Saturday, September 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሚድሮክ በተነጠቀው መሬት ሳቢያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በድጋሚ ተቃወመ

ሚድሮክ በተነጠቀው መሬት ሳቢያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በድጋሚ ተቃወመ

ቀን:

ሚድሮክ በተለያዩ ኩባንያዎቹ የተያዙ ቦታዎች ካርታዎች መምከናቸውን በመቃወም ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ቅሬታ አቅርቦ ውሳኔ እየተጠባበቀ ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቦታዎቹ ላይ ያሉ ዕቃዎች እንዲነሱ ማዘዙን በድጋሚ ተቃወመ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ መስከረም 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የሚድሮክ 11 ቦታዎችን ጨምሮ በግል፣ በመንግሥትና በዲፕሎማቲክ ተቋማት ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ 154 ቦታዎች የሊዝ ውል ተቋርጦ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ለዓመታት ታጥረው ያለ ግንባታ የተቀመጡት አይነኬ የተባሉት ቦታዎች በአጠቃላይ 412.68 ሔክታር ሥፋት አላቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ካርታ ያመከነባቸው ባለይዞታዎች በቦታዎቹ ላይ ያላቸውን ዕቃ እንዲያነሱ ትዕዛዝ የሰጠ ሲሆን፣ እስካሁን 14 የሚሆኑት ዕቃቸውን እንዳላነሱ ተገልጿል፡፡

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዕቃ ያላነሱ ተቋማት በአንድ ሳምንት ጊዜ  ውስጥ ዕቃቸውን ካላነሱ ዕርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል፡፡

ከሚድሮክ በኩል ጉዳዩን የሚከታተሉት አቶ አብነት ገብረ መስቀል አገር ውስጥ ባለመኖራቸው አስተያየታቸውን ማካተት ባይቻልም፣ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ እንዳረጋገጡት ሚድሮክ ቅሬታውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አቅርቧል፡፡

አቶ ኃይሌ እንዳሉት ሚድሮክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቅሬታውን አቅርቦ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዕቃዎቻችሁን አንሱ ማለቱ አግባብ አይደለም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ቦታዎች ካርታ የማምከኑ ዜና ከተሰማ በኋላ ሚድሮክ ለአስተዳደሩ ቅሬታ አቅርቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ቅሬታው ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ እየጠበቀ እያለ፣ አስተዳደሩ ቦታዎቹን ወደ መሬት ባንክ ለማስገባት ዕቃዎቹን እንዲያነሱ መጠየቁ ቅሬታ እንደፈጠረበት ታውቋል፡፡

ሚድሮክ በከተማው የተለያዩ ሥፍራዎች 11 ቦታዎች ላይ በ18 ቢሊዮን ብር በጀት ሕንፃዎችን የመገንባት ዕቅድ ነበረው፡፡

ነገር ግን ዕቅዱ ተግባራዊ ሊሆን ያልቻለው የመሠረተ ልማት ተቋማት ዕቃዎቻቸውን በወቅቱ አለማንሳትና በዲዛይን ለውጥ ችግሮች ምክንያቶች መሆናቸውን ሚድሮክ ገልጿል፡፡

አቶ አብነት በቅርብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የሊዝ ውል እንዲቋረጥ በወሰነባቸው ቦታዎች ላይ ሚድሮክ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሷል፡፡ በተለይ በሸራተን ማስፋፊያ ከሊዝ ውጪ ሚድሮክ ለነዋሪዎች ማስነሻ 87 ሚሊዮን ብር መክፈሉን፣ በፒያሳ ፕሮጀክቱም ለዲዛይን ለውጥና ለግንባታ በርካታ ሚሊዮን ብሮች ማውጣቱን ጠቁመው፣ ‹‹በአሥራ አንዱም ቦታዎች በእኩል ደረጃም ባይሆን ሚድሮክ የተወሰደውን ዕርምጃ ይቃወማል፤›› ሲሉ ገልጸው ነበር፡፡   

ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጊዜ ቦታዎቹ እንዲነጠቁ የውሳኔ ሐሳብ ቢቀርብም፣ አቶ ኃይለ ማርያም የኩባንያው ባለቤት ሼክ መሐመድ አል አሙዲ በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር የሚገኙ በመሆኑ፣ ሐሳባቸውን መግለጽ የማይችሉ ስለሆነና ለአገር ባለውለታም በመሆናቸው ምክንያት በይደር እንዲቆይ አድርገው ነበር፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...