የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከ2011 እስከ 2012 ዓ.ም. ለፍጆታ የሚውል ነዳጅ ለመግዛት ባወጣው ጨረታ፣ ሦስት ዓለም አቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎች በመጫረት ላይ እንደሆኑ ታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት 1.35 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ናፍጣ፣ 240,000 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅና 350,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን የመግዛት ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ መስከረም 2011 ዓ.ም. ግልጽ የሆነ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ጨረታው ጥቅምት 20 ቀን ተዘግቶ ጥቅምት 21 ቀን 2011 ዓ.ም. መከፈት የነበረበት ቢሆንም፣ በተጫራቾች ጥያቄ ለጥቅምት 29 ቀን ተራዝሞ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት 36 ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ የገዙ ቢሆንም፣ የቴክኒክና ፋይናንስ ዕቅዳቸውን አሟልተው ለጨረታ ኮሚቴው በቀነ ገደቡ ያስገቡት ትራፊጉራ፣ ቪቶል ኦይልና ፔትሮ ቻይና ብቻ ናቸው፡፡ የጨረታ ኮሚቴው የቴክኒክ ዕቅዶቹን በመገምገም ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ታደሰ፣ የቴክኒክ ግምገማው በዚህ ሳምንት ተጠናቆ የፋይናንስ ጨረታው እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ሦስቱም ኩባንያዎች የቴክኒክ ጨረታውን ካለፉ በፋይናንስ ግምገማው ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው ኩባንያ አሸናፊ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በሠራው ሥሌት ከ2011 እስከ 2012 በጀት ዓመት የአገሪቱ አጠቃላይ የነዳጅ ፍጆታ 4,197,000 ሜትሪክ ቶን እንደሚሆን ተገምቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2,780,000 ሜትሪክ ቶን ናፍጣ፣ 840,000 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ፣ 494,000 ሜትሪክ ቶን ቤንዚንና 83,000 ሜትሪክ ቶን ቀላልና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ይገኙበታል፡፡ የነዳጅ ግዥ ወጪው ከ2.8 ቢሊዮን እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡
የነዳጅ ውጤቶቹ ሙሉ በሙሉ የሚገዙት በጨረታ እንዳልሆነ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀደም ሲል ከኩዌትና ከሱዳን መንግሥታት በተፈራረመው ውል፣ የአገሪቱ ገሚሱ የነዳጅ ፍጆታ የሚሸመተው ከኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽንና ከሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ነው፡፡
በውሉ መሠረት የኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 50 በመቶ ናፍጣ፣ 75 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ እንደሚያቀርብ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡ የተቀረውን 50 በመቶ ናፍጣ፣ 25 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ በጨረታ ይገዛል፡፡
በተመሳሳይ የሱዳን ፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን 40 በመቶ የሚሆነውን ቤንዚን የሚያቀርብ ሲሆን፣ 60 በመቶ የሚሆነው በጨረታ እንደሚገዛ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ቀላልና ጥቁር ናፍጣ (ፈርነስ) በየካቲት ወር በሚወጣ የተለየ ጨረታ ይገዛል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አብዛኛውን ነዳጅ የሚያስገባው በጂቡቲ ወደብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በጂቡቲ ወደብ የሚገኘው ሆራይዘን የነዳጅ ተርሚናል በመጨናነቁ እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍጆታ ማስተናገድ እየተሳነው ነው፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ የተወሰነውን ነዳጅ በአሰብ ወደብ ለማስገባት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ለማድረግ ድርጅቱ ባወጣው የነዳጅ ግዥ ጨረታ ኩባንያዎች በጂቡቲና አሰብ ወደቦች ነዳጅ የሚያቀርቡበትን ዋጋ እንዲጠቅሱ ተጠይቀዋል፡፡
የጨረታው ውጤት ከታወቀና አሸናፊው ኩባንያ ውል ከፈረመ በኋላ ነዳጁ ከጥር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ መግባት ይጀምራል፡፡ የአሰብ ወደብን መጠቀም ለመጀመር መሠረተ ልማቶች መሟላት ስላለባቸው፣ ወደቡ የኢትዮጵያን ነዳጅ በጥር ወር ለማስተናገድ ዝግጁ ላይሆን እንደሚችል አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በወደቡ መታደስ ያለባቸው መሠረተ ልማቶች አሉ፡፡ የአስፋልት መንገዱም ጥገና መጠናቀቅ ይኖርበታል፤›› ያሉት አቶ ታደሰ፣ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ድርጅታቸው የተወሰነ መጠን ነዳጅ በአሰብ ወደብ ለማስገባት ዝግጁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