በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ እየተፈተነ ያለው መንግሥት፣ በመጨረሻ የግሉን ዘርፍ በስፋት ካላሳተፈ ችግሩን እንደማይፈታው አመነ፡፡ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በግልና በመንግሥት አጋርነት አሠራር፣ የውጭና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን ማሳተፍ የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅቷል፡፡
ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ሚኒስቴሩ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ከግሉ ዘርፍ ተዋናዮች ጋር በሰነዱ ላይ የመጀመርያ ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ ላይ እንደተገለጸው፣ በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሪፖርት መሠረት በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ እ.ኤ.አ. በ2012 ከነበረበት 15.5 ሚሊዮን በ2037 በሦስት ዕጥፍ አድጎ 42.3 ሚሊዮን ይደርሳል፡፡
ነገር ግን የቤቶች ግንባታ እያደገ ካለው የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ ሲከማች የቆየውን የቤት ፍላጎት መፍታት በሚችልበት ደረጃ እየሄደ ባለመሆኑ አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር ዓባይ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ የሕዝብ ቁጥር ምጣኔ ዕድገቱ የመኖሪያ ቤትን ጨምሮ የመሠረተ ልማት አቅርቦትን ፈታኝ አድርጓል፡፡
በ1996 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በ1999 ዓ.ም. ደግሞ በ16 የክልል ከተሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ተጀምሯል ብለዋል፡፡ በዚህ ወቅት 12 ሺሕ በጥቃቅን የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች፣ ሁለት ሺሕ ኮንትክተሮችና አንድ ሚሊዮን ሠራተኞች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ባለፉት 13 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 244,684 ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ 200 ሺሕ የሚጠጉ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ሲተላለፍ፣ በክልል ከተሞ ደግሞ 69,067 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፈዋል፡፡
ይህ የሥራ አፈጻጸም በተለይ የአንበሳውን ድርሻ ለሚይዘው አዲስ አበባ ከተማ ዝቅተኛ ሲሆን፣ በሦስቱ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች ከ900 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በሦስቱ የመኖሪያ ቤት ፕሮግራሞች በመንግሥት 429,750 ቤቶች፣ በመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት 173,700 ቤቶች፣ በግለሰብ አልሚዎች 12,700 ቤቶች፣ በሪል ስቴት አልሚዎች 70 ሺሕ ቤቶች፣ በግልና የመንግሥት አጋርነት ደግሞ 23,500 ቤቶች በድምሩ 750 ሺሕ ቤቶች የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡ በመንግሥት የሚካሄደው እየተጓተተም ቢሆን የቀጠለ ቢሆንም፣ በሌሎች ፕሮግራሞች ግን ተስፋ ሰጪ ግንባታ እየተካሄደ አለመሆኑ ይገለጻል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ እየተገነቡ የሚገኙት 308,566 ቤቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 132 ሺሕ በአዲስ አበባ እየተገነቡ ነው፡፡ ነገር ግን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሦስት ዓመታት 450 ሺሕ ቤቶች መገንባት ቢኖርባቸውም፣ የተጀመሩት ግን 61 ሺሕ ብቻ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ጃንጥራር ፕሮጀክቶቹ ያሉበትን ደረጃ አብራርተዋል፡፡
የመንግሥትና የግል ባለሀብት ሽርክና አዋጅ ቁጥር 1076/2010 መፅደቁ ይታወሳል፡፡ ሰባት ከመንግሥት፣ ሁለት ከግሉ ዘርፍ የተውጣቱ ዘጠኝ አባላት ያሉት ቦርድ በገንዘብ ሚኒስቴር የተቋቋመ ሲሆን፣ ቦርዱ በቅርቡ 6.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ 16 የኤሌክትሪክና የመንገድ አውታር ግንባታዎች ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቶቹ የሚካሄዱት በግልና በመንግሥት አጋርነት አሠራር ሲሆን፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያዘጋጀው የቤቶቹ ግንባታ አዲስ ሰነድ ተቀባይነት ካገኘ የቤቶች ግንባታም በዚሁ አሠራር ይካተታል ተብሏል፡፡
የመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦ አለመመጣጠንና የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች የፕሮጀክት አስተዳደር ደካማ መሆን ያሳሰበው መንግሥት፣ የውጭ ኩባንያዎች በቤቶች ግንባታ ለማሳተፍ እስከ ጨረታ ድረስ ሄዶ ነበር፡፡
ነገር ግን የውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ከውጭ ምንዛሪ ክፍያ ጋር በተገናኘ አዋጭነቱ ጥያቄ ውስጥ ስለገባ ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ የውጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ በግልና በመንግሥት አጋርነት አሠራር በቤቶች ግንባታ በድጋሚ ለማሳተፍ ታስቧል፡፡
የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ዳብሮ፣ ለግልና መንግሥት አጋርነት ቦርድ ቀርቦ ከፀደቀ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል፡፡