Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየካፋ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

የካፋ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄን በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

ቀን:

በደቡብ ክልል የካፋ ዞን ምክር ቤት የካፋ ክልል እንዲዋቀር የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ፡፡ የዞን ምክር ቤቱ ውሳኔውን ያፀደቀው ሐሙስ ኅዳር 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ነው፡፡

የደቡብ ክልል በፌዴራሊዝም መዋቅሩ ላይ በርካታ ትችቶች ሲያስነሳ የነበረ አወቃቀር ያለው ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ከተደነገገውና ሌሎች ክልሎች ከተዋቀሩበት መርህ አንፃር ያልተዋቀረ ክልል ነው ሲሉ የሚተቹ በርካታ ናቸው፡፡ የደቡብ ክልል ከ56 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችን አቅፎ የያዘ ክልል ነው፡፡

የካፋ ዞን ምክር ቤት በዞኑ ወጣቶች የክልልነት ጥያቄ ላይ እንዲወስን ከፍተኛ ግፊት የነበረበት ሲሆን፣ ይህም በቅርቡ በኢትዮጵያ የሚዘጋጀውን የቡና ሁነት አስመልክተው የቡናና ሻይ ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ አንዴ ካፋን አንዴ ጂማን የቡና መገኛ ናቸው በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት ለመቃወም ሠልፍ በወጡ በርካታ ወጣቶች የተንፀባረቀ ሐሳብ ነው፡፡ በሠልፉ ላይ የካፋ ዞን ክልል የመመሥረት መፈክር በጽሑፍም በድምፅም ተስተጋብቷል፡፡

ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ያደረጉ አንድ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹ካሁን በኋላ ነገ ዛሬ ሳይባል ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄው በጽሑፍ እንዲቀርብ ዝግጅት ይደረጋል፤››  ብለው፣ የሕዝቡ ጥያቄ እየሆነ ስለመጣና ሕዝቡ ወደ ክልል ከተማው ከመሄድ ይልቅ፣ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ስለሚቀለው ክልል ሄዶ ጉዳይ ማስፈጸም ከባድ እንደሆነበት ተናግረዋል፡፡

በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን በቀዳሚነት የክልል መመሥረትን ጥያቄ በዞን ደረጃ አፅድቆ በክልል ምክር ቤት ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደረገ ሲሆን፣ የወላይታ ዞን ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ ከተወያየ በኋላ፣ ከውሳኔ በፊት ሕዝቡ ይወያይበት በማለት ለሕዝብ ውይይት አቅርቦታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በደቡብ ክልል በሃዲያ፣ በጉራጌና በተለያዩ አካባቢዎች የክልልነት ጥያቄዎች እየተነሱ ሲሆን፣ ደቡብ ክልል የሚባል ወደፊት ላይኖር ይችላል ሲሉ ግምታቸውን የሚያሰሙ አልጠፉም፡፡

ይሁንና የሁሉም የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ቢገኝ ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም የሚፈለገውን ውጤት ላያመጣ ይችላል ሲሉ ካሁን ቀደም ለሪፖርተር የተናገሩት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ፣ በዋናነት የእነዚህ ጥያቄዎች ምንጮች የልማት፣ የእኩል ተጠቃሚነትና የአገልግሎቶች ተደራሽነት ስለሆነ፣ ለዚህ ምላሽ መስጠት የሚያስችል ጥናት በክልሉ መንግሥት እየተሠራ መሆኑን ተናግረው ነበር፡፡

ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 መሠረት ማንኛውም ብሔር ክልል የመመሥረት መብት ያለው ሲሆን፣ የዞኑ ምክር ቤት ጥያቄውን በሁለት ሦስተኛ ድምፅ አፅድቆ ለክልሉ ምክር ቤት ካቀረበ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚደራጅ ተደንግጓል፡፡ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ ብዙኃኑ ውሳኔውን የሚደግፉ ከሆነ፣ ክልሉ አዲስ ለሚፈጠረው ክልል ሥልጣኑን ያስረክባል፡፡ አዲስ የሚፈጠረውም ክልል ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የፌዴራል መንግሥቱ አባል ይሆናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...