Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመቄዶንያ ሕንፃ ሊገነባ ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመቄዶንያ ሕንፃ ሊገነባ ነው

ቀን:

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል አሥር ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገቡ፡፡ የአየር መንገዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን ጨምሮ ከአንድ ሺሕ በላይ ፓይለቶች እያንዳንዳቸው ከኪሳቸው አሥር ሺሕ ብር በማዋጣት ነው ድርጅቱ ለመርዳት ቃል የገቡት፡፡ ከቀናት በፊትም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለመቄዶኒያ ሁለት አምቡላንሶች መለገሱ የሚታወስ ነው፡፡

  የአየር መንገዱ ሠራተኞች ማዕከሉን በጎበኙበት ዕለት አሥር ተሸከርካሪዎች፣  አልባሳት፣ የምግብ ማብሰያ ዕቃዎችና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች ለማዕከሉ አበርክተዋል፡፡ አየር መንገዱ ከዚህም በተጨማሪ  ወደ ውጭ አገር ሄደው ለሚታከሙ በዓመት የአንድ መቶ ደርሶ መልስ ነፃ የአየር ትኬት፣ እንዲሁም ለመቄዶኒያ የተለያዩ የጁስ ማሽኖችን በመግዛት ከውጭ አገር የሚረከባቸውን ጁሶች በአገር ውስጥመተካት ቃል ገብቷል፡፡

 ተቋሙ አዳዲስ አውሮፕላኖችን ሲያስገባም ለመቄዶንያ ነፃ የካርጎ አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ በበረራ ላይ ባሉ አውሮፕላኖች ሁሉ ማዕከሉን በማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታገዝበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ሳጥኖችም በአውሮፕላን ውስጥ በማስቀምጥከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመሥራት ማዕከሉን ለማገዝ ቃል መግባቱም ታውቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አሕመድ (ዶ/ር) መቄዶኒያን በጎበኙበት ወቅት ሁሉም የመንግሥት ድርጅቶች መቄዶኒያን እንዲረዱ ባሳሰቡት መሠረት ነው ተቋማት እየረዱን ያሉት፤›› የሚሉት የድርጅቱ መሥራች አቶ ቢኒያም በለጠ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ለመቄዶኒያ በየክፍለ ከተማው ቦታ ለመስጠት የገባው ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ወሳኝ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከተቋቋመ ሰባት ዓመታትን ያስቆጠረው መቄዶኒያ በአሁኑ ወቅት 2,000 ለሚሆኑ አረጋውያን፣ የአዕምሮ ሕሙማንና የአልጋ ቁራኛ ለሆኑ ዜጎች ከለላ ሆኗል፡፡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የቅበላ አቅሙን ወደ 10,000 ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ የሚናገሩት መሥራቹ፣ በዚህ ረገድ ከመንግሥት ተቋማት የሚገኘው ድጋፍ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ዋነኛ ችግራችን ሕክምና ነው፡፡ የተለያዩ የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው የሚረዱን ቢሆንም ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ሆስፒታሎች በቀን እስከ 50 ጊዜ ድረስ እንመላለሳለን፡፡ አብዛኛዎቹ በተቋሙ ውስጥ የሚገኙ ተረጂዎች የአልጋ ቁራኛ በመሆናቸው ሕክምና ትልቁ ጉዳያችን ነው፤›› ያሉት አቶ ቢኒያም፣ አያት ኮንዶሚኒየም አካባቢ በሚገኘው የመጠለያ ማዕከል ውስጥ የተጀመረው የሕንፃ ግንባታ ለዚህ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

700 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቀው ባለአሥር ፎቅ ሕንፃው ከ3,000 ካሬ ሜትር በላይ በሆነ ቦታ ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ሕክምና መስጠት የሚያስችል የሕክምና ማዕከሉ ከ12 ሺሕ በላይ አልጋ እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ አጠቃላይ የሕንፃው ግንባታ 70 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቢሆንም ዮቴክ ኮንስትራክሽን በነፃ እየገነባ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ ግንባታውን ለማከናወን የቁፋሮ ሥራም ተጀምሯል፡፡

አጠቃላይ ወጪውን ከማኅበረሰቡና ከተቋማት በሚሰበሰብ ገንዘብ የሚሸፈን ይሆናል፡፡ እስካሁን በተገኘ ድጋፍ 60 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ የተለያዩ የግንባታ ግብዓቶች ተሸምተዋል፡፡

እያንዳንዱ ወለል ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ብር የሚጠይቀውን የዚህን ሕንፃ ግንባታ በተለይም የመንግሥት ተቋማት በስማቸው እንዲገነቡት ታስቧል፡፡ በዚህ መሠረት የሕንፃውን አምስት ወለሎች እንዲገነባ የተጠየቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ራሱን የቻለ ሌላ ሕንፃ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡

ፓይለቶች ከኪሳቸው አዋጥተው ከሚሰጡት አሥር ሚሊዮን ብር ተጨማሪ የሆነው የሕንፃ ግንባታ ማዕከሉ በየክፍለ ከተማው ሊሰጠው ቃል በተገቡ ቦታዎች በአንደኛው እንደሚሆን ለሪፖርተር የገለጹት መሥራቹ በመንግሥትና በማኅበረሰቡ ዕገዛ ያቀድነውን እናሳካለን ብለዋል፡፡ በማዕከሉ የሚገኙ የተረጂዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝና የማስፋፊያ ግንባታዎች በፍጥነት እንዲያልቁ ሁሉም የበኩሉን እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት ማዕከሉን የጎበኙት ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸው የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው ተረጂዎች የሚሆኑ ባለሞተር ዊልቸሮችን ለማዕከሉ ለግሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ አገር በቀል የመረዳጃ ተቋማት መካከል ከግንባር ቀደሞቹ የሚጠቀሰው መቄዶኒያ ከተመሠረተበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ጎዳና የወደቁ የአዕምሮ ሕሙማን፣ ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንን፣ የሚያስታምማቸውም ሆነ የሚታከሙበትን ገንዘብ የሌላቸውና የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ዜጎችን በመጠለያው አሰባስቦ ተገቢውን እንክብካቤ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...