Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጥያቄ ውስጥ የወደቀው የኮንዶም ሥርጭት

ጥያቄ ውስጥ የወደቀው የኮንዶም ሥርጭት

ቀን:

በአንድ ወቅት የዓለም ሁሉ አንገብጋቢ ጉዳይ ነበር፡፡ መንግሥት፣ ማኅበረሰቡ፣ ቀበሌዎችና የወጣት አደረጃጀቶች እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃኑ፣ የኪነ ጥበብ ዘርፉ ሁሉ በአንድ ድምፅ አንድ ሆነው የዘመቱበትም ነበር፡፡ የሁሉም አጀንዳ ለነበረው ኤችአይቪ ዳጎስ ያለ በጀት ተሰፍሮ በየመንደሩ ይጣል ለነበረው ድንኳን ኤችአይቪ ምክንያት እንዳይሆን፣ ሁሉም የበኩሉን እንዲያደርግ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡

     የኤችአይቪን ሥርጭት ከደረሰበት ጫፍ አንስቶ ወደ 0.3 ለማስገባት የተባበረው ክንድ አልሰነፈም፡፡ በተደረገው ዘመቻ በአንድ ወቅት በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዕልቂት ምክንያት የነበረውን የኤችአይቪን ቀንበር መቀልበስ ተችሏል፡፡ አፍሪካን የሞት ቀጣና አድርጎ ከነበረው ወረርሽኙ ኢትዮጵያ ከብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች መካከል በግንባር ቀደምነት ነፃ ነኝ ስትል ውጥረቱ ረገብ አለ፡፡ በተለይም ቀልዱም ቁም ነገሩም ኤችአይቪ ለነበረው ማኅበረሰቡ ትልቅ ዕፎይታ ሆነ፡፡ የዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ትኩረትም ወደ ሌሎች ወቅታዊ አጀንዳዎች ሆነ፡፡

      ይህ መልካም ዜና የፈጠረው መረጋጋት ግን ቀስ በቀስ ወደ መዘናጋት ተቀየረ፡፡ በአንድ ወቅት በጣረ ሞት ይመሰል የነበረው ኤችአይቪ ታክሞ እንደሚድን እንደማንኛውም ዓይነት በሽታ አድርገው የሚያስቡ በዙ፡፡ በዚያም ላይ ሥርጭቱ ከዜሮ በታች ሆኗል መባሉ ኤችአይቪ ከኢትዮጵያ ምድር ጠፍቷል የተባለ ይመስል በበሽታው ላለመያዝ የሚደረገው ጥንቃቄ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ወረደ፡፡ ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤም በዚሁ መጠን አሽቆለቆለ፡፡

     ከዓመት በፊት የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያስቃኘው፣ ስለበሽታው ግንዛቤ ያላቸው ሴቶች 18 በመቶ፣ ወንዶች ደግሞ 31 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ 32 በመቶ የሚሆኑ አዲስ በኤችአይቪ ቫይረስ የሚያዙት ከ15 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡

     ከወራት በፊት የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ይፋ ያደረገው ሪፖርትም እ.ኤ.አ. በ2015 ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር 715,400 ሲሆን፣ 283,877 ወንዶች፣ 431,526 ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን፣ እ.ኤ.አ. 2016 ከቫይረሱ ጋር ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ቁጥር ወደ 718,500 ከፍ ማለቱንም አሳየ፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 754,256 እንደሚያሻቅብ ተተንብይዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2021 ድረስ ባሉት ዓመታት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በአፋር ክልልና እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ የቫይረሱ ሥርጭት እየቀነሰ እንደሚሄድ ሪፖርቱ ቢያሳይም፣ በሐረር፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ ክልል እንዲሁም በአዲስ አበባ የሥርጭት መጠኑ ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ እንደሚሄድ ተመልክቷል፡፡

      በሶማሌ ክልል እ.ኤ.አ. በ2015 የነበረው የቫይረሱ ሥርጭት 0.76 እንደነበር፣ እ.ኤ.አ. በ2021 ግን ወደ 0.8 ከፍ እንደሚል፣ በሐረር ክልል በተመሳሳይ ዓመት የሥርጭት መጠኑ 2.86 እንደነበር፣ በ2021 3.13 እንደሚደርስ፣ በጋምቤላም 4.01 እንደነበርና ወደ 4.49 እንደሚያሻቅብ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡ በአዲስ አበባ ደግሞ የቫይረሱ ሥርጭት መጠን እ.ኤ.አ. በ2015 4.9 በመቶ የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2021 ወደ 5.2 ከፍ እንደሚል ሪፖርቱ ያትታል፡፡   

     የኤችአይቪ ወረርሽኝ ግርሻ ማለት በሚቻል ደረጃ መመለሱን የብሔራዊ ፌዴራል መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤትም ሆነ በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት አድርገው የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት አምነዋል፡፡ ሥርጭቱ ከዜሮ በታች ወርዷል ሲባል የዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ትኩረት መቀየሩ፣ በኤችአይቪ ዙሪያ ይሠሩ የነበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በበጀት ምክንያት መቋረጣቸው ሥርጭቱ እንዲጨምር ምክንያት ከሚባሉት ተርታ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም እንደ ልብ የነበረው የመመርመርያ መሣሪያዎችና የኮንዶም ሥርጭትም ውስን መሆኑ ታይቷል፡፡

     ‹‹ኤችአይቪን በማገርሸት ደረጃ እንዲከሰት የሚያደርጉ ነባራዊ ሁኔታዎች አሉ፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ ቦጋለ በአዲስ አበባ ኤችአይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የማኅበረሰብ ንቅናቄ ባለሙያ ናቸው፡፡ የቅድመ መከላከል ሥራውን ለማከናወን ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ብቻ ተመርጠው ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡

      ‹‹አጠቃላይ የማኅበረሰቡ ክፍል ተመርምሮ ራሱን ለማወቅ ቢፈልግ እንደቀድሞው የመመርመርያ ኪቶችን አያገኝም፡፡ ማን መመርመር አለበት፣ ሥጋት ያለው የት ጋ ነው የሚለው ተለይቶ በሴተኛ አዳሪዎችና በመሳሰሉት ላይ ትኩረት ተደርጎ ነው የሚሠራው፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 90 በመቶ የሚሆነው ከቫይረሱ ጋር የሚኖር ሰው ተመርምሮ ራሱን ማወቅ አለበት የሚለውን ግብ ለማሳካትም ዓይነተኛው መንገድ ይህ ነው፡፡ መመርመርያ ኪቶችም እነዚህን የማኅበረሰብ ክፍል ለመድረስ ታስቦ ነው የሚመጣው፤›› ይላሉ አቶ ተስፋዬ፡፡

     የኮንዶምን ሥርጭት በተመለከተም ተመሳሳይ አካሄድ የተያዘ ሲሆን፣ ኮንዶምን ኑሯቸውን በሴተኛ አዳሪነት ለሚገፉ ሴቶች ቅድሚያ ሰጥቶ የማድረስ ዕቅድ ተይዞ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ‹‹በዚህ ሕይወት ውስጥ ያሉ ሴቶች ራሳቸውን ከበሽታው መከላከል የሚችሉት ኮንዶምን ሁል ጊዜ መጠቀም ሲችሉ ነው፡፡ ስለዚህም በመርህ ደረጃ ለሴተኛ አዳሪዎች የኮንዶም ተደራሽነት በስፋት ሊኖር ይገባል፤›› የሚሉት ባለሙያው ባሉበት ቦታ የማድረሱ ሥራ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡

     ይሁንና በሚፈልጉት መጠንና በአግባቡ እየተሠራጨ ነው ለማለት እንደሚከብድ አልሸሸጉም፡፡ በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ የሚሠሩ ሴተኛ አዳሪዎችን በአግባቡ ማግኘትና ኮንዶም ማድረስ ላይ ክፍተት አለ ብለዋል፡፡ በሆቴል አካባቢ ለሚሠሩትም ቢሆን ሆቴሎች ኃላፊነቱን ወስደው ኮንዶም በየክፍሉ በተገቢው መጠን ማሠራጨት ላይ ችግር አለ፡፡ መንገድ ላይ እየተንቀሳቀሱ ለሚሠሩም ቢሆን ኮንዶም በአግባቡ እየደረሰ አይደለም፡፡

     ከተቋቋመ ስምንት ዓመት ያስቆጠረው የያገባናል ፀረ ኤድስ በጎ አድራጎት ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት መስታወት ስሜ እንደምትለው፣ ያለው የኮንዶም ተደራሽነት ችግር በርካቶችን እየፈተነ ይገኛል፡፡ በመንግሥትና በተለያዩ በዘርፉ በተሰማሩ ተቋማት በነፃ እንዲታደሉ የሚሠራጩ ኮንዶሞችን በሽያጭ የሚያቀርቡ ተረካቢዎች መኖር ችግሩን ውስብስብ አድርጎታል፡፡ ከዚህም ባለፈ መዓዛ ያላቸውን ውድ ውድ ኮንዶሞችን መሸጥ የሚፈልጉ ድርጅቶች በነፃ የሚታደሉ ኮንዶሞች እንደ ልብ እንዳይገኙ የማድረግ ሥራ እንደሚሠሩ፣ በዚህም ሰዎች ሳይፈልጉ ከ50 ብር ጀምሮ እስከ 500 ብር የሚሸጡ ኮንዶሞችን ለመግዛት እንደሚገደዱ ለሪፖርተር ገልጻለች፡፡

     ‹‹በአንድ ወቅት ጥሩ ኑሮ የነበራቸው ባልታሰበ አጋጣሚ የሚበሉትን እስኪያጡ ይቸገራሉ፡፡ የቤተሰባቸውን ችግር ያዩ እናቶች ተደብቀው እየወጡ ተከፍሏቸው ይተኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በአንድ ጊዜ 20 ብር ተከፍሏቸው የሚተኙ ሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች 50 በመቶውን አልጋ ለሚያከራዩዋቸው ሰዎች ይከፍላሉ፡፡ እንዲህ ያሉት ሴቶች የ50 ብር ቀርቶ የአምስት ብር ኮንዶም ለመግዛት በጣም ይቸገራሉ፤›› ትላለች፡፡ በዚህ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት በነፃ የሚቀርበውን ኮንዶም ማግኘት ካልቻሉ አደገኛውን አማራጭ ለመውሰድ ይገደዳሉ፡፡

     ‹‹እየተሠራ ያለው ቀላሉ ሥራ ነው፡፡ የኮንዶም ተደራሽነት ችግር ምንም ጥያቄ የለውም የታወቀ ነው፤›› የሚሉት አቶ ተስፋዬ የኮንዶም ሥርጭት ስትራቴጂ ተቀርፆ ሥራ ላይ ሊውል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች የሚበዙበትን ቦታ በመለየትና የማሠራጫ ጣቢያዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም በጣቢያዎቹ ያለውን የኮንዶም ክምችት እየተከታተሉ ምላሽ የሚሰጥበትን አሠራር ለመዘርጋት በስትራቴጂው ታቅዷል፡፡  

     በድህነት ምክንያት ተገደው በሴተኛ አዳሪነት የሚኖሩ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ በማድረግ ከዚህ ሕይወት እንዲወጡ ለማድረግ ያገባናል ፀረ ኤችአይቪ ማኅበር ከሻዴም ሚዲያ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንት ኦርጋናይዚንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጋር በመተባበር የሚሠሩትን አንድ ፕሮጀክት ኅዳር 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ይፋ አድርገዋል፡፡ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት 72 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ያቀዱ ሲሆን፣ በገንዘቡም ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ8,000 በላይ የሚሆኑ ሴተኛ አዳሪዎችን ከዚህ ሕይወት ሙሉ ለሙሉ እንዲላቀቁ ለማድረግ ግብ ተይዟል፡፡ በዚህ ተግባር ትህትና የተባለው በሻዴም ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን የተሠራው ፊልም የገቢ ማሰባሰቢያው ዋና ግብዓት ይሆናል፡፡ ትህትና የተባለው ከኤችአይቪ ጋር ተያያዥ የሆነ ጉዳይ የሚያነሳውን ፊልም በመላው አገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተዘዋውሮ በማሳየት ግንዛቤ መፍጠርና ገቢ የማሰባሰብ ሥራ እንደሚሠራ የሻዴም ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ሔኖክ ይርጋ ተናግረዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...