Tuesday, October 3, 2023

ፓርላማው ከፓርቲ ዲሲፕሊን ልጓም ዘንድሮ ይፈታ ይሆን?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተለይ ባለፋት ሁለት የምርጫ ዘመኖች ሙሉ በሙሉ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ቁጥጥር ሥር ከወደቀ በኃላ የሐሳብ ፍጭትም፣ የሐሳብ ብዝኃነትም የማይስተዋልበት ነገር ግን የአገሪቱ የመጨረሻ ከፍተኛ የሥልጣን አካልነቱን እንደያዘ ዘልቋል።

በዚህ ምክንያትም በሥራ አስፈጻሚው መንግሥትና መንግሥትን በሚቆጣጠረው ፓርላማ መካከል ሊኖር የሚገባው የሥልጣን ልዩነትና ከፍፍል፣ ገጽታው ምን እንደሚመስል ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል።

የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በፓርላሜንታዊ የመንግሥት ሥርዓት በመንግሥትና በፓርላማ መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊኖር እንደማይችል፣ ምክንያቱ ደግሞ የሁለቱም ተቋማት የመወሰን ኃይል የሚመነጨው በፓርላማው አብላጫ ወንበሮች በያዘ ፓርቲ ነው የሚል አመክንዮ ያቀርባሉ።

ሁለቱም የፓርቲያቸውን ፖሊሲ ለማስፈጸም የተሰየሙ በመሆናቸው፣ በፓርቲ ተወስኖ የሚወርደውን ተቀብሎ የማስፈጸም ፖለቲካዊ ግዴታ እንዳለባቸው ይከራከራሉ። ፓርላማው እንዲህ እንዳሁኑ በኢሕአዴግ ሙሉ ቁጥጥር ውስጥ ባይወድቅ እንኳን በፓርላማ ውስጥ ለይስሙላ የሚደረግ ንትርክ ይኖራል እንጂ፣ ኢሕአዴግ አብላጫ ድምፅ እስከያዘ ድረስ በውሳኔ ላይ የሚለወጥ ነገር እንደማይኖር የገዥው ፓርቲ አመራሮች ይከራከራሉ።

ይኼንን መከራከሪያ በይፋ ከሚያቀርቡት የኢሕአዴግ አመራሮች መካከል በፓርላማው የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ በዋናነት በተደጋጋሚ በማስተጋባት ተጠቃሽ ናቸው። ይሁን እንጂ ከፖሊሲ ባሻገር የመንግሥትን አፈጻጸም በመከታተልና በመቆጣጠር ረገድ የፓርላማ አባላት ከፓርቲ ማዕከላዊነት ነፃ ሆነው፣ በሕግ መሠረት የፈለጋቸውን ማድረግና መወሰን እንደሚችሉ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወቃል።

ከላይ የተገለጸው ፖለቲካዊ ትንታኔ በርካቶች የሚስማሙበት ቢሆንም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጎለበተባቸው ፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች የሚተገበር መሆኑን ባለሙያዎች በተቃራኒው ይጠቅሳሉ።

በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 54(4) ላይ፣ “የምክር ቤቱ አባላት የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው። ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ብቻ ይሆናል፤” ከሚለው ግልጽ ድንጋጌ ጋር የሚጋጭ መሆኑን የሚጠቁሙ ባለሙያዎች፣ መከበር ያለበት የፓርቲ ዲሲፕሊን ነው ወይስ ሕገ መንግሥቱ ሲሉ ክርክራቸውን በጥያቄ ያነሳሉ።

በማከልም በኢትዮጵያ ሁኔታ የመንግሥት የሥራ አፈጻጸም መዛነፍ ከፖሊሲዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ፣ የፓርላማ አባላት በመንግሥት የሥራ አፈጻጸም ላይ የሚያነሷቸው ህፀፆች ፖሊሲዎችን ወደ መተቸት ያደርሳቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ከፓርቲ ዲሲፕሊን እንደ ማፈንገጥ ስለሚወሰድባቸው ዝምታን እንዲመርጡ እያስገደዳቸው መሆኑን ያስረዳሉ።

ይህ ሁኔታም ፓርላማው የአገሪቱ ከፍተኛ ሥልጣን ሆኖ የሚገባውን ክብር ከሕዝቡ እንዳያገኝ፣ ይልቁንም መቀለጃና መዘባበቻ እንዳደረገው በመጥቀስ አማካይ የሆነ መፍትሔ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ።

በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የተቀረቀሩት የኢሕአዴግ ፓርላማ አባላት ከፓርቲ ዲሲፕሊን ልጓም በመውጣት አልፎ አልፎ በሚያሳዩት መንግሥትን በተገቢው መንገድ የመቆጣጠርና ሕግ የማውጣት ተግባር፣ “ፓርላማው ጥርስ አወጣ” የሚል ስያሜ ማኅበረሰቡ ቸሯቸው የሚያውቅ ቢሆንም ተመልሰው በዲሲፕሊን ልጓም መሸበባቸውን ይቀጥላሉ።

የምርጫ ዘመኑን በ2012 ዓ.ም. የሚያጠናቅቀው በኢሕአዴግና በአጋሮቹ መቶ በመቶ የተያዘው አምስተኛ የምርጫ ዘመን ፓርላማ፣ ሰሞኑን የተስተዋሉበት ባህሪያትም ከማኅበረሰቡ አድናቆትን አስገኝተውለታል።

መንግሥት ከምክር ቤት እጁን ያስወጣ?

የ2011 ዓ.ም. የሥራ ዘመኑን በመስከረም ወር ማገባደጃ የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥትን አዲስ የካቢኔ አደረጃጀት አፅድቆ፣ ከዚህ ጋር የሚስማማ አደረጃጀት በምክር ቤቱ ለመፍጠር ማክሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ተሰብስቦ ነበር።

የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያ በራሱ በምክር ቤቱ ወይም ምክር ቤቱ በሚቀጥራቸው ባለሙያዎች ተዘጋጅቶ በአፈ ጉባዔው አማካኝነት የሚቀርብ መሆኑን፣ የምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ይደነግጋል። በዚህ መሠረት የተዘጋጀውን የአደረጃጀት ማሻሻያም አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

አፈ ጉባዔው ያቀረቡት ይህ የውሳኔ ሐሳብ በሥራ ላይ የነበሩት 21 ቋሚ ኮሚቴዎችን እንደገና መልሶ በማደራጀት፣ ቁጥራቸው ወደ አሥር ዝቅ እንዲል የሚያደርግ ነው።

መንግሥት ለሚያከናውነው ሥራ የላቀ ውጤታማነትን ለማረጋገጥና ምክር ቤቱ ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን በተሟላ መንገድ መወጣት እንዲችል፣ ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በቅርቡ ለምክር ቤቱ ያፀደቀውን የአደረጃጀት ክለሳ ተከትሎ የቋሚ ኮሚቴዎቹ አደረጃጀትና ብዛትም ሰብሰብ ብሎ፣ የሰው ኃይልና ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ታስቦ መዘጋጀቱን አፈ ጉባዔው ገልጸዋል።

የቀረበው የአደረጃጀት ማሻሻያ የሚከተሉትን አሥር ቋሚ ኮሚቴዎች ያካተተ ነው። እነዚህም የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሴቶች፣ የወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የግብርና፣ አርብቶ አደርና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የገቢዎች፣ የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው።

በቀረበው የአደረጃጀት ማሻሻያ መሠረትም 21 የነበሩት ቋሚ ኮሚቴዎች ወደ አሥር ዝቅ እንዲሉ፣ የምክር ቤቱን ውሳኔ በመጠየቅ አደረጃጀቱን ይፋ አድርገዋል።

ነገር ግን ከተሾሙ አንድ ወር እንኳን ያልሞላቸው አፈ ጉባዔ ታገሰ የመጀመርያው ምናልባትም ያልጠበቁት ሙግት ገጥሟቸዋል። በዚህ አጀንዳ ላይ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ የፈጀ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ የመናገር ዕድል ካገኙ 20 የሚደርሱ አባላት ከሞላ ጎደል ሁሉም የቀረበውን የቋሚ ኮሚቴ አደረጃጀት በመቃወም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ የቋሚ ኮሚቴዎቹ አደረጃጀት እንዲሻሻል ያስፈለገበትን አመክንዮ የማያሳይ፣ የምክር ቤቱ አባላት በጉዳዩ ላይ አንዳቸውም ምክረ ሐሳባቸውን ሳይጠየቁ የተሰናዳ እንደሆነና በጥናት ላይ ያልተመሠረተ በመሆኑ፣ በድጋሚ ጊዜ ተሰጥቶት በጥልቀት መታየት እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡት አብዛኞቹ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። ማሻሻያውን ማን እንዳሰናዳው እንደማይታወቅና ከላይ ወርዶ በምክር ቤቱ ላይ ለመጫን የተፈለገ እንደሚመስላቸውም ተናግረዋል።

ማሻሻያው እስከ ቀረበበት ቀን ድረስ የባህል፣ ቱሪዝምና የመገናኛ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት መስፍን ቸርነት (አምባሳደር)፣ ጠንካራ የተቃውሞ አስተያየት ከሰጡት የምክር ቤት አባላት መካካል አንዱ ናቸው።

‹‹አንድ እስከ ዛሬ መናገር ያልቻልነውና አሁን ግን ልንናገረው የሚገባው ጉዳይ፣ ይህ ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት የሥራ አስፈጻሚው መንግሥት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለበት ነው፤›› ብለዋል።

የቀረበው የኮሚቴዎች አደረጃጀት ማሻሻያ ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ በራሱ አደረጃጀት ላይ ያካሄደው ማሻሻያ ቅጅ እንጂ፣ ምክር ቤቱ በራሱ መንገድ በጥናት ላይ ተመሥርቶ በሚመቸው መንገድ የተሰናዳ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለቁጥጥር በማይመች መንገድ በርካታ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችን አጭቆ በአንድ ቋሚ ኮሚቴ ክትትል ውስጥ እንዲገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ተችተዋል። አስፈጻሚው አደረጃጀቱን ስላሻሻለ ምክር ቤቱ የግድ የአደረጃጀት ማሻሻያ ማድረግ አለበት ማለት እንዳልሆነም አስረድተዋል።

ሌሎች አባላት በበኩላቸው የምክር ቤቱ ኮሚቴዎችን የሚያግዙ ድጋፍ ሰጪ የባለሙያዎች ቡድን ባልተደራጀበት አንድ ቋሚ ኮሚቴ የማይዛመዱ፣ እንዲሁም በሥራ ኃላፊነት የሚጣረስ ባህሪ ያላቸውን አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች እንዲከታተል ለማድረግ መሞከር፣ ምክር ቤቱ መንግሥትን የመከታተልና የመቆጣጠር ተግባሩ እንዲሰናከል መፍቀድ መሆኑን በመጥቀስ ጊዜ ተወስዶ እንዲታይ ጠይቀዋል። የአደረጃጀት ማሻሻያውን ማነው ያሰናዳው? ከላይ ከአስፈጻሚው የመጣ ከሆነ አስፈጻሚው መቼ ነው? ከዚህ ምክር ቤት እጁን የሚያወጣው? ሲሉም ጠይቀዋል።

አፈ ጉባዔ ታገሰ በሰጡት ምላሽ የአደረጃጀት ማሻሻያው ባለፈው ክረምት በተደረገ ጥናት ላይ ተመሥርቶ መሰናዳቱን ጠቁመዋል። የቋሚ ኮሚቴዎቹ ብዛት ወደ አሥር ዝቅ እንዲል ቢደረግም፣ በእያንዳንዱ ቋሚ ኮሚቴ ሥር ከሁለት እስከ አራት ንዑስ ኮሚቴዎች እንደሚደራጁ በመግለጽ፣ ለአንድ ቋሚ ኮሚቴ ታጭቆ የተሰጠ የሚመስለው የክትትልና ቁጥጥር ኃላፊነት፣ ለየንዑስ ኮሚቴዎቹ እንዳይጣረስ ተደርጎ ሲበተን ለሥራ የሚመች መሆኑን አብራርተዋል።

የአደረጃጀት ማሻሻያው ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ በኃላ የማይመቹ ሁኔታዎችን እያዩ ማስተካከል እንደሚቻልም ገልጸዋል።

መንግሥት የመሠረተው ገዥ ፓርቲ በፖሊሲዎችና በስትራቴጂዎች ዙሪያ የወሰነውን በምክር ቤቱ የገዥው ፓርቲ አባላት መቀበል እንዳለባቸው አሠራሩ የትም አገር ያለ እንደሆነ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ መንግሥት የመመሥረት ወንበር ሳይኖራቸው ቢገቡም፣ ተመሳሳይ ሁኔታን ተወካዮቻቸው እንዲከተሉ ማድረጋቸው የማይቀር መሆኑን አስረድተዋል።

 ‹‹ከዚህ በመለስ ግን ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት በዚህ ምክር ቤት የክትትልና የቁጥጥር ተግባር እንደ ከዚህ ቀደሙ እንዲገባ አንፈቅድም፣ ይህ ሙሉ እምነቴ ነው በጋራ እንወጣዋለን፤›› ብለዋል።

የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ኮሚቴዎችን ለማደራጀት ብቻ እንደሆነ የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፣ የቀረቡ ሌሎች ጉዳዮች በቅርቡ በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ላይ ማሻሻያ የሚደረግ በመሆኑ በአጭር ጊዜ እንደሚመለስ ተናግረዋል።

ከዚህ በመነሳትም የቀረበውን ማሻሻያ ለማፅደቅ ድምፅ እንዲሰጥ ላቀረቡት ጥያቄ የአዎንታ ምላሽ አግኝተው ድምፅ ተሰጥቷል።

የድምፅ ውጤቱ የሚገልጸው ለሁለት ሰዓታት ሲሞግቱ የነበሩት የምክር ቤቱን አባላት ሳይሆን፣ በድጋሚ በፓርቲ ዲሲፕሊን ልጓም ከመሸበብ የማያመልጡ መሆናቸውን ነው። በተሰጠው ድምፅም አደረጃጀቱ በሁለት ተቃውሞ፣ በስድስት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

የምክር ቤቱ አባላት በፓርቲ ማዕከላዊነት የዲስፕሊን መርህ ተሸንፈው አደረጃጀቱን ከተቀበሉ በኃላ እንደ አዲስ የተደራጁትን አሥር ቋሚ ኮሚቴዎች የሚሰበስቡ ሊቃነ መናብርት፣ የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ እንዲሁም አባላትን ለመመደብ አፈ ጉባዔው ዕጩዎችን ሲያቀርቡ ደግሞ፣ ከቀድሞው የገዘፈ ተቃውሞ አሰምተዋል።

ፓርላማው ጥርስ የለውም እያለ ማኅበረሰቡ የሚተቸው ከሥራ አስፈጻሚው በውጤት አልባነት የተነሱ ኃላፊዎች ወደ ምክር ቤቱ ተልከው መሸሸጊያ እንዲያገኙ ሥራ አስፈጻሚው ተፅዕኖ ስለሚያደርግ መሆኑን በመጥቀስ፣ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸውን አዳዲስ አመራሮች ብቻ እንደሚቀበሉ በመግለጽ ተቃውመዋል። በተለይም የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የታጩት በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አማኑኤል አብርሃም፣ እንዲሁም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመሩ የታጩት የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ከምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

 በተለይ በአቶ አማኑኤል አብርሃም ላይ የምክር ቤቱ አባላት ከፍተኛ ትችት ያቀረቡ ሲሆን፣ ቋሚ ኮሚቴውን ለመምራት የትምህርት ዝግጅትም ሆነ ያላቸው ልምድና ዕውቀት በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ ባሉበት ወቅትም ምክር ቤቱ ጠንካራ ሆኖ እንዳይወጣ ከዳረጉት አመራሮች መካከል ናቸው ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡ አቶ ሞቱማ መቃሳ የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው አገልግለው ሲያበቁ፣ ተመልሰው ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራር ሆነው መመደባቸው፣ ምክር ቤቱ ቦታ ማፈላለጊያ እንደሆነ የሚያስመስል ነው የሚል ቅሬታ ከምክር ቤት አባላት ተነስቷል።

ምክር ቤቱ ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ መውጣት እንዳለበትና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል፣ በተለይም የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል መንግሥት በቅርቡ የወሰደውን ዕርምጃ የሚፃረር የሕግ፣ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴን እንዲመራ የተመደበው አመራር አግባብነት እንደሌለው የምክር ቤቱ አባላት አበክረው ተቃውመዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹ምክር ቤቱ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው እየተባለ በተደጋጋሚ መተቸት የለበትም፣ ለወከለን ሕዝብ ተገቢውን አገልግሎት ልንሰጥ ይገባል፣ ውሳኔዎችን ተቀብለን ማፅደቅ ብቻ ሳይሆን ተገቢነት የሌላቸው ውሳኔዎች ለምክር ቤቱ ሲቀርቡ ውድቅ ማድረግ መቻል አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ የአመራርና የአባላት ምደባ እንደገና ጥልቅ ውይይት ተደርጎበት መቅረብ እንዳለበት፣ ብቃት ያለው ሰው በተገቢው ቦታ ላይ በአመራርነት ሊቀመጥ እንደሚገባ ምክር ቤቱ በቀጣይ መወሰን አለበት ተብሏል፡፡

ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ተቃውሞዎችን በተመለከተ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በሰጡት ማብራሪያ፣ የኮሚቴዎቹ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የቀረቡት አባላት በኢሕአዴግ ውይይት የተላለፉ ውሳኔዎችንና የተገኙ ግብዓቶችን መሠረት በማድረግ እንደሆነ በመግለጽ ቢያስረዱም፣ በፓርቲ ዲሲፕሊን ለመጠርነፍ በድጋሚ ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።

በመሆኑም የእያንዳንዱን የቋሚ ኮሚቴ አመራርና አባላት ምደባን በተናጠል በማየት ለሌላ ቀን ሳይተላለፍ ይወሰን ወይም እንደገና ጥልቅ ውይይት ተደርጎበትና በአፅንኦት ታይቶ በሌላ ጊዜ እንዲቀርብ የሚሉ ሁለት አማራጮችን አቅርበው፣ ሁለተኛው አማራጭ አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲያድር ተወስኖ ተበትኖ ነበር።

 የማክሰኞው ስብሰባ ያለ ስምምነት ከተበተነ በኃላ የምክር ቤቱ አባላት በየብሔራዊ ድርጅቶቻቸው ተሰብስበው በመሞከር፣ ያደረውን አጀንዳ ለመጨረስ ዓርብ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ልዩ ስብሰባ አካሂደዋል።

 ባለፈው ስብሰባ ከፍተኛ ትችት የደረሰባቸው አቶ አማኑኤል ከዕጩነታቸው ራሳቸውን በማግለል እንዲነሱ በመጠየቃቸው ወ/ሮ ፎዚያ አሚን የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዕጩ እንዲሆኑ ተተክተው መቅረባቸውን አፈ ጉባዔው ካስተዋወቁ በኃላ፣ በእያንዳንዱ ዕጩ ወይስ በአጠቃላይ በቀረቡት አሥር ዕጩዎች ላይ በተመለከተ ድሞፅ ቢሰጥ ይሻላል የሚሉ ሁለት አማራጮችን አቅርበዋል። ከአቶ ሞቱማ መቃሳና ከሌሎች ጥቂት የምክር ቤቱ አባላት በስተቀር፣ አብዛኞቹ በእያንዳንዱ ዕጩ ላይ ድምፅ መሰጠት አለበት በማለታቸው አፈ ጉባዔው ይኼንኑ አማራጭ ተከትለዋል።

በተሰጠው ድምፅም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር እንዲሆኑ የታጩት አቶ ሞቱማ መቃሳ 109 ድጋፍ ቢያገኙም፣ በ152 ተቃውሞና በ33 የተዓቅቦ ድምፅ ውድቅ ተደርገዋል።

የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር እንዲሆኑ በዕጩነት የቀረቡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አፅበሃ አረጋዊ 102 የድጋፍ ድምፅ ቢያገኙም፣ በ157 ተቃውሞና በ25 ድምፀ ተአቅቦ ሹመቱን ሳያገኙ ውድቅ ተደርገዋል።

ለተቀሩት ስምንት ቋሚ ኮሚቴዎች ከቀረቡት ዕጩዎች በርካቶቹ በሙሉ ድምፅ ሹመታቸው የፀደቀ ሲሆን፣ ሁለት ዕጩዎች በአብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል።

ሹመታቸው ውድቅ በሆነው ሁለት ዕጩዎች ምትክ ሌሎች ዕጩዎች በቀጣዩ ሳምንት እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ከቀደመው ልምድ በመነሳት የፓርላማ አባላቱ ሰሞኑን ያሳዩት ለየት ያለ እንቅስቃሴ ዘላቂነቱ አጠራጣሪ ቢመስልም፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፓርላማ አባላት የመንግሥት ተጠሪ ነን በሚል ምክር ቤቱን ተፅዕኖ ሥር የከተቱ የቀድሞ አመራሮች እየተወገዱ በመሆኑ፣ ዘላቂነት እንደሚኖረው ከፍተኛ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -