Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስፈልግ ፍኖተ ካርታ

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተሳትፎን ለማሳደግ የሚያስፈልግ ፍኖተ ካርታ

ቀን:

በኤርሚያስ አመልጋ

የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንትና ሁለንተናዊ የልማት ተሳትፎ ማሳደግ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ከሰጣቸው የፖሊሲ ግቦች አንዱ ነው፡፡ ዳያስፖራው በአገሪቱ ኢንቨስትመንትና ልማት ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ለማሳደግ የተወሰኑ ጥረቶች ቢደረጉም፣ የተመዘገቡት ውጤቶች ግን ተስፋ አስቆራጭ ናቸው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለባቸው የተለያዩ ተጨባጭ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚጠቀሰው ግን በአገሪቱ ግላዊና ፖለቲካዊ ነፃነት የለም፡፡ የመንግሥት ፖሊሲዎችና አመለካከቶችም ለዳያስፖራውና ለግሉ ዘርፍ አመቺ አይደሉም የሚል አመለካከት መስፈኑ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ እርግጡን ለመናገር ዳያስፖራው መንግሥትን እንደ ጠላት ሲያየው ነው የኖረው፡፡ 

አሁን ግን ዳያስፖራው በመንግሥት ላይ የነበረውን የጠላትነት አመለካከት ቀይሯል፡፡ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ፊታቸውን ወደ አገራቸው እንዲመልሱና ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሚቻልበት ልዩ ዕድል የተፈጠረበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡ ኢትዮጵያን ከዳር እስከ ዳር ያጥለቀለቀው አዲስ የለውጥ ንፋስና መንግሥት የተያያዘው የለውጥ ጎዳና የልጅ አዋቂውን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ሁሉም ለውጡንና መንግሥትን ለመደገፍ ዝግጁ የሆነ ይመስላል፡፡ በውጭ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገሪቱን ወደ አንድነት ለመመለስና በልማት ጎዳና ወደፊት ለማራመድ በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ የራሳቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ያሚያቀርብና መንገድ የሚከፍት አዲስ ዓይነት የዳያስፖራ ንቅናቄ ዳግም እንዲያንሰራራ ለማድረግ ጊዜው አሁን ነው፡፡

ዳያስፖራ አንድ ዓይነት ባህሪና መገለጫ ያለው አንድ የተወሰነ ቡድን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ዳያስፖራ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ በግርድፉ ብናየው፣ 90 በመቶው ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ በካሸርነት፣ በታክሲ ሾፌርነት፣ በመስተንግዶና በመሳሰሉ የአገልግሎት ዘርፎች ዝቅተኛ የሥራ ቦታዎች ላይ ተቀጥሮ የሚሠራ ነው፡፡ ከተቀረው አሥር በመቶ ዳያስፖራ አብዛኞቹ ደግሞ ሬስቶራንቶች፣ ካፌዎች፣ ሱቆችና ጥቃቅን የአገልግሎት ዘርፍ ኩባንያዎችን የመሳሰሉ የአነስተኛ ንግድ ድርጅቶች ባለቤቶችና ሕክምና፣ ሕግና ምህንድስናን በመሳሰሉ የተለያዩ የሙያ መስኮች የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ከአጠቃላዩ የዳያስፖራ ቁጥር አንፃር ሲታይ ገንዘብ፣ ዕውቀትና ልምድ ያካበቱ እንዲሁም ወደ አገራቸው ተመልሰው እሴት የሚጨምሩ፣ መጠነ ሰፊ የንግድ ተቋማትን የማቋቋም ፍላጎቱ ኖሯቸው ኢንቨስተር ሊሆኑ የሚችሉ ዳያስፖራዎች ቁጥር እጅግ አናሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ የሚገኝበትን አጠቃላይ ተጨባጭ ሁኔታ በቅጡ መገንዘብ፣ በየደረጃው ለሚገኘው የዳያስፖራ ቡድን የሚመጥን የዳያስፖራ ፖሊሲና የማበረታቻ ማዕቀፍ ለመቅረፅ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ለ90 በመቶው ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ትርጉም ባለው ማንኛውም ዓይነት ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን በዚህ መደብ ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው ዳያስፖራ አሁንም ድረስ ህልሙ ወደ ኢትዮጵያ መመለስና ቀሪ ሕይወቱንና የጡረታ ዘመኑን በአገሩ ምድር ላይ መግፋት ነው፡፡ የእነዚህኞቹ ዳያስፖራዎች ዕቅድ የጡረታ ዘመናቸውን የሚገፉበት አንድ የመኖሪያ ቤት፣ ከቻሉ ደግሞ እያከራዩ ገቢ የሚያገኙበት ሌላ ሁለተኛ ቤት መግዛት ነው፡፡ እነሱን ከዚህ ያለፈ ከፍ ያለ ነገር ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በራሱ ቀላል የሚባል ነገር አይደለም፡፡ ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ በአግባቡ የተጠናና ዳያስፖራውን ታላሚ ያደረገ ስትራቴጂ ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ፣ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ፍሰቶችን መፍጠር እንደሚቻል ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ባለሙያዎችንና የአነስተኛ የንግድ ድርጅቶች ባለቤቶችን የሚያቅፈው ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ መደብም ቢሆን፣ በጥቅሉ ሲታይ ጡረታ ከመውጣቱ በፊት ወደ አገሩ የሚመለስበት ሁኔታ ላይ የመገኘት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ ይህኛው መደብ ኢትዮጵያ በእጅጉ የምትፈልገውን ዳጎስ ያለ የገንዘብና የሰው ኃይል ሀብት ያካበቱ ዳያስፖራዎች የሚያቅፍ እንደመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነው፡፡

ይኼኛውን መደብ በተመለከተ ልንከተለው የምንችለው አካሄድ፣ ዳያስፖራዎቹ ሙያን መሠረት ባደረገ መንገድ ከፍ ባሉ ቡድኖች ውስጥ የሚደራጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የገንዘብና የሰው ኃይል ሀብታቸውን በማዋጣት፣ ወደ ኢትዮጵያ መምጣትና ሙሉ ጊዜያቸውን ማጥፋት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት ሆነው በአገራቸው ግዙፍ የሙያ ተቋማትን ማቋቋም የሚችሉባቸውን ሥርዓቶች ልንፈጥርላቸውም እንችላለን፡፡ መሰል ዕድሎችን የማግኘት ፍላጎት ያላቸው ዳያስፖራዎች በዚህ አካሄድ ሊያቋቁሟቸውና ሊያንቀሳቅሷቸው ከሚችሉ ግዙፍ ተቋማት መካከልም ሆስፒታሎች/የሕክምና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምህንድስና ኩባንያዎች ወዘተ. በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ እኔ በግሌም መሰል ፍላጎቶችን ለማሳካት የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን ለመፍጠር የሚያስችል ድጋፍ እንድሰጥ ተጠይቄ አስተዋጽኦ ያበረከትኩባቸው አጋጣሚዎች ብዙ ነበሩ፡፡ አሁንም መረሳት የሌለበት መሠረታዊ ነገር፣ ለዚህኛው የዳያስፖራ መደብም የላቀ ትርፍ ሊያስገኙ የሚችሉ፣ በልኩ የተቀረፁና ራሳቸውን የቻሉ ልዩ የፖሊሲና የማበረታቻ ማዕቀፎችን ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ከሁሉም በተለየ ትኩረትን የሚስበውና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሦስተኛው የዳያስፖራ ክፍል ደግሞ ጡረታ የወጡ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተካተቱበት መደብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሰው ኃይል ሀብት ረገድ ያለባት ክፍተት፣ በገንዘብ ሀብት ካለባት ክፍተትም የባሰ ነው፡፡ በየመስኩ የሚታየውን የአስተዳደር መጓደል ያስከተለውን ትልቁን የመንግሥት የአቅም ክፍተት፣ እጅግ ሰፊ የሆነውን ይህን ባለሙያ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ በአግባቡ በማንቀሳቀስና ዕውቀት፣ ልምድና ክህሎቱን በመጠቀም መሙላት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ፣ የትኞቹ የሥራ ቦታዎችና ኃላፊነቶች ለተማሩ የዳያስፖራ ባለሙያዎች ተሳትፎ ክፍት ሊደረጉ ይችላሉ የሚለውን መለየትና ውሳኔ ማሳለፍ ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ መሥፈርቱን ለሚያሟሉ ተወዳዳሪዎች ጥቅል የመመልመያ ሰነድ ማዘጋጀት ይገባል፡፡ ሦስተኛው ነገር ደግሞ፣ ተቋማዊ የሆነ የተሳትፎና የሥራ መዋቅር/ሒደት መፍጠርና መተግበር መሆን አለበት፡፡

ታሪካዊ ዳራ

የዳያስፖራ ወገናቸውን ትርጉም ባለውና ዘላቂ በሆነ መንገድ በአግባቡ በማንቀሳቀስ በቻሉ አገሮች የኢኮኖሚያዊ ልማት ውስጥ፣ ዳያስፖራዎች በትውልድ አገራቸው ልማት ላይ የሚጫወቱት ሚና ቁልፍ ሥፍራ ተሰጥቶት የኖረ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ዳያስፖራ ወገናቸውን በአግባቡ አንቀሳቅሰው ውጤታማ ከሆኑ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኬንያ፣ ግብፅና ናይጀሪያ የሚጠቀሱ ሲሆን ከእስያ ቻይና፣ ህንድና ደቡብ ኮሪያ ይጠቀሳሉ፡፡ የዳያስፖራ ተሳትፎ ዓይነቶች የተለያዩ ሲሆኑ፣ ለአብነትም  ዳያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎች የቀጥታ ኢንቨስትመንት፣ በአገር ቤት የካፒታል ገበያዎች ውስጥ የሚደረግ ኢንቨስትመንት፣ የዳያስፖራ ቱሪዝምና ‹‹የአገር ቤት ምርቶች›› ንግድ፣ የዳያስፖራ በጎ አድራጎት፣ የዳያስፖራ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የዳያስፖራ ዲፕሎማሲና ንቅናቄ ናቸው፡፡

የዲያስፖራ ሥራ ፈጠራ

ሁሉም ዓይነት የሥራ ፈጠራዎች ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት በእኩል መጠን አስተዋጽኦ አያበረክቱም፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሥራ የገቡ ሥራ ፈጣሪዎች ወይም ሥራ መቀጠር ስላልቻሉ ለራሳቸው ሥራ የፈጠሩ ዜጎች፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ነው፡፡ ዕድሎችን ተጠቅመው ወደ ሥራ የገቡ ሥራ ፈጣሪዎች፣ በአንፃሩ በኢኮኖሚው ውስጥ በሚፈጠሩ አዳዲስና በማደግ ላይ ያሉ ዘርፎች ውስጥ ገበያ ሊያገኙ ስለሚችሉ በኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ የመፍጠር ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ፈጠራ የታከለበትና እሴትን የሚጨምር የሥራ ፈጠራ ወደ ኢኮኖሚዋ ሊያስገባላት ከሚችለው ከዚህ ዓይነቱ የዲያስፖራ ተሳትፎ ተጠቃሚ ሳትሆን ቆይታለች፡፡ መሰል ሥራ ፈጣሪ ኢንቨስተሮች የኢኮኖሚ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽንን ዕውን በማድረግ ረገድ የራሳቸውን ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሥራ ፈጣሪዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ወይም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃዎችን በማስተዋወቅ ነባር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራሉ፡፡ ኢኮኖሚውን በማዘመን ረገድ ሰፊና ትርጉም ያለው ተፅዕኖ የሚፈጥሩ አዳዲስ አገልግሎቶችንና የንግድ ሐሳቦችንም ሊያስተዋውቁ ይችላሉ፡፡

የዳያስፖራ ኢንቨስትመንት በካፒታል ገበያዎች

እስካሁን ድረስ የነበሩት የፖሊሲ ትኩረቶች ስደተኞች ወደ አገር ቤት በሚልኩት ገንዘብ ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ፡፡ ስደተኞች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ገንዘብ በፋይናንስ ፍሰት ውስጥ ትልቅና እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ባያጠያይቅም፣ ይህ ገንዘብ ከዳያስፖራው ሊገኙ ከሚችሉት የግል የገንዘብ ፍሰቶች አንዱ ብቻ ነው፡፡ ‹ሬሚተንስ› በመባል የሚታወቀው ይህ የገንዘብ ዝውውር የስደተኞችን ገቢ መልሶ ከማከፋፈል ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ የላቀው ፈታኝ ነገር የዳያስፖራን ሀብት ማንቀሳቀስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የካፒታል ገበያዎች ቁጠባን በማበረታታት ገንዘቡን ወደ ምርታማ ኢንቨስትመንቶች ፈሰስ የማድረግ የተወሰነ ሥራ ያከናውናሉ፡፡

በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚያወጡ ታላላቅ የመንግሥት ድርጅቶችንና ተቋማትን ወደ ግል ንብረትነት ለማዞር አቅጣጫ መቀየሱ፣ እንዲሁም በአገሪቱ እጅግ ሰፊ ነገር ግን መዋቅራዊ ያልሆነና ቁጥጥር የማይደረግበት የአክሲዮን ገበያ በመከናወን ላይ መሆኑ፣ በኢትዮጵያ የተደራጀና ዘመናዊ የአክሲዮን ገበያ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቋቋም ልዩ የሆነ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያ ሲቋቋም ደግሞ ኢትዮጵያዊው ዳያስፖራ ባለበት ሆኖ ገንዘቡና ደኅንነቱ በተጠበቀና አትራፊ የአገር ቤት ኢንቨስትመንት ላይ የሚያውልበት ምቹ መድረክ ያገኛል፡፡ ዳያስፖራዎች ደረጃውን በጠበቀ የአክሲዮን ገበያ መጠቀማቸው ኢንቨስትመንታቸው ‹ሊኩዊድ› (በቀላሉ ወደ ጥሬ ገንዘብ ሊለወጥ የሚችል) እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ፣ በጊዜ ሒደትም አግባብነት ያለው የዋጋ ትመናና አድናቆት እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል፡፡

ዳያስፖራው እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በውጭ አገሮች ባንኮች ውስጥ በቁጠባ መልክ ቢያስቀምጥም፣ ይህ ነው የሚባል ወለድ እያገኘበት አይደለም ያለው፡፡ በኢትዮጵያ በሚፈጠር ትርፋማ የኢንቨስትመንት ዕድል ገንዘባቸውን ከባንክ አውጥተው፣ በአገራቸው ኢንቨስት ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ የዳያስፖራ ኢንቨስተሮችን ይስባል፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አጠቃላይ ዓመታዊ ቁጠባ ከአምስት ቢሊዮን እስከ አሥር ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡

የዳያስፖራ የጋራ ፈንድ

የጋራ ፈንዶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ግለሰብ ኢንቨስተሮች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ ወጪ አውጥተው የግል የኢንቨስትመንት ሥራ አስኪያጅ መቅጠር ሳያስፈልጋቸው፣ ኢንቨስትመንታቸው ሙያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ማድረግ የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኢንቨስተሮች በትውልድ አገራቸው በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት ፍላጎቱ ቢኖራቸውም፣ ሥራውን በግላቸው ለማስተዳደር ጊዜውና የሙያ ብቃቱ የሌላቸውን የዳያስፖራ ኢንቨስተሮችን ቀርበው ማነጋገር ይችላሉ፡፡ በይፋ የሚሸጡ ያላደጉ አገሮች ኮርፖሬሽኖች/ኩባንያዎች ጥቂት ከመሆናቸው ባሻገር፣ የተመዘገቡትም እምብዛም ዕውቅና የሌላቸው እንደ መሆናቸው፣ በእነዚህ አገሮች የዳያስፖራ ፈንዶች የዋጋ ትመና የማድረግ አገልግሎትም ሊሰጡ ይችላሉ፡፡

የዳያስፖራ ቱሪዝምና ‹‹የአገር ቤት ምርቶች›› ንግድ

ዳያስፖራዎች ለቱሪዝምና በትውልድ አገራቸው ለተመረቱ ወይም ከእናት አገራቸው ጋር ተያያዥነት ላላቸው የተለያዩ የአገር ቤት ምርቶች ገበያ በመፍጠር ረገድ ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የተለያዩ የዳያስፖራ ቱሪዝም ዓይነቶች መካከል የሕክምና ቱሪዝም፣ ከንግድ ጋር ተያያዥነት ያለው ቱሪዝም፣ የባህል (Cultural) ቱሪዝም፣ የትውውቅ ቱሪዝም፣ ትምህርታዊ ቱሪዝምና ‹‹የጀብድ ተሞክሮ›› ቱሪዝም (Adventure Tourism) ይገኙበታል፡፡ 

አገሮች ያመረቷቸውን ወይም የእነሱ መገለጫ የሆኑ የተለዩ ምርቶችንና ቁሳቁሶችን ለዳያስፖራ ገበያ በማቅረብና በመሸጥ ጠቀም ያለ ገቢ ያገኛሉ፡፡ በስደት የሚኖሩ ቤተሰቦች የአገር ቤት ምርቶችንና ቁሳቁሶችን በተለይ ደግሞ ምግብ ነክ ነገሮችን በብዛትና በቋሚነት ይጠቀማሉ፡፡ ባህላዊ ዕቃዎችና አልባሳትን የመሳሰሉ የአገር ቤት ምርቶች በአብዛኛው በጉልበት የሚመረቱና ጥበብ የሚንፀባረቅባቸው እንደ መሆናቸው፣ የሚያስገኙት ገቢ በአገር ቤትና በቤተሰብ ደረጃ የሚያስደስት ነው፡፡ በአሜሪካ የባህላዊ ዕቃዎችና አልባሳትን የመሳሰሉ የአገር ቤት ምርቶች በዳያስፖራ የንግድ ትስስሮች በሚገባ የተደራጁ ሲሆኑ፣ ከ50 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ዳያስፖራ የአገር ቤት ምርቶችን ነው የሚገዛው፡፡

የዳያስፖራ በጎ አድራጎት

በግለሰቦች የሚደረግ የበጎ አድራጎት ሥራ በአገሮች የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚጫወቱት ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው የሚገኘው፡፡ ባላደጉ አገሮች አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ውስጥ ከመደበኛው የልማት ድጋፎች ይልቅ የግለሰቦች በጎ አድራጎት ከፍ ያለ ድርሻ የያዘ ነው፡፡ የግለሰብ በጎ አድራጎቶች መደበኛ የልማት ተቋማት የያዙትን ያህል የሙያ ክህሎትና ሀብት፣ እንዲሁም የግል የንግድ ተቋማትን ያህል የረዥም ጊዜ የልማት አቅም ላይኖራቸው ቢችልም ሁነኛ የልማት አቀጣጣችዮና የፈጠራ አመንጪዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡ አንዳንዴም ጠቀም ያለ ሀብት ያቀርባሉ፡፡

ፈቃደኞችን የመመልመልና የመቅጠር ዓላማን አንግበው የሚተገበሩ ፕሮግራሞች እንደ አጠቃላይ በስድስት ዋና ዋና ምድቦች የሚከፈሉ ሲሆን፣ ትኩረት የሚያደርጉባቸው መስኮችም የንግድ ዕድገትና የቴክኒክ ምክር፣ የኅብረተሰብ ጤና የአቅም ግንባታ፣ የድኅረ ግጭት ዕርዳታና መልሶ ማቋቋም፣ የከፍተኛ ትምህርት የአቅም ግንባታ፣ የፖሊሲ ማማከር አገልግሎቶችና የወጣቶች ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ ዳያስፖራዎች በአገር ቤት በሚከሰቱ ርዕደ መሬት፣ ድርቅና ግጭቶችን በመሳሰሉ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና መልሶ ለማቋቋም በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡

የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂካዊ ፖሊሲዎች

አንድ መንግሥት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ ስትራቴጂ በሚቀርፅበት ሒደት ሊያካትታቸው የሚገባቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ግቦችን ለይቶ ማስቀመጥ፣ የዳያስፖራውን የአሠፋፈር ሁኔታና የክህሎት ደረጃ ማጥናትና መለየት፣ በዳያስፖራውና በመንግሥት መካከል በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መፍጠርና በስተመጨረሻም ዳያስፖራው ለዘላቂ ልማት የድርሻውን እንዲወጣ  ማስተባበርና ማንቀሳቀስ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ የሚከናወን ጉዞ በስኬት ተጠናቀቀ የሚባለውም፣ ዳያስፖራውን በማነቃነቅ የእናት አገሩ እውነተኛ የልማት አጋር ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

የዳያስፖራ ተሳትፎ ስትራቴጂ የመንግሥት ተቋማትና የዳያስፖራው ማኅበረሰብ በእያንዳንዱ የትግበራ ሒደት እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመሥራት የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያዳብሩ ለማድረግ ተገቢ ትኩረት የሚሰጥ መሆን ይገባዋል፡፡ ዳያስፖራው በትውልድ አገሩ የልማት እንቅስቃሴ ላይ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችል ስትራቴጂ ለመተግበር ያቀደ ማንኛውም መንግሥት፣ ከሁሉም በፊት ሊያሳካው የሚፈልገውን ነገር ወይም የመጨረሻ ግቡን፣ እንዲሁም ስትራቴጂውን በአግባቡ ለማስፈጸም የሚያስፈልጉትን ውስጣዊ መሣሪያዎችና ሥርዓቶችን (አስተዳደራዊና የፋይናንስ ወዘተ.) በግልጽ መለየትና ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

ለምሳሌ መንግሥት የሚፈልገው ድህነትን መቀነስ ወይም ብሔራዊ የክፍያ ሚዛንን መደገፍ ከሆነ፣ የሚከተለው ፖሊሲ ትኩረቱን የሚያደርገው ከውጭ አገሮች በሚላክ የዳያስፖራ ገንዘብ (ሬሚተንስ)፣ በንግድ ሥራ ኢንቨስትመንቶችና ምናልባትም ደግሞ በካፒታል ገበያዎች ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ የመንግሥት ግብ ብሔራዊ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ከሆነ ደግሞ፣ የሚከተለው ፖሊሲ የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ዳያስፖራው በራሱ ጥረትና አካሄድ ወይም ከአገር በቀል የትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ሊያሳካው ለሚችለው የዕውቀትና የክህሎት ሽግግር ሊሆን ይችላል፡፡

መንግሥት ሊደርስባቸው ያቀዳቸውን ግቦች በግልጽ ካስቀመጠ በኋላ፣ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ደግሞ የዳያስፖራውን አጠቃላይ ሁኔታና ባህሪይ በቅጡ ማወቅ ነው፡፡ ይህን ዕውን ለማድረግም ዳያስፖራውን የሚመለከቱ መረጃዎችን ማሰባሰብና ክህሎትና ልምድን መሠረት ባደረገ መንገድ ዳያስፖራውን በተለያዩ ምድቦች መከፋፈልን ይጠይቃል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም አስፈላጊ መረጃዎችን በጥንቃቄ መፈተሽና ዳያስፖራው ለአገሩ ሊያበረክት የሚችለውንና የሚፈልገውን ነገር፣ እንዲሁም በምላሹም ከመንግሥት የሚጠብቀውን ነገር በግልጽ ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ተደጋጋሚ ምዘና ማድረግ ይገባል፡፡

ዳያስፖራው ለሚያራምደው የየራሱ አጀንዳና ፍላጎት፣ እንዲሁም ስትራቴጂ ዕውቅና መስጠት ግድ ይላል፡፡ መንግሥታት ከዳያስፖራው ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉ መድረኮችን በመፍጠር የሐሳብ፣ የአመለካከትና የአጀንዳ ልዩነቶችን ማስታረቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥታት የዳያስፖራ ተሳትፎን በስኬታማ ሁኔታ ማሳደግ የሚችሉት ዓመታትን በሚፈጁና ቀጣይነት ባላቸው ግልጽ መስተጋብሮች አማካይነት ነው፡፡ በመንግሥታትና በዳያስፖራዎች መካከል ትብብርን ለመፍጠር የሚከናወነው የረዥም ጊዜ ፕሮጀክት ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ከፍ የሚለው፣ በጠንካራ የመልካም ግንኙነትና የጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ነው፡፡ አጋርነት የሁለት ባለድርሻዎች የጋራ ፍላጎትና ተሳትፎ ውጤት ነውና!

የዳያስፖራ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ለኢትዮጵያ

መንግሥታት በመጀመርያ ደረጃ ዕውን ሊያደርጉት የሚችሉት ቀላሉና የማያጠያይቀው ነገር (እርግጥ ሁሌም ቀላል ላይሆን ይችላል)፣ አገራቸው የዳያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎችን በፍቅርና በአክብሮት እንደምትቀበላቸው አስተማማኝ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ ነው፡፡ በርካታ መንግሥታት ተሳትፏቸውን ፍለጋ ወደ ዳያስፖራ ወገኖች በመሄድ ብቻ አይወሰኑም፡፡ ዳያስፖራዎች ለአገር ለወገናቸው ላበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች በይፋ ዕውቅና ይሰጣሉ፡፡ ዳያስፖራዎች በአገራቸው ኢኮኖሚ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ታላቅ የልማት አጋሮች መሆናቸውን አደባባይ ወጥተው በመመስከር በክብር  ይቀበሏቸዋል፡፡

የዳያስፖራዎች ሚና ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ የዳያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎች  በተለይ የሥራ ፈጠራ ባህል ባልዳበረባቸው አገሮች ዘርፉን በማስተዋወቅና በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ በሽምደዳ ላይ የተመሠረቱና ፈተናን ማዕከል ያደረጉ ወይም ለጎምቱዎች ቅድሚያ የሚሰጡ የዕድገት ሥርዓቶች ኃያላንን አብዝቶ ማምለክ፣ ሥልጣንን ተገን አድርጎ ወዳጅ ዘመድን የመጥቀም አድሎአዊነት ሥር መስደድ፣ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ አለመድፈርና ሌሎችም የሥራ ፈጠራን የሚያቀጭጩ አደገኛ ልማዶች ናቸው፡፡ የዳያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎች ንቁ ተሳትፎ፣ አርዓያነትና ተጨባጭ ስኬቶች አገር በቀል የንግድ ሰዎችና ባለሙያዎች የዳያስፖራዎቹን ልምምዶችና ተሞክሮዎች እንዲቀስሙ ሊያበረታቱ ይችላሉ፡፡

መንግሥታት ከዳያስፖራ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር በቋሚነት ውይይቶችን ማድረጋቸው፣ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ መስኮችን ለመለየትና የዳያስፖራ ሀብቶችን ወደ መስኮቹ ለመሳብ ሊያግዛቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ህንድ ከጤና እንክብካቤ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶችንና የሕክምና ቱሪዝምን እንደ ወሳኝ የወጪ ንግድ ዕድሎች የለየች ሲሆን እንግሊዝ፣ ካናዳና አሜሪካን በመሳሰሉ አገሮች ከፍተኛ ወጪ ከፍለው አገልግሎቶችን ለማግኘት ያቃታቸውንና አማራጭ የሚፈልጉ ደንበኞችን በመሳብ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ አገሪቱ በሕክምናው መስክ የሰው ኃይሏን በብቃት በማሠልጠን ከጤና እንክብካቤ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አገልግሎቶችን  ዓለም አቀፍ ፍላጎት ማሟላት በሚችሉበት ደረጃ ለማድረስ እየሠራች ሲሆን፣ ለዚህ ጥረቷ መሳካት በግንባር ቀደም አጋርነት ያሠለፈችውም ዳያስፖራዋን ነው፡፡

ዳያስፖራው በአገር ቤት ኢንቨስትመንት ላይ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስና የንግድ ሥራዎችን እንዲጀምር ለማበረታታት በማሰብ የገንዘብ፣ የማኅበራዊና የፖለቲካዊ ማበረታቻዎችን ማድረግ በመንግሥታት ዘንድ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ከእነዚህ ማበረታቻዎች መካከልም በቁልፍ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የንግድ ሥራ ላይ ለተሰማሩ የግብር ዕፎይታ፣ ወይም የግብር ብድሮች መስጠት ፖሊሲ አውጪዎችን በቀላሉ ማግኘት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር፣ እንዲሁም የንግድ ሥራን ከማቋቋምና ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ አስተዳደራዊ ማነቆዎችንና ቢሮክራሲያዊ አሠራሮችን ማቃለል ይጠቀሳሉ፡፡

ለዳያስፖራ ሥራ ፈጣሪዎች ልዩ ማበረታቻዎችን የማድረግ አካሄድ ራሱን የቻለ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለዳያስፖራዎች ልዩ ማበረታቻዎችን መስጠት እጅግ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም፣ ዳያስፖራዎችን በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርጉ አንዳንድ ማበረታቻዎች ላልተፈለገ ዓላማ ሊውሉ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ዳያስፖራዎች ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉት መኪና ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ፈቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ማበረታቻ ግን ቀስ በቀስ የገቢ ንግድን ማስፋፋቱ አልቀረም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ለዳያስፖራዎች ብቻ የተከፈተው መልሶ የመሸጥ ንግድ እንዲጧጧፍና የመኪኖች ቀረጥና ኤክሳይስ ታክስ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር በር የከፈተውም ይኼው ልዩ ማበረታቻ ነበር፡፡ ቻይና በአንድ ወቅት ለዳያስፖራ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የቀረጥ ቅናሽ አድርጋ ነበር፡፡ ይህ አሠራር ግን የአገሪቱ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ወደ ሆንግ ኮንግና ማካኡ እየላኩ ለዳያስፖራ በተተመነው ቀለል ያለ ቀረጥ መልሰው ወደ አገራቸው እንዲያስገቡትና በዚህም በአገሪቱ የካፒታል ሽክርክሪት ‹‹Round Tripping›› እንዲፈጠር በር ከፍቶ ነበር፡፡

በዲያስፖራ ተሳትፎ ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶችን ማስወገድ

ተመጣጣኝ ግራንቶችን የመሳሰሉ ፈጠራ የታከለባቸው ፕሮግራሞችን ተግባራዊ በማድረግ አዳዲስ ኩባንያዎችን መፍጠር ወይም ነባሮችን ማስፋፋት ይቻላል፡፡ በተለይ በአነስተኛ ደረጃ በሚሠሩ የሥራ ፈጣሪዎች ላይ ከተጋረጡ የተለመዱ እንቅፋቶች መካከል አንዱ የካፒታል አቅርቦት ችግር ነው፡፡ በርካታ የገንዘብ ተቋማት መደበኛውን የመያዣ ዋስትና ማቅረብ የማያስፈልጋቸው አነስተኛ ብድሮችን የሚሰጡበት አሠራር የላቸውም፡፡

አደጋዎችን መጋራት የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ፈጣሪዎችን የመደገፍ ዓላማ ያላቸው ፕሮግራሞች ከንግድ ተቋማት ካፒታል ኩባንያዎች (Commercial Venture Capital Firms) ልምድ በመቅሰም፣ አደጋዎችን መጋራት የሚያስችሉ አሠራሮችን መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ አንድ ኢንቨስትመንት ትርፋማ መሆኑ ከተረጋገጠ፣ ፕሮግራሙ በኢንቨስትመንቱ ትርፍ ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ሌሎች ተጨማሪ ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የኢንቨስትመንት ፈንድ አሠራር፣ ከመደበኛ የብድር ፕሮግራሞች (እርግጥ መደበኛ የብድር ፕሮግራሞችም ጠቀሜታ ሊኖራቸው ይችላል) በተለየ መንገድ የሥራ ፈጣሪውን የዕዳ ተጠያቂ አያደርግም፡፡ ይህም አደጋዎችን የመጋፈጥ ተነሳሽነትን ሊጨምር ይችላል፡፡ የብድር ኢንሹራንስ ፕሮግራሞችና የብድር ዋስትናዎች፣ በአዲስ የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ገንዘብን ማፍሰስ ሊያስከትል የሚችለውን የአደጋ ሥጋት የሚቀንሱ ሌሎች ተጨማሪ መንገዶች ናቸው፡፡ በማኑፋክቸሪንግን ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂና በአገልግሎት ዘርፎች ላይም ትኩረት ያደረጉ የዳያስፖራ የቢዝነስ ፓርኮችም፣ የዳያስፖራ ኢንቨስትመንትን ሊያቀጣጥሉ የሚችሉ ሁነኛ አማራጮች ናቸው፡፡ የአገልግሎትና የቴክኖሎጂ ዘርፎች የወደፊቱ ተመራጭ ዘርፎች ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራም በእነዚህ ዘርፎች ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ሀብት ያካበተ ነው፡፡

ድምዳሜ

ኢትዮጵያ ከሰፊው የዳያስፖራ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስና የማኅበራዊ ሀብት በተሟላ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች፣ ዳያስፖራውን በስፋት በማነቃነቅ በሁሉም የአገሪቱ ብሔራዊ የዕድገትና የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ የሚያስችሉና ፈጠራ የታከለባቸው የተቀናጁ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡

ዳያስፖራው ከመቼውም ጊዜ በላይ የተነቃቃበትና በኢትዮጵያ ልማት ተሳትፎ ለማድረግ የተዘጋጀበት ወቅት ላይ ነው የምንገኘው፡፡ መንግሥትም ይህንን መልካም ዕድል ለመጠቀም ፅኑ ፍላጎት ያሳየበት ወቅት ነው፡፡ ፈታኙ ነገር ግን የዳያስፖራ ተሳትፎ ማዕቀፍ፣ እንዲሁም በሰነዱ ላይ የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በተቀናጀና በሥርዓቱ ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስችል ብቃት ያለው ሒደት የመቅረፅና በስኬታማ መንገድ የመተግበር ጉዳይ ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት ሐሳቦች፣ ጉዳዮችና ስትራቴጂዎች በቀጣይ መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይቶችን ለማጫር ታስበው የቀረቡ ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected]   ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...