Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርከምክንያታዊነት የራቀ አስተሳሰብ የት ያደርሰናል?

ከምክንያታዊነት የራቀ አስተሳሰብ የት ያደርሰናል?

ቀን:

በዳግም መርሻ

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ሰሞኑን በአንድ ካፍቴሪያ በረንዳ ላይ አረፍ ብዬ  እየተዝናናሁ በነበርኩበት ጊዜ፣ አጠገቤ የነበሩ በዕድሜ ጠና ያሉ ሁለት ሰዎች በአሁኑ ወቅት በአገራችን አንዳንድ አካበቢዎች የሚታዩ ስሜታዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ ሲያደርጉ የነበረው የጋለ የሐሳብ ልውውጥ ነው። ግለሰቦቹ በፊት እነሱ ባለፉባቸው ጊዜያት ኅብረተሰቡን ደንብና ሥርዓት እንዲይዝ የማድረግ አቅም የነበራቸውን ባህላዊ ልጓሞች (እሴቶች)፣ አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታ ጋር እያነፃፀሩ በቁጭትና በመቆርቆር ስሜት ሲናገሩ ስሰማ፣ በእርግጥም እነዚህ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችን አሁን ባለንበት ወቅት እየታዩ ላሉት ችግሮች ያላቸው ፋይዳ ቀላል የሚባል አለመሆኑ ተሰማኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ገና ብዙ መባልና መወትወት እንዳለበትም ተረዳሁ። እናም ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ።

ወደ ዋናው ሐሳቤ ከመግባቴ በፊት ስለምክንያታዊነት ምንነት ጥቂት ልበል። ስለምክንያታዊነት ሰፊና የተለያየ ትርጉም መስጠት ቢቻልም ብዙዎችን የሚያስማማና የሚያግባባ ትርጓሜው፣ የሰው ልጅ እውነትን ፈልጎ የሚያገኝበት የተፈጥሮ ችሎታ መሆኑ ነው። በዚህ መሠረት ቃሉ አንድን ሐሳብ ወይም የተወሰነ ጉዳይ መፈተሽ፣ መመርመር፣ መመዘን፣ ማውጣት፣ ማውረድ፣ ወዘተ. በመጨረሻም እውነታው ላይ ከመድረስ ጋር ይቆራኛል። እናም ምክንያታዊነት ከማሰብ ማስረጃንና መረጃን መሠረት አድርጎ ሐሳብን ከመዳሰስ፣ ከመፈተሸ፣ ከመመርመር፣ ከመሞገት፣ ከማውጣትና ከማውረድ. . .  ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። ምክንያታዊነት ከእሴትና ከሞራላዊ ጉዳዮች፣ ለእውነትና ለፍትሕ ወግኖ ከመቆምና ከመቆርቆር፣ ከመቻቻልና ከመከባበር፣ ሰውን በሰውነቱ ከመመዘንና ዋጋ ከመስጠት ጋር ይቆራኛል። በአንፃሩ ዘርን፣ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን ፆታን፣ ወዘተ. መሠረት አደርጎ በሰዎች መካከል ልዩነት መፍጠር፣ መጠቃቀም ወይም በእነዚህ ልዩነቶች ላይ በመመርኮዝ መጠቃቃት ምክንያታዊነትንና አርቆ አሳቢነትን አያመለክትም። ለሰው ልጆች በተፈጥሮ የተቸረውን የማሰብ ልዕልናንም ይፃረራል።

- Advertisement -

ምክንያታዊ ስንሆን ግጭት፣ ንትርክ፣ በጭፍን መጠላላት፣ ጠመንጃ ማንሳት፣ መገዳደልና መጎዳዳት አያስፈልገንም፡፡ የሚያስፈልገን የሐሳብ ልዕልናና የአስተሳሰብ የበላይነት ነው። ይህ ደግሞ ዕውን የሚሆነው ጤናማ በሆነ ውይይትና በመደማመጥ ላይ በተመሠረተ ንግግር ነው። ቀደም ብዬ እንዳልኩት ምክንያታዊነት ሰውን በሰውነቱ፣ በአስተሳሰቡና በማኅበራዊ ፖለቲካዊ የሕይወት እንቅስቃሴ ውስጥ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ የሚመዝን እንጂ በደም፣ በጎጠኝነት፣ በቡድንተኝነት፣ ወይም በመጠቃቀም ላይ የተመሠረተ የእከክልኝ ልከክልህ ግንኙነት አይደለም። ያለ ምክንያታዊነት፣ ያለ ሚዛናዊ ሐሳብና ያለ መርህ በሚመራ ግንኙነት ውስጥ አይሎና ገዝፎ የሚንፀባረቀው ስሜታዊነት እንጂ ምክንያታዊነት አይደለም። በእርግጥ የሰው ልጅ ሙሉ ለሙሉ ከስሜት ነፃ ነው ወይም ደግሞ ስሜት በጭራሽ አያስፈልግም ማለት እንደማይቻል አንባቢያን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ። ችግር የሚሆነው ስሜታዊነት ውሉን ስቶ መጎደዳት፣ መቃቃር፣ መከፋፈልና ጥላቻን ሲያሰከትል ነው፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነገር ከምክንያታዊነት ስንርቅ ስሜታችን ለጅምላ ፍረጃ ቅርብ መሆኑ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን፤ ሌላው ሌላውን ደባልቆ ይፈርጃል፡፡ ብዙዎቻችን በጭፍን ድምዳሜ እንዋጣለን፡፡ አንድን ነገር ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ መርምረን፣ በምክንያት ተንትነን፣ እንዲሁም መረጃና ማስረጃ አቅርበን እውነታው ሳይ መድረስ ሲገባን እንደመሰለን እንናገራለን፣ ብሎም እንተነትናለን። «አትግደል» እና «አትዝረፍ»  የሚለውን  የህሊና ደንብ እንጥሳለን። አብሮና ተሳሰቦ መኖርንም ዋጋ እናሰጣለን። ባስ ሲልም ገጀራ እየነቀነቅን የሚመስለንን ፍርድ እንሰጣለን፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ሚዛናዊ አስተሳሰብና ሰብዓዊነት ተሸርሽሮ ጠባብነት፣ ዘረኝነትና ግዴለሽነት ሲናኝ ነው። እንዲህ ከሆነ ዘንዳ የሰው ልጅ አዕምሮ (ጭንቅላት) የፀጉር ማብቀያ ብቻ ሳይሆን፣ ማሰቢያና የምክንያታዊ አስተሳሰብ መፍለቂያ መሆኑን መረዳት እንችላለን። ከዚህ በተቃራኒ አዕምሯችን ከምክንያታዊ አስተሳሰብ ይልቅ አሉታዊ ስሜታዊነትን ይዞ የሚነዳን ከሆነ የምናደርገው ድርጊት ጎጂነቱ የሚያመዝን ይሆናል። ጉዳቱ ዜጎችንም አገርንም ዋጋ ያስከፍላል።

ስለሆነም ምክንያታዊነት እንዴት? ለምን?  መቼ?  የት?  ምን?  የመሳሰሉትን መሠረታዊና አመክንዮን የተከተሉ ወሳኝ ጥያቄዎችን በማንሳት እውነትን ከሐሰት አብጠርጥሮ ማጥራትን ይጠይቃል፡፡ በዚህ መንገድ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ሲኖር አገርና ዜጎች ከአሉባልታና ከሐሰተኛ ወሬ ይድናሉ። ከዚህም በተጨማሪ ማኅበረሰቡ ራሱን ለተለያዩ ጉዳቶች ሰለባ እንዳይሆን መጠበቅ ይችላል። ከዚህ ሁኔታ በመነሳት በአሁኑ ወቅት በግላጭ የሚታየውን የአገራችንን ሁኔታ ስንቃኝ ከምክንያታዊነት ይልቅ ስሜታዊነት በርትቶ የሚታይበት ጊዜ ላይ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታይና የሚዳሰስ ችግር መሆኑ አሌ አይባልም። ለዚህ ማሳያዎችን በተለያዩ መግለጫዎች በማስደገፍ ማቅረብ ይቻላል።

