በሚንቀለቀለው የጧፍ ብርሃን በያሬዳዊ ዝማሬ፣ ተፈጥሯዊ በሆነ የችቦ ብርሃን፣ ምዕመናን በለበሱት ኅብረ ቀለም የባህል ልብስ እንጂ የእኛ ባልሆነው የፈረንጅ ልቃሚ በሆነ ሰው ሠራሽ ርችት አልነበረም፡፡

ያ ታዋቂ ባለቅኔ ገጣሚና ደራሲ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ (ገሞራው) ‹‹እንግዲህ እርግማኔን ላወርድ›› ነው  ብሎ እንደከተበው ሥነ ግጥም፣ እኔም የምሬን በዚህ ውብና ድንቅ የደመራ በዓል ላይ ርችት ይተኮስ ብሎ ያንን የእኛ ያልሆነ ነጫጭባ ትርዒት እንድናይና እንድናዝን ያደረገን ሰው እንደ ገሞራው ‹‹ከሲኦል መንደር መቀመቅ ያስገባው›› ባልልም፣ እግዚአብሔር የእጁን ይስጠው እላለሁ፡፡ መቼ ይሆን በራሳችን የጫማ ልክ መጫማት የምንጀምረው?

ቸር ያሰንብተን

(ቧዞ፣ ከስዊድን)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...