Friday, March 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በሕግ ያልተገራ ሥልጣን ለአስነዋሪ ድርጊቶች ይዳርጋል!

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን መግለጫ በአንክሮ ለተከታተለ ማንም ሰው፣ በኢሕአዴግ ዘመን ተፈጸሙ የተባሉ ድርጊቶች በጣም ያስደነግጣሉ፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በአገር ሀብት ዝርፊያ ላይ በተሰጠው ማብራሪያ፣ ወትሮ የሚታወቁት ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና የሞራል ልዕልናን ያዘቀጡ ድርጊቶች ተሰምተዋል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በሚቀርቡባቸው መረጃዎችና ማስረጃዎች መሠረት ሕግ ፊት ቀርበው ተገቢውን ፍትሕ የማግኘታቸው ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተፈጽመዋል በተባሉ አስነዋሪ ድርጊቶች ላይ ግን መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ተወግዶ የደርግ ሥርዓት ከተተካ በኋላ በተፈጸሙ የቀይ ሽብር ግድያዎች፣ እስራቶች፣ ማሰቃየቶችና በመሳሰሉት የአንድ ትውልድ ኪሳራ አጋጥሟል፡፡ ይኼንን የከፋ በደል የፈጸመን መንግሥት በትጥቅ ትግል አስወግዶ ሥልጣነ መንበሩን የተቆጣጠረው ኢሕአዴግ፣ የቀይ ሽብር ሰማዕታት ሙዚየም አስገንብቶ ይህ ታሪክ አይደገምም ብሎ ቢያውጅም፣ ራሱ በሚመራቸው የመንግሥት የፀጥታና የደኅንነት አውታራት ተፈጸሙ የተባሉ ድርጊቶች ግን በጣም ይሰቀጥጣሉ፡፡ የኢትዮጵያዊያንን የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች በመናድ፣ ዜጎችን በሽብርተኝነት በመፈረጅ ተፈጽመዋል የተባሉትን አስነዋሪ ድርጊቶች ታሪክና ትውልድ ይቅር አይላቸውም፡፡ ለሕዝብ ነፃነት ታገልኩ ያለ ድርጅት በሕዝብ ላይ ይኼንን ሰቆቃ ማድረሱ፣ በሥልጣን የመባለግን የመጨረሻ ጥግ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ ከአምባገነንነት ወደ ዴሞክራሲ ማድረግ የሚገባት ሽግግር መጀመርያ የተመታው በወርኃ ሰኔ 1983 ዓ.ም. በተቋቋመው የሽግግር መንግሥት ጊዜ ሲሆን፣ ግብዓተ ቀብሩ የተፈጸመው ደግሞ ከምርጫ 97 በኋላ ነበር፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በወጡት የሚዲያ፣ የፀረ ሽብርና የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጆች አማካይነት በተፈጸሙ ገደብ የለሽ ዕርምጃዎች በርካቶች ለእስርና ለስደት ተዳርገዋል፡፡ የሕይወት መስዋዕትነት፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ደግሞ በርካቶች ናቸው፡፡ በእስር ቤቶች ከዚህ ቀደም ታይተው በማይታወቁ የማሰቃያ ዘዴዎች ሳይቀር፣ በርካቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ብዙዎች በግልጽ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያዊያን ባህል፣ ልማድ፣ እምነትና አጠቃላይ እሴቶች ጋር የሚጋጩ አስነዋሪ ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው ታሳሪዎች በተደጋጋሚ  አቤት ብለዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሳይቀር ዋስትና ያገኙ የታሳሪዎች መሠረታዊ መብቶች ማለትም ምግብ፣ መድኃኒት፣ ጠያቂና የመሳሰሉት እየተከለከሉ ከፍተኛ ድብደባ የደረሰባቸው ወገኖች በተደጋጋሚ የፍትሕ ያለህ ብለዋል፡፡ በነውረኛና በጭካኔ ድርጊቶች ምክንያት ቤተሰብ የተበተነባቸውና ያፈሩትን ሀብት አጥተው ሜዳ ላይ የቀሩም እንዲሁ ብዙ ናቸው፡፡

የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ በሕግ ሥልጣንና ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማትና ተሿሚዎች ሰዎችን አፍኖ ከመያዝ እስከ መሰወር፣ በሥውር እስር ቤቶች ከማሰቃየት እስከ አካል ማጉደል፣ እንዲሁም ሐሰተኛ ክሶች በማደራጀትና በማስፈረድ የገዛ ወገንን ለረጅም ዓመታት በማሳሰር አንገት የሚያስደፉ ድርጊቶች መፈጸማቸው ተሰምቷል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን በሕጉ መሠረት በግልጽነትና በኃላፊነት መንገድ መከናወን ሲገባው፣ የሕገወጥ ድርጊቶች ማስፈጸሚያ መሆኑ አስደንጋጭ ነው፡፡ ያለፈውን ሥርዓት በጭራቅነት ሲከስ የኖረው ኢሕአዴግ፣ እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት ውስጥ ሲገኝ አመራሮቹም ሆኑ አባላቱ ሊያፍሩ ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት በፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ፣ አገር ሲያሸብር የነበረው ራሱ መንግሥት ነው በማለት በይፋ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ይቅርታ የኢሕአዴግ መንግሥት ምን ያህል በሕዝብ ተተፍቶ እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ ኢሕአዴግ አሁንም የቅርፅና የይዘት ለውጥ አድርጎ እንደገና ካልተነሳ፣ የተቀባው ጥላሸት አብሮት እየዞረ ያሳጣዋል፡፡ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት የደረሰባት ኪሳራ ከባድ ነውና፡፡ ቁስሉም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ህሊና መቼም አይወጣም፡፡

ሌላው በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውስጥ ተፈጽሟል የተባለው የከበደ ድርጊት የሥልጣን ልቅ መሆንን ያመለክታል፡፡ ያለ ሕጋዊ ጨረታ 37 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የውጭ አገር ግዥ ተፈጽሟል ተብሎ መግለጫ ሲሰጥ፣ በዕውን ነው ወይስ በህልም ያሰኛል፡፡ ሜቴክ ውስጥ ከግዥ ጋር በተገናኘ የሕግ ጥሰቶች የተፈጸሙት በበላይ አመራሮች፣ በሥጋ ዘመዶቻቸው፣ በጥቅም በተሳሰሩዋቸው ግለሰቦችና በደላሎች አማካይነት ነው ሲባልም ግራ ያጋባል፡፡ ምንም እንኳ ሜቴክ በተለያዩ ጊዜያት ስሙ በአሉታዊ ጎኑ ሲነሳ መክረሙ የታወቀ ቢሆንም፣ ግዙፍ የአገር ሀብት ተመዝብሮበታል ሲባል ያስደነግጣል፡፡ ነገር ግን ጠያቂና ተቆጣጣሪ በሌለበት ይህ ሁሉ ድርጊት ተፈጽሟል ሲባል መንግሥት የት ነበረ ያሰኛል፡፡ በተቋሙ አማካይነት በቢሊዮን የሚቆጠር የአገር ሀብት መመዝበሩ ቢሰማም፣ ተጠያቂነት የሌለበት ሥልጣን መጨረሻው ይህ መሆኑ ግን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአዋጅ ሥልጣንና ኃላፊነት ተሰጥቶት ለተወሰነ ዓላማ የተቋቋመ ተቋም መጨረሻው እንዲህ ሲሆን ከማሳፈር አልፎ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ የሜቴክ ጉዳይ አይነኬ ተደርጎ ለዓመታት ዝም በመባሉም የሚሰማው ሁሉ ነገር አንገት ያስደፋል፡፡ ልጓም የሌለው ሥልጣን ውጤቱ ይኸው ነውና፡፡

አሁንም የሕግ የበላይነት ጉዳይ ሲነሳ ቸልተኛ መሆን አይገባም፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ሕጎች ይከበራሉ፡፡ ነገር ግን ሕጎች ባለመከበራቸው ምክንያት ብቻ ግለሰቦች ራሳቸውን ከሕግ በላይ በማድረጋቸው አገር ተበድላለች፡፡ ይህ በደል በተለይ በቀጥታ ያገኛቸው ወገኖች ምን ያህል አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እንዳደረሰባቸው በስፋት ይታወቃል፡፡ አሁንም የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን የሚፈልጉ ወገኖች በሕግ መጠየቅ ያለባቸው እንዲጠየቁ፣ በየትኛውም ኃላፊነት ላይ የሚመደቡ ወገኖችም በሥርዓት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ ሕገወጥነት ከዚህች አገር በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲወገድና ማኅበራዊ ፍትሕ እንዲሰፍን ድምፅ ማሰማት አለባቸው፡፡ ወንጀል እያንዳንዱ ሰው የሚጠየቅበት እንደ መሆኑ መጠን ከብሔር፣ ከእምነትና ከተለያዩ ማኅበራዊ ስብጥሮች ጋር ሊያያዝ አይገባም፡፡ ማንም ይሁን ማን የመንግሥትን ሥልጣን በአግባቡ አለመምራት ማስጠየቅ ይኖርበታል፡፡ ትናንት የተፈጸሙ በደሎችን በሌላ ገጽታ በመድገም የአገርን ክብር ማዋረድ ማብቃት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ይፈልጋል፡፡ ይህ ዕውን መሆን የሚችለው ግን አገር በሕግና በሥርዓት ስትመራ ብቻ ነው፡፡ ሕገወጥነትና ሥርዓተ አልበኝነት ባሉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት አይቻልም፡፡ በስመ ነፃ አውጪነትና እኔ ብቻ አውቅልሃለሁ ባይነት ሕዝብን ማታለል አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትም ሆነ የቡድን ዘረፋ ማብቃት አለበት፡፡ ሥልጣን በሕግ ሊገራ ይገባል፡፡ ተጠያቂነት የግድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በሕግ ያልተገራ ሥልጣን ለአስነዋሪ ድርጊቶች እንደሚዳርግ ማወቅ ተገቢ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካንን ጨምሮ ተመድና ኢጋድ እየታዘቡ ነው

ለሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት...

አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት አሁንም የአገር ፈተና ናቸው!

ማክሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ጥያቄዎቹ በአመዛኙ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ...

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...