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የቆየ አብሮ ተሳስቦና ተዛዝኖ በጋራ የመኖር አኩሪ ባህል ያለን ሕዝቦች እንደሆንን ይታወቃል። በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫ ዘልቆ ያልተጋባ፣ ያልተዋለደና ያልተቀየጠ ሕዝብ የለም። ይህ የሚያሳየው በደም መተሳሰራችንን ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ሁሉም የእኛ ነው ቢባል ስህተት ነው ብዬ አላስብም፡፡ ይሁንና አሁን መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ስናይ ይህ የቆየ እሴትና ኢትዮጵያዊ ማንነት ተዘንግቶና ተሸርሽሮ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚል ግንብ ተገንብቶ የእኛ ብሔር ተነካ፣ እንዲህ ሆንን፣ እኛ እንደዚህ ነን. . . ማለት አብዝተናል፡፡ የጠባብነት ሕልምም ተጠናውቶናል። ይህን በየማኅበራዊ ሚዲያው፣ በየጎዳናው፣ በተለያዩ መድረኮችና በየአካባቢው አስተውለናል። የዚህ ሌላው መገለጫ “ሁሉም የእኛ ነው፣ እናንተ መጤ ናችሁ. . .” ወይም  “አንድ ዓይነት ካልሆንን አንድ አይደለንም” የሚለው አስተሳሰብ ነው። መነሻና ምንጩም በምክንያታዊነት ላይ ያልተመሠረተ ጭፍን ጥላቻ ነው። ይህ ደግሞ ስሜትን አግሎና አንሮ እዚህም እዚያም አሳፋሪ በሆነ መንገድ ሕይወት ሲጠፋና ዘግናኛ ጥፋት እንዲደርስ አድርጓል። እያደረገም ይገኛል። ይህ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ካዳበሩት አብሮ የመኖር ባህልና የማኅበራዊ ሕይወት መስተጋብር በእጅጉ ተፃራሪ ነገር ነው።

ለመሆኑ በፊት በኅብረተሰቡ ውስጥ በስፋት የነበረው ምከንያታዊነትና አስተዋይነት የተላበሰው እሴት ለምን ተዳከመ? ለመዳከሙ ኃላፊነት የሚወስደው ማን ነው? አሮጌውን አፍርሶ አዲስ መገንባት የትስ ለመድረስና ምን ተዓምር ለመፍጠር ነው? አሁን እንደሚታየው ከመጎዳዳት በስተቀር ምን ፋይዳ ያመጣል? እነዚህ ሁሉ ብዙ ንግግርና ውይይት ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ይመስሉኛል። ለነገሩ ይህ ከምክንያታዊነት ርቆ በስሜት የመነዳት ሁኔታ በሌሎችም አካባቢዎች ይስተዋላል። በስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ሁኔታ እንኳን ብናይ ስፖርተኞቻችን በሩጫ ወይም በእግር ኳስ ሲያሸንፉም ሆነ ሲሸነፉ፣ ብዙዎቹ ስሜታቸውን በልኩ መቆጣጠር ተስኗቸው ሲረብሹና ሌላውን ሲያውኩ ማየት የተለመደ ነገር ነው። በስታዲዮሞችና በሰላማዊ ሠልፎች ውስጥም የሚስተዋለው ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። አዳዲስ የመንግሥት ኃላፊዎች ሲሾሙ ተሿሚዎችን ከዕውቀታቸው፣ ከልምዳቸውና ካላቸው ክህሎት ዓይተን ከመመዘን ይልቅ ድጋፍ የምንሰጠውም ሆነ የምንቃወመው ብዙ ጊዜ በብሔር ማንነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በትውልድ አካባቢ ወዘተ. ላይ ተመሥርተን ነው። በእኛ አገር ማን አለ እንጂ ምን አለ ለሚለው ጉዳይ ብዙ ትኩረት አንሰጥም። አንድን ግለሰብ ወይም ፓርቲ ለምን ደገፍከው ተብሎ ጥያቄ ሲቀርብ በብዙዎች የሚሰጠው ምላሽ ምክንያትነቱ ውኃ አያነሳም። እንዲያውም ብዙ ግለሰቦች ስለሚደግፉት ፓርቲ ዓላማና ፖሊሲ በቂ ግንዛቤ የላቸውም። ከጥቂቶች በስተቀር ስለእነዚህ ጉዳዮች አንብበውም ይሁን ጠይቀው የማያውቁም ብዙ ናቸው። ይህ ‹‹ተምረናል›› የሚባሉትንም ይጨምራል።

ስለሆነም እነዚህን መሰል ጥራዝ ነጠቅ አስተሳሰቦች በምክንያታዊ የሐሳብ የበላይነት እስካልተሸነፉና እንደ ሕዝብ ነገሮችን ሰከን ብለን የመመርመር ባህል እስካላዳበርን ድረስ፣ በተሳሳቱ መንገዶች ደግመን ደጋግመን ጥፋት ውስጥ ስላለመመለሳችንና ችግር ውስጥ ስላለመክረማችን ምንም ዋስትና የለም። ምንም እንኳን ከላይ የተጠቀሰው በስሜት የመንጎድ ችግር ጎልቶ የሚታየው በቀለም ባልገፉት ግለሰቦች ላይ ነው ተብሎ ቢታመንም፣ በዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ባህልና አሠራር ዳብረዋል በሚባሉት ምዕራባውያን አገሮች ውስጥ የቀለም ትምህርት ቀስመውና ለረዥም ዓመታት ኑሯቸውን እዚያው አድርገው የመጡ ግለሰቦችም ጭምር የዚህ ዓይነቱ ችግር ሰለባ ናቸው ማለት ይቻላል። እንደሚታወቀው ምሁር ማለት በተለምዶ ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ ዲግሪና ዲፕሎማ የያዘ ወይም ብዙ ያነበበና በተለያዩ መስኮች ጥናትና ምርምርን ያደረገ ነው ማለት ብቻ አይደለም። ምሁርነት ከዚህም ከፍ ያለ ሐሳብ ነው። ምሁርነት በዋናነት ከስሜት ይልቅ በምክንያታዊነት፣ ከአፈሙዝና ከጭፍን ጥላቻ ይልቅ የሐሳብ ልዕልና፣ ከአድርባይነት ይልቅ በመርህና በአመክንዮ መመራት፣ ከውዥንብር ይልቅ አቅጣጫ ማሳየትን፣ ከፕሮፓጋንዳ ይልቅ እውነትን በግብር ከመግለጽ የአኗኗር ዘይቤ ጋር የተያያዘ ነው።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተግባር እየሆነ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት በምክንያታዊነትና ከላይ ከተጠቀሱት የምሁርነት መገለጫዎች አንፃር፣ በሕዝብ ውስጥ በስፋት የሚታወቁ ጥቂት ግለሰቦች ቢኖሩም በዚያው ልክ ደግሞ ከሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ባልተለየ ሁኔታ ከምክንያታዊነት ርቀው በስሜት የሚነዱ፣ ልዩነት ተፈጥሮአዊ መሆኑን በመዘንጋት ሌሎች ወገኖችን የሚፈርጁና የሚያብጠለጥሉ፣ ታሪክንና እውነትን አጣመው የሚያቀርቡ፣ ለርካሽ የፖለቲካ ፍጆታ ሲሉ ሌሎችን የሚያጠለሹ (ስም የሚያጠፉ)፣ አንዱን ብሔረሰብ ከሌላው ብሔረሰብ ጋር ግጭት እንዲፈጥር የሚቀሰቅሱና የሐሰት አሉባልታ የሚነዙ ‹‹ምሁራን›› ተብዬዎች ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አይደለም። በዚህም በተማረውና ባልተማረው የኅብረተሰብ ክፍል መካከል ያለው ልዩነት እየደበዘዘ ሁሉም በአንድ ቦይ ውስጥ በስሜት ሲፈስ ይታያል።

ሌላው ከዚህ ጋር በተያያዘ ትልቅ ችግር የሚስተዋለው በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ነው። ብዙዎቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዓላማቸውንና ርዕዮተ ዓለማቸውን ለሕዝቡ በማሳወቅና በማስረዳት ደጋፊዎችን ከማፍራት ይልቅ፣ አባሎቻቸውን በስሜት ቆስቋሽ ጉዳዮች በመጥመድ ደጋፊን በማብዛት ላይ ስለሚያተኩሩ የሕዝቡን ንቃተ ህሊና ከፍ በሚያደርጉ ሐሳቦች፣ በሕዝቡ (በአገሪቱ) ችግሮችና በሌሎች አጀንዳዎች ዙሪያ በሰከነ መንገድ የሚካሄዱ ንግግሮችና ውይይቶች እጅግ አነስተኛ ናቸው። ሐሳብና ምክንያታዊነትን የሚያበረታታ ሁኔታ በሌለበት ሥፍራ ደግሞ ቦታውን የሚይዘው ግጭት፣ ንትርክ፣ አሉባልታና ውዝግብ ነው። ምክንያታዊ ብንሆን አሁን ላይ እንደሚታዩት ንትርክ፣ መጠላላትና የእርስ በርስ የገመድ ጉተታን ባላስተዋልን ነበር።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሐሳቡን ያካፈለኝ አንድ የሥራ ባልደረባዬ እንደሚናገረው፣ እሱ ተወልዶ ባደገበት በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ መስመሩን እንዳያልፍ ወይም እንዳይፈጽመው የሚጠነቀቅለት በኦሮሚኛ ‹‹ጩቡ›› የሚባል ነገር አለ። ከገዳ ሥርዓት በሚመዘዝ በዚህ የማኅበረሰብ እሴት መሠረት መዋሸት፣ እውነትን መደበቅ፣ ሰውን መበደል፣ ግፍ መሥራት፣ ተመጣጣኝ ያልሆነ ጉልበት መጠቀም፣ ነፍስ ማጥፋት፣ ሰዎች በአግባቡ እንዲጠቀሙ በፈጣሪ የተሰጠን ሀብት ማውደም፣ ወዘተ. ‹‹ጩቡ›› ነው። የአማርኛ አቻ ትርጉሙ ኃጢያት ሲሆን፣ ይህም ዘር ቆጥሮ እስከ ልጅ ልጅ ተከታትሎ በመምጣት ጥፋት ያስከትላል ተብሎ ስለሚታመን በማኅበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ግምት ይሰጠዋል። በዚህ ባህላዊ እሴት ምክንያት ሁለት ሰዎች ተጣልተው ቢደባደቡና አንዱ ቢወድቅ የወደቀውን መምታት እንደማይቻል፣ ቅጣቶች ልክ ልክ የተበጀላቸውና በሰብዓዊነት ስሜት ይፈጸሙ እንደነበር አጫውቶኛል። ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ በአንድ ነገር ላይ በችኮላና በስሜት ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ፣ ከስሜት በራቀና በትዕግሥት ጉዳዩን ወደ ሌላ ጊዜ የማሸጋገር ጥሩ ባህል እንዳለ አውግቶኛል። እነዚህ ወግና ሥርዓቶች አሁንም ቢሆን በብዙ ቦታዎች ማኅበረሰቡ ጠብቆ ያቆያቸው እንደሆነና ይህ የሚጠፋ ከሆነ ግን እንደ ማኅበረሰብ አብሮ ለመቆም ልንቸገር እንደምንችል ሥጋቱን ገልጾልኛል።

ምክንያታዊ ሐሳብ በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሸራረፈ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የግል ዕይታቸውን ያካፈሉኝ የቅርስ ጥበቃና ጥናት ባለሙያውና ተመራማሪው አቶ ኃይለ መለኮት አግዘው በበኩላቸው፣ በተለያዩ የአገራችን ማኅበረሰቦች ውስጥ ኅብረተሰቡ እንደፈለገ እንዳይፈነጭ፣ ያጠፋ ለተበደለ ካሳ የሚክስበት፣ እርስ በርስ ተሳስቦና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር የሚያስችሉ ባህላዊ የአስተደደር ዘይቤዎች በተለያዩ ብሔረሰቦች ዘንድ እንደሚገኙ በማውሳት፣ እነዚህ እሴቶች ምክንያታዊ አስተሳሰብን ለማጠናከር ያላቸው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ በፊት በስፋት የነበሩትና አሁን አሁን እየቀሩ የመጡት የቄስና የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ከቤተሰብ ቀጥሎ ትውልዱ ሥርዓት ይዞና በሥርዓቱ ተቀርፆ እንዲወጣ ከማድረግ አኳያ የነበራቸው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልነበር ያብራራሉ። ይሁንና እነዚህ ተቋማት ሲዳከሙ የአብዛኛው ኅብረተሰብ  የሞራል ልዕልና ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ መምጣቱንና ኢትዮጵያዊነትም አደጋ ላይ መውደቁን አክለው ይገልጻሉ። ለዚህ ደግሞ ከመንግሥት ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የመገናኛ ብዙኃንና ወላጆች ኃላፊነት የሚወስዱ አካላት መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ከላይ የተነሱት ሐሰቦች የሚያስገነዝቡት ነገር ቢኖር አሁን ያለው አብዛኛው ማኅበረሰብ የራሱን ወግና ባህል ወደ ጎን ብሎ ከእኛ ሁኔታና ባህል ጋር የማይሄዱና የማይጣጣሙ አስተሳሰቦች፣ እሴቶችና ባህሎችን በመኮረጅ ላይ ስለተጠመደ ችግር ውስጥ እየገባ መሆኑን ነው። ከዚህ ጋር የሚያያይዘው ሌላው ችግር ያሉንን እሴቶች ለአሁኑ ትውልድ በማሸጋገርና በማሳደግ ረገድ ብዙና በቂ ሥራ እንዳልተሠራ ነው። ይህ ማለት ግን አሁን ያለው ሁኔታ ሙሉ ለሙሉ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው ብዬ አላምንም። አሁን አንኳን በቅርቡ የጋሞ አባቶች ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን በመጠቀም በስሜት ተነሳስተው ጥፋት ሊያደርሱ የነበሩ ወጣቶችን ያስቆሙበት መንገድ፣ ለብዙዎች ተስፋን የጫረና ሌሎች አካባቢዎችም ልክ እንደ ጋሞ አባቶች ባህላዊ እሴቶቻቸውን ለሚታዩ ችግሮች እንደ መፍትሔ መጠቀም እንዳለባቸው ትምህርት ሰጥቶ ያለፈ ነው።

እንደ አጠቃላይ ግን ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሔ ካስፈለገ፣ እንደ ሕዝብ እውነት እውነቱን በተለያየ ደረጃና በስፋት መነጋገር አለብን ብዬ አስባለሁ። ይህን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን መድረክ በመፍጠር ሊያመቻቹ ይችላሉ። በእኔ እምነት የአገራችን የአኗኗር ባህል፣ ሥርዓተ ትምህርቱና የፖለቲካ ግንኙነትና ልማዳችን ለዴሞክራሲው ዕድገት እንድንጠይቅና እንድንሞግት የሚገፋፋና የሚያበረታታ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪም ከላይ ለመጥቀስ እንደ ተሞከረው መንግሥት፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ ልሂቃን፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ ወጣቶችና ሴቶች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ወዘተ. በሐሳብ ልዕልና ዙሪያ በበቂ ሁኔታ እየሠሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡

በሌላ በኩል ሐሳባዊነትና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ዝም ብሎ እንደ ችግኝ የሚበቅል ነገር ሳይሆን፣ ከመንግሥት ጀምሮ በተለያዩ ባለድርሻዎች ብዙ ሥራ ተሠርቶበት የሚመጣ ነገር ነው። ስለሆነም ምክንያታዊነትንና የሐሳብ ልዕልናን በአገር ደረጃ ለማበልፀግ የእነዚህ አካላት ተሳትፎና አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአገር ዕድገት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትም ወሳኝነት አለው። እነዚህ አካላት ዜጎች ልዩነቶችን በምክክር፣ በውይይትና በንግግር እንዴት መፍታት እንደሚቻል ራሳቸው ምሳሌ ሆነው ለኅብረተሰቡ ሊያሳዩት ይገባል። ከዚሁ ጎን ለጎን ሊሰመርበት የሚገባው፣ ነገር ግን በማንኛውም አካል ወይም ቡድን ለሚነሱ ጥያቄዎችም ሆነ ቅሬታዎች አፋጣኝና ወቅታዊ ምላሽ መስጠት ወሳኝ መሆኑን ነው። ዞሮ ዞሮ በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመለወጥና የነቃ፣ በደንብ የሚያስብ፣ የሚጠይቅና የሚመራመር ኅብረተሰብ ለመፍጠር የእነዚህ አካላት አስተዋጽኦና ርብርብ ቁልፍ ነገር ነው። በተለይ ደግሞ በልምድ ለተፈተኑ፣ ለተከበሩና ለበሰሉ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች መድረክ በመክፈት ሐሳባቸውን ለኅብረተሰቡ እንዲያካፍሉና አቅጣጫ እንዲያመላክቱ ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

ሁላችንም እንደምናውቀው ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆዩ ብዙ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ ብዙ የፖለቲካና የልማት ጥያቄዎች አሉ። በአንፃሩ ደግሞ ዓለም መጥቃ በብዙ ርቀት ጥላን ሄዳለች። ከእነዚህ ሁኔታዎች አኳያ ባሉን ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግር ማብዛት አለብን ብዬ አላስብም። ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር እንደ ሠለጠነ ሰው መወያየትና መነጋገር ነው። አንዳችን ለአንዳችን ወዳጅ እንጂ ጠላት አይደለንም። ስለሆነም መፍትሔው ባሉት ችግሮችና ጥያቄዎቻችን ላይ በመወያየት ወደ እውነቱና ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ወደ ሚያጠናክረው መንገድ ተያይዘን መጓዝ ነው። ከምክንያታዊነት በራቀ ሁኔታ ጫፍና ጫፍ ይዘን መሄድ እንደ ትልቅ አገርና ሕዝብ ለእኛ ምንም ጥቅም የለውም። ስለሆነም ለችግሮቻችን መፍትሔ ሰጪዎቹ እኛው እንደ ሆንን አምነን ለዚሁ በሙሉ ልብ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። እንደዚያ ከሆነ ችግሮቻችንን መፍታት እንችላለን። አለበለዚያ ግን በስሜታዊነት ተሸንፈን ተያይዘን መውጣት ወደ ማንችለው ማጥ ውስጥ የመግባታችን ዕድል የሰፋ ይሆናል ባይ ነኝ። ቸር እንሰንብት!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...