Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሴቶች አመራር ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የመጀመርያዋ ሴት ሆነዋል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ንግድ ምክር ቤቱ ባካሄደው ምርጫ ወ/ሮ መሰንበት ተፎካካሪያቸውን በሰፊ ልዩነት በማሸነፍ፣ የፕሬዚዳንትነቱን ኃላፊነት ተረክበው ሥራ ጀምረዋል፡፡ የ54 ዓመቷ ወ/ሮ መሰንበት ከዚህ ቀደም የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አባል በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ ለንግድ ምክር ቤቱ አዲስ አለመሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ወ/ሮ መሰንበት የተወለዱት አዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡ የመጀመርያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተማሩት ቅድስት ልደታ ካቴድራል ነው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንትና ፐብሊክ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ ከእንግሊዝ አገር በቢዝነስ አድሚኒስትሬሸን የማስተርስ ዲግሪ ወስደዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ ሥራ የጀመሩት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ነው፡፡ በልማት ባንክ ከጁኒየር ኦፊሰርነት ጀምሮ እስከ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሠርተዋል፡፡ በአጠቃላይ በልማት ባንክ ከሃያ ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ ከልማት ባንክ የወጡት የዓባይ ባንክን እንዲያደራጁ በቀረበላቸው ግብዣ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ መሠረት ዓባይ ባንክን ከማደራጀት ጀምሮ ሠርተዋል፡፡ ባንኩ ወደ ሥራ ከገባ በኋላም ፕሬዚዳንት ሆነው ለአምስት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ ወ/ሮ መሰንበት በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሁለተኛዋ ሴት ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ እንቆቅልሽ ነው ከሚባለው ከዓባይ ባንክ ኃላፊነታቸው መልቀቅ በኋላ በማማከር ሥራ የተሰማራ የራሳቸውን ኩባንያ በማቋቋም በዋና ሥራ አስኪያጅነት ይመራሉ፡፡ አሁን ደግሞ የንግድ ምክር ቤቱም ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የነበራቸውን ቆይታና በንግድ ምክር ቤቱ  ጉዳዮች ላይ፣ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ሴት የሥራ መሪዎች ወደ ኃላፊነት እየመጡ ከመሆኑ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በማንሳት ዳዊት ታዬ ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጥን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለሃያ  ዓመታት በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በልማት ባንክ ውስጥ የነበረዎን ቆይታ ወደ ኋላ መለስ ብለው ያስታውሱኝ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ልማት ባንክ መጀመርያ የተቀጠርኩበት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ በባንኩ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ሠርቻለሁ፡፡ የሰፖርት ማኔጅመንት፣ የኢንፎርሜሽን ሲስተም፣ የፋይናንስ፣ የኮርፖሬት ፕላኒንግና ስትራቴጂ ውስጥ ሁሉ ሠርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ብድር ሥራ ነው የገባሁት፡፡ ባንኩን ከወጣትነት ዘመኔ ጀምሮ ስለማውቀውና  ትራንስፎም ለማድረግም ለውጡን እመራ ነበር፡፡ እንቅስቃሴያችን በጣም ውጤታማ የሚያደርጉ አሠራሮች ነበሩን፡፡ በወቅቱ ለየት ያሉ ሥራዎችን ሁሉ እንሠራ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት የተለዩ ሥራዎች?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ለምሳሌ ብድሩን ከመፍቀዳችን በፊት ከተበዳሪው ጋር ተነጋግረን  ይሆናል አይሆንም ብለን የምንለይበት ራሱን የቻለ ክፍል ነበረን፡፡ ይሆናል ከተባለ እንዴት መሄድ እንዳለበትና የብድር አካሄዱ እንዴት እንደሆነ የምንሄድበት አሠራር ነበረን፡፡ ክትትል ላይም ጠንካራ የሆነ አካሄድ ነበረን፡፡

ሪፖርተር፡- ከልማት ባንክ እንዴት ወጡ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ቦርዱ በሌላ መልክ ጥያቄ ቀረበለት፡፡ ባንክ ልናቋቁም እንፈልጋለንና እባክህ መሰንበትን ይሉታል፡፡ እኔ ይህንን ስሰማ ደነገጥኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ወ/ሮ መሰንበት፡- እኔ ብዙ ጊዜ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሥራ አግኝቼ አትሄጂም እየተባልኩ ቀርቻለሁ፡፡ እና ይህ ጥያቄ ሲመጣ የቦርድ ሊቀመንበሩ አንድ ባንክ ሊቋቋም ነውና ከባንክሽ ትሄጃለሽ ወይ? ታግዣለሽ ወይ? ይለኛል፡፡ እኔም ግድ የለም አግዛለሁ አልኩኝ፡፡ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ የባንኩን ሁኔታ ሳየው ጥሩ ስላልነበረ ሌላ ቦታ ለመግባት ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በልማት ባንክ የጀመርነው ለውጥ ወደ ኋላ የመመለስ ነገር ስለነበር፣ ስታመጣው የነበረው ለውጥ ወደ ኋላ ከተመለሰ አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህንን ለማስጠበቅ አስቸጋሪ ሆነና ይህ ጥያቄ ሲቀርብልኝ ነገሩን ማጤን ውስጥ ገባሁ፡፡ ያኔ ባንካችን 100ኛ ዓመቱን እያከበረ ነበር፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን ይዤ ይቋቋማል የሚባለው ባንክ ምንድነው? የማነው? የሚለውን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መረጃ በማሰባሰብ ጥናት ውስጥ ገባሁ፡፡ በአንዳንድ ነገሮች ጊዜ ፈጀብኝ፡፡ እኔ ፕሮፌሽናል ነኝ፡፡ እዚህ ሥራ ብጀምር ወዴት አቅጣጫ እንደሚወስዱኝ አሰብኩ፡፡ ስሜን የመጠበቅም ነገር አለ፡፡ እነሱ ደግሞ በጣም ገፋፉኝ፡፡ እኔም ልማት ባንክ መቀመጡን አልወደድኩትም፡፡ አሁን ስለልማት ባንክ ያለውን ነገር የምታውቁት ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቢስተካከል ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ለማንኛውም ሌላም አማራጭ አልነበረም፡፡ ይህን ባንክ ማቋቋም ለእኔ ጥሩ ነው፡፡ እኔ ልማት ባንክ ውስጥ ለመሥራት ፈልጌ ያላሰካሁትን ምኞቴን እዚህ ላይ እተገብረዋለሁ በማለት ጭምር ገባሁ፡፡ በእውነትም አደረግኩት፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት? ምኞትዎ ምን ነበር? ምን አደረጉ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ምክንያቱም መሪ ስለሆንኩኝ በመሪነቴ ልተገብራቸው የሚቻሉ ሥራዎች ነበሩ፡፡ መሪ ማለት ለገንዘብና ለሥልጣን ሳይሆን፣ የምታስበውን ነገር እንዲሆንልህ ማድረግ ጭምር ነው፡፡ ሌሎች የሚናገሩት ነገር ትክክል ከሆነ ደግሞ ትቀይራለህ፡፡ እንዲህም ሆኖ ጥሩ ሆነ፡፡ አዲስ ነገር ልፈጥር እችላለሁም ብዬ ነው የጀመርኩት፡፡ ይህንን ሐሳብ ይዤ በጣም ጥሩ ጥሩ የምላቸው ሰዎች አስገብቼ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በነገርህ ላይ ብዙ ሰዎች በእኔ ተሰቃይተዋል፡፡ ከእኔ ጋርም ባሰብኩት መስመር መኼድ ስላለበት እጫናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ተሰቃይተዋል ሲሉ እንዴት ነው?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ተሰቃይተዋል ስልህ ሁኔታው ይህንን ያህል ደመወዝ ለመክፈል የሚያስችል አልነበረም፡፡ አንዳንዶቹ የባንኩ ነገሮች ከአማራ ክልል መንግሥት ጋር የተቀራረቡ ናቸው፡፡ የደመወዙም ነገር አለ፡፡ እኔም ልማት ባንክ ሆኜ ይከፈለኝ የነበረውን 16 ሺሕ ብር ደመወዝ እያገኘሁ ለሦስትና ለአራት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ እንዲህም ሆኑ ባንኩን በአሥር ወራት አቋቋምን፡፡ የዓባይ ባንክ ቦርድ ሲያመጣኝ እንደ ራስሽ ልጅ አድርገሽ እይው ነበር ያለኝ፡፡ ይህንን አባባል በፍፁም አልረሳውም፡፡ በእውነት ነው የምላችሁ በዓባይ ባንክ የፖለቲካ ጉዳዩም አለ፡፡ የክልሉ መንግሥትም ድርሻ  አለው፣ ግን ባንክ ሲባል የሕዝብ ገንዘብ ነው፡፡  ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው የግል ኩባንያዎችም አሉት፡፡ ብዙ ግለሰብ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡ ይህንን ከየባላገሩ ጋቢያቸውን ለብሰው መጥተው ባለአክሲዮን የሆኑ አሉ፡፡ የሚገርመው ያኔ ባንኩን ስናቋቁም አንድ ባለአክሲዮን መግዛት የሚችለው ዝቅተኛው የአክሲዮን ሽያጭ 50 ሺሕ ብር ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ከየገጠሩ የመጡ ሰዎች የራሳችን ባንክ ነው ብለው በ50 ሺሕ ብር አክሲዮን ገዝተው የገቡ ናቸው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉትን ሰዎች ገንዘብ ጭምር ይዤ ነው እንግዲህ ባንኩን ያቋቋምኩት፡፡

ሪፖርተር፡- ከምሥረታው በኋላ ባንኩን ሥራ ለማስጀመር ምን ዓይነት አሠራር ተግባራዊ አደረጉ?

ወ/ሮ መሠንበት፡- ሥራውን ለመጀመር የመረጥነው ከዩኒቨርሲቲ በተመረቁ አዳዲስ ተማሪዎች ነበር፡፡ እነሱን አምጥተን አሠልጥነን ነው ሥራ ያስጀመርነው፡፡ በራሳችን ባህል ቀርፀናቸው ወደ ሥራ እናስገባቸዋለን፡፡ አዳዲስ ነገር እንዲፈጥሩ እናግዛቸዋለን፡፡ እንደምታውቀው የባንክ ዘርፍ በጣም ቁጥጥር ያለበት ነው፡፡ እንደፈለጉ መሆን አይቻልም፡፡ ወጣት እንደ መሆናቸው ቁጥጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ውስጣዊ ከባቢን ለመቀየር አዳዲሰ ነገሮችን ይፈጥራሉ፡፡ ብቻ እንዲህ ያሉ አሠራሮችን ተከትለን እየሠራን ቶሎ ቶሎ እያደግን መጣን፡፡ ከዚያ ብዙ ጊዜ ከሠራን በኋላ ያው እያደግን ስንመጣ የሚገጥም ነገር አለ፡፡ እኔም ነፃ ሆኜ መሥራት እወዳለሁ፡፡ እኔ የምለካው በሥራ አፈጻጸሜ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላ ግራና ቀኝ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዓባይ ባንክ አወጣጥዎ ግልጽ አይደለም፡፡ የሥራ መልቀቅዎ ምክንያት ምንድነው?

ወ/ሮ መሠንበት፡- ከባድ ነው፡፡ ግን ከዓባይ ባንክ ስወጣ ቦርዱና ሠራተኞቹ መሸኛ አድርገውልኝ እዚያ ላይ የተናገርኩት እኔ ራሴ ለምን እንደወጣሁ አላውቀውም፡፡ ይህንን ወደፊት በመጽሐፍ እጽፈዋለሁ ነው ያልኳቸው፡፡ ሁሉም ሰው ተሰምቶታል፡፡ ትንሽ ብቆይ ደስ ይለኝ ነበር የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ የወጣሁባቸውን ምክንያቶች ይኼ ነው ብዬ ለመናገር ግራ የሚገባኝ ጊዜ አለ፡፡ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች መሀል የሚፈጠር ነገር አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ መነጋገርና መጨቃጨቅ ሲፈጠር ለዕድገትም እንቅፋት ይሆናል፡፡ አለመግባባቶችን ከዚህ በላይ ማሳደግ ተገቢ ባለመሆኑ ነው፡፡ ለማንኛውም ለምን እንደሆነ ብዙ ነገሮች አስብ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ያለመግባባቱ ምክንያት ምንድነው?

ወ/ሮ መሠንበት፡- በዚህ ሥራዬ በጣም ታዋቂ ሆንኩ መሰለኝ፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባለውን ነገር አላውቅም፡፡ እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም፡፡ አልነበርኩም፡፡ ስለዚህ ተቀባይነቱ አልተወደደ ይሁን አላውቅም ነገሩ እንዲያ ሆነ፡፡ እኔ ነፃ ፕሮፌሽናል ሆኜ ነው የምሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- ቅድም ዓባይ ባንክን በሚያቋቁሙበት ጊዜ ደመወዜ 16 ሺሕ ብር ነበር ብለውኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት በግል ባንክ ውስጥ አንድ ፕሬዚዳንት እስከ 100 ሺሕ ብር አንዳንዶቹም ከዚያ በላይ ይከፈላቸዋል በሚባልበት ወቅት፣ እርስዎ በዚህ ደመወዝ መሥራትዎ ከምን የመነጨ ነው? ዓባይ ባንክን እስከለቀቁበት ጊዜ ድረስ ደመወዝዎ ይኸው ነበር?

ወ/ሮ መሠንበት፡- ባንኩን በምንቋቋምበት ጊዜ ደመወዜ 16 ሺሕ ብር ነበር፡፡ ከዚያ ስወጣ ደመወዜ 37 ሺሕ ብር ደርሶ ነበር፡፡ ይህም የሆነው አንድ ጊዜ ለመንግሥት ባንኮች ጭማሪ ሲደረግ ነው እኔም 37 ሺሕ ብር የደረስኩት፡፡ ያኔ በእኛ ባንክ ይህ የደመወዝ መጠን አይታሰብም ነበር፡፡ ቅድም ያልኩህ ጋቢ ለብሰው ስለመጡት ሰዎች ነው የምናስበው፡፡ ለምሳሌ እኛ ጠቅላላ ጉባዔ አድርገን ግብዣ ስናዘጋጅ ለእነዚህ ሰዎች እንጀራ እናዘጋጃለን፡፡ ከባላገር የሚመጡ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይታይሃል ከእነዚህ ሰዎች ብዙ ገንዘብ መውሰድ፡፡ እኔ ራሴ የደመወዜን መጠን አስቤው አላውቅም፡፡ ይበቃኛልም ደስም ይለኛል፡፡ የሚገርምህና በጣም ደስ የሚለው ነገር ዓባይ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሌለባቸው አካባቢ ቅርንጫፍ ይከፍት ነበር፡፡ ብዙ ድሆች ያሉባቸው እነዚህ ቅርንጫፍ የምንከፍትባቸው ቦታዎች፣ ቅርንጫፉን ከከፈትን በኋላ የሆነ ዕድገት ሲመጣ እናይ ነበር፡፡ ቅርንጫፉ ከመከፈቱ በፊት አርሶ አደሮቹ እንግዲህ አያ እከሌ ይህንን ገንዘብ ለእገሌ ስጥልኝ፣ ይህንን አምጣልኝ ሲሉ ተቆርጦ ይመጣል፡፡ በኋላ ግን እህላቸውን ልከው ገንዘባቸውን በባንክ ያንቀሳቅሳሉ፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ብድር ተሰጥቷቸው ራሳቸውን ሲያሳድጉ ታያለህ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ያስደስተን ነበር፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔርን ነው የምልህ ይህንን አላሰብንም፡፡ ደግሞም በቂ ነው፡፡ ሴክተሩ ራሱ ይህንን ያህል ለምን እንደሚከፍል አላውቅም፡፡ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሌላ ትልቅ ደመወዝ የሚከፍለው የባንክ ኢንዱስትሪው ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን የሥራ ትጋትና ኃላፊነት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የልማት ባንክና የዓባይ ባንክ ብዙ ትዝታዎች አለዎት፡፡ ከወጡ በኋላ ግን በተለይ ዓባይ ባንክን ለመደገፍ ሞክረዋል? ቅኝት አድርገው እንዲህ ቢሆን እንዲህ ቢደረግ የማለት ዕድል አጋጥሞዎታል?

ወ/ሮ መሠንበት፡- አንዳንድ ጊዜ ከለቀቅን በኋላ ተመልሰን ለመሄድ መሞከር ከእኔ የተሻለ የለም የሚል ስሜት እንዳያመጣ እፈራለሁ፡፡ ዓባይ ባንክን መሠረቱን ያወጣሁትና እዚያ ደረጃ ያደረስኩት ስለሆነ መጥፎ ነገሮች እንዲመጡበት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን እውነት ለመናገር እንደ መሥራችነቴ ጠጋ ብዬ እንዴት ነው ብሎ ለመመካከር ሊፈልጉ ይችላሉ የሚለው እምነት የለኝም፡፡ በተለይ ቦርድ ላይ ስትመጣ ይህ ፍላጎት ያለ አይመስለኝም፡፡ ከእኛ አስተሳሰብ ጋር ሙሉ ለሙሉ የተለየ ነው፡፡ እኔ የማምነው በመመካከር ነው፡፡ ግን ካየኋቸው ነገሮች እንዲያ ልታደርግ የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ምናልባት ከአሁን በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን ያለው ቦርድ ጥሩ ከሆነ ሊሆን ይችላል፡፡ ባንኩን እወደዋለሁ፡፡ ብዙ ሰው ሊያግዝ የሚችል ነው፡፡ ከሌላው ባንክ የተለየ ነገር አለው፡፡ ከእኛ የፈጠርነው የተለየ ባህል ነበር፡፡ የማኔጅመንት ዘይቤው ዘመናዊ ነው፡፡ ማኔጅመንቱን የተለየ የሚያስብሉ ነገሮች ሁሉ ነበሩት፡፡ ለምሳሌ እኔ ስፖርተኛም ነኝ፡፡ የሜዳ ቴኒስ እጫወታለሁ፡፡ ስፖርት በጣም እሠራለሁ፡፡ ጂም እሠራለሁ፡፡ ግን ስብሰባ በምመራበት ሰዓት የማያቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ሁሌ አራት ሰዓት ስብሰባ አለን፡፡ የቀኑን ሥራ በተመለከተ ሻይ እየጠጣን አራት ሰዓት ላይ እንነጋገራለን፡፡ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ደግሞ ምን አዲስ ነገር አለ ብለን እንነጋገራለን፡፡ ይህ የተለየ ነው፡፡ ማኔጅመንቱ በቡድን ነው የሚሠራው፡፡ ከዚያ በኋላ ሳስብ ሕመም ምናምን እየተባለ እኔ ጤናማ ሆኜ እየሠራሁ፣ እነሱንም በዚያ መንገድ እንዲሄዱ ለምን አላደርግም ብዬ ወሰንኩ፡፡

ሪፖርተር፡- የማኔጅመንት አባላቱን ስፖርት ለማሠራት ማለት ነው?

ወ/ሮ መሰንበት፡- አዎ! በዚህ ረገድ የመጀመርያው ባንክም ነው፡፡ ማኔጅመንቱን ወደ ስፖርት አስገባሁ፡፡ በዚህ ድርጊቴ አይረሱኝም፡፡ በሕይወታቸው ተንቀሳቅሰው የማያውቁ ሁሉ መሥራት ጀመሩ፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ስኳር የለ ደም ግፊት የለ፡፡ ይህ በመሆኑ ለስብሰባ ንቁ ሆኖ መምጣት ተጀመረ፡፡ ሁለተኛ የሜዲካል ወጪያችን ቀነሰ፡፡ ተደስተን እንሠራለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- ግን ስፖርቱን እንዴት ነው የምትሠሩት?

ወ/ሮ መሰንበት፡- እዚህ ኤግዚቢሽን ማዕከል አካባቢ ያለ አንድ ጂም ቤት አለ፡፡ ዋጋው ተመጣጣኝ ነው፡፡ እዚያ በሳምንት ሁለት ጊዜ ኤሮቢክስ ነው የምንሠራው፡፡ ግን ፊትነስ እንዲሠሩ ብረት እንዲያነሱም አደርጋለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ዓባይ ባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ይዞ የመጣው ሌላ አዲስ ነገር ነበር?  የምሽት ሥራ እንዴት ተጀመረ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ይህ የመጣው ስፖርት መሥራታችን ያገኘነውን ውጤት ዓይተን ነው፡፡ ማታ ማታ ሰዎች ንግዳቸውን ሁለትና ሦስት ሰዓት ላይ ይዘጋሉ፡፡ ይህንን ሳይ ለምንድነው ባንካችንን ምሽት ላይ እስከ ሁለት ሦስት ሰዓት የማናሠራው ብዬ አሰብኩ፡፡ ወጪያችንን አስበን ብዙ ሰው ሳናስገባ ንቁ በሆኑ ቅርንጫፎቻችን እስከ ምሽቱ ሦስት ሰዓት እንሥራ አልን፡፡ ለምሳሌ መርካቶ አካባቢ ምሽት ላይ የሚዘጉ የንግድ ሱቆች ገንዘባቸውን እዚያው ሊያሳድሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እኛ ብናመሽ ገንዘቡን ገቢ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል ይፈጠራል፡፡ እንዳይሰረቅ፣ እሳት ቢነሳ እንዳይወድም ጭምር ይረዳል ብለን እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት የባንክ አገልግሎት የጀመርነው እኛ ነን፡፡ በነገራችን ላይ እሑድም ለመሥራት አስቤ ነበር፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መልስ ከአራት ሰዓት በኋላ ለመጀመር መንቀሳቀስ ጀምሬ ነበር፡፡ ይህም በበዓላት ቀን ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ተቀብሎ ወደ ባንክ ለማስገባት ነበር፡፡ ይህንን አገልግሎት ለመጀመር በጊዜው ብፁዕ አቡነ ጳውሎስን ማነጋገር ፈለግኩ፡፡ በሰው በሰው አድርጌ አቡነ ጳውሎስን አገኘኋቸው፡፡ ‹‹አባታችን እርስዎ ለመሆኑ ከየበዓላት ቀኑ ከየምዕመናኑ በጃንጥላ የሚሰበሰበው ገንዘብ በሙሉ ይገባል ብለው ያስባሉ?›› በማለት ጥያቄ ነበር ያነሳሁት፡፡ ይህንን ነገር ልናግዝ እንፈልጋለን አልኳቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ባለው መንገድ ገንዘብ ማሰባሰቡንና ተቀማጩን ስለምንፈልገው ነው፡፡ እናም ብፁዕ አቡነ ጳውሎስን እናንተ አካውንት ከከፈታችሁ፣ እኛ በበዓላት ቀን በየቤተ ክርስቲያኑ ቆመን ሰው ገንዘቡን ሲያስገባ ደረሰኝ እየሰጠን ልንሰበስብ እንችላለን ብለን አግባባን፡፡ እሱን ለመጀመር ሁሉ ተዘጋጅተን ነበር፡፡ 

ሪፖርተር፡- ሐሳቡን ተቀብሉዋችሁ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- አዎ! ሐሳቡ ጥሩ ነው ብለዋል፣ ተፈጻሚ እንዲሆንም ወደ ታች መርተዋል፡፡ ግን በየት በኩል እንጀምር? በየት በኩል እንግባ? እዚያ የሚበላው መዓት ገንዘብ ነው፡፡ እሳቸው በሐሳቡ ተስማምተው ከመሩት በኋላ ወደ ታች ሲወርድ አስፈጻሚ ጠፋ፡፡ ይህ በዚያው ቀረ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሥራ ወደ መስጊድም ለመውሰድ ታስቦ ነበር፡፡ አዲስ ነገር ለማምጣት ነበር፡፡ አሁን ያለበትን ደረጃ አላውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በነገራችን ላይ እስከ ምሽት ሦስት ሰዓት ድረስ በመሥራታችሁ ውጤት አግኝተንበታል ብላችሁ ታስባላችሁ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ለውጡ መጥቷል፡፡ አንዱ የደንበኛ እርካታ ነው፡፡ እንደ ቢራ ፋብሪካዎች ያሉ ተቋማት ሽያጫቸውን ሰብስበው ማታ ያስገባሉ፡፡ ብዙዎች ይጠቀሙበታል፡፡ እኔ አንዳንድ ጊዜ ማታ ላይ እየዞርኩ አያለሁ፡፡ የምሽት ሥራውን የጀመርንባቸው አካባቢዎችም የምሽት ሥራ ሊኖርባቸው እንደሚችሉ የታመነባቸው  ስለነበሩ ብዙዎች ይጠቀምባቸዋል፡፡ ይህም የተቀማጭ ገንዘብ መጠናችን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ጥሩ ስም አግኝተንበታል፡፡ ከደንበኞች ያገኘነውም ምላሽ ቀላል አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- የባንክ ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? ምን ጎደለው? ምን አለው?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ሁሉም እንደሚያውቀው የባንክ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን አንቀሳቃሽ ነው፡፡ ፋይናንስ ከሌለ ምንም ነገር የለም፡፡ አቅም በፈቀደው የሚሠሩት ሥራ ቀላል አይደለም፡፡ ይህ በጎ ነገር ነወ፡፡ ነገር ግን ባንክ ማለት ለእኔ በሌሎች አገልግሎቶች የሚያገኘው ገንዘብ ሳይሆን ትልቁ ነገር የፋይናንስ ተደራሽነት ነው፡፡ ያልተመቻቹ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ እንደ 27 በመቶ ያለው መመርያ ዓይነት ያሉ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ሚና ሲጫወት ማን ነው የሚያገለግለው ነው? እኔ አሁን ንግድ ምክር ቤት ስላለሁ ሳይሆን ነጋዴውን ማሳደግ ነው፡፡ ከታች ጀምሮ የንግድ ኅብረተሰቡን ማሳደግ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ለማሳደግ ይህንን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን እንደምናየው ግን የፋይናንስ ተደራሽነቱ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የሚጮኹትም ለዚህ ነው፡፡ ይህ ነገር ለምን ሆነ ካልክ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጋር የሚሄድ በመሆኑ ነው፡፡ ባንክ ማለት በሕዝብ ገንዘብ የሚሠራ ነው፡፡ መጠንቀቅም ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ትልቁ ነገር የአገልግሎት አሰጣጦች ተመሳሳይነት ነው፡፡ ካፒታሉ ውስን ነው፡፡ አሁን ባለው ደረጃም ቢሆን እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ መሠራት ያለበት ብዙ ነገር አለ፡፡ እዚህ አገር እንደሚታወቀው ገንዘብ ያላቸው ብቻ አይደሉም ወደ ንግድ የሚገቡት፡፡ ቴክኒካዊ ምክር መስጠት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ አንዴ ብድር ሰጥተህ መሸሽ አይደለም፡፡ ከሚከፈለው ደመወዝና ወለድ አኳያ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአትዮጵያ የወደፊት ሁኔታ ሊብራል እየሆነ ነው የሚመጣው፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ትሆናለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁ ነገር የክፍያ ሲስተም ጉዳይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት መግባታቸው የግድ ይሆናል፡፡ ያን ጊዜ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ ከደንበኛ ግንኙነት አኳያ የብድር አሰጣጡ ቀልጣፋ የመሆኑ ነገር ላይ ስለሚያጎድል እዚህ ላይ መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ለፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ መቀላጠፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሠራሮችና አንዳንድ መመርያዎች መቀየር አለባቸው ይባላል፡፡ በዚያ ላይ ምን ሐሳብ አለዎት?

ወ/ሮ መሰንበት፡- በዓለም አቀፍ ያሉ ማዕከላዊ ባንኮች የሚሠሩት ሥራ አለ፡፡ በእኛ አገር ሁኔታም የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ባንክ የሚሠራቸው ሥራ ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲውም መታየት አለበት፡፡ በማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲው ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ሁኔታ ሊያስቀይረን ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም በአጠቃላይ ከንግዱ ጋር ያለው ሁኔታ ከሌሎች ጋር ለመነገድ በሚያስችለን ደረጃ አጠቃላይ ፖሊሲው መቀየር አለበት፡፡ ከገንዘብ እንቅስቃሴው ጋር በተገናኘ ማስተካከያ ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በእርግጥ የሕዝብ ገንዘብ ስለምናንቀሳቅስ የተወሰኑ ፖሊሲዎች አሉ፡፡ ከተወሰነ ፐርሰንት በላይ ከተቀማጭህ ብድር እንድትሰጥ የሚከለክል ነገር አለ፡፡ የሕዝብን ገንዘብ ለመጠበቅ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጥሩ ጥሩ ፖሊሲዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊገቡ የማይችሉ አንዳንድ ሁኔታዎች በራሳችን መሄድ የምንችላቸውና ለእኛ የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ማዕከላዊ ባንክ ቀደም ብዬ ያነሳሁት ነገር እንዳለ ሆኖ፣ መሠረታዊ ሁኔታዎች ላይ አተኩሮ መሥራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ የሕዝቡን ገንዘብ እንቅስቃሴው ላይ ያለውን ነገር ከመቆጣጠር ባለፈ ሌላውን ሥራ ለባንኮች መተው አለበት፡፡ እኔም በነበርኩበት ጊዜ በጣም የሚያስጨንቁ ጥቃቅን ነገሮች ነበሩ፡፡ መቀየር  ያለባቸው መመርያዎች አሉ፡፡ አንዳንዳቹ እኮ ከጃንሆይ ጀምሮ የነበሩ መመርያዎች ናቸው፡፡ ስለዚሀ ከጊዜው ጋር በሚጣጣም ሁኔታ መቀየር ያለባቸው ነገሮች መኖር ይኖርባቸዋል፡፡ አሁን ፖሊሲዎችን ለመከለስ ጥናት እየተደረገ ስለሆነ የምናየው ነው፡፡ ባንኮች ደግሞ በዚያው ልክ አሠራራቸውን መቃኘት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ንግድ ምክር ቤቱና እርስዎ እንዴት ተዋወቃችሁ?

ወ/ሮ መሰንበት-፡- ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር የተዋወቅኩት ከልማት ባንክ ወጥቼ ዓባይ ባንክ ስገባ ነው፡፡ ልማት ባንክ በነበርኩበት ጊዜም ቢሆን በንግድ ሥራ የተሰማሩ ነጋዴዎችን አውቃለሁ፡፡ ዓባይ ባንክ ስመጣ የግል ባንክ ነውና የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳደግ የተለያዩ ድጋፎች እንሰጣለን፡፡ እኔም በግሌ በንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ቢታገዝ የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዴት ሥራቸውን መምራት ይችላሉና በመሳሰሉት ብናግዛቸው ጥሩ ውጤት ማምጣት ይችላሉ፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር እኔም ለማድረግ ጥሬያለሁ፡፡ ወደ ቻምበሩ የመጣሁትም እንዲህ ያለውን ፍላጎቴን የተገነዘቡ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት ብታግዥን በሚል በተለያዩ መንገዶች በቀረበልኝ ጥያቄ ነው፡፡ ማገዝ ጥሩ ነው ብዬ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ቻምበር መግባት ሌላ ነገር የለውም፡፡ መጀመርያ ቻምበር ስመጣ ያለውን ባህል አላውቀውም፡፡ የምርጫ ሒደቱ እንዴት እንደሆነ አላውቀውም፡፡ በኢትዮጵያና  በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤቶች መካከል አለ የሚባል ሽኩቻ ነበር፡፡ በንግድ ምክር ቤቶች ላይ የተጻፉ ብዙ ጋዜጦች አገኘሁ፡፡ የነበረውን ችግር ለማወቅ ብዙ አነበብኩ፡፡ ከባድ ነገር እንደሆነ ያሳያሉ፡፡ ዋና ነገሩን ባላውቀው እንዲህ ያሉ ችግሮች ስለነበሩ ውዝግቡን ማርገብ አለብኝ፡፡ በተፈጥሮዬ መፈተን እወዳለሁ፡፡ ችግር ከሌለ ሕይወት ትርጉም የለውም፡፡ ከዚህ ችግር ተወጥቶ ጥሩ ነገር ላይ ተደረሰ የሚለው ነገር ያስደስታል፡፡ ስለዚህ የቦርድ አባል ሆኜ ገብቼ መሥራቴ ጥሩ ነው አልኩ፡፡ የተጠቆመውን ባላውቅም ተመርጬ የቦርድ አባል ሆንኩ፡፡ የነበረውን ውዝግብ ሴትል ለማርገብ ሞክረናል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን አድርገናል፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ኃላፊነቱን ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ኃላፊነትዎ በመጀመርያዎቹ መቶ ቀናት ምን ያከናውናሉ? ብዙ ችግር ያለበት ነው የሚባል ንግድ ምክር ቤት ነውና ከዚህ አኳያ ምን ላደርግ እችላለሁ ብለው ያምናሉ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- የመጀመርያው ተግባር የሚሆነው በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤቶችና በዘርፍ ምክር ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ማለሳለስ ነው፡፡ በእነዚህ የመቶ ቀናት ሥራዬ በንግድ ምክር ቤቶች መካከል ያለው ግንኙነት ለስላሳ የሚያደርግ ሲስተም መፍጠር ነው፡፡ በቅርቡ እንደታዘብኩት ቦርዱ የሥነ ምግባር መመርያ የለውም፡፡ ይህም ይፈጠራል፡፡ እያንዳንዱ የቦርድ አባል ያለውን ማወቅ አለበት፡፡ መለካት አለበት፡፡ ስክሬታሪየቱ ጠንካራ ነው፡፡ በደንብ ይሠራል፡፡ ስለዚህ የቦርድ አባላቱም በደንብ እንዲሠሩ ሁኔታዎች መመቻቸት አለባቸው፡፡ ለዚህ የሚሆን ሲስተም እዘረጋለሁ፡፡ ሌሎች የከተማ ቻምበሮችን ማገዝና ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በጋራ መሥራት ከቻልን መሻከር አይኖርም፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ለንግድ ኅብረተሰቡ ጠቃሚ መሆኑንና ከመንግሥት ጋር ደግሞ ሕግና ደንቦች ላይ መተማመን መፍጠር ይገባል፡፡ ሌላው የቀድሞ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቶችና አመራሮች አብረውን እንዲሠሩ ማድረግ ትኩረት ሰጥቼ የምሠራበት ጉዳይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በአገር ደረጃ እየተደረገ ካለው ለውጥ ጋር ተያይዞ ሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራር እየመጡ ነው፡፡ ወደ አመራር የሚመጡ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ሴቶች ወደ አመራር መምጣታቸው ምን ያመለክትዎታል?

ወ/ሮ መሰንበት፡- በእኔ ቤተሰብ ውስጥ ያለነው ሰባት ነን፡፡ ከሰባታችን ውስጥ አምስት ወንዶች ሁለታችን ደግሞ ሴቶች ነን፡፡ ከወንድ ጋር ነው የኖርኩት፡፡ በሠፈር ደግሞ ብዙ ጊዜ ከወንዶች ጋር ነበር የምጫወተው፡፡ የሴትና የወንድ የሚባለውን ነገር ብዙ ትኩረት አልሰጠውም፡፡ አንዳንድ ነገሮችን ስታነብ ነው የምታውቀው፡፡ እኛ አገር እንዲያውም ጥሩ ነው፡፡ እኔ በአባቴ ስም ነው የምጠራው፡፡ ሌላው አገር በባሎቻቸው ስም ነው የሚጠሩት፣ ይህ በጣም ይገርመኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ስታየው ለምን የወንድና የሴት የሚባል ነገር ይኖራል? የሴቶችን አኮስሶ የወንዶችን የሚያጎላው ሕግ ከየት እንደመጣ ራሱ ይገርመኛል፡፡ በጋርዮሽ ዘመን ልጆች እኮ አባታቸውን አያውቁም፡፡ ልጆቻቸውን ይዘው የሚያሳድጉት ሴቶች ናቸው፡፡ ለማንኛውም አሁን ሴቷ ልጆቿንና ቤቷ ትይዛለች፡፡ ወንድ ውጭ ወጥቶ እየሠራ ገቢ የሚያመጣ በመሆኑና ገንዘብ ኃይል ስላለው፣ የወንድ የበላይነት ከዚያ የመጣ ሊሆን ይችላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በዓለም ላይ ትልቅ ትርምስ የሚፈጠረው የሴት መሪዎች ብዙ ባለመሆናቸው ነው ብዬ የማስበው፡፡ ወንዶችም የሚያምኑት ጉዳይ ነው፡፡ በእኔ ደረጃ በነበርኩባቸው ቦታዎች አመራር ስሰጥ የማየው ነገር አለ፡፡ የምንከፍለው ደመወዝ ትንሽ ነው፡፡ በተለይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ላሉ ሠራተኞች የሚከፈለው አምስት መቶና ስድስት መቶ ብር ነው፡፡ በዚህ ደመወዝ ስድስትና ሰባት ልጅ ታሳድጋለች፡፡ ይህንን አብቃቅታ ነው ቤቷን የምትመራው፡፡ ወንዱ ያገኛትን ሲሰጥም እሷን ይዛ ቤቷን ትመራለች፡፡ ስለዚህ የቤቷ የቤተሰብ መሪ ሴት ነች፡፡ ከዚህ ነው የሚጀምረው፡፡ ቤት ውስጥ ያለውን ሰላም አረጋግታ ልጆቿን አንተም ተው አንተም ተው ብላና ይዛ እንዳይራቡ ሁሉ ታደርጋለች፡፡ ወንዱን ሳይቀር መስመር የምታስይዝ ሴት ናት፡፡ አሁን እኔ ልዩነት ለመፍጠር አይደለም፡፡ ግን አጠቃላይ ለለውጥ ወይም አንድን ነገር ለመለወጥ በሚደረግ ሒደት ላይ የሴቶች ጉዳይ ከታች የሚነሳ ነው፡፡ ሥራን ለማሳለጥና ሰውን ለመምራት ነው፡፡ በዚህ ላይ ሰዎች በተረጋጋ መንገድ እንዲሄዱ አንድን ሠራተኛ ከሥራው ውጪ  ሕይወቱ ውስጥ ጭምር ገብተህ ማረጋጋት ይኖርብሃል፡፡ ይህንን ሒደት እኔ እጠቀምበታለሁ፡፡ ከሚስቱ ጋር ተጣልቶ ሊመጣ ይችላል፡፡ ከእጮኛው ጋር ሊጋጭ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ስታይ ዞር በል ብለህ አትተወውም፡፡ እንዲህ ሆኖ የመጣ ቀን የሚሠራው ሥራ ውጤት የለውም፡፡ ስለዚህ ሥራ ስትሠራ የሆነ ነገር ሆኖ የመጣውን ሰው ማንበብ አለብህ፡፡ እናት ልጇን ምን ሆነ ዛሬ? ባሏንም ምን ሆንክ? ብላ ታረጋጋለች፡፡ ከዚህ በመነሳት በተለይ የሥራውን ዓለም ለተቀላቀልን እየመሩ ማረጋጋት ትልቅ ነገር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ አቅምና ችሎታ ያላት ሴት አለች፡፡ ነገሮችን ለማገናዘብ በተፈጥሯችን የተሰጠን ነገር አለ፡፡ ከሁሉም ወንዶች የተሻሉም አሉ፡፡ ከሁሉም ሴቶች የተሻሉም አሉ፡፡ ነገር ግን እጅግ የተሻሉ ሴቶች በማይሻሉ ወንዶች ሊተኩ አይገባም፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ እኔ ብዙ የማውቃቸው ሴቶች አሉ፡፡ በጣም ጎበዝ ሴቶች አሉ፡፡ ግን ዕድሉን ባለማግኘት ብዙ ያልወጡ ማለት ነው፡፡ እኔ በሆንኩ ይህንን በሠራሁት የሚሉ ብዙ ሴቶች አሉ፡፡ አሁንም በአገር ደረጃ ይህንን ነገር የማየው ስለተወራ አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ መሪነት በሴት ላይ ያለ ነው፡፡ የሴቶች አመራር ለውጥ ያመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በአገር ደረጃ በአመራር ላይ የተቀመጡትን ሴቶች የመምራት አቅም እንዴት ያዩታል?

ወ/ሮ መሰንበት፡- አሁን የተመረጡትንና ወደ ኃላፊነት የመጡትን ሴቶችን ሳይ ጥሩ ናቸው፡፡ ለውጥ ያመጣሉ ብዬም አምናለሁ፡፡ የመሪነት ጉዳይን ስናነሳ በአንድ ሰው ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ከታች ያሉትን ሴቶችንና ወንዶችን በማስተባበር በእኔ አስተሳሰብ እንዲሄዱ ብላ መሥራት አለባት፡፡ የአመራር አቅጣጫዋ የበለጠ ውጤት እንዲያመጣ መፍጋትና መትጋት ይፈልጋል፡፡ ሌላው ዓለም እንዴት ነው ብሎ ማንበብ ይፈልጋል፡፡ እዚያ ቦታ ላይ የተቀመጠ ሰው መተኛት የለበትም፡፡ እኔ ዓባይ ባንክን ይዤ በአዲስ አሠራር ለመሥራት ስጀምር ጭንቅ ነበር፡፡ የሆነ መልዕክት ልልክ እችላለሁ፡፡ ይኼ ነገር እንዴት ሆነ ልል እችላለሁ፡፡ ጭንቀት የምልህ እሱ ነው፡፡ ሠርቶ የማያውቅ አለ፡፡ እኛ አገር ብዙ የሚሠራ የለም ይባላል፡፡ በአንድ በኩል እውነት ነው፡፡ ስለዚህ መሪዋ ሌሎችንም አስተባብራ ማሠራት አለባት፡፡ ልትታገዝም ይገባል፡፡ ውጤት የማምጣቱ ነገርም በሴቷ ላይ ብቻ መሆን የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤቶች የአመራርነት ዘመንዎ ምን አዲስ ነገር አመጣሁ ብለው ያስባሉ? በዚህ መንገድ ልቀይረው እችላለሁ ብለውስ የሚያስቡት ነገር አለ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- አሁን በዓለምም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ አለ፡፡ በጣም ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ተለይታ ልትቀመጥ አትችልም፡፡ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆኗ ቀላል አይደለም፡፡ እንዲህ ካለው ነገር ስንነሳ ብዙ በሮች ተከፍተዋል፡፡ ስለዚህ ቻምበሩ ላይ ለውጥ ለማምጣት መነሻ የሚደረገው አባላቱ ላይ ነው፡፡ አባላቱ ላይ ያለውን ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው እንጂ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትን በተለየ ሁኔታ ሰብሮ የሚመጣ ነገር አለ ማለት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የለውጡ መነሻ አባላቱ ላይ ያነጣጠረ ነው ሲሉ አባላትን ማብዛት ላይ ነው?

ወ/ሮ መሰንበት፡- አንደኛው አባላት ላይ ያለው ሁኔታ ለምሳሌ ከመንግሥት ጋር በተገናኘ ባሉ ችግሮች በጣም ለውጥ ማምጣት ይኖርብኛል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከንግድ ሥነ ምግባሩ አኳያ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እያንዳንዱ የንግድ ኅብረተሰብ አሁን ካለበት እንዴት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያድግ ይችላል? የሚለውን ነገር ላይ መሥራት ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር ያለውን ችግር የማስተካከል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የራስንም ዕድገት እንዴት ነው ማምጣት የሚቻለው የሚለው ነገር ላይ ለውጥ ለማምጣት እንጥራለን፡፡ ስለዚህ አባላቱ ንግድን የሚያሳልጡበትን ሥርዓትና ያለባቸውን ችግር ዓይቶ መፍትሔ ማበጀት ላይ ጭምር ለመሥራት ነው፡፡ እንዲውም የተፅዕኖ ግምገማ ሁሉ እንሠራለን፡፡ የቻምበሩን አባላት መጨመር ሌላው ተግባር ነው፡፡ አባላትን መጨመር ማለት ንግድን ከማሳለጥ አኳያ ሥነ ምግባር ያለው የተከበረ አባል እንዲኖረን ማድረግ ነው፡፡ የምክር ቤቱ አባል የሆነ ሰው የሚከበርበትን ለውጥ ማምጣት አለብኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ እንዴት?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ለምሳሌ በሌሎች አገሮች የምክር ቤት አባል የሆነ ኩባንያ ሌላው ኅብረተሰብ ወይም ሸማች ስለሚያምነው ከእሱ ኩባንያ ብቻ ይገዛል፡፡ የቻምበር አባል መሆን መልካም አስተዳደር ያለው፣ የቢዝነስ ሥነ ምግባር ያለው፣ በትክክል የሚሠራ ነው ብሎ ስለሚያምን፣ እኔ ከእሱ ብገዛ ጥራቱን የጠበቀ ምርት አገኛለሁ ብሎ ስለሚያምን ከሌላ አይገዛም፡፡ ይህንን መቼ ነው ልናመጣላቸው የምንችለው? የሚለው ጥያቄ መልስ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ግብር ይቀነስ አይቀነስ ብቻ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ምክር ቤቶች አካባቢ ሁሌም የምንሰማው የንግድ ኅብረተሰቡን መብት ለማስጥበቅ እንሠራለን የሚሉ ተመሳሳይ ዲስኩሮችን ነው፡፡ የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው የተበላሸ የንግድ ሥርዓት ያለበት ነው፡፡ የተበለሻሸውን የንግድ ሥርዓት ወደ መስመር ለማምጣት ቻምበሩ ኃላፊነት የለበትም? የንግድ ምክር ቤትስ ድርሻ ምንድነው? ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምርቶችን ለሸማች የሚያቀርቡ ኩባንያዎች እኮ የዚህ ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ለመቅረፍ በእርስዎ የአመራር ዘመን ምን ያደርጋሉ?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ለእኔ የሚታየኝ ነገር ለምን እንዲህ ያለው ነገር ተፈጠረ የሚለው ጉዳይ መጀመርያ መታየት አለበት፡፡ ለምን ይህ ነገር ተፈጠረ? እኔ አንድ ብዙ ጊዜ የማነሳው ነገር አለ፡፡ አራጣ አለ፡፡ አራጣ ሕጋዊ አይደለም፡፡ ሰዎች ለምንድነው እዚያ ውስጥ የገቡት? የሚለውን ስናነሳ የፋይናንስ ተደራሽነት ስለሌለ ነው፡፡ ሌላ መንገድ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ስቶክ ማርኬት ቢኖር ሌላ መንገድ ይኖረን ነበር፣ ግን የለም፡፡ አሁን ለዘመናት እንደምንሰማው በመንግሥትና በንግዱ ኅብረተሰብ መካከል ያለው ችግር ሳይፈታ፣ ሕጋዊ ያልሆነ ነጋዴ እየጨመረ እየመጣ ነው እየተባለ ይወራል፡፡ ይኼ ነገር ሊጠፋ ያልቻለው ዋና ችግሩ ስላልታወቀ ነው፡፡ መጠናት አለበት፡፡ አንድ ንግድ ላይ የተሰማራ ሰው በትክክል ነግዶ የሚገባውን ትርፍ አግኝቶ፣ ግብሩን ከፍሎ ሊቀጥል ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ብለን በማጥናት መጀመርያ ዋናውን ጉዳይ ማወቅ አለብን፡፡ ይህንን አውቀን ሲስተሙን አመቻችተን መሄድ የምንችልበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ሁሉም ያማርራል፡፡ ለምሳሌ እኔ ግብር እየከፈልኩ ሌላው አይከፈልም ይላል፡፡ ሌላው ደግሞ ዕቃ ይሸሽጋል፡፡ ከውጭ ያልተፈቀደ ዕቃ ገባ፣ ወዘተ. ይባላል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው ነገር ለምን ተፈጠረ የሚለውን ነገር መታወቅ አለበት፡፡ አንዳንዴ በተፈጥሮው ስግብግብ ስለሆነ ነው ይልሃል፡፡ ይኼ ፕሮፌሽናል አይደለም፡፡ እኔ እያልኩ ያለሁት ይህን ያህል ሰው አሠለጠንን የሚለውን አይደለም የምንፈልገው፡፡ እኛ የምንፈልገው ይኼንን በማድረግ ምን አመጣን ነው፡፡ ውጤቱ ምንድነው? በሚል ጭምር ነው፡፡ እኛ ደግሞ ለውጥ ልናመጣ የምንችለው ብቻችንን አይደለም፡፡ ከመንግሥት ጋር ሆነን ነው፡፡ በትንሹ ልንገርህና ግብር በትክክል የሚከፍለውም ግብሩን ለመክፈል ብዙ ጊዜ ይወስድበታል፡፡ ከዚህ አንፃር የማስበው ከመንግሥት ጋር በግሉ ሴክተር ቅርፅ አገልግሎቱን መስጠት አለብን ብዬ ነው፡፡ አሁንም በትክክል አገልግሎት ለማግኘት ችግር አለ እኮ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ሥነ ምግባር የንግድ ባህልም እየጠፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የነጋዴው የትርፍ ህዳግ በዘፈቀደ የሚሰላ ነው፡፡ ሥነ ምግባር እንዲቀድም መሠራት አልነበረበትም?

ወ/ሮ መሰንበት፡- መሠራት አለበት፡፡ ቅድም ያልኩህ ሥልጠናና የመሳሰሉት ነገሮች ይሰጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለዓመታት እኮ ሥልጠና ተሰጠ ይባላል፡፡ ለውጥ ግን የለውም እየተባለ እኮ ነው?

ወ/ሮ መሰንበት፡- ልክ ነህ፡፡ ለውጥ ያልመጣበትን ምክንያት እያየን አለመሥራታችን ነው፡፡ እንዴት ነው ለውጥ እየመጣ ነው ወይ? የሚለውን ስናይ በተለመደው መንገድ ነው ሥልጠናውን እየሰጠን ያለነው፡፡ አሁን ሥልጠናውን በምን ዓይነት መንገድ ነው የምንሰጠው? የሚለውን ነገር ስታይ የንግድ ኅብረተሰቡን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቡንም ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሸማች ከማን ጋር ነው መሥራት ያለበት? የሚለውን ማወቅ አለበት፡፡ በሌላው ዓለም ብዙ እየተሠራበት ነው፡፡ አንድ መጽሐፍ ላይ እንደየሁኔታው ‹‹አይ ፈርስት›› የሚለው ቀርቶ ‹‹ዊ ፈርስት›› ሆኗል ይላል፡፡ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ተብሎ ካልተሠራና ማኅበራዊ ኃላፊነትን ካልተወጣ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ በቢዝነስ ሥነ ምግባር ላይ ያልተሠራ ሊኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ እኔ አካባቢ ያለ ሱቅ ሁለት ብር የሚሸጥልኝ ዕቃ ሌላ ሱቅ አንድ ብር እገዛለሁ፡፡ የመጀመርያው ሱቅ ሁለተኛ አልሄድም፡፡ እንዲህ ማድረግ ይቻላል፡፡ አሁን እኮ ሕዝቡ ተቀብሎታል፡፡ የተለየ እዚህ አገር ያልተደረገው ነገር ከማን ጋ ነው የምገዛው የሚለው መታወቅ አለበት፡፡ አሁን እንዲህ ያለ ነገር ሲደረግ ጠቁሙ ይባላል፡፡ ግን መሆን ያለበት ኅብረተሰቡን ማስተማር ነው፡፡ ያኔ መስመር ይይዛል፡፡ ስለዚህ የቢዝነስን ሥነ ምግባር  በተመለከተ የምናያቸው ችግሮች ሁሉ፣ ኅብረተሰቡ ዝም ብሎ በቃ እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ እያለ የሚሄድበት ሁኔታ ስላለ ነውና ኅብረተሰቡ አንድነት ቢፈጥር በጣም ለውጥ ይመጣል፡፡ በእኛ በኩል የንግዱ ኅብረተሰብ ደግሞ ወደዚህ እየመጣ ነው፡፡  የንግድ ምክር ቤት አባል የሚለው ዓርማ ይቀመጥ፡፡ ዓርማው ያለበት በትክክል የሚሠራ ስለሆነ ሸማቹ ከዚያ ነው መግዛት ያለበት፡፡ ይህ ክብር ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ማድረግ ከቻልን ችግሩ እየጠፋ ይሄዳል እንጂ፣ እያሰርክና እየደበደብክ የሚለውን ነገር አይሠራም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

 የክልሎች ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በመከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል እንዲካተቱ ጥናት እየተደረገ ነው

የክልሎችን ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በአገር መከላከያ ሠራዊት ተጠባባቂ ኃይል...

ኢትዮጵያ በትክክለኛ ግንዛቤ ላይ የተመሠረተ ሕገ መንግሥት ማበጀት እንደሚገባት ማሳሰቢያ ተሰጠ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንስቶ ለተለያዩ ጥያቄዎችና ሐሳቦች...