Friday, March 31, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚያከራያቸው ንግድ ቤቶች ላይ የዋጋ ማሻሻያ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከስምንት ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ  በሚያከራያቸው ንግድ ቤቶች ላይ የኪራይ ተመን ጭማሪ አደረገ፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኪራይ ተመን ማሻሻያ ያደረገባቸው አሥር ዋና ዋና ምክንያቶችን በመያዝ፣ ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ከደንበኞቹ ጋር በካፒታል ሆቴል መክሯል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው፣ ኮርፖሬሽኑ ለንግዱ ማኅበረሰብ የሚያከራያቸው ንግድ ቤቶች በግል ባለሀብቶች ተገንብተው ከሚከራዩ ቤቶች ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ልዩነቱ ከፍተኛ ነው፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከግል ባለሀብቶች ባነሰ ዋጋ የሚያከራይ በመሆኑ፣ ከግል ባለሀብቶች ተከራይተው የሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ የገበያ አለመረጋጋት መፍጠሩ በኮርፖሬሽኑ ተመልክቷል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኪራይ ተመኑን ለማሻሻል የሚያስገድዱ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡

የመጀመርያው ኮርፖሬሽኑ ከግሉ ዘርፍ እጅግ ባነሰ ዋጋ የሚያከራይ በመሆኑ፣ የገበያ ውድድር ሜዳው እንዲዛባ አድርጓል የሚል ነው፡፡

አቶ ረሻድ በመቀጠል እንዳስቀመጡት፣ በኮርፖሬሽኑ የንግድ ቤቶች መካከል እንኳ የተለያየ የኪራይ ተመን ስላለ በዚህም ከፍተኛ ቅሬታ በመፈጠሩ ነው፡፡

‹‹በኮርፖሬሽኑና በግሉ ዘርፍ መካከል የተራራቀ የኪራይ ተመን በመኖሩ፣  በዜጎች መካከል ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኮርፖሬሽኑ የኪራይ ተመን ማነስ ምክንያት ያላግባብ ተጠቅመው በአቋራጭ የሚበለፅጉ ዜጎች ተፈጥረዋል፤›› ሲሉ አቶ ረሻድ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩልም ኮርፖሬሽኑ መንግሥታዊ የልማት ተቋም እንደ መሆኑ፣ ህልውናው በሚሰበስበው የኪራይ ገቢ ላይ የተመሠረተ ነው ብለዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2009 ዓ.ም. እንደ አዲስ ሲቋቋም ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ አዳዲስ የመኖሪያና የድርጅት ቤቶችን በመገንባት በአዲስ አበባ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት መፍታት እንደመሆኑ የሚያከራያቸው ቤቶች የበጀት ምንጭ መሆን ይኖርባቸዋል በሚል ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በውይይቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ቤቶች የኪራይ ተመን አነስተኛ ስለሆነ በሕገወጥ መንገድ ለሦስተኛ ወገን እየተላለፈ መሆኑን፣ አንዳንድ ግለሰቦች የቤቶቹን ቁልፍ የሚሸጡ ስለሆነ ይህ ተግባር መገታት ይኖርበታል ተብሏል፡፡ ደንበኞች ደግሞ የኮርፖሬሽኑ የኪራይ ተመን አነስተኛ መሆኑን በማመን፣ ጭማሪው ግን ተመጣጣኝ መሆን እንደሚኖርበት በውይይቱ ወቅት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡   

የኮርፖሬሽኑ የዋጋ ማስተካከያ ያነጣጠረባቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያወጣቸው ከአንድ እስከ ሦስት የቦታ ደረጃዎች፣ የአካባቢ ደረጃዎችና የቤቶች ደረጃዎች ናቸው፡፡ በጥናቱ ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዳድራቸው ቤቶች፣ ቤተ ክህነት የምታከራያቸው ቤቶች፣ የግል ባለሀብቶች የሚያከራያቸው ቤቶች፣ በኮርፖሬሽን የሚከራዩ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ቤቶች ግምት ውስጥ መግባታቸው ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ፒያሳ አካባቢ የሚገኝ ንግድ ቤት በካሬ ሜትር 59 ብር ሲያከራይ፣ የግል ባለሀብቶች ደግሞ 848 ብር፣ ካቴድራል አካባቢ ኮርፖሬሽኑ በካሬ ሜትር 20 ብር ሲያከራይ፣ የግል ባለሀብቶች 682 ብር፣ ኮርፖሬሽኑ ካዛንቺስና ኡራኤል  በካሬ ሜትር 20 ብር ከ66 ሳንቲም ሲያከራይ፣ የግል ባለሀብቶች 1,300 ብር በአማካይ እንደሚያከራዩ ተገልጿል፡፡ አቶ ረሻድ የተደረገው ማሻሻያ አሁንም ቢሆን አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬደዋ ከተሞች 11,871 የመኖሪያ፣ 4,960 የድርጅት፣ 1,614 የንግድ ቤቶች በአጠቃላይ 18,445 ቤቶች አሉት፡፡ በአሁኑ ወቅት በሙሉ አቅሙ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች