የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት ረቡዕ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. በሚያካሂደው ጉባዔው፣ ላለፋት ዘጠኝ ዓመታት በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ማግሥት በራሳቸው አነሳሽነት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት፣ የሁለቱ አገሮችን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ወዳጅነት ዳግም ከመሠረቱ በኋላ፣ ለተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ የጣለውን ማዕቀብ እንዲያነሳ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ኤርትራ ድንበሬን በኃይል በያዘችበት ሁኔታ ማዕቀቡ መነሳት እንደሌለበት በመግለጽ ጂቡቲ በወቅቱ ተቃውሞዋን ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ አደራዳሪነት በኤርትራና በጂቡቲ መካከል የተፈጠረው መቃቃር እንዲፈታና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ዳግም እንዲጀመር ማግባባት በመቻሉ፣ ተመድ ማዕቀቡን ለማንሳት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮለታል።
ይኼንን ተከትሎም በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳት በእንግሊዝ መንግሥት አማካይነት በተዘጋጀው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት አባል አገሮች ተወካዮች ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በመምከር፣ በረቂቁ ላይ መግባባታቸውን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
በእንግሊዝ መንግሥት የተዘጋጀው ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ በኤርትራ ላይ የተጣለው የመሣሪያ ማዕቀብ፣ በባለሥልጣናት ላይ የጣለው የጉዞና የሀብት ዕገዳ በቀጥታ እንዲነሳ የሚጠይቅ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የውሳኔ ሐሳቡ ሊፀድቅ የሚችለው ቢያንስ በምክር ቤቱ ዘጠኝ አባል አገሮች መደገፍና ድምፅን በድምፅ መሻር የሚችሉት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ ተቃውሞ ካላቀረቡ ነው፡፡ የውሳኔ ሐሳቡ ኤርትራና ጂቡቲ በመካከላቸው ያለውን የድንበር ውዝግብ በመፍታት ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ፣ እንዲሁም የተመድ ዋና ጸሐፊ ይኼንን ጉዳይ በመከታተል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት እንዲያደርጉና በየስድስት ወሩም ተመሳሳይ የግምገማ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይጠይቃል።
ኢትዮጵያና ኤርትራ በድንበር ምክንያት ጦርነት ካደረጉ በኋላ ኢትዮጵያ በኤርትራ መንግሥት ላይ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ማዕቀብ እንዲቀጥል የአካባቢውን አገሮች በማስተባበር፣ የማዕቀቡ ይዘትም በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ተረቆ ለተመድ እንዲቀርብ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደነበራት ይታወሳል። የዚህ ዓላማም የኤርትራ መንግሥትን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገለል ማድረግ የነበረ ሲሆን፣ ዓላማውም ለበርካታ ዓመታት ውጤታ እንደነበር ተንታኞች ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ በኢራንና በባህረ ሰላጤው የዓረብ አገሮች መካከል ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በተቀሰቀሰው ፍጥጫ፣ በቀይ ባህርና በኤደን ባህረ ሰላጤ አካባቢ የምትገኘው ኤርትራ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት አገር እንድትሆን አስችሏታል። ይህም የተለያዩ ዕድሎችን ለኤርትራ እየከፈተላት እንደሚገኝና ማዕቀቡም እንዲነሳ ነገሮችን እንዳቀለለ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ።