Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምክትል ከንቲባው የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀጥል የመፍትሔ አማራጭ አስቀመጡ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ራይድ ታክሲ የከተማውን የትራንስፖርት አገልግሎት በማዘመን ሊመሠገን ይገባል ብለዋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ከወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ ጋር በመወያየት፣ ራይድ የጀመረው ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠል በሚችልበት አማራጭ መፍትሔ ዙሪያ መከሩ።

ምክትል ከንቲባው ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሥራ ኃላፊን በጽሕፈት ቤታቸው በመጥራት አነጋግረዋቸዋል፡፡ በራይድ ትራንስፖርትና በከተማው ትራንስፖርት ቢሮ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በቀላሉ ተፈቶ፣ በከተማው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈር ቀዳጅ የሆነውና በቀላሉ ተደራሽ የሆነ ዘመናዊ አሠራር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚቻል መምከራቸውን፣ ምክትል ከንቲባው ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

ራይድ የትራንስፖርት አገልግሎትና የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ አለመግባባት ደረጃ ሳይደርሱ ተነጋግረው በቀላሉ መፍታት የሚችሉት ችግር እንደነበር ያስረዱት ምክትል ከንቲባ ታከለ፣ ዘመናዊ የሆነውን የትራንስፖርት አገልግሎት የጀመሩትን ወ/ሪት ሳምራዊት አድንቀዋል። የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት መጥሪያ አፕሊኬሽንን በማበልፀግ ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ፈቃድ ያለው ሆኖ ሌላ ሕጋዊ ፈቃድ በሚጠይቅ የትራንስፖርት ኦፕሬሽን ሥራ ላይ በመሰማራቱ የተፈጠረ ውዝግብ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ሕገወጥ መሆኑን ጠቅሶ የወሰደው ዕርምጃ የሕግ ስህተት የሌለበትና ኃላፊነትን መወጣት ተግባር ቢሆን፣ አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ እንዳይቆምና ማኅበረሰቡ ጠቀሜታ አግቼበታለሁ የሚለው አገልግሎት እንዳይስተጓጎል ቀላል የነበረውን መፍትሔ መጠቆም እንደነበረበት ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት የከተማ ትራንስፖርት ሥምሪት ፈቃድ በማውጣት የሚሰጠውን አገልግሎት መቀጠል እንደሚችል ትራንስፖርት ቢሮው መፍትሔ መጠቆም እንደነበረበት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ ከወ/ሪት ሳምራዊት ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅትም ይህንን እንደገለጹላቸው አስረድተዋል።

‹‹እንደ ከተማው አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮው ሕግ እንዲጥስ መፍቀድ አልችልም፤›› ያሉት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹ራይድ ትራንስፖርት አሁን የሚጠቀምበትን ፈቃድ ወደ ሥምሪት ፈቃድ በቀላሉ በመቀየር አገልግሎቱን አጠናክሮ መቀጠል ይችላል፤›› ብለዋል።

ራይድ እንደጀመረው ዓይነት ሌሎችም ተደራሽና ዘመናዊ የአገልግሎት ድጋፍ እያገኙ የከተማውን ትራንስፖርት አገልግሎት ቢያግዙ የከተማ አስተዳደሩን ጫና የመቀነስ ጠቀሜታንም እንደሚያበረክቱ፣ ይህም የከተማ አስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ የቁጥጥር ተግባር ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ዕድል እንደሚሰጠው ጠቁመዋል። በውይይታቸውም ከኃላፊዋ ጋር መግባባታቸውን ገልጸዋል። የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሪት ሳምራዊት ከምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ጋር መምከራቸውን ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው የመሩትና የአዲስ ከበባ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊዎች የተገኙበት ረጅም ሰዓታት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸውን፣ የትራንስፖርት ሥምሪት ፈቃድ በማውጣት አገልግሎቱን መቀጠል እንደሚቻል መግባባት ላይ መደረሱን ወ/ሪት ሳምራዊት አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ የሥምሪት ፈቃድ ለማውጣት የተቀመጡት መሥፈርቶች በአክሲዮን ማኅበር በተደራጀ ድርጅት የሚጠየቅ ከሆነ በትንሹ 50 እና ከ50 በላይ የታክሲ ባለቤቶች የሚጠይቅ፣ ታክሲዎቹም የትራንስፖርት ቢሮው የሚያወጣቸውን መሥፈርቶች (ስፔሲፊኬሽን) ማሟላት ስለሚኖርባቸው፣ ራይድ ትራንስፖርት ከተደራጀበት ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ቅርፅ ጋር የማይስማማ መሆኑን በመጥቀስ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው የራይድ ትራንስፖርት አገልግሎት በነበረበትና በሥሩ ባሉት ተሽከርካሪዎች መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን፣ ሌሎች ሥራውን ለማስቀጠል እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ከትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመመካከር እንዲፈታ መመካከራቸውን ተናግረዋል።

ራይድ የትራንስፖርት አገልግሎት ከታክሲ ባለንብረቶች ጋር በቅርቡ በመምከር የሥምሪት ፈቃድ ለማውጣት እንደሚወስን፣ ነገር ግን ዋናው መፍትሔ የትራንስፖርት ቢሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥምሪት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚኖርበት ወ/ሪት ሳምራዊት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች