Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክመንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውል ሕግ ጉዳይ

መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውል ሕግ ጉዳይ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነው፡፡ ኢንፎርሜሽን በተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ታግዞ ለሰው ልጅ ሕይወት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ንብረት የሆኑ በርካታ ፈጠራዎች መኖራቸውም ይታወቃል፡፡ የእነዚህ ንብረቶች ባለቤት የሆኑ ወይም ባለመብት የሆኑ ሰዎች ንብረቶቹን መጠቀም ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ውልን መሠረት ያደረገ ግንኙት ይፈጥሩባቸዋል፡፡  ከእነዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የኮምፒዩተር ፕሮግራምና (ሶፍተዌር) እና የኮምፒውተር ፍላጮች (ማይክሮችፕ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ የሚያጠነጥነው የውሉ ጉዳይ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መካከል የኮምፒውተር ፕሮግራምና የኮምፒውተር ፍላጭ በሚሆኑበት ጊዜ የውል ሕጋችን ምን እንደሚመስል በማሳየት ሕግ አውጭው መላ እንዲይዝለት ማመላከት ነው፡፡ በውል ሕግ ትምህርት እንደሚታወቀው ውል በተዋዋዮቹ መካከል ሕግ ነው፡፡ ውል የሚዋዋሉ ሰዎች በመካከላቸው ሕግ እየሠሩ ነው፡፡ ተዋዋዮቹ የሚያደርጉት ግንኙነት ምን እንደሆነ፣ ምን መደረግ እንዳለበት፣ ሳይፈጸም ቢቀር ስለሚያስከትለው ውጤት ራሳቸው ሕግ ያበጁበታል፡፡ የውልን ምንነትና አንድ ውል ማሟላት ያለበትን ዝቅተኛ መሥፈርት ማስቀመጥ የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ በኢትዮጵያም አሁን በሥራ ላይ ያለው በ1952 ዓ.ም. የወጣው የፍትሐ ብሔር ሕግ የውልን ምንነት፣ የውል አደራረጉ መሥፈርቱንና ውጤቱን በሚመለከት በርካታ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡

- Advertisement -

ይህ የፍትሐ ብሔር ሕግ በጥቅሉ ለማንኛውም ውል መሠረት የሆኑ አንቀጾችንና ልዩ ልዩ ውሎችን ደግሞ ልዩ ባህሪያቸውን ከግምት በማስገባት ተጨማሪ ድንጋጌዎችን መያዙ ይታወቃል፡፡ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የቅርብ ጊዜ ክስተት በመሆኑ የፍትሐ ብሔር ሕግ ስለዚህ ጉዳይ ራሱን የቻለ ክፍል ይኖረዋል ተብሎ አይጠበቅም፤ የለውምም፡፡ ነገር ግን ለሁሉም የውል ዓይነቶች በመነሻነት የሚያገለግለው ክፍል ደግሞ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶች የውሉ ጉዳይ በሚሆኑበት ጊዜ በቂ ባለመሆናቸው ተጨማሪ ልዩ ሕግ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሕጉ ውልን ‹‹ንብረታቸውን የሚመለከቱ ግዴታዎችን ለማቋቋም ወይም ለመለወጥ ወይም ለማስቀረት ባላቸው ተወዳዳሪ ግንኙነት በሁለት ወይም በብዙ ሰዎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ነው፤›› በማለት አንቀጽ 1675 ላይ ብያኔ አስቀምጧል፡፡ ከትርጓሜው ብዙ ነጥቦችን ነቅሶ በማውጣት መወያየት ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውልን የሚመለከት ስለሆነ ከእዚሁ አንፃር እንቃኘዋለን፡፡ ውል የሚደረገው ንብረትን የሚመለከት ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራምና የኮምፒውተር ፍላጭም የንብረትነትን መሥፈርት የሚያሟሉ ናቸው፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም የማይጨበጥና የማይዳሰስ ንብረት ነው፡፡ የኮምፒውተር ፍላጭ (ማይክሮችፕ) ደግሞ በውስጡ የኮምፒውተር ፕሮግራም የተጫነበት ዕቃ ስለሆነ ፕሮግራሙ የማይዳሰስና የማይጨበጥ፣ ዕቃው ደግሞ የሚታይና የሚዳሰስ የንብረት ዓይነት ናቸው፡፡ ሁለቱም ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም ንብረት በመሆኑ ባለቤቱ ወይም የባለቤትነት መብት የተላለፈለት ሰው በቅጅ ሕጉ መሠረት ጥበቃ ይደረግለታል፡፡  ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ዝቅ ብለን እንመለስበታልን፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤት የሆነን ንብረት በሚመለከት ሁለት ወይም ከእዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ውል ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በውሉም አዲስ መብትና ግዴታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት ተነፃፃሪ መብትና ግዴታ የሌላቸው ሰዎች አዲስ ግንኙነት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ የነበረን መብትና ግዴታም በአዲስ ውል ሊለውጡት ወይም ቀሪ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ውሉ በመሠረቱ ስምምነት ነው፡፡ ስምምነት ሳይኖር ውል አይኖርም፡፡ አንድ በሕጉ የተቀመጡትን መሥፈርቶች ያሟላ፣ አስገዳጅነት ያለው ውል ተደርጓል ለማለት መሟላት ያለባቸው ዝቅተኛ ሁኔታዎች አሉ፡፡ የመጀመርያው የተዋዋዮቹን ውል የማድረግ ችሎታ ይመለከታል፡፡ በሕግ ውል መዋዋል አይችሉም እስካልተባለ ድረስ ማንም ሰው ውል የማድረግ መብት አለው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሕጉ ውል መዋዋል እንደማይችሉ በጥቅሉ የተቀመጡት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ (የራሱ በስተቀሮች ቢኖሩትም) እንዲሁም በሕግ ወይም በፍርድ የተከለከሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የኮምፒውተር ፕሮግራም ለመሥራትም ይሁን ከዚሁ ጋር በተገናኘ ውል የሚያደርግ ሰው በመርህ ደረጃ እንዲሁ 18 ዓመት የሞላውና ክልከላ የሌለበት ሊሆን ይገባል ማለት ነው፡፡

ሌላው ውል ስምምነት በመሆኑ ተዋዋዮች ወደውና ፈቅደው በነፃ ህሊናቸው ማንም ሳያስገድዳቸው፣ ሳይጭበረበሩና ሳይታለሉ የሚያደርጉት ተግባር ነው፡፡ መታለል፣ መሳሳት፣ መጭበርበርና መገደድ ካለ ስምምነት አለ አያሰኝም፡፡ ሦስተኛው ነጥብ ደግሞ ውል የሚደረግበትን ጉዳይ ይመለከታል፡፡ ውሉ የሚደረግበት ነገር ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ ውሉ ሕገወጥ መሆን የለበትም፡፡ ከሞራል የማይፃረር፣ በግልጽ ምንነቱ የታወቀና ተዋዋይ ወገኖች ሊፈጽሙት ወይም ሊያከናውኑት የሚችሉት መሆን አለበት፡፡ በመሆኑም የኮምፒውተር ፕሮግራሙም ይህንን የኮምፒውተር ፍላጭ ሕገወጥ ነገር ለመፈጸም ተብሎ የሚሠራ መሆን የለበትም፡፡ ከሞራል የሚፃረር፣ በግልጽ ምንነቱ የተበየነና የታወቀ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ አንድ ሁለት ምሳሌዎችን በማንሳት ነገሩን ለማብራራት እንሞክር፡፡ አንድ የሶፍትዌር ኢንጂነርን ከባንክ የተቀመጠ ገንዘብን ባንኩ የሚጠቀምበትን ሶፍትዌር ሰብሮ በመግባት ገንዘብ ወደ ሌላ የባንክ ሒሳብ ቁጥር ለማዛወር የሚያስችል ሶፍትዌር ለመሥራት የሚደረግ ውል በሕግ ፊት ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ አይጸናም፡፡ አለፍ ሲልም ወንጀል ነው፡፡ ወንጀል በሆነ ጉዳይ ላይ ውል መዋዋል አይቻልም፡፡ አንድ ምሳሌ እንጨምር፡፡ አንድ የሶፍትዌር ኢንጂነር ጋር የተደረገው ውል ፈጣሪን (እግዚአብሔርን ወይም አላህን) በኮምፒውተር ላይ ማሳየት የሚችል ፕሮግራም ለመሥራት ቢዋዋሉ ሊተገበር የሚችል ነው ተብሎ ፍርድ ቤት ሠርቶ እንዲያስረክብ ሊያዘው አይችልም፡፡ ሲጀመርም ሊፈጸም የሚችል ስላልሆነ፡፡

የመጨረሻውን ቅድመ ሁኔታ እንመልከት፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ባሰኛቸው መልኩ ውል ሊዋዋሉ ይችላሉ፡፡ ሲፈልጉ በጽሑፍ፣ ካሻቸው ደግሞ በቃል አለበለዚያም በምልክት ውል ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢዋዋሉ፣ ውል መኖሩን ማስረዳት እስከቻሉ ድረስ ውሉ በተዋዋዮቹ ላይ ሕግ ሆኖ መጽናቱ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ሕግ ቆርጦ ውሉ የሚደረግበትን መንገድ ወይም ፎርም ካስቀመጠ በዚያው መሠረት ብቻ ነው መደረግ ያለበት፡፡ ሕግ በጽሑፍ እንዲሆን ካዘዘ በአንድ ሚሊዮን ሰው ፊት የተደረገ ውል ቢሆን እንኳን ውሉ አስገዳጅ አይሆንም፡፡ ለአብነት የማይንቀሳቀስ ንብረትን በሚመለከት ሕጉ በጽሑፍ እንዲሆን ስላዘዘ በቃል ቤት መግዛት ወይም መከራየት በሕግ ፊት የሚያስገድድ ግዴታና መብትን አያስከትልም፡፡ ውል እንደተደረገም አይቆጠርም፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራምና የኮምፒውተር ፍላጭን በሚመለከት የሚደረጉ ውሎች በጽሑፍ እንዲሆኑ የሚያስገድድ በግልጽ የተቀመጠ ሕግ የለም፡፡ ነገር ግን ቀጥለን እንደምንመለከተው የኮምፒውተር ፕሮግራምን በሚመለከት የሚደረጉ ውሎች ውስብስብና በተዋዋዮች መካከልም የሚያስከትሉትም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከፍተኛ በመሆኑ ተዋዋዮች እንዳሻቸው ይስማሙ ዘንድ መተው ጥያቄ ያጭራል፡፡ ስለ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውሎች ለየት ያለ ባህሪያት ከማተታችን በፊት የጽሑፉ ማጠንጠኛ ስለሆነው ሶፍትዌር በቅጅ መብት ጥበቃ አዋጁ ላይ እንደ ንብረት የተወሰደው ምኑ እንደሆነ አስቀድመን እንይ፡፡ ዓላማውም ሶፍትዌር ዕቃ ወይም ሸቀጥ (Goods) አለበለዚያም አገልግሎት (Service) መሆኑን ለመለየት ስለሚረዳ ነው፡፡ ዕቃ ከሆነ በሽያጭ ውል ሕግ ይገዛል፡፡ አገልግሎት ከሆነ ግን የአገልግሎት አቅርቦት ውልን (Contract of Service) የሚመለከቱት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

የኮምፒውተር ፕሮግራም (ሶፍትዌር) እና ዳታቤዝ (በሥርዓትና በዘዴ የተሰደሩ የመረጃ ግብዓቶች) በአዋጅ ቁጥር 410/1996 በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የቅጅ መብት ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ ስለኮምፒውተር ፕሮግራም ምንነት ትርጉም ተሰጥቷል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም (ሶፍትዌር) በመሣሪያ የሚነበብ ጽሑፍ ነው፡፡ የሚያነበው መሣሪያ የሚገኘው ኮምፒውተር ውስጥ ነው፡፡ የኮምፒውተሩ አካል ነው፡፡ ሲያነበውም ኮምፒውተሩ ተግባሩን ማከናወን ይችላል፡፡ አለበለዚያም የታለመለትን ውጤት ወይም የሚፈለግበትን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራም ከቃላት፣ ከኮዶች፣ ከዘዴዎች ወይም ሌላ አኳኋን የተቀነባበሩ የመመርያዎች ስብስብ ነው፡፡ መመርያነታቸው ለኮምፒውተር ነው፡፡ ኮምፒውተሩን ይመሩታል፡፡

የኮምፒውተር ፕሮግራም የሚባለው በመሣሪያ የሚነበበው እንጂ በኮምፒውተሩ ላይ የምንመለከተው ወይም የምንሰማው ወይም የምናገኘው ውጤት አይደለም፡፡ ውጤቱ ጥበቃው ውጤቱን እንዲመጣ ኮምፒውተሩን ለሚያዙት የመመርያዎች ስብስብ ነው፡፡ አንድ የኮምፒውተር ፕሮግራም ንብረት ሆኖ ጥበቃ እንዲሰጠው ማሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንድ ሰው ለሥራው የቅጅ መብት ጥበቃ የሚያገኘው እንደ ሁኔታው የሥነ ጽሑፍ፣ ኪነ ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ መስክ ፈጠራ የሆነ ሥራ የሥራው አንጪው የአዕምሮ ውጤት እስከሆነ ድረስ የሥራው ዓላማና ጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ወጥ (ኦርጅናል) ከሆነና የተቀረፀ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራው በመውጣቱ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ ያገኛል፡፡ በመሆኑም የሥራው አመንጪ ለሥራው ጥበቃ ለማግኘት ሥራው በመጀመርያ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን አለበት፡፡ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ሲባል የሥራ አመንጪው የሠራው ሥራ ከሌሎች ሥራዎች ላይ ያልተቀዳ መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሐሳብ ነው፡፡ ይህም ማለት ሶፍትዌሩ የፕሮግራመሩ የአዕምሮ ውጤት፣ ከሌላ ሰው እንዳለ ያልቀዳው፣ መሆን አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛ መሥፈርት ደግሞ ሥራው ግዙፋዊነት ያገኘ መሆን አለበት፡፡ ግዙፋዊነት (የተቀረፀ) መሆን ማለት አንድ ሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ ሥራ የሥራ አመንጪው የአዕምሮው ውጤት የሆነ ወጥነት ያለው ሆኖ ግዙፍ በሆነ ነገር ላይ መሥፈር አለበት ማለት ነው፡፡

ይህም ማለት የአዕምሮ ውጤት የሆነው ሥራው በሐሳብ ደረጃ የቀረ ሳይሆን አንድ ግዙፍ በሆነ ዕቃ ላይ የሰፈረ መሆን አለበት፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራሙም በወረቀት ወይም ዲጂታል ሆነ ኮምፒውተር ላይ የተቀመጠ መሆን አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ጥበቃ የሚሰጠው ሐሳቡ በመገለጹ ነው፡፡ ይህን የአዕምሮ ውጤቱ የሆነውን ፕሮግራም በወረቀት ላይ ካሰፈረው ወይም ኮምፒውተር ላይ ከጻፈው ነው ጥበቃ የሚያገኘው፡፡ ይህንን ሁኔታ አዋጁ አንቀጽ 2(1) ላይ ማብራሪያ አስቀምጦለታል፡፡ በመሆኑም መቅረጽ ወይም ግዝፈት እንዲያገኝ ማድረግ ማለት አንድ ሥራ፣ ምስል ድምፅ ወይም የአንደኛቸው አምሳያ ምትክ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ ማሳያ አማካይነት እንዲታይ፣ እንዲባዛና እንዲሠራጭ ማድረግ ማለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራምም በተለያዩ መንገዶች ግዙፍነት ሊያገኝ ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ ጥበቃ የሚያገኘው፣ የሆነ ሰው ንብረት ነው ለመባል ግዙፋዊ ነገር ላይ መቀረጽ አለበት ለማለት ነው፡፡

አዋጁ የኮምፒውተር ፕሮግራም በማለት ዕውቅና የሚሰጠው ለኮምፒውተር ብቻ ወስኖ ነው፡፡ ጥያቄው ኮምፒውተር ማለት ምን እንደሆነ ትርጓሜ አልተሰጠውም፡፡ ለአብነት ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮች፣ የኮምፒውተር ፍላጮች (ማይክሮችፕስ) ኮምፒውተር መሆናቸውን የሚያመለክት ፍንጭ በአዋጁ ላይ አናገኝም፡፡ ሶፍትዌር (የኮምፒውተር ፕሮግራም) ግን እነዚህንም መሣሪያዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡም ሆነ በእነሱ አማካይነት የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የግድ ሶፍትዌር አስፈላጊ ነው፡፡ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ እነዚህን ጨምሮ ነው ኮምፒውተርን የተረጎመው፡፡ ስለሆነም፣ የእጅ ስልክ (ሞባይል) እና ሌሎች መሣሪያዎች ላይ የሚሠሩ ሶፍተዌሮች ጥበቃ አልሰጠም፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ አለ፡፡ በሕግ እንደ ንብረት ተቆጥረው ዕውቅና ያልተሰጣቸውን፣ ጥበቃ ያልተደረገላቸውን ነገሮች ዞሮ ዞሮ የአዕምሮ ውጤት፣ ሰው የፈጠራቸው ስለሆኑ፣ የውል ጉዳይ በማድረግ ሌሎች መብቶችን ለመፍጠር ይቻላል ወይ? በሌላ አገላለጽ በሕግ እንደ ንብረት ያልተቀጠረን ነገር በውል ወይም በሌላ ዘዴ ንብረት ማድረግ ይቻላልን?

የኮምፒውተር ፕሮግራም ንብረት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ የማይታይና የማይጨበጥ የማይዳሰስ ሀብት ነው፡፡ ለንብረቱ ባለቤትም በሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 እና 41 ላይ የተገለጹት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡ የንብረቶቹ መሠረት የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ ወይም ሳይንሳዊ የፈጠራ ሥራ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ኮምፒውተር ፕሮግራምም በእነዚህ ሥር የሚገኝ በመሆኑ የተለያዩ የኢኮኖሚና የሞራል መብቶችን ያስገኛል፡፡ የፕሮግራመሩ ኢኮኖሚያዊ መብት ማለት ከፈጠራ ሥራው የሚያገኘው በገንዘብ ሊለካ የሚችል መብት ማለት ነው፡፡ አንድ የሥራ አመንጪ በሥራው ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ መብት ለሌላ ሰው በውል አሳልፎ መስጠት ይችላል፡፡ የሚተላለፉበት ሥርዓት ግን በማስተላለፍ (Assignment) ወይም ፈቃድ (License) በመስጠት ነው፡፡ ይኼ የሚያሳየው በመብቱ መጠቀምን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘትን ለሌላ ሰው በመስተላለፍ እንዲጠቀምበት ማድረግን ነው፡፡ ይህን ያህል ስለኮምፒውተር ፕሮግራምና ማይክሮችፕ እንደ ንብረት የተሰጣቸውን የጥበቃ መጠን ካየን እስኪ እንደ ንብረትነታቸው የውል ጉዳይ በሚሆኑበት ጊዜ የሚኖራቸውን የተለየ ፀባይ ምሳሌዎችን እያቀረብን እንዳስስ፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውሎች ውስብስብ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ቀላል ነው፡፡ በአንድ በኩል ይህንን ዓይነቱን ውል በሚገባ አመልና ፀባዩን አጥንቶ የሚያርቅ፣ የሚገራና የሚመራ ሕግ ባለመኖሩ ተዋዋይ ወገኖች እንዳሻው የሚያደርጉት በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በራሱ ውስብስብና ተለዋዋጭ ብሎም ያልሰከነ (ምናልባትም የማይሰክን) ሙያ በመሆኑ ነው፡፡ እስኪ አንዱን አስቸጋሪ ባህሪውን እናስቀድም፡፡ ሶፍትዌር ዕቃ ነው ወይስ አገልግሎት? ዕቃ ነው ካልን እንደ ማንኛውም የሚሸጥ ነገር በመቁጠር የሽያጭ ሕጉን ተፈጻሚ ማድረግ ይቻላል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ሶፍትዌር ሻጩ በሚሸጠውን ዕቃ (ሶፍትዌር) በተመለከተ ምንም ዓይነት ጉድለት ወይም እንከን (Defect) የሌለው ስለመሆኑ እንዲሁም ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ ጉድለቱ ከታወቀም ይህንኑ ለማስተካከል ኃላፊነት (Warranty Against Defect) ይወስዳል ማለት ነው፡፡ ለተገዛበት ዓላማ በትክክል መስጠት የማይችል፣ አግልግሎቱ ሌላ ከሆነም እንዲሁ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ባለፈም የባለቤትነት ጥያቄ ይዞ የሚመጣ ሰው ካለም የመመለስ ኃላፊነት (Warranty Against Dispossession) አለበት፡፡

እነዚህ ከቁም ነገር ሊገቡ የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዛሬ አንዱን ብቻ እንይ፡፡ በሽያጭ ሕግ መሠረት ገዥው በሚገዛበት ወቅት የቻለውን ያህል አይቶና መርምሮ የመግዛት ግዴታ እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ሶፍትዌርም ለታለመለት ዓላማ መዋል ስለመቻሉ በሚገዛበት ጊዜ የሚታወቅ ሊኖር የመቻሉን ያህል በትክክል የተፈለገውን አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ሊታወቅ እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በአጭር ጊዜ ጉድለት እንዳለበት ላይታወቅ ይችላል፡፡ ፕሮግራሙ ሲሠራ ከአንድ በታች እጅግ አነስተኛ የሆነ ቁጥር ስህተት ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክስተት የሚፈጠረው ተጠራቅሞ ተጠራቅ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች “Last Bug” በማለት ይጠሩታል፡፡ ለአብነት አንድ በጨረር ካንሰር ማከሚያ መሣሪያን እንዲሠራ የሚያደርገው ሶፍትዌር ለአምስት ዓመታት በትክክል ሲሠራ ቆይቶ ያጠራቀማት በጣም ትንሽ የሒሳብ ሥሌት በአምስተኛ ዓመቱ ላይ ማሽኑ ከፍተኛ ጨረር በመልቀቅ ታካሚውን ሊገድል ይችላል፡፡ (ብዙ አገሮችም ተከስቷል)፡፡ በዚህን ጊዜ ሶፍትዌሩ እንከን (ጉድለት) ስለነበረው ያስከተለውን ጉዳት የመካስ ኃላፊነቱ የሻጩ ይሆናል ማለት ነው፡፡  

ለዛሬው እዚህ ላይ ጎርደን እንተወው፡፡ ሀተታው ብዙ ስለሆነና በአንድ ክፍል ማጠቃለል አስቸጋሪ ስለሆነ፡፡ የሆነ ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ግቡ እንዲህ ሲል የሶፍትዌር ኢንዱስትሪው ደግሞ በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕድገት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ በመሆኑና ወደፊትም ስለሚቀጥል ይህንን ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት በመስጠት በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ከሥራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚበረታቱበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት በሌላ በኩል ደግሞ ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆነውና ገንዘቡን የሚከፍለው የኅብረተሰብ ክፍልም ጠበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ መንግሥት ተረድቶ ለዚህ ተስማሚ የሚሆን ሕግ እንዲያወጣ አበክሮ ለመጠየቅ ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...