በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የመያዣ ዋራንት ተቆርጦ ሲፈለጉ የነበሩት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ (ሜቴክ) የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው፣ በሁመራ አድርገው ወደ ሱዳን ሊወጡ ሲሉ በትግራይ ክልል ልዩ ኃይል በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ አዲስ አበባ ገቡ፡፡
በኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ የነበሩ 27 ኃላፊዎች ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው ሲታሰሩ የቀድሞው ዋና ዳይሬክተር ባይያዙም፣ ከአራት ቀናት ቆይታ በኋላ ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ውለው በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅበውና በካቴና እጆቻቸው ታስረው ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡
ማክሰኞ አመሻሽ 11፡15 ሰዓት ላይ በመከላከያ ሔሊኮፕተር ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የደረሱት ጄኔራሉ፣ እንደ ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ዛሬ ወይም ነገ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ ይጠየቅባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ኮርፖሬሽኑን በዋና ዳይሬክተርነት ከሰኔ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በመምራት ላይ የነበሩ ሲሆን፣ በከባድ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ከተፈጸሙ ግዥዎች ጋር በተያያዘ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ለስድስት ተከታታይ ዓመታት በውጭ ግዥዎች ያለምንም ጨረታ የ37 ቢሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙን፣ እንዲሁም በአገር ውስጥም በከፍተኛ ዋጋ ግዥዎች መፈጸሙን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት በቢሊዮኖች የሚቆጠር የአገር ሀብት መመዝበሩን ጠቁሟል፡፡
ሜቴክ በደንብ ቁጥር 183/2002 ሰኔ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. በተፈቀደ አሥር ቢሊዮን ብርና በዓይነትና በገንዘብ በተከፈለ 3.1 ቢሊዮን ብር የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ይታወሳል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ይኽን ድርጅት በኃላፊነት ሲመሩ ሕግን፣ ደንብንና መመርያን መሠረት አድርገው መቆጣጠር ሲገባቸው ባለማድረጋቸው በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ መጠርጠራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ሜጀር ጄኔራል ክንፈ ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የፓርላማው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ ለሚባክኑ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ተጠያቂው ማነው በማለት አቅርቦላቸው ለነበረው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ሜቴክ አጠፋ ለሚባለው ነገር በግሌ በብቸኝነት መጠየቅ ያለብኝ እኔ ብቻ ነኝ፡፡ ከእኔ ውጪ ማንም እንዲጠየቅ አልፈልግም፡፡ የሚፀፅተኝ የለም፡፡ ሊታወቅ የሚፈለገው ይህ ከሆነ ለዚህ ዝግጁ ነኝ፤›› ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