የግእዝ ሥነ ጽሑፍ በብራና ላይ ተጽፎ መታየት በጀመረበት የአክሱም ግዛተ አፄ (ኢምፓየር) ዘመን ለንባቡ ከበቁት መጻሕፍት መካከል ከግሪክ ቋንቋ የተተረጐመው ፈሳልጎስ ይገኝበታል፡፡
መጽሐፉ በአራዊት፣ በእንስሳት፣ በአዕዋፋት፣ በማዕድን ምሳሌነት የሚተርክ ሥነ ምግባርን ከክርስትና መሠረተ እምነት ጋር እያስተሳሰረ የሚገልጽ ነው፡፡ ስለ ነጩ ዖፈ ከራድዮን፣ በየ500 ዓመት ስለሚታደሰው ስለፊኒክስ፣ ዕንቁ ስለምታገኘው ዖፈ ብርጋና እና ስለ ሌሎች 43 የእንስሳት፣ የአራዊትና የአዕዋፍ ዓይነቶች ይተርካል፡፡
በተለያዩ የዓለም ቋንቋዎች የተተረጐመው ፊሳሊጎስ ለየአገሮቹ ድርሰቶች ለሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎቻቸው መነሻ ሆኖ ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ከአንድምታ ትርጓሜዎች ባለፈም በተለያዩ የሥነ ግጥምና የልቦለድ ሥራዎች በጥቂቱም ቢሆን አሻራ ማሳረፉ አልቀረም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ሥራዎች ‹‹ፊኒክስዋ ሞታም ትነሳለች›› ‹‹ዖፈ ከራድዮን›› ይጠቀሳሉ፡፡
በ1500 ዓመት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ በየዐረፍተ ዘመኑ በተለያዩ ዘርፎች መጻሕፍት ተተርጉመዋል፣ ተደርሰዋል፣ ተዘጋጅተዋል፡፡ ከሃይማኖታዊ ሥራዎች ባሻገር በፍልስፍና፣ በታሪክ፣ በባሕረ ሐሳብ፣ በሕግ፣ በሕክምና፣ በቋንቋ በሰዋስውና በቅኔ አያሌ ትሩፋቶች ለዚህ ዘመን ደርሰዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያንን ለሥርዓተ አምልኮና ለሥነ ጽሑፍ አገልግሎት ከመዋሉ በተጓዳኝ በልሳነ ግእዝ የክርክር መድረክም በ1960ዎቹ አጋማሽ በአዲስ አበባ ቅድስት ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዘጋጅቶበት እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ የክርክሩ ጭብጥ ‹‹አማርኛ ያለ ግእዝ ምሉዕ ይሆናል ወይስ አይሆንም›› በሚል ሊቃውንቱ በሁለት ቡድን ተከፍለው የተከራከሩበት ነበር፡፡ ይህም ‹‹ትንሣኤ ግእዝ›› በሚል ታትሞ ነበር፡፡
በ1990ዎቹም የልሳነ ግእዝ ቤተሰብ የሚባል ንቅናቄም ተጀምሮ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ የግእዝ ፍኖተ (መንገድ) በኋላ ነው ‹‹ጦማረ መዋቲ›› የተሰኘና በነጋሢ ግደይ የተደረሰ ረዥም ልብወለድ ታትሞ የወጣው፡፡
‹‹ግእዝ ቋንቋ በተለያዩ ዐውደ ጥናቶችና መገናኛ ብዙኃን በየጊዜው እንደሚገለጸው፣ በውስጡ ገና ያልተዳሰሱ፣ በጥናትና ምርምር እንደ መነሻ በመሆን ሊያገለግሉ የሚችሉ አገር በቀል ዕውቀቶችና እሴቶችን ይዟል፡፡ በመሆኑም ቋንቋውን ማስተማርና ማሳወቅ በውስጠ ምልከታ የተቃኘ ትምህርታዊና ምርመራ አስተሳሰብ በማዳበርና የነባሩ ዕውቀት መሠረትነት አዳዲስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በማፍለቅ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤›› የሚል ሐተታ ያቀረቡት ደራሲ ነጋሢ ግደይ ናቸው፡፡ ለግእዝ ልብ ወለዳቸው በጻፉት መግቢያቸው ግእዝ ቋንቋን በተመለከተ ሁለት ዓይነት እይታዎችና አካሄዶች እንደሚስተዋሉ አውስተዋል፡፡ አንደኛው ቋንቋውን አስተምሮ ኅብረተሰቡ በቀጥታ የቋንቋው ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የሚደረግ ጥረት ሲሆን ሁለተኛው በቋንቋው የተከማቹ ሀብቶች ጠፍተው እንዳይቀሩ በማሰብ የመተርጐም ሥራ ነው፡፡ ሁለተኛውን መንገድ የተደበቀውን ሀብት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ከማድረግ አንፃር የሚበረታታ ቢሆንም ቋንቋውን ማሳደግ ደግሞ ብዙ ጠቀሜታዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ እስማማለሁ ይላሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ግእዝ ቋንቋን ለማሳደግ በአብዛኛው መዝገበ ቃላትን በማዘጋጀትና የግእዝ ቋንቋን ሰዋስዋዊ ትንታኔ በመስጠት ዙርያ የተወሰኑ ቢሆኑም በርካታ መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቋንቋውን ለማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊጠቀምበት የሚችል ወጥ የሆነና በግእዝ ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ አለ ለማለት አያስደፍርም የሚሉት ደራሲ ነጋሢ ይህች ‹‹ጦማረ መዋቲ›› በሚል ርዕስ የተሰየመችና ቀለል ባለ የአጻጻፍ ዘዴ የተጻፈች መጽሐፍ ‹‹በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈች ልቦለድ መጽሐፍ ናት ማለት ይቻላል፤›› ከማለት አልተመለሱም፡፡
እንደ ደራሲው አገላለጽ፣ የመጽሐፏ ዋና ዓላማ ለብዙ ዓመታት ኍልቁ መሳፍርት የሌለው ረሃብ፣ መከራንና እርዛትን ታግሰው ለተማሩና በተማሩት ትምህርት የሚገባቸውን ጥቅም ሳያገኙ አሳዛኝ ኑሮ ለሚገፉ ጓደኞቻቸውና መምህሮቻቸው አዲስ አቅጣጫ ማሳየት ነው፡፡ ምክንያቱንም እንዲህ ገልጸውታል፡፡ ‹‹ይህ አዲስ ዕይታ በመማርና በማስተማር ካካበቱት ወርቃማ የሆነ ሁለንተናዊ ሀብታቸው ተነስተው ማኅበረሰባዊ ዕይታዎቻቸውና የሕይወት ገጠመኞቻቸውን በቋንቋው እየጻፉ ባንድ በኩል ኑሮአቸውን እንዲደግሙ፣ በሌላ በኩል ትውልድን በመቅረጽ ረገድ የነበራቸውን አይተኬ ሚና አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል፡፡›› በየመገናኛ ብዙኃኑ ‹‹ግእዝ ቋንቋ ሙቷል ወይስ አልሞተም›› እየተባለ ለሚጠየቀው ጥያቄ ቋንቋው ዛሬም እንደ ጥንቱ የሥነ ጽሑፍና የምርምር ቋንቋ ሆኖ ለማገልገል ከነጉልበቱና ከነውበቱ እንዳለ ለማስረገጥና ተግባራዊ ምላሽ ለመስጠት ልብ ወለዱ መዘጋጀቱ በእግረ መንገድም የቋንቋው ሥነ ጽሑፋዊ እሴትና አጠቃላይ ማኅበረሰባዊ ጠቀሜታው እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ለማድረግ እንደሆነም አስተምረውታል፡፡
በመጽሐፉ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር መጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ፣ ‹‹አንዲት አገር ልታድግ የምትችለው ትናንትናዋን ከዛሬው ስታገናኝ፣ ዛሬዋን ከነገዋ ስታቆራኝ ነው፡፡ ትናንት የነበረንን ለመጠየቅ፣ ዛሬ ያለንን ለማወቅ፣ ነገ የሚኖረንን ለመተንበይ ደግሞ ወደ ኋላ ተመልሰን ጥንታውያን መጻሕፍትን መመርመር ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