Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው የሞባይልና የኮምፒዩተር መገጣጠሚያ በ50 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ሥራ ጀመረ  

ተዛማጅ ፅሁፎች

አይፕሮ ኢትዮጵያ የተሰኘው የሞባይል፣ የኮምፒዩተርና መለዋወጫዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ከውጭ በመጡ ባለሀብት በ50 ሚሊዮን ብር ካፒታል ተገንብቶ ሥራውን በቅርቡ ጀምሯል፡፡ ይህንኑ በማስመልከትም በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ፋብሪካው በይፋ ወደ ምርት ተግባር መግባቱ ተበስሯል፡፡

 የድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ መኮንን፣ ፋብሪካውን ጥቅምት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በማስመረቅ ሥራ መጀመሩን ባስታወቁበት ወቅት፣ የደሴ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ፍሰሐ አያሌው ፋብሪካውን መርቀው ነበር፡፡

ባለሀብቱ ወደ አገር ቤት በመምጣት በተወለዱባት ከተማ ‹‹ለአገር አንድ ቁም ነገር ልሥራ›› በሚል ቁጭት ተነሳስተው እንደመጡና አሁን የጀመሩትን የሞባይልና ኮምፒዩተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመክፈት መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥራው እንዲጀመር የተፈለገው የሞባይል መገጣጠሙ ተግባር ብቻ ቢሆንም፣ በቅርቡ የኮምፒውተር መገጣጠሙ ሥራ እንደሚጀመር የተናገሩት አቶ መሐመድ፣ አይፕሮ ኢትዮጵያ ሞባል ፋብሪካ አሁን ባለበት ደረጃ ‹‹M.N›› እና ‹‹A9›› የተሰኙ ሁለት ዓይነት ሞዴሎችን እያመረተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው በቀን ከ600 በላይ ሞባይሎችን እያመረተ በማምረት ሥራ ጀምሯል፡፡ ሠራተኞቹም ዕውቀቱና ክህሎታቸው እየጨመረ ሲመጣ ሙሉ በሙሉ ከቴክኒክና ከሙያ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ በመሆናቸውና ሥራውን እየተላመዱ ሲሄዱም የሞባይል ስልኮችን ገጣጥሞ የማምረት አቅሙ በቀን ከ3500 እስከ 4000 እንደሚደርስ ተጠቅሷል፡፡ አይፕሮ ሞባይል በብራንድነት በቻይና የሚመረትና በቻይና መመረት ከጀመረም ከ10 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ይህ የሞባይል ስልክ ከ100 አገሮች በላይ የገበያ መዳረሻ እንዳለው የገለጹት፣ የአይፕሮ ድርጅት የሽያጭ ኃላፊ ሚስተር ሁ ናቸው፡፡

እንደ ሚስተር ሁ ከሆነ ኩባንያው በየዓመቱ 25 ሚሊዮን ስልኮችን በመሸጥ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮጵያው ፋብሪካ የሙከራ ሥራው በመጀመር በሳምንት ውስጥ በቀን ከ800 በላይ ስልኮችን እንዳመረተ ጠቅሰዋል፡፡ በጥቂት ጊዜ ውስጥም ወደ 2000 ስልኮች በቀን ወደ ማምረቱ እንደሚሸጋገር ጠቅሰዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ ገበያዎችን እንደሚያዳርስ የሚጠበቀው የአይፕሮ ፋብሪካ ምርት፣ በአፍሪካ በተለይም በአልጄሪያ፣ ሞሮኮና ግብፅ ቀድሞውን የተገነባ ጠንካራ ገበያ እንዳለውም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ ፋብሪካው ለ70 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተጠቅሶ ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ለ400 ሠራተኞችም ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል፡፡ ሞባይሎቹን የሚገጣጥሙት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤቶች የተመረቁ ወጣቶች በመሆናቸው የሥራ ዕድሉንም በተማሩባቸው መስኮች ማግኘታቸው ለሥራውም ለወጣቶቹም መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አቶ መሐመድ ይገልጻሉ፡፡ ከቻይና በመጡ ባለሙያዎች ተጨማሪ የቴክኒክ ሥልጠና ከአንድ ወር በላይ በማግኘታቸው በሚሠሩት ሥራ ተጨማሪ ዕውቀት እንዲያገኙ ማገዙም ተጠቅሷል፡፡

አይፕሮ ሞባይል ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ስማርት ስልኮች ያሉትን የተለያዩ የሞባይል ዓይነቶችን እንዲሁም ታብሌት ስልኮችንና ኮምፒዩተሮችን በማምረት፣ ከእስያ ባሻገር፣ በአውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም በአፍሪካ የገበያ መዳረሻዎች ያሉት ኩባንያ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ ከሞባይልና የኮምፒዩተር የመለዋወጫ ዕቃዎች መገጣጠሚያ በተጨማሪ፣ የወረቅት ምርት ላይ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙም ታውቋል፡፡ የከተማው አስተዳደርም የወረቀት ፋብሪካው የሚገነባበበትን ቦታ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለውና ሥራውን በቶሎ እንዲጀመር ድጋፍ እንደሚያደርግ የደሴ ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች