Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተጋረጠው አዲሱ አገራዊ ፈተና

በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተጋረጠው አዲሱ አገራዊ ፈተና

ቀን:

በአየለ አዲስ አምበሉ

ክፍል አንድ

ይህ ጽሑፍ እየፈረሰ ያለውን የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን (የሕዝብ ግንኙነት) ዘርፍ መንግሥት እንደገና እንዲያጤነውና በመፍረሱ ሊያመጣቸው የሚችሉ ችግሮችን ያትታል፡፡

የመንግሥት ሥራዎችን ከሕዝቡ ጋር ለማስተዋወቅ (ኮሙዩኒኬት ለማድረግ)፣ በጠንካራና ሰፊ የመረጃ ፍሰት በአገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆንና የአገሪቱን ሁለንተናዊ ገጽታ ለመገንባት ዘመናዊ የኮሙዩኒኬሽን ሥርዓትና ብቁ ባለሙያ ማፍራት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሥራ በእጅጉ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ አሁንም ሰፊ ክፍተት ያለበት ነው፡፡ ክፍተቱ ባልከፋ፣ የከፋው ተቋሙ የሕግ መሠረቱ ጠፍቶ የደረሰበት የመጥፋት ክስተት እንጂ፣ እንደ አንድ በዘርፉ እንደተማረ ሰው ሐሳቡን ይዤ የመንግሥትን የመረጃ ፍሰትና አሰተዳደር ሰነዶችን አጠናቅሬ፣ ከሰዎች ጋር ተነጋግሬ ሐሳቤን እንደሚከተለው አቅርቤያለሁ፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት የፖሊሲ ሰነድ የሆነው ‹‹የኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች›› ሚዲያን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹ሚዲያና ኩሙዩኒኬሽን የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባትና ዴሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዳበር አስፈላጊ የሆነውን የጋራ እምነትና አመለካከት በመፍጠር ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል፡፡ ሕዝቡ ለልማትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እንዲነሳሳ ያደርጋል፡፡ መረጃ በማቅረብ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ያጎለብታል፡፡ ሚዲያው የወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ምንጭ፣ የውይይትና የክርክር መድረክ ሆኖ በማገልገል በሚደረጉ የፖለቲካ ውይይትና ክርክር መድረኮች ሐሳቦች በነፃ እንዲንሸራሸሩና የዴሞክራሲ ባህል እንዲያብብ፣ እንዲሁም የጋራ እምነትና አመለካከት እንዲፈጠር ያደርጋል፤›› (ማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ግንቦት 1994፣ ከገጽ 120 እስከ 121)

በአገራችን ውስጥ ያለው ብሔራዊ መግባባት የተዛነፈ ነው፡፡ መልክ ያለው የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አሠራርና አመራር ነጥሮ ባለመውጣቱ ነው፡፡ በአገራችን ታሪክ፣ በሚገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሥርዓቱ በሚከተለው ልማታዊና  ዴሞክራሲያዊ መስመር ላይ ያልጠራ ብዥታ ያለው፣ የመረጃ ረሃብ ያጠቃው ማኅበረሰብና የነጠፈ የመረጃ ቅብብሎሽ መስመር በመዘርጋቱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየታየ ያለው ሰፊ የሆነ የአመለካከት ዝንፈት ደግሞ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ መሆኑ ሲታሰብ፣ በእርግጥም በዘርፉ ውስጥ ያለውን የተቋም፣ የሰው ኃይል አመለካከት፣ ዕውቀትና ክህሎት ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ መሥራት እንደሚገባን  ያመላክታል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መፍረስ ለክልሎች ዕለታዊ ከቀበሌ ጀምሮ የተፈጠሩ ክስተቶችን እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ የሚያደርሱበት ሥርዓት እንዲበጠስ በር የከፈተ ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መፍረስ ተዓማኒነቱና ትክክለኛነቱ የራሱን ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የሕዝብን አሰተያየት በየሳምንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀብለውን መረጃ ማጣት ነው፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን መፍረስ በሁሉም ተቋማት የመረጃ ፍሰትና አደረጃጀት ላይ የሚሠሩ የሕዝብ ግንኙት አካላት የሚያሰተባብራቸውና የሚመራቸው አካላት ማሳጣት ነው፡፡ የመረጃ ነፃነትና የመገናኛ ብዙኃን ሕግ በአዋጅ ከወጣና የዝግጅት ዓመታቱ ከተጠናቀቀ በኋላም፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሕጉ መሠረት መረጃን የማጠናቀርና የማቅረብ ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ ይህን አንዱ በአዋጅ ሥልጣን የተሰጠው አካል ኃላፊነት የሚወስድበትና የሚጠየቅበት አሠራር አለመመሥረቱ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ1946 ዓ.ም. በውሳኔ ቁጥር 59/I እንዳመለከተው፣ የመረጃ ነፃነት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት ከመሆኑም በላይ ለሁሉም መብቶች መከበር መሠረት ነው በማለት ወስኗል፡፡

ይህንኑ ውሳኔ መሠረት በማድረግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በ1948 ዓ.ም. ባወጣው “Universal Declaration of Human Rights” አንቀጽ 19 ላይ የመረጃ ነፃነት መሠረታዊ ሰብዓዊ መብት መሆኑን ደንግል፡፡ በአጭሩ የተቀጨው ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ አሳማኝና ተግባቢ ኮሙዩኒኬተሮችን በየመሥሪያ ቤቱ የማፍራት ግቡም በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ለሥራው የሚሰጠው ግምት፣ እንዲያውም እያደር እየተሸረሸረ የሚመስልበት አጋጣሚ ነው ወደ የማያስፈልግበት ውሳኔ ያደረሰው፡፡ በቅርቡ የሰው ሀብት ሚኒስቴር ለቦታው የሰጠው የሥራ ድርሻ ሰንደቅ ዓላማ መስቀልና ማውረድ የሚል ነው፡፡ ይኼ በልዩ ዕርምጃ መስተካከል ያለበት ዝንፈት ነው፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት የመንግሥት ኦፊሴላዊ አንደበት (ቃል አቀባይ) የመሆኑን ያህል፣ ኃላፊነቱን በዚያ ደረጃ አይፈጸምም ከሚለው ወቀሳ ሳንወጣ፣ ፈርሷል የሚለው ዜና የመረጃ አደረጃጀትና አመራር ላይ ያለች አገር በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የሁሉንም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነት ሥራ በበላይነት የሚመራ የመሆኑን ያህል፣ መረጃዎቹ ላይ ተመጣጣኝ የበላይነት የለውም ከሚለው አፈጻጸሙ ሳይላቀቅ መፍረሱ በመረጃ ረሃብ ለሚሰቃየው ሕዝብ የበለጠ የመረጃ ድህነቱን ማስፋት ነው፡፡

መንግሥት ሊናገርባቸው የሚገቡ በርካታ ዓበይት ጉዳዮች በአርምሞ የሚያልፈው ድርጅት ሊታገዝ፣ ሊረዳ፣ ሊደገፍ ሲገባው የበለጠ ወደ ዝምታ መሸጋገሩ ጉዳዩን የዝምታ ድባብና የመረጃን ዕጦት የሚንሸራሸርበት ተቋም ታጥቷል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ እንኳን ፍላጎት ያደረባቸው ጉዳዮች ቀርቶ ፍላጎትን ፈጥሮ በተለያዩ ርዕሶች ላይ ማብራሪያና መግለጫ መስጠት ሲገባው፣ ሕዝቡ ግልጽነትና የመንግሥትን አቋም ማወቅ በሚፈልግባቸው ሁነኛ አጋጣሚዎች ላይ ጭምር ጽሕፈት ቤቱ በኦፊሴል አለመናገሩ እንደ ችግር ታይቶ ይስተካከል ባልንበት አፋችን፣ የመንግሥትን ጉዳይ እስከ ታችኛው ቀበሌ ድረስ የሚመራና የሚያግባባ አካል ጠፍቷል፡፡ በእርግጥ በአመራሩ ለሕዝብ ግንኙነት የሚሰጠው ግምት አዳራሽ አስዋቢ፣ መድረክ መሪ ከሚለው ያለፈ መሆኑን ለማሳየት ሁል ጊዜ በቀውስ ውስጥ መሆን የለብንም፡፡ የተቋሙ መፍረስ የማያረካ መረጃ አቀረራብ ቢኖርም የማያቋርጥ የመረጃ ፍሰት በጽሕፈት ቤቱ ደረጃ ሊከናወን የሚገባው ዓብይ ሥራ አሳጥቷል፡፡ በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ በቋሚነት መግለጫና ማብራሪያ የመስጠት አሠራር ታጥፏል፡፡ በጥናት ረገድ በተለይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ፈጣን የሕዝብ አስተያየትን ለመሰብሰብና ለመተንተን የሚያደርገው ጥረት አልባ አድርጎታል፡፡

