Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ ደረጃ አያሟሉም

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ ደረጃ አያሟሉም

ቀን:

52 ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነው ተዘግተዋል

አጠቃላይ የትምህርት ጥራትንና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ በአዲስ አበባ  ከሚገኙና በውጭ ኢንስፔክት ከተደረጉ 1,407 የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ70 በመቶው በላይ ደረጃ ያላሟሉ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሪጉላቶሬ ኤጀንሲ ገለጸ፡፡

በ2010 ዓ.ም. ከቅድመ መደበኛ እስከ መሰናዶ የሚገኙ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የደረጃ ውጤትን አስመልክቶ፣ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የኤጀንሲው ዳይሬክተር ወ/ሮ ብሩክነሽ አርጋው እንደተናገሩት፣ የውጭ ኢንስፔክሽን ከተደረገባቸው 1,407 ትምህርት ቤቶች በቅድመ መደበኛ 41 ትምህርት ቤቶች ደረጃ አንድ እንዲሁም 560 ደረጃ ሁለት፣ በመጀመርያ ደረጃ በደረጃ አንድ አሥር እንዲሁም 409 በደረጃ ሁለት፣ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በደረጃ አንድ ስድስት እንዲሁም በደረጃ ሁለት 80 በአጠቃላይ 1,106 (78.6 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር ያወጣውን ደረጃ  ያላሟሉ ናቸው፡፡

ትምህርት ቤቶቹ የተመዘኑበት መለኪያ ግብዓት፣ ሒደትና ውጤት መሆኑንና ከ50 በመቶ በታች ያመጡ ትምህርት ቤቶች ደረጃ አንድ ማለትም ደረጃ ያላሟሉ፣ከ50 እስከ 69.99 በመቶ ደረጃ ሁለት (ደረጃቸውን በማሻሻል ላይ ያሉ) ከ70 እስከ 89.99 በመቶ ደረጃ ሦስት ማለትም ደረጃ ያሟሉ እንዲሁም 90 በመቶ እና ከዚህ በላይ ውጤት ያመጡ ደረጃ አራት ማለትም ደረጃቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያሟሉ ተብለው እንደሚለኩ ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፣ በቅድመ መደበኛ 108፣ በመጀመርያ ደረጃ 125 እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ 66 በአጠቃላይም 299 (21.3 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ደረጃ ሦስት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ከሚገኙ የግልና የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በመንግሥት ስምንት (0.57 በመቶ)፣ በግል 49 (3.48 በመቶ) በአጠቃላይ 57 (3.84) ትምህርት ቤቶች ደረጃ አንድ ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

ከ954 (68.2 በመቶ) ትምህርት ቤቶች ውስጥ 142 (አሥር በመቶ) በመንግሥት 817 (58.1 በመቶ) የግል ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት ደረጃ ሁለት ላይ የወደቁ ናቸው፡፡

የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ደረጃ አንድና ሁለትን አስመልክቶ ሲነፃፀሩም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በተሻለ ደረጃ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኢንስፔክሽን ሥራው ከዚህ ቀደም ከነበረው የኢንስፔክሽን ውጤት በማነፃፀርም ደረጃቸውን ያሻሻሉ፣ ያላሻሻሉና ከነበራቸው ደረጃ ዝቅ ያሉትንም አመላክቷል፡፡ ወ/ሮ ብሩክነሽ እንዳሉትም፣ ደረጃቸውን ያሻሻሉ በቅድመ መደበኛ 146፣ በመጀመርያ ደረጃ 125 እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ 33 በአጠቃላይ 304 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡

ደረጃቸውን ያላሻሻሉት ደግሞ በቅድመ መደበኛ 464፣ በመጀመርያ ደረጃ 372 እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ 93 በአጠቃላይ 929 ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ 119 ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ደረጃ ዝቅ ብለው ተገኝተዋል፡፡ እነዚህም ከደረጃ ሁለት ወደ አንድ ዝቅ ያሉ 39፣ ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ ሁለት 77 እንዲሁም ከደረጃ ሦስት ወደ ደረጃ አንድ ዝቅ ያሉ ሦስት ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ 66 የቅድመ መደበኛ፣ 30 የመጀመርያ ደረጃ እንዲሁም 23 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መሆናቸውን ወ/ሮ ብሩክነሽ ገልጸዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ላይ በተደረገው ኢንስፔክሽን ሁለት ትምህርት ተቋማት ብቻ አራት ማለትም ከ90 በመቶ በላይ በማግኘት የትምህርት ሚኒስቴርን መሥፈርት ማሟላታቸውን አሳይቷል፡፡

ለነባርና ለአዲስ ተቋማት የፈቃድ ዕድሳት የሚሰጠው ኤጀንሲው፣ ደረጃቸውን ጠብቀው ባልተገኙት ላይ ዕርምጃ መውሰዱም ተነግሯል፡፡

በ2010 ዓ.ም. ፈቃድ የሚታደስላቸው ቅድመ መደበኛ ነባር ተቋማት 363 የነበሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ 309 ትምህርት ቤቶች ሲታደስላቸው 28ቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ለአንድ ዓመት እንዲቀጥሉና እንዲያሻሽሉ መደረጉን 26 ደግሞ ከደረጃ በታች በመሆናቸው መዘጋታቸውን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ 275 ትምህርት ቤቶች የፈቃድ ዕድሳት ማድረግ የሚገባቸው የነበረ ቢሆንም ከእነዚህ 237 ደረጃ አሟልተው ታድሶላቸዋል፡፡ 16 በአንድ ዓመት ማስጠንቀቂያ ሲታደስላቸው 22 ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል፡፡

ከሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ፈቃድ ከጠየቁ ነባር ትምህርት ቤቶች 42 ታድሶላቸዋል፡፡ ሰባት በአንድ ዓመት ማስጠንቀቂያ ሲታደስላቸው፣ አራት ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ሆነው መዘጋታቸውንም አክለዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተደረጉ ሁለት ጥናቶች ውጤትም ተገልጿል፡፡

ከሌሎች ክልሎች በተለየ የአዲስ አበባ የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ እየሆነ የመጣበትን ምክንያት አስመልክቶ የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ጥናትም፣ ለውጤቱ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ መምጣት ተማሪዎች ለትምህርት ያላቸው አሉታዊ አመለካከት፣ በከተማው ያለው ሥራ አጥነት የፈጠረው የተማረ የት ደረሰ የሚል ጫና፣ ሳንማር ጥሩ ገንዘብ ማግኘት እንችላለን የሚል ምልከታና የወላጆች ክትትል ማነስ እንደ ምክንያትነት ተነስቷል፡፡

በመምህራን በኩልም ከመረጣ እስከ ሥልጠና ክፍተት መኖሩን ጥናቱ ማመላከቱን የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኤልአዛር ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ከ2006 ዓ.ም. እስከ 2008 ዓ.ም. በ1,298 የግልና የመንግሥት ተቋማት ላይ ያረገውን ኢንስፔክሽን አስመልክቶ በኅዳር 2009 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ በአዲስ አበባ 25 በመቶ ያህል የትምህርት ተቋማት ብቻ የተቀመጠውን ደረጃ አሟልተው እንደነበር መግለጹ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...