Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየመልካም አስተዳደር የቤት ሥራ ጣጣችን

የመልካም አስተዳደር የቤት ሥራ ጣጣችን

ቀን:

በሸዋዬ ተስፋዬ

በኢትዮጵያ ብልሹ የመንግሥት አስተዳደር ያልተጠናቀቀ የቤት ሥራ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በሚል የሚገለጸው ብልሹ አስተዳደር ወይም አሠራር በማናቸውም የመንግሥት አደረጃጀት የሚታይና የተዛመተ ሲሆን፣ በተለይ ሕዝብ ራስን በራስ እንዲያስተዳድር ለማስቻል በታችኛው የአደረጃጀት እርከን በተቋቋሙ ተቋማት ችግሩ ይበልጥ አስከፊ ሆኖ ይታያል፡፡ የአገራችን የመልካም አስተዳደር ችግር የከፋ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ የተሟላ ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤን መነሻ ያደረገ የተዛመደና የተቀናጀ፣ ከችግሩ ውስብስብ ባህሪና ጥልቀት አንፃር ተመጣጣኝና በወቅቱ የታቀደ፣ እንዲሁም ሕዝብ የመከረበት የመፍትሔ ዕርምጃ ያልወሰደ በመሆኑ እስካሁን ድረስ መሻሻል አልታየም፡፡

በመልካም አስተዳደር መስክ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በየጊዜው በሚያጠናቅሯቸው ዘገባዎች አማካይነት፣ በአገራችን የአፈጻጸም ጉድለት ላይ ትችት በመሰንዘር የእርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ በተደጋጋሚ አሳስበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የእርምት ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ትችቱን የሐሰት ውንጀላ በሚል በማጣጣል፣ እንዲሁም ድርጅቶቹን በሊበራል ዴሞክራሲ ጠበቃነትና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጠላትነት መፈረጅ የተለመደ የመንግሥት ምላሽ ነበር፡፡ ሆኖም ለችግሩ መፍትሔ ካልተበጀለት በአገራችን መፃኢ ዕድል የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም፡፡

የእዚህ ጽሑፍ ዓላማ በአገራችን በተያዘው የመደመርና የይቅርታ ለውጥ እንቅስቃሴ የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ማስፈን ተገቢ ትኩረት እንዲሰጠው ለመጠቆም ያለመ ነው፡፡ የጽሑፉ መልዕክት በሦስት ምዕራፎች የተሰናዳ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ለግንዛቤ እንዲረዳ የመልካም አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ ትርጉም እንዲሁም የአፈጻጸም መሥፈርትን አስመልክቶ አጭር ማብራሪያ ያቀርባል፡፡ ከእዚህ የሚከተለው ምዕራፍ የኢትዮጵያን መልካም አስተዳደር አፈጻጸም (አጠቃላይ፣ በአራት ዓብይ ዘርፎች፣ በ14 ንዑስ ዘርፎች፣ እንዲሁም 102 መለኪያዎች) ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ያመለክታል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑንና በዚህ ረገድ ሊካተቱ የሚያስፈልግ ተግባራትን በመጠቆም የጽሑፉን መልዕክት ያጠቃልላል፡፡

መልካም አስተዳደር ምንድነው?

የመልካም አስተዳደር መስፈን የአገሮችን ልማትና ብልፅግና በዘላቂነት ለማረጋገጥ ዋስትና ስለመሆኑ ዓለም አቀፍ የጋራ ግንዛቤ በመስፋፋት ላይ ሲሆን፣ በሁሉም አካላት እኩል ተቀባይነት ያገኘ ትርጉም እንዲሁም ለአገሮች አፈጻጸም ምዘና የሚያገለግል መሥፈርት አሁንም ቢሆን አልተገኘም፡፡ በመሆኑም ስለመልካም አስተዳደር ካላቸው ግንዛቤ በመነሳት የተለያዩ ተቋማት በራሳቸው የተዘጋጁ የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በእዚህ መሠረት ዕውቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገለገሉበትን የመልካም አስተዳደር ትርጉም ብንመለከት፣ ዓለም ባንክ (World Bank) መልካም አስተዳደር የአንድን አገር የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሀብት ጥቅም ላይ በማዋል በልማት ለመራመድ የሚያስችል የመንግሥት ሥልጣን አተገባበር ሥርዓትን ያመለክታል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም

መልካም አስተዳደር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የአስተደደር ሥልጣን የሚተገበርበት፣ የአንድ አገር ጉዳዮች በሁሉም ደረጃዎች የሚከናወኑበት፣ ዜጎችና ቡድኖች ፍላጎቶቻቸውን የሚገልጹበት በሕግ የታወቁ መብቶቻቸውን የሚያስከብሩበትና ግዴታዎቻቸውን አግባብነት ባለው መንገድ የሚወጡበት፣ እንዲሁም በመካከላቸው የሚኖሩ ልዩነቶችን የሚያቻችሉበት የአስተዳደር ዘይቤዎችን የአሠራር ሒደቶችንና ተቋማትን ያካትታል፡፡

ዓለም አቀፍ የመልካም አስተዳደር መለኪያዎች

መልካም አስተዳደር በአንድ አገር ሥልጣን የሚተገበርበትን የአስተዳደር ልምድና ተቋማትን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም መንግሥት ለሥልጣን የሚመረጥበትን ሒደቶች፣ ቁጥጥር የሚደረግበትንና በሌላ የሚተካበትን፣ አግባብነት ያላቸው ፖሊሲዎችን ከመንደፍና ከማስፈጸም አንፃር ያለውን ብቃት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስተጋብርን በመምራት ረገድ ዜጎችና መንግሥት በተቋማት ላይ የሚኖራቸውን መተማመንና ይህን መነሻ በማድረግ የሚሰጧቸውን ክብር ያካትታል፡፡

የመልካም አስተዳደር ተቋም  

መልካም አስተዳደር ማን ሥልጣን እንደሚገባው፣ ማን ውሳኔዎችን እንደሚሰጥና የሌሎች አካላት ሐሳብ በምን ዘዴ እንደሚስተናገድ፣ እንዲሁም ተጠያቂነት እንዴት በተግባር እንደሚረጋገጥ የሚደነግግ የአሠራር ሒደት ነው፡፡

ኢብራሂም ፋውንዴሽን

የፋውንዴሽኑ መሥራች መሐመድ ኢብራሂም (ዶ/ር) ዜጎችን ማዕከል ከሚያደርግ ዕይታ በመነሳት መልካም አስተዳደር ለዜጎች በይፋ የተገለጸ ቃል ኪዳንን በመፈጸም ላይ የሚያነጣጥር ሲሆን፣ መንግሥታት የሚያጋጥማቸው ተግዳሮት የዜጎችን የሕይወት ጥራት ደረጃ ማሻሻል መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት መልካም አስተዳደር ቅንጦት ሳይሆን፣ ድህነትን ለማስወገድና በልማት ለመራመድ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ መሆኑን በቅርቡ በሞት የተለዩት የፋውንዴሽኑ ቦርድ ኃላፊና የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን ይገልጻሉ፡፡ መልካም አስተዳደር የመንግሥት ሥልጣን አተገባበርና የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓትን፣ እንዲሁም ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ሒደትን የሚያካትት መሆኑን ከእዚህ በላይ ከቀረበው አጭር ማብራሪያ መገንዘብ ይቻላል፡፡

መልካም አስተዳደር ለልማትና ለብልፅግና የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ በአገራችን በሁሉም አካላት ዘንድ በመርህ ደረጃ ስምምነት ቢኖርም፣ ከእዚህ በላይ ከቀረበው ማብራሪያ አኳያ ግልጽና የተሟላ የመልካም አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ ያለመኖሩን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ አካል ካለው ግንዛቤ አንፃር ትኩረት የሚሰጣቸው የመልካም አስተዳደር ችግር መገለጫዎች ላይ ያነጣጥራል፡፡ በዚህ መሠረት፣

መንግሥት

የመንግሥት ኃላፊዎች ሥልጣንን ሕዝብን ከማገልገል ዓላማ በተቃራኒ የግል ጥቅም ለማግኘት የማዋል አመለካከት፣ የአገልግሎት አቅርቦትን በብቃት ያለመምራት ቁልፍ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን፣ እንዲሁም በከተሞች የተንሰራፋ የመልካም አስተዳደር ችግር ከኪራይ ሰብሳቢነት አደጋና ከማስፈጸም አቅም ማነስ የሚመነጭ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል፡፡

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

በነፃና ፍትሐዊ የምርጫ ውድድር የመንግሥት ሥልጣን ለመያዝ እንዳይችሉ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ እየጠበበ መምጣቱንና ምቹ መደላደል ያለመኖሩን በምሬት ይጠቅሳሉ፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች

ከተመሠረቱበት ዓላማና ተልዕኮ አንፃር በነፃነት ለመንቀሳቀስ የፖለቲካ ተፅዕኖ፣ ሕገወጥ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ቁጥጥር አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች እንደሆኑ ይመክራሉ፡፡

ኅብረተሰቡ

በሕግ የታወቁ ሰብዓዊ መብቶች ያለመከበር፣ የፍትሕ መጓደል፣ የአገልግሎቶች አቅርቦት በብቃት ያለመከናወን፣ እንዲሁም ሙስናና ምግባረ ብልሹ አሠራር አስቸኳይ መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚያስፈልግ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መሆናቸውን በምሬት ይገልጻል፡፡

የኢብራሂም የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር

የኢትዮጵያን መልካም አስተዳደር አፈጻጸም ለማሳየት የተመረጠው በሞ ኢብራሂም ፋውንዴሽን የሚጠናቀረው የኢብራሂም የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር በመሆኑ፣ ለእዚህ ታሳቢ ምክንያቶችን በቅድሚያ መግለጽ ያስፈልጋል፡፡ በእዚህ ረገድ የፋውንዴሽኑ ዋና ተልዕኮ የአፍሪካ አገራገሮች መልካም አስተዳደር አፈጻጸም በትክክል መመዘንና በየጊዜው የሚኖር መሻሻልን መከታተል መሆኑ፣ የአፍሪካ አገሮችን መልካም አስተዳደር አፈጻጸም ለማሻሻል አኅጉራዊ ንፅፅርና ተሞክሮ ላይ የሚያነጣጥር አኅጉር በቀል ተቋም በመሆኑ፣ በምዕራቡ ዓለም የሊበራል ዴሞክራሲ ጠበቃነት ሊፈረጅ የማይችል በመሆኑ፣ በአፍሪካ ኅብረት ከተነደፈው ለአፍሪካ ልማት አዲስ የኢኮኖሚ ትብብር፣ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር የአገሮች አቻ ለአቻ ግምገማ ሒደት ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ አብዛኞች የአፍሪካ አገሮች በምጣኔ ሀብትና በማኅበራዊ ዕድገት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑ፣ በአኅጉሪቱ ሕዝብ መካከል የባህልና ሥነ ልቦና ተቀራራቢነት የሚታይ በመሆኑ፣ እንዲሁም የአኅጉሪቱ የመልካም አስተዳደር ችግር መገለጫ ባህሪና በመስኩ መሻሻል ለማሳየት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ተመሳሳይ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ኢብራሂም የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር ደኅንነትና የሕግ የበላይነት፣ ተሳትፎና ሰብዓዊ መብቶች፣ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድልና ሰብዓዊ ልማት በሚሰኙ አራት ዓብይ ዘርፎች መንግሥት ለዜጎች እንዲያሟላ የሚጠበቁ ፍጆታዎችና አገልግሎቶችን ያካትታል፡፡ በእዚህ ሳምንት ፋውንዴሽኑ በይፋ ያሳወቀው እ.ኤ.አ. የ2017 የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ዘገባ በአራት ዓብይ ዘርፎች፣ በ14 ንዑስ ዘርፎች፣ እንዲሁም በ102 የአፈጻጸም መመዘኛዎች ከልዩ ልዩ የመረጃ ምንጮች የተሰበሰቡ መረጃዎችን በማጠናቀር የተዘጋጀና የ54 የአፍሪካ አገሮች ዓመታዊ አፈጻጸምን የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር የአገሪቱን አጠቃላይ አፈጻጸም ከዜሮ እስከ 100 በመመዘን ያመለክታል፡፡ በእዚህም ውጤት ከ71.0 በላይ ከፍተኛ፣ ከ54.0 እስከ 70.9 መካከለኛ ከፍተኛ፣ ከ41.0 እስከ 53.9 መካከለኛ፣ ከ23.0 እስከ 40.9 መካከለኛ ዝቅተኛ፣ እንዲሁም ከ23.0 በታች ዝቅተኛ አፈጻጸም በሚል ደረጃ ይመደባል፡፡ በተጨማሪ የአኅጉሪቱን አፈጻጸም መሠረት በማድረግ ከአንደኛ እስከ 54ኛ በደረጃ ሰንጠረዥ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ  አጠቃላይ መልካም አስተዳደር አፈጻጸም

ፋውንዴሽኑ ያዘጋጀው እ.ኤ.አ. የ2018 የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ዘገባ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ. በ2017 የኢትዮጵያ አጠቃላይ አፈጻጸም 46.5 ሲሆን፣ ይኼም መካከለኛ ደረጃ የሚመደብና ከአፍሪካ አገሮች አማካይ ውጤት 49.9 በንፅፅር ዝቅተኛ በመሆኑ አገራችን ከ54 የአፍሪካ አገሮች 35ኛ ረድፍ ያስቀምጣታል፡፡ በሌላ በኩል ከአኅጉራችን እጅግ በጣም የላቀ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ካስመዘገቡ አገሮች መካከል አንደኛ ሞሪሸስ 79.5፣ ሁለተኛ ሲሾልስ 73.2፣ ሦስተኛ ኬፕ ቬርዴ 71.1፣ አራተኛ ናሚቢያ 68.6፣ እንዲሁም አምስተኛ ቦትስዋና 68.5 በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ፡፡ ይህ የፋውንዴሽኑ ዘገባ አገሮቹ በዓመቱ ካሳዩት አፈጻጸም በተጨማሪ፣ እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2017 ያለውን የአሥር ዓመት እንዲሁም እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2017 ያለውን የአምስት ዓመት አፈጻጸም አዝማሚያ ያመለክታል፡፡ ከእዚህ አንፃር የኢትዮጵያ አጠቃላይ አፈጻጸም ባለፉት አሥር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ መሻሻል ያላሳየ፣ ነገር ግን በቅርብ አምስት ዓመታት የማሽቆልቆል አዝማሚያ በማሳየት በማስጠንቀቂያ ምልክት ምድብ እንደሚፈረጅ ያመለክታል፡፡

ከእዚህ አኳያ የችግሩን ባህሪና ጥልቀት በውል ለመገንዘብ፣ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚያስፈልግ የማሻሻያ ዕርምጃዎችን በመጠቆም ካለው ፋይዳ በመነሳት የአገራችን አፈጻጸም በአራት ዓብይ ዘርፎች፣ በአሥራ አራት ንዑስ ዘርፎች እንዲሁም በአንድ መቶ ሁለት የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ማየት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በሁለት ዓብይ ዘርፎች፣ በስድስት ንዑስ ዘርፎችና በአርባ ሦስት የአፈጻጸም መለኪያዎች ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ ነገር ግን በቀሩት ሁለት ዓብይ ዘርፎች፣ ስምንት ንዑስ ዘርፎችና 59 መለኪያዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም ያስመዘገበች ሲሆን፣ ዝርዝሩ በሚከተለው ክፍል ይቀርባል፡፡

ደኅንነትና የሕግ የበላይነት ዘርፍ አፈጻጸም

በዚህ ዓብይ ዘርፍ የአገሮች አፈጻጸም ከ77.0 በላይ ከፍተኛ፣ ከ60.0 እስከ 76.9 መካከለኛ ከፍተኛ፣ ከ45.0 እስከ 59.9 መካከለኛ፣ ከ25.0 እስከ 44.9 መካከለኛ ዝቅተኛ፣ እንዲሁም ከ25.0 በታች ዝቅተኛ ምድብ እንደሚፈረጅ ፋውንዴሽኑ ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያሳየችው አፈጻጸም 46.4 ከአፍሪካ አገሮች አማካይ 52.6 በንፅፅር ዝቅተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በመካከለኛ ምድብ እንደሚፈረጅ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓብይ ዘርፍ ኢትዮጵያ ያላት አፈጻጸም ባለፉት አሥር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ መሻሻል ያሳየ ሲሆን፣ በቅርብ አምስት ዓመታት ግን ፈጣን የማሽቆልቆል አዝማሚያ ያመለክታል፡፡

በዘርፉ ከተካተቱ አራት ንዑስ ዘርፎች መካከል ከአንድ (ግልጽነትና ተጠያቂነት) በስተቀር በሦስት ንዑስ ዘርፎች (የሕግ የበላይነት፣ የግለሰብ ደኅንነትና ብሔራዊ ደኅንነት) የኢትዮጵያ አፈጻጸም ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ በአራቱ ንዑስ ዘርፎች ለአፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ 27 መለኪያዎች መካከል በዘጠኝ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ ነገር ግን በቀሩት 16 መለኪያዎች በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በዘርፉ ሥር ባሉት አራት ንዑስ ዘርፎችና 27 የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች የኢትዮጵያ አፈጻጸም ከእዚህ ቀጥሎ በዝርዝር ይቀርባል፡፡ አንደኛ የሕግ የበላይነት ንዑስ ዘርፍ ከሚያካትተው ስድስት መለኪያዎች መካከል በሁለት (የፍርድ ሒደት ነፃነትና ግልጽነት፣ የፍትሕ ተደራሽነት) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በቀሩት አገሮች መለኪያዎች (የፍርድ ቤት ነፃነት፣ የንብረት መብቶች፣ የተረጋጋ የሥልጣን ሽግግር ሥርዓት፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማዕቀብ) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አላት፡፡ ሁለተኛ በግልጽነትና ተጠያቂነት ንዑስ ዘርፍ ከሚካተቱ ዘጠኝ መለኪያዎች መካከል በአምስቱ (በሥልጣን ከአግባብ ዉጪ መጠቀም ማዕቀብና ክልከላ፣ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙስና ያለመኖር፣ በሕዝብ አስተዳደር ዘርፍ ሙስና ያለመኖር፣ በግል ዘርፍ ሙስና ያለመኖርና አድልኦ ያለመኖር) ከአኅጉሪቱ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ ነገር ግን በቀሩት አራት መለኪያዎች (የሕዝብና የሕግ መረጃዎች ተደራሽነት፣ በመንግሥት ይዞታ ያሉ ድርጅቶች መዛግብት ተደራሽነት፣ የመንግሥትና የሕዝብ አገልግሎት ሠራተኞች ተጠያቂነትና የፀረ ሙስና ሥርዓት) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

ሦስተኛ የግለሰብ ደኅንነት ንዑስ ዘርፍ ከሚያካትታቸው ስድስት መለኪያዎች መካከል በአንድ (ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ያለመኖር) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በቀሩት አምስት መለኪያዎች (ስለግለሰብ ደኅንነት ያለ አስተያየት፣ የፖሊስ አገልግሎት ላይ ያለ መተማመን፣ የሕዝባዊ አመፅ ያለመኖር፣ የወንጀል ድርጊት ያለመኖርና በመንግሥት አማካይነት በዜጎች ላይ የሚደርስ አመፅ ያለመኖር) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ አራተኛ በብሔራዊ ደኅንነት ንዑስ ዘርፍ ከተካተቱ ስድስት መለኪያዎች መካከል በአንድ (የስደተኞች ያለመኖር) ኢትዮጵያ ከአኅጉሪቱ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ በቀሩት አምስት መለኪያዎች (የመንግሥት በትጥቅ ግጭት ተሳትፎ ያለመኖር፣ በአገር ውስጥ የትጥቅ ግጭትና የግጭት ሥጋት ያለመኖር፣ በዜጎች ላይ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት አማካይነት የሚፈጸም ግጭት ያለመኖር፣ በጠረፍ አካባቢዎች ውጥረት ያለመኖርና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያለመኖር) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

በአገራችን በተያዘው ለውጥ ማግሥት የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ውዝግብን በሰላም ለመፍታት በተወሰደው ዕርምጃ፣ ቀደም ሲል በውጭ አገር በትጥቅ ትግል የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ንቅናቄዎችና ፓርቲዎች በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል  እንዲሳተፉ መንግሥት ላቀረበው ጥሪ በጎ ምላሽ መታየት፣ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ዕቅድ መዘጋጀትና የዚህን አፈጻጸም በኃላፊነት ለመምራት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት በሙያ ብቃትና ልምድ መመዘኛ መመደብ የንዑስ ዘርፉ አፈጻጸም በመጪው ጊዜ የተሻለ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ በተቃራኒ ባለፉት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ሁለት ሚሊዮን ያህል ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች የሚኖሩ መሆኑ፣ በንዑስ ዘርፉ አፈጻጸም አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል፡፡

ተሳትፎና ሰብዓዊ መብቶች ዘርፍ አፈጻጸም

በዘርፉ የአገሮች ውጤት ከ69.0 በላይ ከፍተኛ፣ ከ54.0 እስከ 68.9 መካከለኛ ከፍተኛ፣ ከ37.0 እስከ 53.9 መካከለኛ፣ ከ20.0 እስከ 36.9 መካከለኛ ዝቅተኛና ከ20.0 በታች ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደሚፈረጅ ፋውንዴሽኑ ያመለክታል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ውጤት 35.7 ከአፍሪካ አገሮች አማካይ 49.2 አንፃር ዝቅተኛ መሆኑንና በመካከለኛ የአፈጻጸም ምድብ እንደሚፈረጁ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በዓብይ ዘርፉ ያላት አፈጻጸም ባለፉት አሥር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ መሻሻል፣ ነገር ግን በቅርብ አምስት ዓመታት አዝጋሚ መሻሻል ያመለክታል፡፡

በዘርፉ በሚካተቱ ሦስት ንዑስ ዘርፎች በሁሉም (ተሳትፎ፣ መብቶችና ሥርዓተ ፆታ) የኢትዮጵያ አፈጻጸም ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ ነው፡፡ በተጨማሪ በሦስቱ ንዑስ ዘርፎች ለአፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ 19 መለኪያዎች መካከል በስድስት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ ነገር ግን በቀሩት 13 መለኪያዎች በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በዘርፉ ሥር ባሉ ሦስት ንዑስ ዘርፎችና 19 የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች ኢትዮጵያ ያሳየችው አፈጻጸም ዝርዝር ከእዚህ ቀጥሎ ይቀርባል፡፡ በቅድሚያ የተሳትፎ ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና በሚያገለግሉ አምስት መለኪያዎች (የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ፣ የምርጫ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን አቅምና ብቃት፣ ሕዝብን የማስተዳደር ብቃት) በሁሉም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ሆኖም ከለውጡ ወዲህ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ ውድድር አመቺ ለማድረግ የፀረ ሽብርና የሲቪል ማኅበራት ሕግጋትና የምርጫ ቦርድን ለማሻሻል ሊወሰዱ በሚታሰቡ ዕርምጃዎች ምክንያት፣ በመጪው ጊዜ የንዑስ ዘርፉ አፈጻጸም የተሻለ እንደሚሆን መገመት ይቻላል፡፡

ሁለተኛ በመብቶች ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ስድስት መለኪያዎች መካከል በሁለት (ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነትን ማፅደቅና የአፈጻጸም ዘገባ ማቅረብና የብሔር፣ የሃይማኖት፣ መገለልን መከላከል) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ አፈጻጸም ያላት ሲሆን፣ በተቃራኒ በቀሩት አራት መለኪያዎች (ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብና በማኅበር የመደራጀት መብት፣ የሲቪል ማኅበራት በነፃነት መንቀሳቀስ መብትና በመንግሥት አማካይነት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ያለመኖር) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን በነፃነት መንቀሳቀስን ጨምሮ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች፣ በመጪው ጊዜ አገራችን በንዑስ ዘርፉ የሚኖራትን አፈጻጸም እንደሚያሻሽል ይገመታል፡፡

በመጨረሻም በሥርዓተ ፆታ ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ስምንት መለኪያዎች መካከል በአራት (የፆታ እኩልነትን ማበረታታት፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ የሴቶች በሥራ ተሳትፎ፣ በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ትንኮሳን ለመከላከል የሚያግዙ ሕግጋት) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በተቃራኒ በቀሩት አራት መለኪያዎች (በመጀመሪያና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ምጣኔ፣ በሥራ ቦታ የፆታ እኩልነት፣ በዳኝነት የሴቶች ውክልና እንዲሁም፣ የሴቶች ለፖለቲካ ተሳትፎ መደፋፈር)፣ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ባደራጁት ካቢኔ በገሚሱ የሴቶች መመደብ፣ የክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በርዕሰ ብሔርነት መሾም፣ እንዲሁም የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያን ለመተግበር ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ መመደባቸው፣ አገራችን በመጪው ጊዜ በንዑስ ዘርፉ የሚኖራትን አፈጻጸም ለማሻሻል አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድል ዘርፍ አፈጻጸም

በዘርፉ የአገሪቱ አፈጻጸም ከ63.0 በላይ ከፍተኛ፣ ከ48.0 እስከ 62.9 መካከለኛ ከፍተኛ፣ ከ37.0 እስከ 47.9 መካከለኛ፣ ከ23.0 እስከ 36.9 መካከለኛ ዝቅተኛና ከ23.0 በታች ዝቅተኛ ደረጃ የሚመደብ መሆኑን ፋውንዴሽኑ ያመለክታል፡፡ በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ውጤት 49.3 ሲሆን፣ ይኼም ከአፍሪካ አገሮች አማካይ 44.8 በንፅፅር የተሻና በመካከለኛ ከፍተኛ ምድብ እንደሚፈረጅ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አገራችን በዘርፉ ያላት አፈጻጸም ባለፉት አሥር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ መሻሻል፣ ነገር ግን በቅርብ አምስት ዓመታት በፍጥነት ማሽቆልቆል አሳይቷል፡፡

በዘርፉ ከሚካተቱ አራት ንዑስ ዘርፎች መካከል በሦስት (ሕዝብ አስተዳደር፣ መሠረተ ልማትና የገጠር ዘርፍ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ ነገር ግን በተቃራኒ በአንድ ንዑስ ዘርፍ (የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በተጨማሪ በአራቱም ንዑስ ዘርፎች አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ 30 መለኪያዎች መካከል 16 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ የተሻለ፣ ነገር ግን በቀሩት 14 መለኪያዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ይህ ዘርፍ በሚያካትታቸው አራት ንዑስ ዘርፎችና 30 መለኪያዎች ያለውን የኢትዮጵያ አፈጻጸም የሚከተለው ክፍል በዝርዝር ያቀርባል፡፡ በቅድሚያ በሕዝብ አስተዳደር ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ዘጠኝ መለኪያዎች መካከል በሰባት (የመንግሥት የስታትስቲክስ አቅም፣ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ፣ የመንግሥት ሠራተኞች አገልግሎት ብቃት፣ በኢንተርኔት አማካይነት የሕዝብ አገልግሎት በቀጥታ ማግኘት፣ የበጀትና የፋይናንስ አስተዳደር፣ የፊስካል ፖሊሲና የታክስ ገቢ መሰብሰብ) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ በተቃራኒ በቀሩት ሁለት መለኪያዎች (የወጪ ንግድ ገቢ ምንጭ፣ ብዙኃነትና የበጀት ሚዛን) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ሁለተኛ የቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና በሚያገለግሉ ሰባት መለኪያዎች (የቢዝነስ ቁጥጥር ሥርዓት፣ ከመጠን ያለፈ የቢሮክራሲ ማነቆና እክል ያለመኖር፣ በውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ ገደብ ያለመኖር፣ የጉምሩክ አሠራር ሒደት ብቃት፣ የባንኮች አትጊ አሠራር፣ በሥራ ፈጠራ የሚያረካ መሆንና የቀጣና ትስስር በመንግሥት መጠናከር) በሁሉም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ሆኖም አየር መንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የንግድ መርከብና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን በመሳሰሉ ድርጅቶች የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር መንግሥት በያዘው ዕቅድ፣ በመጪው ጊዜ የንዑስ ዘርፉ አፈጻጸም የተሻለ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ሦስተኛ የመሠረተ ልማት ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ስድስት መለኪያዎች መካከል በሁለት (መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታ መኖርና የትራንስፖርት መሠረተ ልማት) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ በተቃራኒ በቀሩት አራት መለኪያዎች (የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ መሆን፣ የዲጂታል መረጃ ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት፣ የንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የውኃና የመፀዳጃ አገልግሎት አቅርቦት የሚያረካ መሆን) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

በመጨረሻ በገጠር ዘርፍ ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ስድስት መለኪያዎች መካከል በአንድ (የገጠር ድርጅቶች ተሳትፎ) ኢትዮጵያ ከአኅጉሪቱ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም ስታሳይ፣ በቀሩት አምስት መለኪያዎች (ለግብርና የሚውል መሬትና ውኃ አቅርቦት፣ የገጠር ቢዝነስ ከባቢ ሁኔታ፣ ለገጠር ልማት የሚውል መዋዕለ ንዋይ በመንግሥት መመደብ፣ የግብርና ምርምርና ድጋፍ አገልግሎት ተደራሽነት፣ ለግብርና ፖሊሲ የሚውል በጀት ሚዛን፣ በገጠር ድርጅቶች የፆታ እኩልነትን ማበረታታት፣ የገጠር ግልጽነትና ተጠያቂነት) በንፅፅር የተሻለ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

የሰብዓዊ ልማት ዘርፍ አፈጻጸም

የፋውንዴሽኑ አሠራር በዘርፉ የአገሪቱ አፈጻጸም ከ74.0 በላይ ከፍተኛ፣ ከ56.0 እስከ 73.9 መካከለኛ ከፍተኛ፣ ከ45.0 እስከ 55.9 መካከለኛ፣ ከ25.0 እስከ 44.9 መካከለኛ ዝቅተኛ፣ እንዲሁም ከ25.0 በታች ዝቅተኛ አፈጻጸም ደረጃ ይመደባል፡፡ በእዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ውጤት 54.6 ከአፍሪካ አገሮች አማካይ 52.8 በንፅፅር የተሻለና በመካከለኛ ምድብ እንደሚፈረጅ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አገራችን በዘርፉ ያላት አፈጻጸም ባለፉት አሥር ዓመታት አማካይ ዓመታዊ መሻሻል፣ ነገር ግን በቅርብ አምስት ዓመታት በፍጥነት ማሽቆልቆል ያሳየ በመሆኑ በማስጠንቀቂያ ምልክት ይገለጻል፡፡

በዘርፉ ከሚካተቱ ሦስት ንዑስ ዘርፎች መካከል በሁለት (ማኅበራዊ ረድኤት፣ ጤና) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በተቃራኒ በቀሪው አንድ ንዑስ ዘርፍ (ትምህርት) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በተጨማሪ በሦስቱም ንዑስ ዘርፎች አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ 26 መለኪያዎች መካከል 12 ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ ነገር ግን በቀሪዎች 14 መለኪያዎች ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ በዘርፉ በሚካተቱ ሦስት ንዑስ ዘርፎችና 26 አፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች የኢትዮጵያ አፈጻጸም ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር ይቀርባል፡፡ በቅድሚያ በማኅበራዊ ረድኤት ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ አሥር መለኪያዎች መካከል በአምስት (የማኅበራዊ ረድኤት ፖሊሲዎችና አገልግሎቶች፣ ወጣቶችን በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች ማካተት፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲዎች፣ የድህነት ቅነሳ ጥረትና ዘላቂ የተፈጥሮ አካባቢ ማበረታታት) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ፣ በተቃራኒ በቀሩት አምስት መለኪያዎች (ማኅበራዊ ሴፍቲኔት፣ ማኅበራዊ አካታችነት፣ የሕይወት ዘመን ድህነት ያለመኖር፣ የገቢ ክፍፍል ልዩነትን በማጥበብ እርካታና የተፈጥሮ አካባቢ ፖሊሲዎች) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡ ሁለተኛ በትምህርት ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ሰባት መለኪያዎች መካከል በሁለት (የትምህርት ጥራትና የትምህርት ከገበያ ፍላጎት ጋር መጣጣም) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በተቃራኒ በቀሩት አምስት መለኪያዎች (በትምህርት አገልግሎት አቅርቦት እርካታ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሰው ኃይል፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ማጠናቀቅ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ፣ የሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ተሳትፎ) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

በመጨረሻም በጤና ንዑስ ዘርፍ አፈጻጸም ምዘና ከሚያገለግሉ ዘጠኝ መለኪያዎች መካከል በአምስት (የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ቅስቀሳ፣ የሕፃናት ሞት ያለመኖር፣ የወላድ እናቶች ሞት ያለመኖር፣ የተላላፊ በሽታዎች ያለመኖርና የኤአርቲ አቅርቦት) ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የተሻለ በተቃራኒ በቀሩት አገሮች መለኪያዎች (በመሠረታዊ የጤና አገልግሎቶች እርካታ፣ የመፀዳጃ አገልግሎት ተደራሽነት፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለመኖርና የሕፃናት ክትባት) በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይታለች፡፡

የኢብራሂም የአፍሪካ መልካም አስተዳደር ቀመር ከሚያካትታቸው 102 የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች መካከል ኢትዮጵያ በ43 መለኪያዎች ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር የላቀ አፈጻጸም ያሳየች ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል በአኅጉሪቱ ደረጃ ሰንጠረዥ ቅድሚያ በመያዝ እጅግ በጣም የላቀ አፈጻጸም ያላት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ያለመኖር፣ የወንጀል ድርጊት ያለመኖር፣ የበጀትና ፋይናንስ አስተዳደር፣ መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታ መኖር፣ የማኅበራዊ ረድኤት ፖሊሲዎችና አገልግሎቶች፣ ዘላቂ የተፈጥሮ አካባቢ ማበረታታት፣ የድህነት ቅነሳ ጥረት፣ የፊስካል ፖሊሲ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና ፖሊሲዎች፣ የሴቶች ሥራ ተሳትፎ፣ የሕዝብ አገልግሎቶች ብቃት፣ በኢንተርኔት መረብ አማካይነት በቀጥታ አገልግሎት ማግኘት፣ የአድልኦ አሠራር ያለመኖር፣ እንዲሁም የትምህርት ጥራትና አፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች ቅድሚያ ይይዛሉ፡፡

በተቃራኒ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች አማካይ በንፅፅር ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየችው በ59 የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል እጅግ በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም በማሳየት በአኅጉሪቱ ደረጃ ሰንጠረዥ ታችኛው ረድፍ የተሠለፈችው የመጠጥ ውኃ አቅርቦት 52ኛ፣ የሲቪል ማኅበራት ተሳትፎ 52ኛ፣ በመንግሥት አማካይነት በዜጎች ላይ የሚደርስ አመፅ ያለመኖር 49ኛ፣ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት 49ኛ፣ የሲቪል መብቶች ነፃነት 48ኛ፣ የመሰብሰብና በማኅበር የመደራጀት ነፃነት 48ኛ፣ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ 48ኛ፣ ሕዝባዊ አመፅ ያለመኖር 46ኛ፣ እንዲሁም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያለመኖር 46ኛ ዘጠኝ የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ፋይዳ

በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ማዘጋጀትና መተግበር ወቅቱ የሚጠይቀው ቅድሚያ ተግባር ነው፡፡ የአገራችን መልካም አስተዳደር ችግር ውስብስብና ሥር የሰደደ እንደ መሆኑ፣ በተጨባጭ መረጃዎችና በጥልቅ ጥናት ላይ በመሞርኮዝ የሚወሰዱ የመፍትሔ ዕርምጃዎች አጥጋቢ ውጤት ለማግኘት ይረዳሉ፡፡ የአገራችን ምሁራንና ልሂቃን በዳተኝነት ዳር ተመልካች ከመሆንና ትችቶችን ከመሰንዘር ይልቅ፣ ለችግሮች አገር በቀል የመፍትሔ ዕርምጃዎችና ምክረ ሐሳብ እንዲያፈልቁ መልካም ዕድል ያመቻቻል፡፡ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ከሌሎች የልማት ዕቅዶች (የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ) ጋር በተቀናጀ መንገድ እንዲተገበር፣ ይህም የላቀና ዘላቂ ውጤት ለማግኘት ያስችላል፡፡ በመልካም አስተዳደር አጀንዳ አገራዊ መነቃቃትና መግባባት ለማዳበር፣ እንዲሁም በሁሉም አካላት ዘንድ መተማመን እንዲዳብር ያግዛል፡፡ መልካም አስተዳደር በመንግሥት በጎ ፈቃድ የሚታደል ገጸ በረከት ባለመሆኑ የዕቅዱ ዝግጅት አግባብነት ያላቸው አካላትን ንቁ ተሳትፎ በማረጋገጥ ፍላጎታቸውን ከማካተት በተጨማሪ፣ በዕቅዱ አፈጻጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ያስችላል፡፡ የሚታቀዱና የሚተገበሩ የመፍትሔ ዕርምጃዎች ግብዓታዊ፣ የተነጣጠሉና ተያያዥነት የጎደላቸው እንዳይሆኑ ይረዳል፡፡

የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ግልጽና የተሟላ ጽንሰ ሐሳብ ግንዛቤ በመጨበጥ ከላይ የተመለከቱ የመልካም አስተዳደር አራት ዓብይ ዘርፎች፣ 14 ንዑስ ዘርፎችና 102 የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎችን በማካተት የሚዘጋጅ ቢሆን አጥጋቢ ውጤት ለማግኘት ይረዳል፡፡ ይህ የማሻሻያ ዕቅድ ግልጽ ራዕይ፣ ዓላማና ግብ፣ ዝርዝር ተግባራት፣ የትግበራ ቅደም ተከተልና የጊዜ ሰሌዳ፣ የፋይናንስ ፍላጎት፣ የአስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት ድርሻ፣ የአቅም ግንባታ መርሐ ግብር፣ እንዲሁም የክትትልና ግብረ መልስ ሥርዓት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዕቅድ ዝግጅት የሚከተሉት ዋና ዋና ተግባራትን ያካትታል፡፡ አግባብነት ያላቸው ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ተቋማት ከሚገለገሉባቸው የአፈጻጸም ምዘና መለኪያዎች አኳያ፣ በሁሉም የመልካም አስተዳደር ዘርፎች የኢትዮጵያን አፈጻጸም (የወቅቱና ያለፉ ዓመታት አዝማሚያ) አስመልክቶ መረጃ ያጠናቅራል፡፡ የአገራችን መልካም አስተዳደር የሚመለከት የሕዝብ አስተያየት መረጃ ያጠናቅራል፡፡ ለማሻሻያ ዕቅድ ዝግጅት የሚረዳ የነባራዊ ሁኔታዎች (ጠንካራ ጎን፣ ድክመት፣ መልካም አጋጣሚዎች፣ እንዲሁም የሚያጋጥም ተግዳሮት) ትንተና ያካሂዳል፡፡ ለመልካም አስተዳደር መስፈን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ቁልፍ ተቋማትን ዓላማና ተልዕኮ፣ ተግባራት፣ ከፖለቲካ ተፅዕኖ በነፃነት መንቀሳቀስ፣ ሕግ፣ ደንብና የአሠራር መመርያዎች፣ የአመራር ኃላፊዎች ሥነ ምግባርና ብቃት፣ እንዲሁም የማስፈጸም አቅም ጥልቅ ፍተሻ በማካሄድ የማሻሻያ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡

ይህም በተለይ ቁልፍ ተቋማት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ የፍርድ ቤቶች፣ የፍርድ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች (ፖሊስና ማረሚያ ቤቶች)፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የመገናኛ ብዙኃን ድርጅቶች፣ የዋና ኦዲተር ጽሕፈት ቤት፣ የመንግሥት ሠራተኞች አስተዳደር ኮሚሽን፣ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡

የማሻሻያ ዕቅዱ በማኅበራዊ ኢኮኖሚ እንዲሁም በፖለቲካ መስክ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበራት፣ በልዩ ልዩ መብቶች ጥበቃ የሚሠሩ ድርጅቶች፣ የቡድን ፍላጎትን የሚያራምዱ ተቋማት፣ እንዲሁም የማኅበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር የሚያስችሉ የአሠራር ሒደቶችን ይጠቁማል፡፡ አግባብነት ባላቸው የማሻሻያ ጉዳዮች የሕዝብ አስተያየት በልዩ ልዩ ዘዴዎች (የውይይት መድረኮችና በጥናት) ይሰበስባል፣ ለዕቅድ ዝግጅት በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡ በመስኩ አግባብነት ያላቸው አገራችን ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍና አኅጉራዊ ስምምነቶችን ለመተግበር የሚያስችሉ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች እንዲቀረፁ ምክረ ሐሳብ ያቀርባል፡፡ በመልካም አስተዳደር መስክ የአገራችን አፈጻጸምና ግድፈቶችን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያዘጋጁትን ዘገባና መረጃ ይሰበስባል፡፡ የእርምት ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚረዳ ምክረ ሐሳብ ይሰነዝራል፡፡ በአገራችን ልዩ ልዩ አካባቢዎች የመልካም አስተዳደር አፈጻጸምን ለማሻሻል አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ባህሎችና ልምዶችን በመለየት በዕቅድ ዝግጅት እንዲካተቱ ምክር ይሰጣል፡፡ የላቀ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ያላቸው አገሮችን ልምድና ተሞክሮ በመቀመር በግብዓትነት ይጠቀማል፡፡ የማሻሻያ ዕቅዱን ለመተግበር የአቅም ግንባታ ዕቅድ (ሕግና ተቋማት፣ የሰው ኃይል ሥልጠና፣ እንዲሁም የአሠራር ዘዴ) ያዘጋጃል፡፡ በመልካም አስተዳደር ጽንሰ ሐሳብ፣ በአገራችን ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችና በማሻሻያ ዕቅዱ ይዘት ግንዛቤ ለማዳበር የሚረዳ የሕዝብ ውይይት መድረክ በየደረጃው ያዘጋጃል፣ በብዙኃን መገናኛ ዘዴዎች ያሠራጫል፣ በመልካም አስተዳደር ማሻሻያ አጀንዳ አገራዊ መነቃቃት እንዲኖር የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ በመዳሰስ፣ ችግሮችን በመተንተን፣ መንስዔዎችን በመለየትና የማሻሻያ ዕርምጃዎችን በቅደም ተከተል በማመልከት ግልጽና አሳታፊ ሒደት በመከተል የመንግሥት ኃላፊዎች የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ምሁራንና የምርምር ባለሙያዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የግል ንግድ ዘርፍ ማኅበራት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሙያ ማኅበራት መሪዎች (ሠራተኞች፣ መምህራን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፣ መሐንዲሶች. . . )፣ የሕዝባዊ ማኅበራት ተወካዮች (ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ጡረተኞች፣ አረጋውያን፣ አርበኞች)፣ የማኅበረሰብ ድርጅቶች (ዕድር)፣ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመሳሰሉ እንዲሳተፉ ያመቻቻል፡፡

የእዚህን ማሻሻያ ዕቅድ ዝግጅት የሚመራና የሚያስተባብር ግብረ ኃይል ማደራጀት አስፈላጊ ሲሆን፣ የሚመረጡ አባላት ከፖለቲካ ወገንተኛነት ገለልተኛ የሆኑና በነፃነት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ አባላት በመልካም አስተዳደር ዘርፎች የሙያ ተዋጽኦ እንዲኖራቸው (ለምሳሌ የፖለቲካ ሳይንስ፣ የሕግ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ ታሪክ፣ የንግድ ሥራ አመራር) እንዲሁም የሙያ ብቃትና ክህሎት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ለዕቅድ ዝግጅት ግብረ ኃይል አስፈላጊ ድጋፎችን (ከመንግሥትና ከሌሎች አግባብነት ያላቸው አካላት) የሚያቀናጅ አስተባባሪ ቡድን ማደራጀት ለስኬት አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡ አገራችን በዘመናት በሚቆጠር ሥልጣኔ የምትታወቅ፣ ሉዓላዊነቷንና ነፃነቷን አስከብራ የቆየች፣ እንዲሁም የረዥም ጊዜ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት የነበራት ከመሆኑ አንፃር፣ በቅርብ ዓመታት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃነታቸውን ከተቀዳጁ የአፍሪካ አገሮች በንፅፅር ዝቅተኛ የመልካም አስተዳደር አፈጻጸም ደረጃ ላይ መገኘቷ በጣም ቁጭት የሚቀሰቅስ ነው፡፡

በአገራችን የመልካም አስተዳደር ሥርዓት መስፈን ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ መካከል የዜጎች ነፃነትና ደኅንነትን በማረጋገጥ የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ ማስቻል፣ የሕዝብ አገልግሎት አቅርቦት ብቃትና ተደራሽነትን በማሳደግ የዜጎችን ሕይወት ጥራት ደረጃ ማሻሻልና የቢዝነስ ተወዳዳሪነትን መደገፍ፣ በመንግሥት አስተዳደር ላይ ዜጎች በሚያሳድሩት መተማመን ምክንያት ፖሊሲ ሕግ ደንብና መመርያ ያከብራሉ፣ ያስከብራሉ፡፡ በአጠቃላይ በኢኮኖሚና ማኅበራዊ ልማት እንቅስቃሴዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ይሳተፋሉ፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ በመጪው ጊዜ አገራችን መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ የያዘችውን ራዕይ በዕውን ለማሳካት፣ የመልካም አስተዳደር መስፈን የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በውል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም መልካም አስተዳደር በሕዝብ ምኞትና በመንግሥት በጎ ፈቃድ ብቻ የሚሰፍን ሳይሆን፣ አስፈላጊና አግባብነት ያለውን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋትና ተግባራዊ አፈጻጸምን በየጊዜው ክትትል ማድረግ ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም በአገራችን በተያዘው የመደመርና የይቅርታ ለውጥ እንቅስቃሴ፣ ሕዝብ ለብዙ ዓመታት በተስፋ ሲጠብቅ የኖረውን የመልካም አስተዳደር ትሩፋት በተሟላ ሁኔታ ለመቋደስ እንዲችል በዚህ ረገድ የሚደረግ ጥረት ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...