Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‹ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል…›

ሰላም! ሰላም! ‹‹የጊዜ እንጂ የሰው ጀግና የለውም›› ይባል ነበር አሉ፡፡ ጊዜ ይህንን ያህል ክብር ሲያገኝ እኛ ለምን እንረክሳለን? ግራ ይገባኛል፡፡ የጊዜ ነገር ሲነሳ ብዙ የሚባሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ ጊዜን የመሰለ ዳኛ እያለ እንዴት አይባልም፡፡ የሰሞኑ አገርኛ ጉዳያችን ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እስከ የአገር ሀብት ዘረፋ ተጠርጣሪዎች ላይ መሆኑ ደርሶ እንደ ወፈፌ ብቻዬን ያስቀባጥረኛል፡፡ ተፈጸሙ የተባሉትን ጉዶች የሰማ ወገኔ እንደ እኔ ብቻውን ‘ወቸ ጉድ!’ እያለ ሲያወራ የአማኑኤል ምሩቅ ቢመስል ምን ይገርማል? ‹‹ይገርማል እኮ ባሻዬ ጊዜው እንዴት ይሮጣል?›› ብላቸው በቀደም ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ፣ “ከስቅለት እስከ ትንሳዔ ያለውን ነው? ወይስ ከፋሲካ ወደ ፋሲካ የሚሮጠውን ማለትህ ነው?›› ብለው አዞሩብኝ። ‹‹የሦስት ቀናት ዕድሜና የዓውደ ዓመት ቆጠራ ምንና ምን ሆኖ?›› ብላቸው፣ በጣር ሦስት ቀናት ሦስት ዓመታት፣ በትፍስህት ደግሞ ዓመት ማለት ቅፅበት እንደሆነ አብራሩልኝ። ወይ ጣርና ጊዜ አያ! ታዲያ ባሻዬ ጣርና ትፍስህት ተሰባጥረው በተሰፉባት ዓለም ጊዜ እንደ ቆጣሪው ይወሰናል ማለታቸው ነው። ‹‹የሰሞኑን ጉድ ከሰማሁ ወዲህ እንቅልፍ አጣሁ፤›› ብዬ ደግሞ የባሻዬን ልጅ ባዋየው፣ ‹‹አገርና ሕዝብን እርር ሲያደርግ የከረመው ይህ ዓይነቱ ዘግናኝ ጉድ በአደባባይ አይነገር እንጂ ከሕዝብ እኮ የተደበቀ አልነበረም፤›› ብሎ የባሰ አስደነገጠኝ። አንዳንዴ ሳስበው ስንቱን በሆዳቸው አምቀው የኖሩ ወገኖቼ ፅናት ይገርመኛል፡፡ ፅናቱን ይስጠን እንጂ ስንት ያልተነገረ ጉድ አለ መሰላችሁ? ኧረ ብዙ ነው ወገኖቼ!

‹ሁሌም እንደ ልብ መሆን የለም› የሚባለው አባባል እኮ አሁን አሁን ለአንዳንዶቻችን ‘መቼም የፈለጉትን መሆን የለም’ ወደሚለው የተሸጋገረ መሰለኝ። መቼም ጊዜው የሽግግር ነው። የሀብት ሽግግር ላይ የነበሩት ዘመን አበቃ ማለት ነው? ለነገሩ ሙሉ ለሙሉ እንዲያ ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ በየቦታው የመሸጉ የሥቃይ ፊታውራሪዎችና ዘራፊዎች ጉዳይ ምኑን ተነካና? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ግን፣ ‹‹ገና ያልተነገሩ ጉዶች ወይ ጨርቃችንን አስጥለው ያሳብዱናል አሊያም አገር አስጥለው ያስኮበልሉናል. . . ›› እያለ ብቻውን ሲስቅ ዕብደት የጀማመረው መስሎኝ በድንጋጤ ክው አልኩ፡፡ ይገርማችኋል በአንድ ወቅት አኗኗራችንን በማስመልከት አንድ የተሠራ ጥናት በሬዲዮ ሳዳምጥ ነበር። በተለይ የበዓል አከባበራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ ምን ዓይነት መልክ እንደያዘ ይተነትናል፡፡ በእውነቱ በጣም አስደንጋጭና ግራ አጋቢ ነገር ሰማሁ። አብዛኛው ሰው በሰጠው አስተያየት በዓል የሚያከብረው ከጠዋት እስከ ማታ ተጠቅልሎ ተኝቶ በመዋል ነው አሉ። ምን ግራ አጋባህ አትሉኝም? በዓውደ ዓመት ቀኑን ሙሉ ተኝተን ከዋልን፣ በአዘቦት ቀን 24 ሰዓት ነው የምንተኛው ማለት እኮ ነው። ለይቶልናል ማለት ነው!

መቼም ጨዋታ ነው አትቀየሙኝም። ይኼውላችሁ ሐበሻ የሚታማው ውስጡ አምቆ በያዘው ገመናው ብቻ ነው ይባላል። ካላመናችሁ በየግላችሁ ለሐሜት የምትፈጁዋቸውን ማገዶዎች ብዛት አስቡና መልሱን ድረሱበት። ‘የለም ሐበሻ የሚታማው በስንፍናው ነው’ የምትሉ ወደ እናንተ ሐሳብ ስለምመጣ ተረጋጉ። አሁን ልብ ብላችሁ ብታስቡት የበዓል ቀንና የአዘቦት ቀን አዋዋላችን ሲታይ በሥራ የተጠመድን የምንመስለው በየትኛው ነው? ይህንን ስል ግን በዘረፋ ሀብት አካብተው በውስኪ ሲራጩ ውለው የሚያድሩትን እንደማይመለከት ልብ ይባልልኝ፡፡ የታሰሩ ጥቅል ገንዘቦችን እንደ ፈንዲሻ እየበተኑ ሲጫጫሱ የሚያነጉ ወንበዴዎችን ማለቴ ነው፡፡ ቆይ እስቲ ሰሞኑን ውስኪ ቤቶችና ጮማ መቁረጫዎች ባዶ ሆነዋል የሚባለው እውነት ነው? አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ ‘አስረሽ ምቺው’ የሚባልባቸው መጨፈሪያዎች ባዶአቸውን ቀርተዋል፡፡ እንግዲህ ዝምባቸውን እሽ ይበሉ!

 አንዱ የሆነ ጊዜ በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት ላይ ሊሳተፍ ደውሎ፣ “እኔ!” አለ። ‹‹እኔ. . . ከወዲሁ ያስጨነቀኝ የዋጋ ጭማሪ ሳይሆን የሥጋ ጥራት ጉዳይ ነው፤›› ሲል ሰምቼው ባሻዬን ትክ ብዬ ሳያቸው፣ ‹‹ልክ እንደ ሥጋው ለአገር አብዝተን ብንጨነቅ የት እንደርስ ነበር?›› ብለው አቀረቀሩ። ባሻዬ ደግሞ በትንሽ በትልቁ ማቀርቀር ይወዳሉ። ምናልባት እኔ በዕድሜ ስለማንሳቸው ይሆናል ጉድ ሰምቼና ሁሉ ነገራችንን ታዝቤ ቀና የምለው? እንዲያውም አንዳንዴ ራሳቸው ባሻዬ፣ ‹‹ሆድህን ሰፋ አድርገው፤›› ይሉኛል። እኔ ደግሞ ቀጥታ ተርጉሜ፣ “ከዚህ በላይ?” እላለሁ። ከዚህ በላይ ካሰፋነውማ ሌላ ሦስት ሺሕ ዘመን ሆድና ሆድ ተኮር እሳቤዎች እንደ ነገሡ፣ እንዳስጨነቁንና እንዳሳሰቡን ቀረን በቃ። በአዕምሮ የምንሰፋበት ጊዜ ስለሚናፍቀኝ እኮ ነው በዚህ ዘመን እነ ሆድ አምላኩን የምኮንነው። ‹ማዘን ያለብን ለተራበው ሳይሆን ለጠገበው ነው. . . › እየተባልን አድገን አገሩን የዘረፋና የጭካኔ አምባ ማድረጋችን እያቃጠለኝ ሰነበተ፡፡  የአገር ሀብት ተዘርፎ እንቅልፍ አለ እንዴ?

እናላችሁ እንዲህ የባጥ የቆጡን ስሰማና ሳይ በመሀል በመሀል አንድ ገጽ የፈጀው የማንጠግቦሽ አስቤዛ ዝርዝር ትዝ እያለኝ ልቤ ድንግጥ እያለ ተቸገርኩ። ገበያው እንደምታዩት ነው። ሁሉም ‘ታላቅ ቅናሽ’ እያለ ቢለጥፍም ከስንት ወደ ስንት እንደቀነሰ አናውቅ፣ ምን ያህል እንደ ጨመረ አናውቅ። ‹‹ሰውን ማመን ገዝቶ ነው? ሸጦ ነው?›› ስለው፣ ‹‹አንተ ደላላ ሆነህ ያላወቅከውን እኔ እንዴት አውቃለሁ?›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው። አንድ ያልገባው ነገር ምን መሰላችሁ? ምናልባት መንግሥት ራሱ ተናግሮት ሲያበቃ ለራሱ ያልገባው . . . ደላላ ያልሆነ በከተማው ላይ ቢፈለግ አለመኖሩን ነው። እዚህ ጋ አባባሌን አዛብታችሁ እንዳትረዱብኝ ደላላ ሁለት ትርጉም አለው። አንድ ፈላጊና ተፈላጊን ከመሀል ሆኖ ማገናኘት። ሁለት አባብሎና አዘናግቶ ገደል መክተት። ስም በመለጠፍ መቼም አንታማም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጥናቸውን ሕገወጥ ደላላ ብለን አውግዘናል። ‹‹እኛ አላልንም መንግሥት ነው፤›› ትሉ ይሆናል እኮ በልባችሁ። ለነገሩ አገሩን የደላላ መጫወቻ ያደረገው ራሱ መንግሥት እኮ ነው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ኮሚሽን ሲበላ ነበር እኮ ነው የተባልነው፡፡ ግልጽ መሰለኝ፡፡ በውጭ አገር ግዥ ሳይቀር ኮሚሽን እንደ ደላላ የሚቀረጥፉ የመንግሥት ሹማምንት እኮ ናቸው ተጠርጥረው የተከሰሱት፡፡ አሁንስ ገባችሁ? ካልገባችሁ ዓቃቤ ሕግን ጠይቁ!

  የጀመርኩትን ልጨርስላችሁና ሌላውን በሌላ ጨዋታ ልመለስበት። “ታላቅ ቅናሽ” ብሎ ነገር የሮኬት ሳይንስ ሆኖብኛል እያልኳችሁ ነበር። አዎ። ከሰሞኑ ሽቀላ እኔም ወግ ይድረሰኝ ብዬ በግ ተራ ሄጄ ላቱን መትሬ አንድ መለስተኛ በግ መረጥኩና፣ ‹‹ስንት ነው?›› ስለው ሻጩን፣ ‹‹ተጽፎበታል እኮ፤›› ብሎ ወደ ሆዱ ጠቆመኝ። አዙሬ ሳየው 15 በመቶ ቅናሽ ይላል። ‹‹ምን ማለት ነው?›› ብዬ ስጠይቀው ሻጩ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ከአምናው የኅዳር ወር የበግ ዋጋ ሲነፃፀር 15 በመቶ ጭማሪ ማለት ነው፤›› አለኛ። ከዚህ በላይ ሕገወጥነት አለ አሁን? ‘ሲወልዱ ዓይታ ምን አለች’ አሉ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሁሌ ምቾት ቢኖር ድለላውን ትቼ የበግ ነጋዴ እሆን ነበር። ኋላማ ትቼው ስሄድ ባለበጉ፣ “ነጋዴ ለዘለዓለም ይኑር!” አይልም መሰላችሁ በእኔ እየሳቀ?! “ምን?” ብዬ ዞሬ አየሁት። “በኸኸኸኸኸ!” ብሎ የደገመው መሰለኝ በበግኛ። ምን አስዋሸኝ እንዴ?! ቂቂቂ! ምድረ ዘራፊ ደንበኞቹ እስር ቤት የገቡ እንደሆነ እኔ መቀለጃ መሆኔ አናዶኛል፡፡ ስንቱ ይቀልድብን?

