Thursday, February 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 63 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በከፍተኛ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 63 ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

ቀን:

የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተጠይቆ ተፈቅዷል

በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ሰዎችን ወደ መደበኛ እስር ቤት ከመቅረባቸው በፊት በአገሪቱ በተለያዩ ቦታ በሚገኙ ሥውር እስር ቤቶች ውስጥ በማሰር ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ፣ እንደሁም ሕገወጥ ግዥ በመፈጸም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ዘርፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ 63 ግለሰቦች ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

በተጠረጠሩባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ከባድ የሙስና ወንጀሎች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች 36 በዓለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘን፣ ይርጋ የማያግደውን፣ ምሕረትና ይቅርታ የማይሰጠውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ ናቸው፡፡ 27 ደግሞ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሆነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ያለምንም ጨረታ ከ37 ቢሊዮን ብር በላይ (ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ) የውጭና የአገር ውስጥ ግዥ ያለጨረታ በመፈጸም፣ ከፍተኛ ዝርፊያ ፈጽመዋል የተባሉ ናቸው፡፡

በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ጎሃ አፅበሃ ግደይ (የአዲስ አበባ የደኅንነት ኃላፊ)፣ አቶ አማኑኤል ኪሮስ መድኅን (የአገር ውስጥ ደኅንነት ጥበቃ ዋና መምርያ ዳይሬክተር)፣ አቶ ደርበው ደመላሽ (የውስጥ ደኅንነት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩና የኢኮኖሚ ጉዳዮች መምርያ ኃላፊ)፣ አቶ ተስፋዬ ገብረ ፃዲቅ (የውስጥ ደኅንነት ጥናትና የወንጀል ምርመራ መምርያ ኃላፊ)፣ አቶ ቢኒያም ማሙሸት (የውስጥ ደኅንነት ጥበቃ ዋና መምርያ የኦፕሬሽን ጉዳይ መምርያ ኃላፊ ወይም በዋናነት የግንቦት 7 ጉዳይ ክትትል)፣ አቶ ተሾመ ኃይሌ (የአማራ ክልል የደኅንነት ኃላፊ የነበሩና የጥበቃ ዋና መምርያ ዳይሬክተር)፣ አቶ አዲሱ በዳሳ (በአገር ውስጥ ደኅንነት የኦሮሚያ ክልል ደኅንነት ኃላፊ)፣ አቶ ዮሐንስ ወይም ገብረ እግዚአብሔር ውበት (የውጭ መረጃ)፣ አቶ ነጋ ካሴ (በፀረ ሽብር መምርያ የኦነግ ክትትል ኃላፊ)፣ አቶ ተመስገን በርሄ (በፀረ ሽብር መምርያ የኦነግና ኦብነግ ክፍል ዋና ኃላፊ)፣ አቶ ሸዊት በላይ (በአገር ውስጥ ደኅንነት ኦፕሬሽን መምርያ የግንቦት 7 ክትትል ምክትል መምርያ ኃላፊ)፣ አቶ አሸናፊ ተስፋሁን (በአገር ውስጥ ደኅንነት የአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደኅንነት አስተባባሪ)፣ አቶ ደርሶ አያና (በውጭ መረጃ አማራ ክልል ክትትል)፣ አቶ ሰይፉ በላይ (በውስጥ ደኅንነት የደቡብ ክልል ክትትል ኦፊሰር)፣ አቶ ኢዮብ ተወልደ (በውስጥ ደኅንነት የደቡብ ክልል ደኅንነት ኃላፊ)፣ አቶ አህመድ ገዳ (በውስጥ ደኅንነት ኦሮሚያ ክልል ክትትል ምክትል ኃላፊ)፣ ምክትል ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉ ባባታ (ቀድሞ የፌዴራል ፖሊስ የሽብር ወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር የነበረና ዋና ዳይሬክተር ሆኖ ያገለገለ)፣ ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰን (የሽብር ወንጀል መርማሪ)፣ ዋና ሳጅን እቴነሽ አረፋይኔ (የሽብር ወንጀል መርማሪ)፣ ኤንስፔክተር ፈይሳ ደሜ (የሽብር ወንጀል መርማሪ)፣ ምክትል ኢንስፔክተር ምንላድርግ ጥላሁን (የሽብር ወንጀል መርማሪ)፣ ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽን (የሽብር ወንጀል መርማሪ)፣ ኦፊሰር ገብረ ማርያም ወልዳይ፣ ኦፊሰር አስገለ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ሐዋርያት (የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደኅንነት ኃላፊ)፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተክላይ ኃይሉ (የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ)፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አቡ ግርማ (የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ኃላፊ የነበረና በዝዋይ ማረሚያ ቤት ኃላፊ) ሆኖ ሲያገለግል የነበረ፣ ዋና ሱፐር ኢቴንደንት አዳነ ሐጎስ (የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ሠራተኛ)፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ተስፋ ሚካኤል አስገለ (በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከፍተኛ የደኅንነት ባለሙያ)፣ ዋና ሱፐር ኢንቴንደንት ገብራት መኮንን (የዝዋይ ማረሚያ ቤት የጥበቃና ደኅንነት ኃላፊ የነበረና የሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት ጥበቃ ደኅንነት ኃላፊ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ)፣ ረዳት ኢንስፔክተር ዓለማየሁ ኃይሉ ወልዴ (በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ)፣ ረዳት ኢንስፔክተር መንግሥቱ ታደሰ አየለ (በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀል መርማሪ)፣ አዳነች ወይም ሐዊ ተሰማ ቶላ፣ አቶ ጌታሁን አሰፋና ሙሉ ፍሰሐ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ደግሞ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁርንዲ ኢጄታ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የማርኬቲንግ ኃላፊ)፣ ብርጋዴር ጄኔራል ብርሃን በየነ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኃላፊ)፣ ብርጋዴር ጄኔራል ጥጋቡ ፈትላ መረሳ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ ኃላፊ)፣ ብርጋዴር ጄኔራል ሃድጉ ገብረ ጊዮርጊስ ገብረ ሥላሴ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ተስፋሁን (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የወታደራዊ ምርቶች ኦፕሬሽን ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል ገብረ እግዚአብሔር (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ የነበሩ)፣ ኮሎኔል ዙፋን በርሄ ይህደግላ (የመከላከያ ጤና ኮሌጅ ሠራተኛ) ሌተና ኮሎኔል አስመረት ኪዳኔ አብርሃ (የጋፋት አርማመንት ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተወካይ ኃላፊ የነበሩ)፣ ኮሎኔል ዓለሙ ሽመልስ ብርሃን (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የትራንስፖርት ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ያሬድ ኃይሉ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የፕሮጀክት ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ተከስተ ኃይለ ማርያም አድሃኑ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ) የነበሩ፣ ኮሎኔል አዜብ ታደሰ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ማርኬቲንግ የሽያጭ ኃላፊ)፣ ሻለቃ ሰመረ ኃይሌ ሐጎስ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በደጀን አቪዬሽን የኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ)፣ ሻምበል ይኩኖአምላክ ተስፋዬ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በብረታ ብረትና ኢንጂነሪነግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ማርኬቲንግና ሽያጭ የፕሮሞሽን ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ብርሃን (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የአዳማ እርሻ ሥራዎች ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅ)፣ ሌተና ኮሌኔል ሰለሞን በርሄ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በብረታ ብረት ፋብሪኬሽን ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ)፣ ሻለቃ ይርጋ አብርሃ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኅብረት ማሽን ቢዩልዲንግ ኢንዱስትሪ የፋይናንስ ኃላፊ)፣ ኮሎኔል ግርማ ታረቀኝ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ሎጂስቲክስና ሰፕላይ የንብረት አስተዳደር ኃላፊ)፣ ሻምበል ገብረ ሥላሴ ገብረ ጊዮርጊስ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የአቅም ግንባታ ማዕከል ኃላፊ)፣ ሻምበል ሰለሞን አብርሃ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ትራንስፎርሜሽን የሥልጠና ኃላፊ)፣ ሻለቃ ጌታቸው ገብረ ሥላሴ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የደን ምንጣሮ ክትትል ኃላፊ)፣ ሌተና ኮሎኔል ይስሐቅ ኃይለ ማርያም አድሃኖም (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ኮሜርሻልና ሲቪል ምርቶች ኦፕሬሽን የፕላኒንግና ኮንትሮል ኃላፊ)፣ ሻለቃ ክንደያ ግርማይ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተለያዩ ኢንዱስትዎች የፋይናንስ ኃላፊ)፣ ሌተና ኮሎኔል አዳነ አገርነው (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በኮርፖሬት ሎጂስቲክስ ሰፕላይ የንብረት ክፍል ኃላፊ)፣ ሻለቃ ጌታቸው አፅብሃ (በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኢንፍራስትራክቸርና ኮርፖሬሽን ማሽነሪ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኦፕሬሽን ኃላፊ)፣ ቸርነት ዳና (የዋይቲኦ ኩባንያ ባለቤትና ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን አመራሮች ጋር የጥቅም ትስስር የነበረው ደላላ)፣ አያልነሽ መኮንን አራጌ ማስረጃ ልታጠፋ ስትል በቁጥጥር ሥር የዋለች መሆኗ የተገለጸ ሲሆን፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለተጨማሪ ምርመራ የጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ተፈቀዶለት፣ ለኅዳር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡      

   በሰብዓዊ መብቶች ጥሰትም ሆነ በሜቴክ ላይ ተፈጽሟል የተባለው ከባድ ዝርፊያ በየትኛው የመንግሥት ተቋም እንዴትና በእነማን እንደተፈጸመ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ብርሃኑ ፀጋዬ ሰኞ ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ እንደ ዋና ዓቃቤ ሕጉ ገለጻ፣ ዘግናኝ የሆነው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመው በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ነው፡፡ አፈጻጸሙም በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙና በማይታወቁ ሥውር ማሰቀያ ቦታዎች መሆኑንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ ሰባት ሥውር የማሰቃያ እስር ቤቶች በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(1) በግልጽ፣ ‹‹ማንኛውም የመንግሥት አካል የሰዎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት አለበት፤››  ይላል፡፡ በተለይ ለፍትሕ አካላት ዜጎች ተጠርጥረው በሚያዙበት ጊዜ እንዴት ሰብዓዊ መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት፣ ድንጋጌው ድርብ ኃላፊነት እንደሚጥልም አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ የማይጣስ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተጥሶ፣ በተለይ በሽብር ድርጊት ተጠርጥረው በተያዙ ኢትዮጵያውያን ላይ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አመራሮችና አባላት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስረድተዋል፡፡ ዜጎች በተጠረጠሩበት የሽብር ድርጊትን ሲያዙ ወደ መደበኛ እስር ቤት ከመቅረባቸው በፊት በሕግ በማይታወቁ ሥውር እስር ቤቶች ይታሰሩ እንደነበር ዋና ዓቃቤ ሕጉ ጠቁመዋል፡፡ ዜጎች በድብቅ እስር ቤት የሚታሰሩት ያልፈጸሙትን ወንጀል በድብደባ እንዲያምኑ፣ ደብዳቢዎቹንም ከተጠያቂነት ለማዳንና ማንነታቸውም እንዳይታወቅ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ተጠርጣሪ ናቸው የሚባሉ ዜጎች ከተያዙበት ቦታ ወደ ሥውር መግረፊያ ቤት የሚወሰዱት፣ ዓይናቸው ታስሮና በአምቡላንስ መሆኑንም አክለዋል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ሲውል ለምን እንደተያዘና ማን እንደያዘው የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳለው የተደነገገ ቢሆንም፣ ይኼ መብታቸው መታለፉንም ተናግረዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ በዝርዝር እንዳስረዱት፣ ተጠርጣሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ከሆኑ ተገደው ከአባልነታቸው እንዲወጡ ይገደዳሉ፡፡ ይኼንን የማያደርጉ ከሆነ ከፍተኛ የሆነ ድብደባ ይፈጸምባቸው እንደነበር፣ የተሰበሰቡ ማስረጃዎች እንደሚያስረዱ ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችንና ሌሎች ሰነዶችን ‹‹የራሴ ነው›› ብለው እንዲፈርሙ ይደረጉ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

በሥውር እስር ቤቶች የተገደሉና የተሠወሩ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ በእስር ላይ የነበሩ ዜጎች ከተፈጸሙባቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል በዋናነት፣ በፖሊስ ጣቢያ በማረሚያ ቤቶች የተለያዩ የማሰቃያ ድርጊቶች ሲፈጸምባቸው እንደነበር አብራርተዋል፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጽ ያህል አካላቸውን በኤሌክትሪክ ማደንዘዝ (ሾክ ማድረግ)፣ ገልብጦና አንጠልጥሎ መግረፍ፣ የብልትን ቆዳ በፒንሳ መሳብ፣ በዛፍ ላይ ሰቅሎ መግረፍ፣ ለረዥም ጊዜ በጨለማ ቤት በማሰር ፀሐይ እንዳያገኙ ማድረግ፣ ጫካ ውስጥ ራቁታቸውን እንዲያድሩ ማድረግ፣ ምግብና ውኃ መከልከል፣ አንጋሎ በአፍንጫቸውና በአፋቸው ውስጥ ፎጣና ሌሎች ነገሮች በመወተፍ ማሰቃየት፣ በአፍንጫቸው እስክርቢቶ አስገብቶ ማሰቃየት፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ሙቀት ባለባቸው አካባቢዎች ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ፣ በዕቃ ውኃ ሞልቶ በብልታቸው ላይ ማንጠልጠል፣ ጥፍራቸውን መንቀል፣ በጦር መሣሪያ ሰደፍ መምታት፣ በአናታቸው ላይ ጥይት መተኮስ፣ ከከተማ ውጪና በታሰሩበት አካባቢ ጉድጓድ በመቆፈር ጉድጓዱን እንዲያዩ በማድረግ ማሰቃየት፣ ዓይናቸውን አስረው ከከተማ በማውጣት ጫካ ውስጥ ራቁታቸውን መጣል፣ አልፎ አልፎ ከአውሬ ጋር የማሰር ድርጊት መፈጸምና በመሳሰሉት ከባድ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ ታሳሪዎቹ የአካል ጉዳት፣ የሥነ ልቦናና የኢኮኖሚ ጉዳትም ደርሶባቸዋል ብለው፣ በተለይ በእጃቸው፣ በእግራቸው፣ በዓይናቸውና በጥርሳቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን በማስረጃ የተጣራ መሆኑን አክለዋል፡፡ በቀጣይ በፍርድ ቤት የሚጣራ ቢሆንም በፖሊስ ጣቢያ፣ በማረሚያ ቤት፣ በሕክምና ቦታዎችና በተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ሰነዶች መገኘታቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ ረዥም ጊዜ በጨለማ ቤት ታስረው የነበሩ ዜጎች ዓይነ ሥውር መሆናቸውን፣ በብልታቸው ላይ በደረሰ ጉዳት ቀጣይ ዘር እንዳይኖራቸው መኮላሸታቸውን፣ በወንዶች ላይ ግብረ ሰዶም መፈጸሙንና ሴቶችን ተፈራርቆ የመድፈር ወንጀል መፈጸሙን የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱ አብራርተዋል፡፡ በሌላ በኩል ዘርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲፈጠሩ የተቋሙ ኃላፊዎችና አባላት ሲያከናውኑ እንደነበርም አክለዋል፡፡ የተጠርጣሪዎች ቤተሰቦችም ከተከራዩበት ቤት እንዲወጡ በማድረግ፣ ከማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲገለሉና እንዲወጡ በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ እስከዚያ ደርሶ እንደነበርም ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አመራሮች አሠራር ሆኖ የቀጠለና ግምገማ እየተደረገ፣ ተጨማሪ አቅጣጫዎች ይሰጡ እንደነበር የተሰበሰቡ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡ አስረድተዋል፡፡ ይኼንን ያከናውኑ የነበሩ መርማሪዎችንና ፖሊሶችን በማካተት ምርመራው መሠራቱንም አክለዋል፡፡

የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰፊና ፈርጀ ብዙ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፣ በሽብር ተግባር ተጠርጥረው የሚከሰሱ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በቤታቸው ውስጥ የተለያዩ ዓርማዎች በማስቀመጥ የራሳቸው የማስመሰል ድርጊት ሲፈጸም እንደነበርም ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከሉ የወንጀል ድርጊቶችን በዜጎች ላይ ሲፈጽሙ ነበር የተባሉ 36 ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑንና እነዚህ ግለሰቦች በቀጣይ የሙስና ወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑም አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

ዋና ዓቃቤ ሕጉ ሌላው ትኩረት ተሰጥቶ ላለፉት ስድስት ወራት ሲሠራበት የነበረውንና ከፍተኛ ሙስና ተፈጽሞበታል ስለተባለው፣ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የአገር ውስጥና የውጭ አገር ግዥን በሚመለከት አብራርተዋል፡፡ እሳቸው እንደገለጹት፣ የሙስና ወንጀል በትልልቅ የመንግሥት ፕሮጀክቶች (Mega Projects) ላይ ምርመራ ተደርጓል፡፡ በትልልቅ ግዥዎች፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በፋይናንስ ተቋማትና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ማጣራት ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከተጀመሩት ምርመራዎች መካከል የተጠናቀቀና በተለይ ደግሞ ከደረሰው ጥፋት አንፃር በአገሪቱ ገጽታ ላይ ካሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ፣ ከባከነው ገንዘብና ለሌሎች ሥራዎች ካለው ተፅዕኖ አንፃር፣ ሜቴክና የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር ላይ ዕርምጃ መውሰዱን አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡

ምርመራው የተጣራው ሕጎችና አሠራሮችን ተከትሎ መሆኑንና የተከናወኑ ተግባራት ምን እንደሚመስሉ፣ በውጭና በአገር ውስጥ ኦዲተሮች የተረጋገጡ ምርመራዎች ምን ያሳያሉ፣ የሚሉትን በማየት መሆኑን አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ የወንጀል ፍሬ ይሆናሉ ተብለው የተለዩ ሕንፃዎች፣ ተሽከርካሪዎች፣ መኖሪያ ቤቶች፣ አክሲዮኖችና ሌሎች ነገሮችንም ለመለየት ጥረት መደረጉን አክለዋል፡፡ ንብረቶቹ በተለያዩ ሰዎች ተመዝግበው የተገኙ በመሆናቸው፣ በተጠርጣሪዎቹና በባለንብረቶቹ መካከል ያለው ግንኙነት ‹‹የዝምድና ነው? የጥቅም ግንኙነት ነው? ምንድነው?›› የሚለውን ለመለየት ጥረት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በሜቴክ ላይ ለምርመራ መነሻ የተደረጉት ግዥዎች ናቸው፡፡ ‹‹የውጭ አገርና አገር ውስጥ ግዥዎች ምን ይመስላሉ?›› የሚሉትን፣ የህዳሴ ግድብን ግንባታ በተመለከተም ከሜቴክ ጋር ያለውን ተያያዥነት ለማጣራት ጥረት መደረጉን፣ ምርመራው የተጀመረው የሕዝቡን ጥቆማና ሌሎች ነገሮች መሠረት በማድረግ መሆኑን ዋና ዓቃቤ ሕጉ ጠቁመው ምርመራው ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና ከሌሎች ባለሙያዎችን በማደራጀት መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አስታውቀዋል፡፡ ምርመራው የተጣራው ማንም ሳይታሰር በመሆኑ በፍርድ ቤት የተወሰነ ማጣራት ካላስፈለገ በስተቀር፣ በቀጥታ ክስ መመሥረት በሚያስችል ሁኔታ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሜቴክ በደንብ ቁጥር 183/2002 ሰኔ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. የልማት ድርጅት ሆኖ በአሥር ቢሊዮን ብር የተፈቀደና 3.1 ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተቋቋመ ተቋም ነው ብለዋል፡፡ ተልዕኮውና ዓላማው የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ዲዛይን ማድረግ፣ የኢንዱስትሪ ዕቃዎችንና መለዋወጫዎችን ማምረት፣ የመከላከያ አቅም መለኪያ ቴክኖሎጂ መገንባት፣ የኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ መገንባትና ማስፋፋት መሆኑንም የጠቆሙት ዋና ዓቃቤ ሕጉ፣ ሜቴክ ግን ከተቋቋመበት ዓላማና ተልዕኮ ውጪ ሌሎች ተግባራትን ሲፈጽም እንደነበር አብራርተዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ እንዳብራሩት፣ ተቋሙ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ከ37  ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ አገር ግዥ ፈጽሟል፡፡ ግዥዎቹ በሙሉ የተፈጸሙት የመንግሥት የግዥ መመርያ በመጣስ ያለምንም ጨረታ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ሲታይ ግዥ የተፈጸመው ከተቋሙ የበላይ ኃላፊዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት ካላቸውና ኮሚሽን በሚከፈላቸው ደላላዎች አማካይነት ነው ብለዋል፡፡ የድለላውን ሥራ የሚሠሩት ደግሞ የኃላፊዎቹ የቅርብ የሥጋ ዘመድ የሆኑ ወንድም፣ እህትና የአክስት ልጅ መሆናቸውንና የውጭ አገር ኩባንያዎችን በድለላ የሚያመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ግዥው የሚፈጸመው ለአንድ ጨረታ እስከ 400 ፐርሰንት ጭማሪ እየተደረገ መሆኑንና በጣም የተጋነነ ጭማሪ መሆኑንም አክለዋል፡፡ ደላላዎቹ ክፍያ የሚያገኙት በተዘዋዋሪ ከውጭ ኩባንያዎች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ደላላዎቹ በአገር ውስጥ የተወሰነ ንብረት ያፈሩ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወደ ውጭ እንዲሸሽ የተደረገ መሆኑን አቶ ብርሃኑም አክለዋል፡፡ ሌላው የሚገርመው ነገር ያሉት ግዥው የተፈጸመው ከአንድ ተቋም ከ40 እስከ 50 ጊዜ ድግግሞሽ ባለው ሁኔታ መሆኑን ነው፡፡ ከውጭ ግዥዎች እንደ ምሳሌ የተጠቀሰው ያገለገሉና አዳዲስ ክሬኖችና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ከቻይናና ከሲንጋፖር ያለጨረታ መገዛታቸውን ጠቁመው፣ የተገዙት ክሬኖች አምስት ቢሆኑም፣ አንዱ ቀረጥ እንዳይከፈልበት በሱዳን በኩል እንዲገባ ተደርጎ ለግለሰብ መጠቀሚያ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ግዥው የተፈጸመው መከላከያን ከሚመለከት ሚስጥራዊ ግዥ ጋር ግንኙነት ለሌላቸው ማሽነሪዎች መሆኑን፣ እስከ 105 ጊዜ ተደጋጋሚ ግዥ ከተፈጸመባቸው ተቋማት የተገዙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የአገር ውስጥ ግዥም ሲታይ ግዥ ሲፈጸም የነበረው ያለጨረታና የተወሰኑ ነጋዴዎች (ድርጅቶችን) ‹‹አጋር›› በማለት እንደነበር ከኮርፖሬሽኑ አመራሮች ጋር ዝምድናና ጥቅም ካላቸው ግለሰቦች ሲፈጸም የቆየ መሆኑን፣ በምርመራ መረጋገጡን ዓቃቤ ሕጉ ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹን ለመጥቀም ሲባል ከገበያ ዋጋ በላይ በብዙ ዕጥፍ ግዥ ሲፈጸም እንደነበርና ከአንድ ድርጅት ያለምንም ጨረታ ለ21 ጊዜያት፣ ከሌሎች ድርጅቶች ደግሞ ለ15 እና ለ18 ጊዜያት ግዥ መፈጸሙን አክለዋል፡፡ ከአንድ ድርጅት በአንድ ጊዜ የ205 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን በምሳሌነት ጠቁመዋል፡፡ ይኼ ግዥ ትልልቅ ግንባታዎችን ሳይጨምር የተፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ሌላው ከተቋሙ ተልዕኮና መመርያ ውጪ ሁለት ግዥዎች መፈጸማቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ አንደኛው የመርከቦች ግዥ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ንብረት የሆኑ ‹‹ዓባይ›› እና  ‹‹አንድነት›› የሚባሉ ከ28 ዓመታት በላይ ያገለገሉ መርከቦች መሆናቸውንም አቶ ብርሃኑ ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ በባለሙያ አስጠንቶ መርከቦቹ ከዚህ የአገልግሎት ዘመን በኋላ ትርፋማ እንደማይሆኑ በማረጋገጡ፣ በቦርድ ውሳኔ ለሽያጭ እንዲውሉ ተደርጎ እንደነበር አቶ ብርሃኑ አስታውሰዋል፡፡ መርከቦቹ ለውጭ ድርጅት ከሚሸጡ ተቆራርጠው ብረታቸው ለአገር ውስጥ ሥራ ይዋሉ ተብሎ ሜቴክ በ3.276 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ውል መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡ ሜቴክ መርከቦቹን አፍርሶ ብረቱን በመቆራረጥ ለመጠቀም የገዛቸው ቢሆንም፣ ያንን ትቶ ወደ ንግድ ሥራ እንዳስገባቸው ጠቁመዋል፡፡  

መርከቦቹ ለንግድ ሥራ እንዲውሉ የሜቴክ ቦርድ መስከረም 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ውሳኔ በማስተላለፍ፣ መርከቦቹ በጂቡቲ ወደብ ረዥም ጊዜ ከቆዩ በኋላ ለጥገና ወደ ዱባይ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡ 513,837 ብር ለጥገና ሲከፈል፣ ጠጋኝ ለማፈላለግ የተመደቡት ጥቅምና ዝምድና ያላቸው ደላሎች መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ መርከቦቹ ዱባይ ከተጠገኑ በኋላ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መንቀሳቀስ ስለማይቻል፣ በኢራን ሰንደቅ ዓላማ ወደ ሞቃዲሾ እየተመላለሱ እስከ 500 ሺሕ ዶላር የሠሩ ቢሆንም፣ ገንዘቡ ለሜቴክ አለመግባቱን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ፈቃድ ማግኘት ባለመቻሉ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት፣ ማሪታይምና መንገድ ትራንስፖርት ተቃውሞ በማቅረባቸው በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲቆም መመርያ የተሰጠ ቢሆንም ሊያቆሙ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻ መርከቦቹ በኪሳራ 2.6 ሚሊዮን ብር መሸጣቸውንም አክለዋል፡፡

ሁለተኛው የአውሮፕላኖች ግዥ ሲሆን፣ ‹‹አገራዊ ፕሮጀክቶችን በአውሮፕላን ታግዞ ለመከታተል›› በሚል ምክንያት ግዥ እንደተፈጸመ ተናግረዋል፡፡ ያለምንም ጨረታ ከእስራኤል ኩባንያ በ11,732,520 ብር አምስት አውሮፕላኖች መገዛታቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ አውሮፕላኖቹ ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገሉ፣ የሚጠቀሙት ነዳጅ ውድ የሆነ፣ የቴክኒክ ችግር ያለባቸውና ጥቅም ላይ ሊውሉ የማይችሉ መሆናቸው በባለሙያ የተረጋገጠ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የሚገርመው ነገር አራቱ ከአገልግሎት ውጭ ሆነው የቆሙ ሲሆን፣ አንደኛው አውሮፕላን የት እንዳለ እንደማይታወቅም አክለዋል፡፡ በአውሮፕላኖቹ ግዥ መንግሥት ከ24.9 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትም አክለዋል፡፡ ተቋሙ የሆቴሎች ግዥዎችን መፈጸሙን የገለጹት አቶ ብርሃኑ፣ ለሠራተኞች ማረፊያና በተለያዩ አገልግሎቶች ተብለው የተገዙ ቢሆንም፣ እጅግ በጣም በተጋነነ ዋጋ የተገዙና አንዳንዶቹም የባንክ ዕዳ ያለባቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ግዥው የተፈጸመው በጥቅም ትስስር ካላቸው ሰዎች አማካይነት መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በሌሎች ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈጸሙ ድርጊቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም የተፈጸመውን የሙስና ወንጀል በሕግ አግባብ በመመርመርና በተጠርጣሪዎችም ላይ ክስ በመመሥረት ለማስቀጣት 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው እየተመረመሩ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ይፋ አድርገዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ብርሃኑ፣ ከአገሮቹ  መንግሥታት ጋር ግንኙነት ማድረግ መጀመሩንና አገሮቹም አሳልፈው ለመስጠት ስምምነት ላይ እየተደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አገር ውስጥ በተለያዩ ክልሎችና ቦታዎች የተደበቁ እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበው፣ ኅብረተሰቡ የተለመደ ጥቆማውን እንዲያደርሳቸው የተጠርጣሪዎቹንም ፎቶ በመገናኛ ብዙኃንና በተለያዩ መግለጫዎች ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በኤግዚቢትነት የተያዙ ተሽከርካሪዎች፣ ሊብሬዎች፣ ብዛት ያላቸው ካርታዎች፣ አክሲዮኖች፣ የባንክ ደብተሮች፣ በርካታ የቤት ሽያጭ ውሎች፣ ቦምቦች፣ ክላሾች፣ ሽጉጦች መኖራቸውን አክለዋል፡፡  

ሌላው አቶ ብርሃኑ የገለጹት፣ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ን ለመደገፍ በወጣ ሕዝብ ላይ ስለተወረወረው ቦምብ ነው፡፡ የቦምብ ውርወራን ያስተባበሩትና የመሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ የአገልግሎቱ ኃላፊ መኖሪያቸውን ኬንያ አገር ካደረጉት ገነት (ቶለሺ) ታምሩ ከተባሉ ተጠርጣሪ ጋር በመተባር ድርጊቱን እንዳቀነባሩት አስረድተዋል፡፡ ነዋሪነታቸውን ኬንያ ያደረጉት ግለሰብ በፋይናንስና ቦምቡን የሚወረውሩትን በመመልመል መሳተፋቸውን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ በቦምብ ውርወራውና በተለያዩ ድርጊቶች የተሳተፉ ግለሰቦች ምርመራ ተጠናቆባቸው ክስ እንደተመሠረተባቸውና በፍርድ ቤት በክርክር ላይ መሆናቸውን አክለዋል፡፡ በቦምብ ፍንዳታው በመሳተፋቸው ክስ የተመሠረተባቸው አምስት ግለሰቦች ሲሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ በግለሰቦቹ ላይ ያቀረበው ክስ፣ ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ በተመሠረተው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ስም የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን በክሱ መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ በመስቀል አደባባይ በደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንና ከ160 በላይ ግለሰቦች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...