የውጭና የአገር ውስጥ ሚዲያዎችን ተከታትሎ (Monitoring) መረጃውን በወቅቱ በማቅረብና በማተንተን ረገድ ያለው አቅም፣ አገሪቱ ውስጥ የውጭ ግንኙነት የሚሰጥበት አሠራር የሚመራ አካል ጎድሏል፡፡ ይህም አዎንታዊ ዘገባዎችን፣ ክስተቶችን በከፍተኛ የአጠቃቀም ደረጃ ፋይዳ ላይ ለማዋልና ለገጽታ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ እስከ መጨረሻው ጫፍ ለመገልገል፣ ለዚህም ሥልት ነድፎ ሁሉንም ወገን ያስተባበረ የአጠቃቀም ብልኃት መዘርጋት፣ አሉታዊ ዘገባዎችንና ክስተቶችን የመድፈቅ፣ የማጋለጥና የማስተካከል ሥራ ለመሥራት፣ ከዚህም አልፎ ‹‹በማጥቃት የመከላከል ሥልት›› አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው አድርጎ የሚጠቀምበትን አመራር የሻረ ሥርዓት ተፈጥሯል፡፡ ከኢሕአዴግ የሕዝብ ግንኙነት ከፍል ጋር የሚጋጭ ቢሆንም፣ በየብሔራዊ በዓሉ በተሻለ ሁኔታ ጽሕፈት ቤቱ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚሠራጩ ጽሑፎችን የማምረት ሥራም ዛሬ የለም፡፡ የመንግሥት ግልጽ አቋም ተቋሙን በማፍረሱና የፌዴራል ሥርዓቱን ተከትሎ ያልተማከለ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮዎች ኦሮሚያ፣ ደቡብና ትግራይ ቢሮውን ያስቀጠሉት ሲሆን፣ ሌሎች በውል አፍረሰውታል፡፡ በክልልና በአካባቢ ደረጃ ጭምር ለሕዝቡ ተደራሽ የሆነ ሚዲያ ዕጦትም ለሕዝቡ የተጋረጠ ፈተና ሆኗል፡፡  ዴሞክራሲ የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ ሁሉ ይህንን የሚመራ ተቋምም ሕጋዊ ሥልጣን ሊኖረው ይገባል፡፡ አለበለዚያ ጉዳቱ ዘርፉን አልፎ ለሥርዓቱ ይሆናል፡፡

የመረጃ ፍሰት ይገደባል፣ ሰፊ የሐሳብ ማንሸራሸር ይጠፋል፣ ተደራሲው/ታዳሚው ዘንድ ተዓማኒነቱና ተቀባይነቱ በቂ ሆኖ አይገኝም፡፡ የተፅዕኖ ፈጣሪነት አቅሙ ይገደባል፡፡ ምንም እንኳን የመረጃ ነፃነት (አዋጅ 590/2000 ክፍል ሦስት) የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተም እንዲመራ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም፣ መረጃን የማስተዳደር ሥልጣን የለውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የተከሰተው ፈተና የኮሙዩኒኬሽን ሥራን ዓበይት ተልዕኮዎች መሠረት ያደረገ ሥምሪት እንዳኖር የሚደርግና ሊታረም የሚገባው ጉድለት ነው፡፡ የጋራ አገራዊ እምነትና አመለካከት መፍጠር ላይ ችግሩ የበለጠ ይከፋል፡፡ ሕዝብን ማነሳሳትና ማሳተፍ ይጎድላል፡፡ የወቅታዊና የትክክለኛ የመረጃ ምንጭ የመሆን ተልዕኮዎችን ለማሳካት ሚዲያው የውይይትና የክርክር መድረክ፣ የጥልቅ ትንታኔዎች ዓውድ፣ የተስፋዎቻችንና የሥጋቶቻችን መስታወት እንዲሆን የሚያስችለው የተተነተነ የተልዕኮ ግልጽነትና የማስፈጸሚያ ሥልት ሰነድና መግባባት እንዳይኖር ሊያደርግ የሚችለውን መጥፎ አጋጣሚ በድክመት ተገምግሞ ፈጣን የማስተካከያ ዕርምጃዎች ሊደረግለት ይገባል፡፡

ይህን ስል ከአሁን በፊት የነበረበትን የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን አመራር ጥበብ ያጣ ለፖለቲካ ሥርዓቱ ፍፁም ታማኝነት፣ ሕዝብን ያገለለ፣ ረቂቅ ኢንዶክትሪኔሽን ከመሆን ይልቅ ያገጠጠ ፕሮፓጋንዳነቱ መስተካከል ይገባዋል፡፡ ያደጉት አገሮች ሚዲያዎች የሥርዓቱን ፍላጎት የሚያስጠብቁበት አስተሳሰብ የሚቀረፁበትና ከፖለቲካል ኢኮኖሚው ተፃራሪ የሆኑ አመለካከቶችን የሚደፍቁበት ሥልት ፍላጎትን (Intention) አጋልጦ የማያሳይ፣ ይልቁንም የተደራሲውን ስሜትና ጥሞና የጠበቀ ሚዛናዊነትን ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ እጅግ ጥበባዊና የረቀቀ ከሙዩኒኬሽን ተቋም አላቸው፡፡ ይህ ትልም ከአመራር ይጀምራል፡፡ አመራሩ ኮሙዩኒኬተሮችን በሚቀርፅበት ዘዴ ይወሰናል፡፡ በእኛ ደረጃ የላይኛው አመራር በመካከለኛው አመራር ውጤት ላይ የተመሠረተ አፈጻጸም እንዲኖረው የሚያስችል ሙያዊ የተፅዕኖ የመፍጠር አቅሙ ገና አልዳበረም፡፡

መካከለኛው አመራርም ጋዜጠኛውንና ኮሙዩኒኬተሩን ሙያዊ በሆነ ልቀት ከመምራት ይልቅ፣ አስተዳደራዊ አስፈጻሚነቱ ይበዛል፡፡ እዚህም ላይ ክፍተቱ የክህሎት ነው፡፡ መካከለኛ አመራር ወይም ኤዲተሩ የረቀቀ የኢንዶክትሪኔሽን ሥራ ሠርቶ የማሳየት አቅሙ ውስን ነው፡፡ ይልቁንም በረኛ (Gate Keeper) ተደርጎ የሚወስድበት አረዳድ ይሰፋል፡፡ ስለዚህ የፖለቲካል ኢኮኖሚው ጥልቅ የረቀቀ ጥበብ የሚጠይቅ ከመሆኑ አንፃር፣ አመራሩ የረቀቀ ዓላማን የማስፈጸም ክህሎቱ የሚፈለገውን ያህል እንዲያድግ በአገሪቱ ዘርፉን የሚመሩና የሚያሠለጥኑ አካላት እንዳይከስሙ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በመንግሥት አዳዲስ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምክንያት ሲበተን መረጃ ያለ ሥርዓት እንደተበተነ ማንም የተረዳ የለም፡፡ እንዲያውም ባለፉት ዓመታት የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ መርሐ ግብሮች ዙሪያ በቂ ግንዛቤና ጠንካራ አመለካከት እንዲፈጠር ለማስቻል፣ መላው የአገሪቱ ሕዝቦች በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው ተብሎ በተሠራው ሥራ ውስጥ የብዙ ነገሮች መዳፈን ታይቷል፡፡ በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ያለው አመራርና ባለሙያ በመሠረታዊ የመንግሥት የልማት፣ የዴሞክራሲና የሰላም አቅጣጫዎች ዙሪያ የዳበረ ግንዛቤና ወጥ አመለካከት ይዘው መንቀሳቀስ የሚገባቸው ቢሆንም፣ በተጨባጭ ያለው ግን የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በአንድ በኩል በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ ውስጥ ያለው አመራርና ባለሙያ መንግሥት በሚከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ምንነትና ይዘት፣ በሚከናወኑ የለውጥ ጉዞ ምንነትና ይዘት፣ እንዲሁም በለውጡ ጉዞ ፊት በተደቀኑ ተግዳሮቶች ዙሪያ ማኅበረሰቡን በተሻለ ደረጃ ወጥና ትክክለኛ አመለካከት በማስያዝ ረገድ ሰፊ ክፍተት እስካሁን እንዳለ በቅርቡ የፈረሰው የመንግሥት ከሙዩኒኬሽን ጉዳዩች ጽሕፈት ቤት ያቀረበው ጥናት ያመለክታል።

የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ በሁሉም ጉዳዮች ዙሪያ የተስተካከለ አመለካከት በመቅረፅ፣ ብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ብሎም በጠንካራና ተከታታይ የሕዝብ ተሳትፎ የአገሪቱን ህዳሴ የማረጋገጥ ኃላፊነት የተሸከመ ዘርፍ ነው። ይህንን ዘርፍ በማፍረስ የሕዝብ ግንኙነት ክንፉን፣ አደረጃጀትና አመራሩን የሚያወያይ፣ ሳምንታዊ የመንግሥት መረጃዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ የሚያቀብል ዘውግ ተሰብሯል፡፡ ይሁን እንጂ ዘርፉ እስካሁን ባለፈበት መንገድም በበርካታ የአመለካከት ችግሮች የተተበተበ ነው። ስለሆነም የአገራችንንና የዓለምን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ጥልቅ ግምገማ በማካሄድ፣ የዘርፉ ተቋማዊ ምሳሌና አመራር መመለስና መመሥረት የሕዝብ ግንኙነትን ክንፉን ከሞት እንደመታደግ ነው፡፡  (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሦስተኛ ዲግሪ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...