 የውድ ባለቤቴን ማንጠግቦሽን ጥያቄ ለማሟላት አንድ ቪላ ጆሮውን አስመትቼ ሳበቃ ኮሚሽኔን ለመቀበል ቀለበት መንገድ ዳር ተቀጣጠርኩ። አሁን እስኪ ካልጠፋ ቦታ ሰው ቀለበት መንገድ ዳር ይቀጣጠራል? አንዳንድ ሰዎች ቀለበታቸው ውስጥ አልገባ ስንላቸው ቀለበት መንገድ ዳር ይቀጥሩናል። ግርግሩ ደርቷል። ክንፍ ላይ የመደብነው መንገድ የአማካይነቱን ሥፍራ ወስዶ ከተማ መሀል ለመሀል ተዘርግቶ ፀሐይ የሚሞቅ ዘንዶ መስሏል። ‹ቀለበት መንገድ መዝለል ክልክል ነው› ብሎ መለጠፍ ከተከለከለ ቆየ መሰለኝ። ኮሚሽኔን የሚያቀብለኝ ሰው ሲቆይብኝ መንገድ መንገዱን እያየሁ አንድ ነገር ማሰብ ጀመርኩ። ዘንድሮ ምን የማይታሰብ አለ?

ይኼኔ አንዱ አልፎ ሂያጅ አጠገቤ መጥቶ ቆመና አላፊ አግዳሚውን እየቃኘ፣ “እየው ያንን!” ብሎ ጠቆመኝ። አንድ ልጅ እግር በግ ተሸክሞ ቀለበት መንገድ ያቋርጣል። ‹‹እስኪ አሁን ያ ሲኖትራክ ቢዳምጠው ለማንኛቸው ልናዝን ነው?›› እያለ አንገቱን ያወዛውዛል። ይኼን ጊዜ በጣም አጭር ቁምጣ የታጠቀ ስስ ካኔቲራ የለበሰ ፈረንጅ እየሮጠ በአጠገባችን አለፈ። መንገደኛው ሸክሙን አውርዶ የገበያ መንገዱን ረስቶ እንደ ትንግርት ያየዋል። ‹‹ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ቀለበት መንገድ ዳር ተለማምዶ መስሎታል ኮከብ የሆነው? አይ ፈረንጅ?›› እያለ አላስቀምጥ ሲለኝ እኔ ማዶ አያለሁ። አምጠው ወልደው አንድ ጥሩ ጎልማሳ የሚያደርሱ እናት፣ ቦርሳቸውን እንዳነገቱ ከዘርፋፋው ቀሚሳቸው ጋር እየታገሉ የመንገዱን አጥሮች ይዘላሉ። ይኼን ይኼን ግን አናይም። በዚህ በዚህ አናፍርም። ምክንያቱስ አትሉኝም? ለጤናው አስቦ ጥጉን ይዞ የሚሮጥ ፈረንጅ ለሕይወታችን ከማንሳሳው ከእኛ ቀድሞ ዓይን ይገባላ። ከዓይን ያውጣችሁ እንጂ ሌላ ምን እላለሁ! ከዓይን ወጥተን አይደል ይህንን የሰሞኑን ጉድ እየሰማን ያለነው? ገንዘባችንን ፈረንጅ አገር እያሸሹ አይደል እንዴ በአንድ ዓይናችን የምናለቅሰው? ከዓይን ይሰውረን!

