Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየሥርዓተ ፆታ እኩልነት በረከት ወይስ እርግማን?

የሥርዓተ ፆታ እኩልነት በረከት ወይስ እርግማን?

ቀን:

በሀብታሙ ግርማ

መጣጥፉን ሳሰናዳ በትዳርና ቤተሰብ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ትንታኔ ለመስጠት የሚያስችል የትምህርት ዝግጅት ኖሮኝ ሳይሆን፣ እንደ ግለሰብ የተሰማኝን ትዝብት ለመግለጽ፣ በዚያውም የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች (Sociologists) ወይም የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ምሁራን (Social Psychologists) ትንታኔ እንዲሰጡበትና ጥናት እንዲያደርጉበት ለመጠቆም ያህል ነው፡፡

በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ምኅዳር በቅርብ ዓመታት ካስተዋልናቸው ሁነቶች ውስጥ የሥርዓተ ፆታ ለውጥ አንዱ ነው፡፡ ይህ የሥርዓተ ፆታ ለውጥ ማኅበራዊ ልማታችንን ሊያሳድጉ፣ ትዳርና ቤተሰብን ሊያበለፅጉ የሚያስችሉ በርካታ ዕድሎችን የመፍጠሩን ያህል ትዳራችንን ሊያውኩ፣ ቤተሰባችንን ሊበክሉ የሚችሉ በርካታ አጋጣሚዎችም ይዟል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ዋናው የሥርዓተ ፆታ ለውጥ ነው፡፡ በዘመናችን ከትዳርና ከቤተሰባዊ ጉዳዮች አንፃር የምናያቸውን ለውጦችን (አሉታዊ ነገሮችን) ለመረዳት፣ የትዳርና የሥርዓተ ፆታን ቁርኝት ማንሳት ይጠይቃል፡፡ የዚህ መጣጥፍ ዓላማ በተለይ በቅርብ ዓመታት ወዲህ እየታየ ስላለው የሥርዓተ ፆታ ለውጥና ይህም በትዳር (ቤተሰብ) ላይ እያሳደረ ያለው፣ ወደፊትም የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድነው? የሚለውን መቃኘት ነው፡፡

ትዳር ምንድነው? ዓላማውስ?

ሁለት ጥንዶች በአንድ ጎጆ ለመኖር መስማማት የሚለው ትዳር ምንድነው ለሚለው ጥያቄ የተሟላ መልስ አይሆንም፡፡ የትዳር ምንነት የትዳርን ባህሪያት ከማሳየት አንፃር መሆን አለበት፡፡ የትዳርን ባህሪያት ከመረመርን የትዳርን ዓላማ እንገነዘባለን፡፡ በመንፈሳዊ ዓላማው ትዳር የሰውን ልጅ ከብቻ ሕይወት መንፈሳዊ (ሥነ ልቦናዊ) ስንክሳሮች ለመጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ትዳር የሰው ልጅ የመፍጠር ዓላማ ማስፈጸሚያ መሣሪያ ነው፡፡ የአምላክ ደመወዙ ምሥጋና ነውና ፈጣሪ የሰውን ልጅ የመፍጠሩ ዓላማ ምንም ሳይሆን ምሥጋናን እንዲቸሩት ነው፡፡ ቢያንስ ፈጣሪን መፍራት ከሰው ልጆች ሁሉ ይጠበቃል፡፡ ፈረኃ እግዚአብሔር ያለው፣ በዚህም ፈጣሪውን ከሚያስከፉ ድርጊቶች እንዲታቀብና ፈጣሪን እንዲያስብ፣ ለሕግጋቱና ለአስተምህሮቱ የተገዛ፣ በአካልና አዕምሮ እንዲሁም መንፈሳዊ ጤንነት ያለው የሰው ዘር የሚፈጠረው ደግሞ ከጤነኛ ትዳር ነው፡፡

ከዓለማዊ ሕይወት አንፃር ደግሞ ትዳር የአንድ አገር ህልውና ነው፡፡ የአንድ አገር ሉዓላዊነት ሳይሸራረፍ የሚከበረው ጠንካራ አገር ሲኖር ነው፡፡ ጠንካራ አገርን የሚገነባው ጠንካራ ሕዝብ ነው፡፡ የጠንካራ ሕዝብ ምንጩ ደግሞ ጠንካራ ትዳርና ቤተሰብ ነው፡፡ በመሆኑም የትዳርና የቤተሰብ ጉዳይ የአገርና ሕዝብ ህልውና (ሉዓላዊነት) ጉዳይ ነው፡፡ እናም ትዳርን ለመደገፍና ከጥፋት ለመጠበቅ የሚደረግ ጥረት አርበኝነት ነው፡፡

ሥርዓተ ፆታ ምንድነው?

ከማኅበረ ኢኮኖሚ፣ ባህላዊ፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንፃር የሁለቱን ፆታዎች (ወንድና ሴት) ግንኙነት የሚያጠና የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ሥርዓተ ፆታ ይባላል፡፡ ሥርዓተ ፆታ የወንዶችና የሴቶች ቤተሰባዊና ማኅበረሰባዊ ሚና የሚለይበት፣ የሁለቱን ፆታዎች የማኅበረ ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካዊ ግንኙነታቸው ስለሚቃኝበት መርህ፣ ስላላቸው ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት፣ የተቀባይነት (ተፅዕኖ የመፍጠር ደረጃ) የሚመረምርና ትንተና የሚሰጥ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ሥርዓተ ፆታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ የንቃት ደረጃ ሥነ ልቦናዊ ሁነቶችና ባህላዊ ይዘቶች እንዳሉት ልብ ልንል ይገባል፡፡ እነዚህ ይዘቶች ደግሞ ከማኅበረሰብ ማኅበረሰብ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊቀያየሩ የሚችሉ በመሆናቸው ሥርዓተ ፆታ ከእነዚህ ሁኔታዎች ጋር ይቀየራል፡፡ የሥርዓተ ፆታ ዋነኛው ባህሪም ይህ ተለዋዋጭነቱ ነው፡፡

ሥርዓተ ፆታ ከትዳርና ከቤተሰብ አንፃር ያለው ግንኙነት እንዴት ይታያል?

ወንዶችና ሴቶች በትዳር (ቤተሰባዊ ግንኙነት) ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት የመወሰን አቅም፣ ያላቸው ቦታ (ደረጃ) በተለያዩ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ተፅዕኖ ምክንያት ሊቀየር ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢኮኖሚ፣ ባህልና የማኅበረሰቡን የአስተሳሰብ ደረጃ (ንቃተ ህሊና) ተለዋዋጭነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ለአብነትም በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ገፊ ምክንያትነት ቀደም ሲል ልጆችን የመንከባከብ ብቸኛ ኃላፊነት የነበረባቸው ሴቶች፣ ቤተሰባቸውን ለመደጎም ገቢ በሚያስገኙ ሥራዎች መሰማራት መጀመራቸው አይቀሬ ነው፡፡

ይህን ተከትሎም በቤተሰባቸውና በማኅበረሰባቸው ያላቸው ቦታና የመወሰን ደረጃ መቀየሩ አይቀሬ ነው፡፡ የፆታ መድልኦን ለመቅረፍ የሚደረጉ ማኅበራዊ ፖሊሲዎች (Social Interventions) የትምህርት መስፋፋት፣ የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ማደግ፣ የሴቶችን የማኅበረ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ተሳትፎና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ደረጃ የሚያሳድጉ ፖሊሲዎች የአንድ ፆታ የበላይነት (በአብዛኛው የወንድ የበላይነት) እንዲቀንስ ከማስቻል አኳያ ትልቅ ሚና አላቸው፡፡

ከሥርዓተ ፆታ አንፃር የመጡ ለውጦች በትዳር ላይ እያሳደሩት ያለው ተፅዕኖ ምንድነው?

ሥርዓተ ፆታ ከትዳርና ቤተሰብ አንፃር ያለውን ግንኙነት ስንፈትሽ፣ በወንዶችና ሴቶች መካከል ባሉ ግንኙነቶች የተለወጠው የመወሰን አቅም መቃኘት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን በጎ ለውጥ በአግባቡ ከተረጎምነው በወንዶችና በሴቶች መካከል ባለው ግንኙነት ፍትሐዊነትንና መከባባርን ስለሚያመላክቱ ጤነኛ ትዳርና ቤተሰብ በመፍጠር በኩል በጎ ተፅዕኖ አለው፡፡ ከሥርዓተ ፆታ ለውጥ ጋር አብሮ ሊመጣ የሚገባ ለውጥ ከሌለ ለውጡን በተሳሳተ አግባብ መረዳት ይመረጣል፡፡ ይህ ደግሞ ጤነኛ ትዳርና ቤተሰብ እንዳይኖረን ያደርጋል፡፡

በኢትዮጵያዊያን ማኅበራዊ ሥሪት ውስጥ ለዘመናት የኖረውና በወንዱ የበላይነት የተቃኘው የባልና ሚስት ግንኙነት ዛሬ እየተለወጠ ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ወንዱ ሴቷን ጨቁኖና ረግጦ መግዛትና ቤተሰባዊ ጉዳዮችን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ውሳኔዎች በብቸኝነት ይዞት የቆየው የመወሰን ሥልጣን እየከሰመ ነው፡፡ ሴቶች በቤተሰባዊ፣ በማኅበረሰባዊ፣ ከፍ ሲልም በአገራዊ ጉዳዮች ጭምር ከወንዶች ባልተናነሰ ደረጃ የሚወስኑበት አቅም አግኝተዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የወንድ የበላይነት (Patriarchial) ባህላዊ መሠረቶችን በያዘበት ማኅበረሰብ ውስጥ፣ ይህንን የሥርዓተ ፆታ ለውጥ በአግባቡ ለመተርጎምና ለመረዳት በተለይ ለወንዱም ሆነ ለሴቷም መክበዱ አይቀሬ ነው፡፡ በተጨባጭ የሚስተዋለውም ይህ ይመስለኛል፡፡

በእኔ ትዝብት የሴቶች የዕውቀት፣ የንቃተ ህሊናና የኢኮኖሚ ኃይል መጨመሩ ለብዙ ወንዶች አልተዋጠም፡፡ በዚህም ሳቢያ ነፃነቴን ያሳጣኛል በሚል አጉል ፍራቻ ትዳርን መሸሽ የመረጡ ይመስላል፡፡ አብዛኞቹ ሴቶችም (ሚስቶች) ያገኙትን አቅም በአግባቡ አልተጠቀሙበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያገኙትን አቅም የበላይ ሆነው ለመታየት፣ ወንዱ (ባል) በቤተሰቡ ጉዳይ ላይ ያለውን የመሪነት ሚና ለመንጠቅ፣ ሲከፋም ባልን በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ለመጠቀም ሲሞክሩ እታዘባለሁ፣ ይህ ለዘመኑ ወንዶች ራስ ምታት የሆነ ይመስለኛል፡፡

መፍትሔው ምንድነው?

ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባ የሚመስለኝ የሥርዓተ ፆታ ለውጥ (ሥርዓተ ፆታ እኩልነት) በትዳር ውስጥ ያለውን ተፈጥሯዊ የወንድና ሴት ግንኙነት ይለውጣል ማለት አይደለም፡፡ ይህ ሊለወጥ የሚችል አይደለም፡፡

በትዳር ውስጥ ያለውን ተፈጥሯዊ የወንድና ሴት ግንኙነት መገንዘብ

በመሠረቱ በየትኛውም ተቋማዊ ግንኙነት ውስጥ መሪና ተመሪ አለ፡፡ ሊኖርም ይገባል፡፡ ቤተሰብም አንድ የማኅበራዊ ተቋም እንደ መሆኑ መሪና ተመሪ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት መስፈኑ ታዲያ መሪና ተመሪ የለም ማለት አይደለም፡፡ በቤተሰብና ትዳር ውስጥ ባል የቤተሰቡ መሪ እንደሆነ፣ ሚስትም በቤተሰባዊ ጉዳዮች የውሳኔ አካል ማድረግ እንዳለበት ተፈጥሯዊም ሆነ ሃይማኖታዊ መሠረቶች ያስገድዱታል፡፡ በቅዱሳን መጻሕፍት እንደተጠቀሰው ወንዱ የሴቷ ራስ ነው፡፡ ይህ ሲባል የቤተሰቡን ደኅንነትና ህልውና በሚወስኑ ገዘፍ ያሉና ወሳኝ ጉዳዮች እንጂ፣ በትንሹም በትልቁም ባል ይወስን ማለት አይደለም፡፡ ባል በሚስቱ ላይ ፈላጭ ቆራጭነትና የገዥነት ሚና ይኑረው ማለትም አይደለም፡፡ ሚስትን የውሳኔው አካል አያድርግ ማለትም አይደለም፡፡ ባል ይህን ማድረግ የማይችልበት ተፈጥሯዊም ሆነ ሃይማኖታዊ መሠረቶች አሉ፡፡ ሴቶች በብልኃት ነገሮችን በተለያዩ አቅጣጫዎች የማየት ከወንዶች የተሻለ ተፈጥሮ ስላላቸው ወንዱን በመደገፍ እጅግ የላቀ ሚና አላቸው፡፡

ቅዱሳንን መጻሕፍት እንደ ሚያስገነዝቡንም ባል ሚስቱን ማማከርና ማድመጥ አለበት፡፡ በአጠቃላይ ተፈጥሯዊውን የባልና ሚስት ግንኙነት መረዳት ለትዳራችን ጤንነትና ዕድሜ ወሳኝ እንደሆነ መገንዘብ ይገባል፡፡

ዘመነኛ ባለትዳሮች ግን በትዳር ውስጥ የባልና ሚስት ግንኙነት ምን መምሰል አለበት የሚለውን በአግባቡ የተረዳነው አልመሰለኝም፡፡ ሃይማኖታዊና ወይም ተፈጥሯዊ ሕግጋትን በጣሰ መንገድ በርካታ የዘመናችን ሴቶች የወንዱን ውሳኔ ሰጭነት መቀበል ማለት ከወንድ አንሶ መታየት እንደሆነ መቁጠር፣ ወንዶችም እንዲሁ በቤተሰባዊ ጉዳዮች ሚስትን የውሳኔው አካል ማድረጉ ሽንፈት ያደረጉት ይመስለኛል፡፡ በዚህ ምክንያት ትዳር ይፀና ዘንድ የሚፈልገውን የመከባበርና የመደማመጥ ባህል እየራቀን ነው፡፡ ይህ በአጭሩ ካልተገታም የአገርና የሕዝብን ህልውና የሚፈታተን አደገኛ መርዝ ነው፡፡

በትዳር ውስጥ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ምን ማለት እንደሆነ መገንዘብ

እንደምታዘበው ትክክለኛውን የባልና ሚስት እኩልነት መገንዘቡ ላይ ተምታቶብናል፡፡ ባል ምግብ ማብሰል፣ ቤት ማፅዳት፣ እንዲሁም ልጆችን መንከባከብ የመሳሰሉትን ቤተሰባዊ ጉዳዮችን ከሚስት ጎን በመሆን ድጋፍ ማድረግ ቢችል መልካም ነው፡፡ ወንዱ ይኼን ማድረጉ ግን የሴቶችና የወንዶች እኩልነት መለኪያ ተደርጎ መቆጠሩ  ትክክል  አይደለም፡፡ በትዳር ውስጥ የሴቶች እኩልነት ማለት ሴት ቀድሞ የወንድ ሥራ ተደርጎ የሚቆጠሩ ተግባራትን መከወንና ከቤት ውጪ ውላ መግባት ማለት አይመስለኝም፡፡ በትዳር ውስጥ የሥርዓተ ፆታ እኩልነት መስፈን ማለት የባልና ሚስት መደማመጥ ሲኖር፣ መከባበርና መቻቻል ሲሰፍን፣ የአንድ ወገን የበላይነት አለመኖር ማለት ነው፡፡

ቸር ያሰማን!!!

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻው [email protected] ማግኘት ይቻላል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...