Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአገልግሎት ሰንኮፎች 

በፖለቲካውም በኢኮኖሚውም ዙሪያ መፈታት ያለባቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ የችግሮቹ ምንጮች ቢለያዩም ሕግና ሥርዓት እንዲከበር የሚደረጉ ጥረቶች በግልጽና በተሰወረ ምክንያት ሲደነቃቀፉ ይታያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ወደተሻለ ደረጃ ለማራመድ ጥረቶች የመኖራቸውን ያህል ጥቅማቸውን በማሰብ ከለውጡ በተፃራሪ ሊቆሙ የሚችሉ አካላት እንደሚኖሩ አይጠረጠርም፡፡

ለማንኛውም ለውጥ ያስፈልገናል፡፡ ለዓመታት እየተጠራቀመ ሲንከባለል የመጣውን ችግር ነቅሎ ለመጣል ብሎም ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲጓዝ ለማድረግ ብርቱ ጥረት መጠየቁም ግድ ነው፡፡

በየአካባቢው ያለውን ችግር በአንዴ ፈር ለማስያዝ መሞከሩ ከባድ ቢሆንም፣ በቀላሉ ሊስተካከሉ የሚችሉ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ሕግና ደንብን በአግባቡ በመተግበር ብቻ ሊስተካከሉ የሚችሉ የአገልግሎት አሰጣጦች እንዳሉ ይታመናል፡፡ አገልግሎት ተቀባዩን ሲያንገሸግሹ የከረሙትን ችግሮች ማረም የሚችልባቸውን አሠራሮች በመተግበር፣ በንፅህና ሊሠራ የሚችል ባለሙያ በመደብ ሊፈጸሙ የሚችሉ ተግባራት አሉ፡፡

ይህ ይባል እንጂ በመልካም አስተዳደር ያልተቃኙ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና በማሳደር እንቅፋት ሆነዋል የተባሉ የመንግሥት ተቋማት ግን ዛሬም ሥር ነቀል ለውጥ ሲደረግባቸው አይታዩም፡፡

ዛሬም ሙስና የተንሰራፉባቸው፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸው ደንበኛ ተኮር ከመሆን ይልቅ ሳንቲም ተኮር የሆኑ ተቋማትን እናያለን፡፡ በዚህም ሳቢያ የሕዝብ እሮሮ ሊቆም አልቻለም፡፡

ሕግና ሕገወጥነትን በማቀላቀል ከሚታሙና ለሙስና ተጋላጭ ከሚባሉ ተቋማት ውስጥ የቀድው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣኑ የአሁኑ አዲሱ ሙሽራ ተቋም የገቢዎች ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥ ቁልፍ ሥራ የሚሠራው ይህ ተቋም፣ ከብልሹነት የፀዳበት ጊዜን ለመጥቀስ ይቸግራል፡፡

የተሸከመው የኃላፊነት ብዛት ከባድ ቢሆንም፣ ሲታማበት የኖረውና አሁንም ገና ያልተላቀቀው የአሠራር ክፍተት እንዲሁ በቸልታ የሚታይ አይደለም፡፡ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቱም መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ያህል ገቢ መሰብሰብ አለመቻሉን ከሰሞኑ በሚኒስቴሩ ይፋ የተደረገው መረጃ ያስረዳናል፡፡ ከዚህ ተቋም ተገንጥሎ የወጣው የጉምሩክ ኮሚሽንም ጣት ይቀሰርበታል፡፡  

ከጉምሩክ አሠራር አኳያ እጅግ ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያለው ዘርፍ ነው፡፡ የመንግሥትና የግል ተቋማት ከዚህ በጋራ አብረውት ይሠራሉ፡፡ በተቋሙ ላይ የሚነሳው አቤቱታ ለዘመናት የዘለቀ ከመሆኑ አንፃር ብዛቱም አይጣል ነው፡፡ በዚህ ተቋም ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች ግን ከችግሮቹ አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ውጤት አላመጡም፡፡

ሌለውን ነገር ሁሉ ትተን በወደብና በደረቅ ወደብ አካባቢ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ፉርሽ ነበሩ፡፡ እንደ ምሳሌ መጥቀስ የምንችለው በጂቡቲ ወደብ ብሎም በሞጆና በሌሎችም ደረቅ ወደቦች የተከማቹ ንብረቶችን በአግባቡና በሕጉ መሠረት ወቅቱን ጠብቆ በማስነሳት ረገድ ችግር በመኖሩ ኢትዮጵያ የምታጣውን ጥቅም ማሰብ ይችላል፡፡ ዕቃዎች ያላግባብ ለአንድም ቀን ቢሆን በወደቦች ላይ መከማቸት እዚህች ደሃ አገር ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ መገንዘብ የሚችሉ ተሿሚዎች አሉን? ነበሩን ወይ? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡

ከሰሞኑም በደረቅ ወደብ የተከማቹ ንብረቶች እየፈጠሩ ያለውን ችግር እንደ ከዚህ  ቀደሙ ሁሉ ሰምተናል፡፡ ያላግባብ ኮንቴይነሮች መከማቸታቸው ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈጸሙ ያልተገቡ ተግባራትም አፍጥጠው ይታያሉ፡፡ ይህ ችግር ግን ዛሬ የተከሰተ ሳይሆን እንደተከማቹት ኮንቴይነሮች ለዓመታት ተከማችቶ የቆየ ለመፍትሔውም ከልብ ያልተሠራበት እጅግ አደገኛ ጉዳይ እየሆነ በመምጣቱ በዚህ አካባቢ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልግ መሆኑን ነው፡፡

‹‹በወደቦች ንብረቶች አለመነሳታቸው ችግር እየፈጠረ ነው›› የሚለውን የቆየ ዜና አሁንም ደግመን ብንሰማ የማይቀንቀንም ዘላለም ስለችግር እየተወራ ለመፍትሔ የሚሆን መላ በማጣታችን ብቻ ሳይሆን፣ አስፈጻሚ አካላቱ በእጃቸው ያለውን ሕግ የማስከበር ሥልጣን መተግበር አለመቻላቸው ነው፡፡

ይህ ችግር በግልጽ የመታወቁን ያህል ለምን መፍትሔ አልተበጀለትም ካልን በዚህ አካባቢ ያለው ብልሹ አሠራር ሥር የሰደደ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል፡፡

ከዚህም የከፋ የሚያደርገው አንዳንድ ወደብ የደረሱት ንብረቶች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር ደግሞ የገቢ ንግድ ሕጋችን ክፍተት ስላለበት የተፈጠረ ነው? ወይስ ሌላ? እነዚህ በአገር በመከራ በቃረመችው የውጭ ምንዛሪ የገባውን ዕቃ ለማንሳት አልቻሉም የሚባሉት ደግሞ የግል ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት ጭምር መሆናቸው ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ዕቃ አምጥተው ወደብ ያከማቹ ተቋማት ለምን እንደተነሱ ሲጠየቁ ከሚሰጡ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ዕቃውን ለማንሳት ተቋማቱ የፋይናንስ እጥረት ስለሚገጥማቸው ነው የሚል ነው፡፡ ይህ ምክንያት ውኃ የሚያነሳ አይደለም፡፡

ምክንያቱም ወደብ ከደረሰ በኋላ ምርቱን በትራንስፖርት ከማጓጓዙ ከሚመጣበት አገር ምርትን ገዝቶ ወደ አገር ማስገባት እጅግ ቀላሉን ነገር ነው፡፡ በተለይ ሰሞኑን እንደሰማነው አንሺ ጠፋላቸው ከተባሉ ምርቶች ውስጥ የምግብ ዘይት ተጠቅሷል፡፡ ይህንን ባለማሠራጨቱ በገበያ ውስጥ የሚፈጠረው እጥረት አንዱ ነው፡፡ ይህንን ንብረት ማቆየት የተፈለገው ገበያ ውስጥ ችግር ለመፍጠርስ ሆነ ተብሎ ታስቦ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ንብረት በአስቸኳይ መነሳት እንደሚኖርበት ለመረዳት የነበረባቸው የጉምሩክና የደረቅ ወደቡ አስተዳዳሪዎች ያላቸው ሥልጣን ተጠቅመው ዕርምጃ አለመወሰዳቸው ነገሩን የበለጠ አነጋጋሪ ያደርገዋል፡፡

አሁንም ለመፍትሔው ያደርሳሉ የተባሉ ዕርምጃዎችን ማመን የምንችለው ቢያንስ እስካሁን ባለው ግልጽ ዕርምጃ ሲወስድ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ አዳዲስ ድንጋጌዎችን አውጥቶ ዕርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አሠራሩን ያደረጉት ጥረት መልካም ቢሆንም አሠራሩን ለማሻሻል ግን እንሠራለን በሚል ብቻ መታለፍ የለበትም፡፡ አፋጣኝ ዕርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት