የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ዘሪሁን ዛሬ ኅዳር 7 ቀን 2011 ዓ.ም. በተጠረጠሩበት ወንጀል ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 10ኛ ምድብ ችሎት ቀርበው፣ ከቀድሞ አለቃቸው አቶ ጌታቸው አሰፋ ትዕዛዝ እየተቀበሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
አቶ ያሬድ ዜጎችን ጉንዳን ያለበት ቦታ በማሰር፣ ራቁታቸውን ገልብጠው በማስገረፍ፣ በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ወደ ውጭ በመላክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብለው ሀብት በማከማቸት፣ እንዲሁም በእሳቸው ትዕዛዝ የሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስረድቷል፡፡
አቶ ያሬድ በበኩላቸው ከቤተሰብ ጋር እንዳይገናኙ ተደርገው በአንድ ክፍል እንደተቆለፈባቸው ተናግረው፣ ከሕግ አማካሪያቸው ጋር ተነጋግረው በተጠረጠሩበት ወንጀል ላይ ምላሽ እንደሚሰጡ አስታውቀዋል፡፡ ለፊታችን ማክሰኞ ኅዳር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ተቀጥረዋል፡፡
አቶ ያሬድ ረቡዕ ኅዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ዱከም ከተማ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው አይዘነጋም፡፡
በተጨማሪም በሰኔ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የመስቀል አደባባይ የቦምብ ጥቃት የተጠረጠሩት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፣ እንዲሁም ኮሎኔል ጉደታ ኦላናና ኮሎኔል ሰጠኝ ካሳዬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ኮሎኔል ጉደታ ቴሌኮም የጥበቃና ደኅንነት ዲቪዝዮን ኃላፊ ሲሆኑ፣ ሰሞኑን በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል፡፡