በሉ እንሰነባበት። ኮሚሽኔን ተቀብዬ ያንን የምባዝንለትን በግ ገዛዝቼ ቤት ላደርስ አሸክሜ ተጣደፍኩ። ቤት ስንደርስ ተሸካሚው ግራ ገባው። ‹‹እዚህ ነው ሠፈርዎ?›› አለኝ። “አዎ” አልኩት። ‹‹ይኼ ነው ቤትዎ?›› አለኝ ደግሞ። “ምነው?” አልኩት። አንዳች ነገር የተጠራጠረ መሰለ። መንደሬም ኑሮዬም እንደ ማንኛውም ተራ ሰው መሆኑን ዓይቶ በግ የመግዛት አቅሜን ሲገምተው ለካ ግራ ገብቶት ኖሯል። ‹‹በል እንካ. . . ›› ብዬ 20 ብር ስሰጠው፣ ‹‹ከመቶ ብር በታችማ አያዋጣም፤›› አለኝና አረፈው። ‹‹ትቀበላለህ አትቀበልም?›› ስለው፣ ‹‹ዋጋዬን ተናግሬያለሁ፣ ካልከፈሉ እጠቁማለሁ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? መጣቻ የእኔዋ ማንጠግቦሽ እሳት ለብሳ እሳት ጎርሳ። ‹‹ምን ብለህ ነው የምትጠቁመው አንተ?! በዓመት አንዴ  ሥጋ በሉ ብለህ እኛ ላይ ነው ለመንደርተኛው ላይ የምትጠቁመው? የእኔ አንበርብር ምንተስኖት ላይ ታች ብሎ ለፍቶ ላቡን ጠብ አድርጎ ኑሮውን በጥበብ የሚኖር አርዓያ ባሌ ነው። ከጠቆምክ ሰርቆና አምታቶ ከአገር ከሕዝብ ቀምቶ አውሮፓና አሜሪካ ገንዘቡን የሚያሸሸውን ጠቁም። እኛ መርከብ ወይም አውሮፕላን የሸጥን ወይም የህዳሴ ግድቡን በጀት የዘረፍን መሰለህ እንዴ? የእኛ ግልገል በግ መግዛት ገረመህ? አሉልህ እኮ ተነግሮ የማያልቅ የሕዝብ እንባ ያፈሰሱልህ፤›› ስትለው ላብ አጠመቀው። እኔን ላብ ያጥምቀኝ? ፍርድ ቤት ተከሶ የቀረበ መሰለ እኮ?

በእሱ ቤት እንግዲህ ‘መኒ ላውንድሪ’ ሊያጋልጥ ጫፍ ደርሶ ነበር። ሐሜትና ትችቱን ባለምደውና ልብ ባልገዛ ኖሮ በለፋሁበት ገንዘቤ ሳቢያ ጣቢያ አድሬ ነበር። መቼስ የማይለመድ የለም ለመድነው። ክፉንም ደጉንም ማለቴ ነው ታዲያ። እንዲያው ስታስቡት ስንቱ ነው አሁን በባዶ ቤት ገንዘቡንና ንብረቱን በጉቦ አሟጦ፣ በፍትሕ ዕጦት ለፈሪሳውያን ባደላ ችሎት ፊት ቆሞ ተረትቶና ንብረቱን ተነጥቆ ቆሎ ያረረበት? ስንቱ ያለ ቤትና ያለ ትዳር ቀረ? ስንቱ ተበላ? ስንቱ አበደ? ስንቱ ወደቀ? ስንቱ ከሰረ? ‹‹ለሰላሳ ዲናር ሊያጣ ነፍስ ይማር. . . ›› ያለው እኮ ዘፋኙ ሀቅ ነው። ታዲያ ይሁዳ ዋጋውን እስኪያገኝ እስኪ እኛ አጠገባችን ያሉትን አግኝተው ያጡትን፣ ስቀው ያዘኑትን እያሰብን እንረዳዳ። አይመስላችሁም? በእርግጥም ሞቆ የቀዘቀዘባቸው ስንት ይሆኑ? ስንቶቹ ይሆኑ በሥነ ልቦና ጉዳት ተሰብረው የቀሩ?  ግና በዳይና ተበዳይ መዳኘታቸው አይቀርም፡፡ ግፍ የፈጸመም ለፍርድ መቅረቡን ስሰማ፣ ‹ለሁሉም ጊዜውን ይጠብቅለታል. . . › ያለው አንጋፋ ድምፃዊ ምን ታይቶት ነበር አሰኘኝ! ጊዜው ይራቅ እንጂ አንዳንዱ እንደ ራዕይ ይታየዋል! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት