Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የኦሮሚያ ልማት ማኅበር የብር ኢዮቤልዩ አበርክቶ

የኦሮሚያ ልማት ማኅበር (ኦልማ) በ1986 ዓ.ም. ሲቋቋም ክልሉ እንደ ሌሎች ክልሎች መሠረተ ልማት ያልተስፋፋበትና ያሉትም መሠረተ ልማቶች ቢሆኑ በከተማ አካባቢ የተወሰኑበት ነበር፡፡ መንግሥት አካባቢውን ለማልማት ከሚሠራው በተጨማሪ ኦልማ ክፍተቶችንና ጉድለቶችን ለመሙላት እየሠራ ይገኛል፡፡ የብር ኢዮቤልዩን የተለያዩ የልማት ሥራዎቹንና ጅማሮዎችን በማስተዋወቅ እያከበረ የሚገኘው ኦልማ የሩብ ምዕት ዓመት ጉዞውን በተመለከተ ዋና ዳይሬክተሩን አቶ ደጀኔ ኢትቻን ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ መቋቋም ምክንያት ምን ነበር?

አቶ ደጀኔ፡- መንግሥት በክልሉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ብቻውን ስለማይችል ለምን ሚናችንን አንወጣም በሚል በሃይማኖትና በጾታ ሳንለያይና ነጋዴ ገበሬ ሳንል የለማችና ዜጎቿ የተባበሩባት፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ክልል ተፈጥራ ለማየት አልመን ነው ያቋቋምነው፡፡ ኅብረተሰቡ የራሱን ጉዳይ በራሱ መወሰን እንዲችል የማብቃት ራዕይም ይዞ ነው የተቋቋመው፡፡ ስንነሳ የእናቶችና የሕፃናት ሞት የቀነሰባትና የለማች የኦሮሚያ ክልልን ማየትን አልመን እንጂ ይህንን ራዕይ ለማሳካት ገንዘብ አልነበረም፡፡ እናቶች መሠረተ ልማት ባለመኖሩ በትንሽ የሕክምና እገዛ መዳን ሲችሉ ሁለት ነፍስ ይዘው ይሞቱ ነበር፡፡ ይህንን ችግር አልፈው የሚወለዱት ደግሞ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ የከብት እረኛ እየሆኑ ሕዝቡ ከፍተኛ ኋላቀርነት ውስጥ ነበር፡፡ ደኑ እየተመነጠረ በመሄዱም የክልሉ የተለያዩ ዞኖች ለረሃብና ለችግር እየተጋለጡና ነዋሪዎችም ከቤታቸው የሚሰደዱበት ወቅት ነበር፡፡ ማኅበሩ የተቋቋመው እነዚህን ዋና ዋና ቸግሮች ለመቅረፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ምን ሠራችሁ?

አቶ ደጀኔ፡- በዋናነት ትምህርት ነው፡፡ ንፁህ ውኃ ማቅረብ፣ የጤና አጠባበቅን ተደራሽ ማድረግና የአካባቢ እንክብካቤ ማኅበሩን ስናቋቁም ዋና ዓላማ አድርገን የተነሳንባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ይህንን ዓላማ ለማሳካት የክልሉ ተወላጅ በገንዘቡና በእውቀቱ እየተሳተፈ ችግሩን እንዲቀርፍ እያደረግን ነው፡፡ ከአባላት ገንዘብ መሰብሰብ፣ የገቢ ማሰባሰቢያ ማካሄድ፣ ከዕርዳታ ሰጪዎች ገንዘብ ማግኘትና የገቢ ምንጭ ማጎልበት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የነደፍነው ስትራቴጂ ነው፡፡ ሥራችንም መንግሥት ያቀደበትን ሳይሆን ቀዳዳ ያለበትና መሥራት ያልቻለው ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአካባቢው የነበረው አንዱ ችግር የትምህርት ቤት ዕጥረት ነው፡፡ ማኅበሩ በትምህርት ዙሪያ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል?

አቶ ደጀኔ፡- 731 ትምህርት ቤቶች ገንብተንና ሙሉ ቁሳቁስ አሟልተን ተማሪዎች እንዲገቡ አድርገናል፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች መጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ናቸው፡፡ ቀድሞ የነበሩ ከ1,000 በላይ ትምህርት ቤቶችን በማስፋፋት፣ በማሻሻልና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በመሥራት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የሠራችሁት የለም?

አቶ ደጀኔ፡- ጅማ ዩኒቨርሲቲ እንዳሁኑ ሳይጠነክር ልማት ማኅበሩ ድጋፍ ሲያደርግ ነበር፡፡ የመምህራን ኮሌጆችና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይም ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ትምህርት ቤት ስትገነቡ መምህራንና የትምህርት ግብአትም ወሳኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ ያላችሁ እገዛ ምን ይመስላል? ልጆች ትምህርት ቤት እንዲመጡስ ምን አግዛችኋል?

አቶ ደጀኔ፡- የእኛ ሥራ ዕድሉን መፍጠር ነው፡፡ የልማት ሥራውን ከሠራንና ቁሳቁስ ካሟላን በኋላ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እናስረክባለን፡፡ የውስጥ ሥራውን አንሠራም፡፡ በጎልማሶች ትምህርት ላይ ግን በሠፊው ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግር በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ማኅበሩ በዚህ ዘርፍ ምን አበርክቷል?

አቶ ደጀኔ፡- የንፁህ መጠጥ ውኃ ስንል ማዕከል የምናደርገው ሴቶችን ነው፡፡ በትምህርትም ሆነ በጤናው ዘርፍ ስንንቀሳቀስ በዋናነት የሴቶችን ችግር ለመቅረፍ አልመን ነው፡፡ የመጠጥ ውኃን በተመለከተ ከ1,800 በላይ የውኃ ፕሮጀክቶችን ሠርተን በተሠሩባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ አድርገናል፡፡ ዜጎችም በውኃ ወለድ በሽታ እንዳይጠቁና ምርታማ እንዲሆኑ አግዘናል፡፡ በሐረርጌ የምግብ ዋስትና ባልተረጋገጠበት አካባቢ በመድረስ በመስኖ ሥራ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው መስኖ በስፋት እየተሠራበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ የማኅበሩ አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

አቶ ደጀኔ፡- የጤና ኤክስቴንሽን እንዳሁኑ ሳይለመድ የዛሬ 17 ዓመት ነበር ኦሮሚያ ልማት ማኅበር በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የጀመረው፡፡ ቀይ ዩኒፎርም የለበሱና ኮፍያ ያደረጉ በጎ ፈቃደኖች የጤና ባለሙያዎች አሳትፈን በየገጠሩ ሲሠሩ ነበር፡፡ በክልሉ 206 ጤና ጣቢያ ሠርተንና ቁሳቁስ አሟልተን አስረክበናል፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ ጥረት አድርገናል፡፡ በአጠቃላይ ባለፉት 25 ዓመታት ከአራት ሺህ በላይ ፕሮጀክቶችን አራት ቢልዮን ብር ያህል ወጪ በማድረግ በክልሉ ሠርተናል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ሕዝቡ የራሱን ችግር በራሱ የመፍታት አቅሙን በተግባር ያረጋገጠበት ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ጣቢያዎችና የውኃ ፕሮጀክቶች ሲሠሩ በጉልበትና በባለቤትነት ስሜት ሲያግዝ ቆይቷል፡፡ በተለይ በ2003 ዓ.ም. መልሰን ከተቋቋምን በኋላ ጥሩ ሠርተናል፡፡ ከ1989 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ማኅበሩ ምንም የማይታይበት ወቅት ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከ1989 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ለምንድነው ደብዛው የጠፋው?

አቶ ደጀኔ፡- ሕዝቡ በጋራ ተሰብስቦ መሥራቱ የማይፈለግበት ወይም የፖለቲካ ችግር ይሆናል ብለን ነው የምናምነው፡፡ በ1989 ዓ.ም. ቴሌቶን አዘጋጅተን 107 ሚልዮን ብር ተሰብስቦ ገንዘቡም ገቢ ሆኗል፡፡ በወቅቱ ሕዝቡ በነቂስ መውጣቱ ይመስለናል ማኅበሩ ለ12 ዓመታት ያህል እንዳይታይ ያደረገው፡፡ ህዝቡን ለማወያየት፤ ስራዎችን ተከታትሎ ለማስፈጸም የሰው ኃይሉ የተዳከመ ነበር፡፡ ስለሆነም 2002 ዓ.ም. ላይ ተወያይተን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት አዳዲስ የማኔጅመንት አባላት ተመድበው መሥራት ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- 107 ሚሊዮን ብሩስ?

አቶ ደጀኔ፡- እንቅስቃሴው ጠፋ እንጂ በብሩ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ያነሳኋቸው ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡ 2002 ዓ.ም. ላይ ችግራችንን ከመፍታታችን በፊት የነበረው ዋናው ችግር የሕዝብ ግንኙነት አለመኖር ነው፡፡ የአደረጃጀት ችግርም ነበር፡፡ የነበሩን አባላትም ከአንድ ሚልዮን በታች ነበሩ፡፡ ከአባላት የሚሰበሰበውም በቂ አልነበረም፡፡ ትልቁ ገቢም አራት ሚልዮን ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ በዓመት ከአንድ ሚልዮን በታች ነበር ከአባላት የሚሰበሰበው፡፡  ረጂ ድርጅት በዓመት ከሚሰጡት ውጭ ማኅበሩ ስም ይዞ ነበር የቆየው፡፡ ስለሆነም ሥራውን ማስተዋወቅ፣ አባላት ማፍራትና ገቢ መጨመር፣ ገቢ የሚያስገኝ ሥራ መሥራት፣ ከዕርዳታ ሰጪ የምናገኘውን ማሳደግና ሌሎችንም መሥራት እንዳለብን አስቀምጠን ተነሳን፡፡ ለማኅበሩ ሕንፃ መሥራትና ልዩ የአዳሪ ትምህርት ቤቶች መገንባት ብቻ ሳይሆን በክልሉ ውስጥ ጥሩ ውጤት የሚያመጡ ተማሪዎችን ማስተማር በሚል በ2005 ዓ.ም. 65 አባላት ያለው ኮሚቴ አዋቅረን ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ለመገንባት አቀድን፡፡ በስትራቴጂያችን ያስቀመጥነው ሦስት ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንገነባለን፣ ተማሪም እንቀበላለን ብለን ነው፡፡ በአጭር ጊዜ በተለይ የክልሉ ተወላጆች ተረባርበው በ2006 ዓ.ም. በአዳማ በተገነባው ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት 200 ተማሪዎች ተቀብለን ማስተማር ጀመርን፡፡ በ2007 ዓ.ም. በጉደር በነባር ትምህርት ቤት ላይ ጀመርን፡፡ ሦስተኛው ለገጣፎ ላይ በ436 ሚልዮን ብር ለመገንባት ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ትምህርት ቤቶቹን ስንከፍት የነበረን ራዕይ ሕዝብና ኮሚቴዎቹ ብቻ ነበሩ፡፡ ኮሚቴው ተሰብስቦ የተወሰነ ገንዘብ አዋጣ፣ የሐረርጌ ገበሬዎች ደግሞ 300 በሬ ሰጡን፡፡ በዚህ ትምህርት አስጀመርን፡፡ በ2006 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ስምንት ሴቶች ሁሉንም ‹‹ኤ›› አምጥተዋል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ላይ ደግሞ 48 ሴቶች ሁሉንም ‹‹ኤ›› አምጥተዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ጉደር ላይ 113 ተማሪ ተፈትኖ 112ቱ ሙሉ ‹‹ኤ›› አምጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከስምንተኛ ክፍል ነው የሚቀበለው?

አቶ ደጀኔ፡- ከስምንተኛ ክፍል ጥሩ ውጤት ያመጡ ተወዳድረው ነው የሚገቡት፡፡ አዳሪ ትምህርት ቤቱ ከዘጠኝ እስከ 12ኛ ክፍል ነው፡፡ በትምህርቱ ሲታይ ሴቶቹ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ አፈርማቲቭ አክሽን ለሴቶች አንጠቀምም፡፡ የሴቶች ችግር በገመገምነው መሠረት ከስምንተኛ ክፍል በፊት መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ሴቶች ዕድሉ ከተፈጠረላቸው ይሠራሉ፡፡ ያነሰ ውጤትም የላቸውም፡፡ በ2009 ዓ.ም. ዩኒቨርሲቲ ከገቡት 163 ተማሪዎች አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው፡፡ በ2010፣ 103 ተማሪዎች ተፈትነው በአገር ደረጃ ከ600 በላይ ካመጡት 96 ተማሪዎች ዘጠኙ የእኛ ተማሪዎች ናቸው፡፡ ሪከርድ የሰበሩም ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲም ገብተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ከገቡ በኋላ ያላቸውን አቀባበልም አይተናል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎች ከ3.8 በላይ ነው ያላቸው፡፡ በትምህርት ቤታችን በተለይ በአራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንሰጣለን፡፡ በአገርም በዓለምም ተወዳዳሪ መሆን ስላለባቸው አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ቻይንኛና እንግሊዝኛ ይማራሉ፡፡ ቻይና ውስጥ ስኮለካርሺፕ አግኝተው በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ እየተጠማሩ ያሉ ልጆች አሉን፡፡ በትርፍ ጊዜያቸው ቻይናዎችን እንግሊዝኛ ያስተምራሉ፡፡ ትምህርትን በተመለከተ ባለፉት 25 ዓመታት ስኬታማ ነበርን ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን አገራቸውን እንዲያገለግሉ፣ በሥነ ምግባር እንዲታነጹ የሚሠሩ ሥራዎችን ቢገልጹልን? ጎበዝ ተማሪዎች የውጭ ዕድል ሲያገኙ በዛው ይቀራሉ፡፡ ይህ እንዳይሆንስ ምን ተሠርቷል?

አቶ ደጀኔ፡- ተማሪዎቻችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንፈልጋለን፡፡ የምናስተምራቸው ደግሞ የቤተሰባቸው ሳይሀኑ የሕዝብ መሆናቸውን ነው፡፡ የጉደሩን በፀጥታ ችግር ምክንያት ዘግተን ወደ አዳማ ያመጣናቸውንና በአዳማ የነበሩትን በአጠቃላይ ጨምረን 612 የአዳሪ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አሉን፡፡ ለተማሪዎቹ የሚያስፈልገውን በሙሉ ልማት ማኅበሩ ይሸፍናል፡፡ ላይብረሪ 16 ሰዓት ይሠራል፡፡ ኢንተርኔት 24 ሰዓት አለ፡፡ ልማት ማኀበሩ ቢያቀናጅም ይህንን ሁሉ የሚያሟላው ሕዝብ ነው፡፡ የፀጥታ ችግር ባለበት ወቅት ተማሪዎች ትምህርት እንዳያቋርጡ የምዕራብ ሸዋ ገበሬዎች 250 ኩንታል ጤፍ ሰጥተዋል፡፡ ወለጋ የፀጥታ ችግር መኖሩን እንሰማለን፡፡ ሆኖም ከምዕራብ ወለጋ 140 ኩንታል ጤፍ አምጥተውልናል፡፡ ከአርሲና ከሌሎች አካባቢዎች ምግብ ይመጣል፡፡ ልጆቹን እያስተማረ ያለው ሕዝቡ ነው፡፡ በመሆኑም ልጆቻችን ከዚህ ወጥተው ሕዝቡን ለማገልገል ነው ችኮላቸው፡፡ ራስ ወዳድ አይደሉም፣ በሥነ ምግባር የታነጹም ናቸው፡፡ የሕዝቡን ሰብዕና የሚያከብሩ ናቸው፡፡  ዩኒቨርሲቲ ሲገቡም ተከታትለን ዓይተናል፡፡ መልካምና ሌሎችን የማገልገል ፍላጎት አላቸው፡፡ ጡረታ ከወጡ ሰዎች ልምድ እንዲቀስሙም እያደረግን ነው፡፡ ትልቁ ሥራ ስብዕናቸው ላይ ነው፡፡ ነገ ሕዝብ እንደሚመሩ፣ እንደሚያገለግሉ፣ ገበሬው ባዶ እግሩን እየሄደ እንደሚያስተምራቸው፣ ልማት ማኅበሩን በብዛት የሚደግፈው የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ባለሀብቱ ሳይሆን አርሶ አደሩ መሆኑን ያውቃሉ፡፡ የሚማሩት ውለታ ለመመለስና አገር ለማልማት እንጂ ውጭ ሄዶ ለማገልገል አይደለም፡፡ የልማት ማኅበሩ ዓላማ ሙሉ ሰው መፍጠር እንጂ በቀለም ትምህርት ብቻ ማካበት አይደለም፡፡ የትኛውም የፈረሰ አገር የሚገነባው ልጆችን በማስተማር ነው፡፡ ትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ የልማት ሁሉ ልማት የሰው ሀብት ልማት ነው፡፡ ይህን ስንሠራ አገር ትሻገራለች፡፡ አገሪቱ ያላትን ሀብት ማስተዳደር የሚችሉ ብቁ ዜጎች መፍጠር አለብን ብለን እየሰራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የተፈጥሮ ሀብት እንደማንኛውም የአገሪቱ ክፍል በክልሉም እየተጎዳና ፓርኮች እየተመናመኑ ይገኛሉ፡፡ ማኅበሩ እዚህ ላይ ምን ሠራ?

አቶ ደጀኔ፡- ማኅበሩ 7.1 ሚሊዮን አባላት አሉት፡፡ ከነዚህ 300 ሺሕ ያህሉ ያለምንም ክፍያ የሚሠሩ ናቸው፡፡ በአካባቢ ልማት ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በክልሉ ወደ 47 ፓርኮች አሉ፡፡ ደን ማልማት ብቻ ሳይሆን መሬቱን በመጠበቅና በመጠቀም ገበሬው ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን ፓርኩን መልሶ የማረስ ችግር እየገጠመን ነው፡፡ ከብቶችን መልቀቅም አለ፡፡ ሰበታ ደበል አካባቢ 600 ሔክታር መሬት ፓርክ እያለማን ቢሆንም ትልቅ ፈተና እየገጠመን ነው፡፡ የፓርኩ ዛፎች መልሰው በቅለዋል፡፡ ግን ሌሊት ላይ ታርሶ የሚያድርበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህ እንዳይሆን እያስተማርን ቢሆንም ትልቅ ፈተና አለ፡፡ በተለይ በአምስት ዓመት ውስጥ ችግኝ ተከላን ጨምሮ በዘርፉ ትልቅ ትምህርት ያገኘንበት ነው፡፡ ሰበታ ሃሮ ጅራ፣ ዲማ ሆሮ ጉድሩና ሌሎችም ላይ እየሠራን ጫካ እየሆኑ ነው፡፡ ሆኖም መሬቱ እያነሰ ሰው እየበዛ መምጣቱ  ፓርኮቹን በቅጡ ለማልማት ፈተና ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- በዓመት ከአባላት ምን ያህል ትሰበስባላችሁ?

አቶ ደጀኔ፡- እስከ 130 ሚሊዮን ብር ከአባላት እንሰበስባለን፡፡ የአባላትን፣ የዕርዳታ ሰጪዎችንና የማኅበሩ ደጋፊዎች ለማመሥገንም ዘንድሮ ማክበር የጀመርነው የልማት ማኅበሩ 25ኛ ዓመት ወሳኝ ነው፡፡ አባላት እንዲጨምሩ፣ ማኅበሩ እንዲጠናከር፣ የልማት ሥራዎች እንዲጎለብቱ ዓላማ አድርገንም በዓሉን እያከበርን ነው፡፡ ትምህርት ዋናው ሥራችን ሲሆን፣ በክልሉ የሚማር የማንኛውም ብሔር ተወላጅ ትምህርት እንዲያገኝ፣ በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ተወዳድሮ ገብቶ ለአገሩና ለሕዝቡ እንዲጠቅም አልመን እየሠራን ነው፡፡ ማኅበሩ በአባላት ላይ ብቻ እንዳይመረኮዝ ገቢ የሚገኝበት ሥራም ተጀምሯል፡፡ በአዳማ በ241 ሚሊዮን ብር አንድ የንግድ ማዕከል እየሠራን ነው፡፡ ለገጣፎ እየተሠራ ያለው አዳሪ ትምህርት ቤት ትልቁና ብዙ ተማሪ ሊያስተናግድ የሚችል የአገራችን ተስፋ ነው፡፡ ይህን ሁሉ የምንሠራው አገራችንን ወደ ዕድገት ለማሻገር ነው፡፡ ከብሔራዊ ሎተሪ ጋር ቶምቦላ አዘጋጅተናል፡፡ ሕዝቡም እየተሳተፈ ነው፡፡ እንዲሳተፍም እንጠይቃለን፡፡ ሩጫና ኮንሰርቶችም ይከናወናሉ፡፡ በውጭ ደግሞ የሕክምና ባለሙያ የሆኑት በሙያቸው እንዲሳተፉ፣ ለልማት ማኅበሩ ገንዘብ እንዲደግፉ፣ በቁሳቁስ እንዲያግዙ በተለይ  በጤናና ትምህርት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ አቅደን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሲታቀድና ሲሠራ ሰላም ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ማኅበሩ ከሰባት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት፡፡ ወጣቶችም የማኅበሩ አባላት ናቸው፡፡ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳይደናቀፉ ዕድሉ ያላቸው አባሎቻችሁ የተለያየ ዘዴዎችን በመጠቀም ስለሰላም እንዲሰብኩ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ ደጀኔ፡- ልማትና ሰላም መለያየት አይችሉም፡፡ ሰላም ከሌለ እንኳን ተማሪ ማብቃት አንድ ስኒ ቡና መጠጣት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ትምህርት ቤቶቻችን የእውቀት ማዕከል እንዲሆኑ መዝናኛቸው ቤተ መጻሕፍት እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡ ልጆች በማያውቁት ጉዳይ የማያውቁት ቦታ መዋል የለባቸውም፡፡ ለዚህም ቤተሰብ ልጁ እንዲማር ከብጥብጥ ደም መፍሰስ እንጂ ምንም እንደማይገኝ፣ ዛሬ ልጅ ቢሆንም ነገ አገር እንደሚጠቅም ማስተማር አለበት፡፡ የሃይማኖት አባቶች፣ መምህራን መላ ኅብረተሰቡ የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ሰላም እያንዳንዱ ቤት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ወላጅ የልጁን ውሎ ካወቀ ሰላም ይሆናል፡፡ የሰላም ዋጋ ውድ ነው፡፡ በአገራችን ያለንን ሀብት ብንጠቀም አርሲና ባሌ ያለውን ለጥ ያለ መሬት ብናርስና በዓመት ሦስቴ ብናመርት ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን መመገብ እንችላለን፡፡ ስለሆነም ሁሉም አካባቢ ለሰላም እንዲሠራ ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት የቆመው የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ፋውንዴሽን

የቀድሞ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት አባላት ለአገራቸው የሕይወት መስዋዕትን ለመክፈል የወደዱ፣ ለአገራቸው ክብር ዘብ የቆሙና ውለታን የዋሉ ናቸው፡፡ እነኚህ የአገር ጌጦች በአገሪቱ በተከሰተው የሥርዓት ለውጥ...

ገደብና አፈጻጸም የሚሹ የአየር ሙቀት መጠንና የካርቦን ልቀት

የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቋቋም የዓለም ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያስተሳስረው ቡድን (ግሩፕ) ሲ-40 (C-40) ተብሎ ይታወቃል፡፡ ከተቋሙ ድረ ገጽ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ አዲስ አበባን ጨምሮ የ40ዎቹ ከተሞች...

ሕፃናትን ከመስማት ችግር የሚታደገው የቅድመ ምርመራ ጅማሮ

‹‹መስማት ለኢትዮጵያ›› በጎ አድራጎት ማኅበር በጨቅላ ሕፃናት ደረጃ የመስማት ችግር እንዳይከሰትና በሕክምናውም ዙሪያ በዘመኑ ሕክምና መሣሪያዎች በመታገዝ ሕክምና ለመስጠት ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የተመሠረተ ነው፡፡...