Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውል ሕግ ጉዳይ

መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውል ሕግ ጉዳይ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ባለፈው ሳምንት በዚሁ አምድ የጀመርነውን ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፈው ጽሑፍ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ሲባል የሚደረጉ ውሎችን እንዴት እንደሚቋቋሙ አጠር አድርገን ተመለክተናል፡፡ በተጨማሪም የኮምፒውተር ፕሮግራምን (ሶፍትዌርን) በምሳሌነት በመውሰድና ከባህርይውና ሥሪቱ ጋር በሚስማማ መልኩ ምን ዓይነት ውሎችን ማድረግ ይቻላል ሶፍትዌርስ ግብይትስ እንደሸቀጥ ነው ወይስ በአገልግሎት የሚሉትን በማንሳት ተከታይ የሕግ ጣጣዎችን ቃኝተናል፡፡

በዚህ ክፍል ደግሞ ሶፍትዌርና መካነድር (website) ለማዘጋጀት የሚደረጉ ስምምነቶችን በተጨማሪ አስረጅነት በማቅረብ የጉዳዩን አሳሳቢነት ለመንግሥት፣ የሕጉን ጎዶሎነት በመረዳት የዘርፉ ተዋናዮች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው፣ የሕግ ባለሙያዎችም ቢሆኑ ትኩረት እንዲያደርጉ መጠየቅ ነው፡፡ 

ሶፍትዌር የመጻፍ ውል

አንድ ድርጅት ወይም ሰው የተለያዩ ዓላማዎችን ለማሳካት ሲሉ ሶፍትዌር መጠቀም ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የፈላጊውን ሰው ወይም ድርጅት ዓላማ ማሳካት የሚችል ሶፍተዌርን በተለያዩ ዘዴዎች ማግኘት ይቻላል፡፡

የመጀመሪው አማራጭ ድርጅቱ ለሚፈልገው ዓላማ የሚስማማ፣ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ገበያ ላይ የዋለ፣ ሶፍትዌር ካለ እሱን ገዝቶ መጠቀም ነው፡፡ ይሁን እንጂ የግዥ ሁኔታው የራሱ ልዩ ጠባይ አለው፡፡ ይኼውም የሚገዛው ነገር የንብረትነት ዕውቅናው የሚቀዳው ከቅጅ መብት ስለሆነ ሶፍትዌርን መግዛት ማለት ለመጠቀም ፈቃድ ማግኘት ማለት እንጂ ግዙፋዊ ሀልዎት እንዳለው ሸቀጥ የሚመሳሰል ካለመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ንብረት ቢሆን የተገዛውን ነገር ወደ ገዢው እጅ ከተዛወረ ጀምሮ ገዥው እንዳሻው ያለ ማንም ከልካይ መጠቀም ይችላል፡፡ ሶፍትዌር ሲሆን ግን ለመጠቀም ፈቃድ መስጠት ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ አንድ ሰው ፈቃድ ማግኘትም ሌላው እንዳይጠቀም አይከለክለውም፡፡  የሆነ ሆኖ ቀድሞ የተዘጋጀ ስለሆነ እንደማንኛውም ሸቀጥ ከመደርደሪያ ላይ አንስቶ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሶፍትዌርን በመግዛት ጥቅም ላይ በሚውልበት ጊዜ በሻጩና በገዥው መካከል የተከናወነው ሽያጭ ከዕቃ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡

ሁለተኛው አማራጭ ሶፍትዌር ማዘጋጀት ሙያቸው የሆኑ ድርጅቶች ተጠቃሚው ማንም ይሁን ማን፣ የአገልግሎት ዓይነቱ ተመሳሳይ ለሆነ ዓላማዎች እንዲውሉ ታስቦ የሚዘጋጁ “ስታንዳርድ’’ ሶፍትዌሮችን በመግዛት ነገር ግን እንደገዥው ድርጅት ባህርይ የሚስተካከሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ‘’ስታንዳርድ” ሶፍትዌሮችን በማዘጋጀት እንደተጠቃሚው ድርጅት ነባራዊ ሁኔታ ይስተካከላሉ፡፡ ለምሳሌ ለዩኒቨርሲቲ የተማሪዎችን መረጃ የሚይዝና የፈተና ውጤቶች የሚያሰላ ሶፍትዌር ሬጅስትራር ጽሕፈት ቤቱ ቢፈልግ አስቀድሞ ለዚህ ዓላማ የተሠራን መግዛት ይችላል፡፡ ነገር ግን እንደ ዩኒቨርሲቲው ነባራዊ ሁኔታ መስተካከል ይፈልጋል፡፡

ሦስተኛው አማራጭ ሶፍትዌር የሚሠራ (የሚጽፍ) ባለሙያ በመቅጠር ነው፡፡ እንደማንኛውም ሠራተኛ ተቀጥሮ፣ በቅጥር ውሉ ላይ የተገለጸውን ተግባር የሚፈጽም ሶፍትዌር እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ ምናልባት ለእንዲህ ዓይነቱ ሥራ የሚቀጠር ሰው ውሉ ዘርዘር ያለ ሠርቶ (ጽፎ) ሲጨርስ ሶፍትዌሩን እውን ያደረገውን ወይም ሶፍትዌሩ የተጻፈበትን ቋንቋ (source code) ለአሠሪው እንዲያስረክብ በማድረግና ማሻሻል ሲፈለግ ለማበልጸግ እንዲመች የሚያስችል ውል ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል፡፡

የሆነው ሆኖ አሠሪው የሚፈልገውን ግልጋሎት ማከናወን (ማቀላጠፍ) የሚችል ሶፍትዌር የሚሠራ ሰው በመቅጠርም ማግኘት ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው አንድ ቁምነገር አለ፡፡ ይኼውም አንድ ሶፍትዌር ለማዘጋጀት አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ተግባራት ያሉ መሆናቸው ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እነዚህ ተግባራት በአንድ ሰው ሊፈጸሙ የሚችሉ አይደሉም፡፡

አስቀድሞ ሶፍትዌር እንዲዘጋጅለት የተፈለገውን አሠራሩን አጥንቶ፣ ተንትኖ፣ እንዴት ሥርዓቱን አንጥሮ ማውጣት ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሆስፒታል የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት ለማስተዳደር የሚያገልግል ሶፍትዌር መሥራት ቢፈለግ አስቀድሞ አንድ ታካሚ ወደ ሆስፒታሉ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ታክሞ እስኪሄድ ድረስ ያለውን አሠራር በሙሉ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ካርድ የሚቆርጠው፣ ሐኪሙ፣ የላቦራቶሪ ሠራተኛው፣ ክሊኒካል ፋርማሲስቱ ወዘተ የሚያደርጉትን በቅድም ተከተልም የእርስ በርስም ወደፊትም ወደ ኋላም ሊኖራቸው የሚችለውን ግንኙነት በሙሉ አጥንቶ ማቅረብ የሚችል ሰው ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ሌላው አሠራርና ሥርዓት መተንተን ብሎም ዲዛይን ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህንን ሪፖርት አጥንቶ ለዚህ የሚሆን “አልጎሪዝም” የሚሠራ ሰውም አስፈላጊ ነው፡፡ ማለትም አንድ የሕንፃ ዲዛይን ማዘጋጅት እንደማለት ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የተዘጋጀውን ፕላን (አልጎሪዝም) መሠረት በማድረግ ሶፍትዌር የሚጽፍ ወይም ፕሮግራመር ያስፈልጋል፡፡ ይኼ የሕንፃውን ዲዛይን እያነበበ ሕንፃውን እንደሚሠራው ግንበኛ ወይም አናጺ ወይም የቧንቧ ሠራተኛ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ ሦስት የተለያዩ ዋና ዋና ተግባራት ይከናወናሉ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ጎበዝ ፕሮግራመር ሆኖ ነገር ግን ጎበዝ አሠራርና ሥርዓት የሚተነትንና ዲዛይን ሰው ላይሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም በአገራችንም ሶፍትዌር ለማጻፍ ሰው የሚቀጥሩ ድርጅቶች ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ሰዎችን በመቅጠር አለበለዚያም አንድም ሰውም ቢሆን እንኳን ዋና ዋና ተግባራቱን ማከናወን እንደሚያስፈልግ መገንዝብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጥናት ከማከናወን ጀምሮ ሶፍትዌሩን በማለማመድ ጉድለቶቹን በማስተካከል የተፈለገውን ተግባር ሙሉ በሙሉ ማከናወን እስከሚችል ድረስ የድርጅቱንና የተቀጠረውን ሰው ተባብሮ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም ውሉ ሲዘጋጅ የሁለቱን ትብብር በግዴታ መልክ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡

እንግዲህ ወደ ዝርዝር መግባት ያስፈለገው ሶፍትዌር የሚጽፍ ሰውን ለመቅጠር ውል እንዲያዘጋጅ የተጠየቀ ባለሙያም ሆነ ቀጣሪው ራሱ ከግምት ማስገባት የሚኖርበት በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ለማስታወስ ነው፡፡ በተጨማሪም በአንድ ድርጅት ተቀጥሮ ሶፍትዌር የሠራ ሰው ሠርቶ ሲያጠናቅቅ የሶፍትዌሩ ባለቤትነት ጉዳይም እንዲሁ በውሉ መካተት ካለባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ አንድ ድርጅት በርካታ ገንዘብ ከፍሎ ያሠራውን ባለሙያው ለተመሳሳይ ድርጅቶች እንዳሻው አሳልፎ መስጠት አይገባውም፡፡

ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል አንድ በአሠራሩ ሁኔታው የተማረረ የሆቴል ባለቤት  የሰው ኃይሉን፣ ንብረቱን፣ ፋይናንሱን፣ የግዥ ሥርዓቱን የምግብ፣ የመጠጥ፣ የመኝታ አግልግሎቱን ወዘተ በሙሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስተዳደር በመወሰን ለዚሁ አገልግሎት የሚውል ሶፍትዌር ከፍ ያለ ገንዘብ ክፍሎ አሠራ እንበል፡፡ ከዚያም በርካታ አላስፈላጊ ብክነቶችን በመቀነስ አሠራሩን በማቀላጠፉ የሆቴል አገልግሎቱን በማሻሻሉ ገቢው ጨመረ፡፡

ሆቴሉ በርካታ ገንዘብ ከፍሎት ለሆቴል ብቻ የሚውል ሶፍትዌር የሠራው ባለሙያ፣ ይህንን ሶፍትዌር ለሌሎች ሆቴሎች በአንፃራዊነት በዝቅተኛ ዋጋ በመሸጥ ከፍ ያለ ጥቅም ማግኘት ጀመረ እንበል፡፡ ጥያቄው ይህ ባለሙያ ተከፍሎት የሠራውን ሶፍትዌር ለሌላ ሆቴል መሸጥ ይችላል ወይ ነው? በሌላ አገላለጽ እንዲህ እንዳያደርግስ የሚከለከል ሕግ አለን?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በአንድ በኩል ወደ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጁ በማማተር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ንግድ ሕጉ በመጓዝ መፍትሔ ለማግኘት እንሞክር፡፡ ወደ ቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ቁጥር 410/1994 ስንመጣ ለያዝነው ጉዳይ በመፍትሔነት ሊያገልግል የሚችል ድንጋጌ የምናገኘው አንቀጽ 21 (4) ነው፡፡ የኮምፒውተር ፕሮግራምን በሚመለከት የሥራ አመንጭው (author) የሚባለው ፕሮግራሙን የጻፈው ሰው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ባለቤትነትን በሚመለከት ግን የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 21 (4) “አንድ ሥራ በተቀጠረ ወይም የአገልግሎት ክፍያ በተከፈለው ሰው የተሠራ ሲሆን፣ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለ በቀር የኢኮኖሚያዊ መብቶች የመጀመሪያው ባለቤት ቀጣሪው ወይም ሥራውን እንዲሠራ ያደረገው ሰው ይሆናል፤” በማለት ተገልጿል፡፡

ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ቀጥሮ ሶፍትዌር ያሠራው ሆቴል እስካልተስማማ ድረስ ሶፍትዌሩን ተቀጥሮ የሠራው ሰው ለሌላ ሆቴል እንዲጠቀሙበት ከሰጠ፣ ወይም ከሸጠ ተጠያቂ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በውል ለሶፍትዌር ባለሙያው በመሸጥና ፈቃድ በመስጠት የሠራውን የኮምፒውተር ፕሮግራም እንዲጠቀምበት ካልፈቀደ በቀር ሕጉ ከልክሏል፡፡ ብልጣብልጥ የሶፍትዌር ባለሙያዎች ውል ሲያዘጋጁ የቅጅ መብት ባለቤትነትን በውል ወደ ራሳቸው ሊያዞሩት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም የሕግ አማካሪዎችም እንደ ደንበኞቻቸው ፍላጎት ሊያማክሩ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡

ወደ ንግድ ሕጉ (Commercial Code) በምንመጣት ጊዜ የንግድ መድበል (business)  የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች መካከል ከዋናው መልካም ዝናው (good will) ቀጥሎ ካሉት ውስጥ አንዱ የቅጅ መብት እንደሆነ በአንቀጽ 127 (2) (መ) ላይ ሠፍሯል፡፡ ከላይ በምሳሌነት ወደጠቀስነው ሆቴል ስንመለስ፣ ለአንድ ሆቴል እንደ አንድ የንግድ መድበል፣ ንብረት ከሚሆኑት ነገሮች መካከል የቅጅ መብት በመሆኑ ቢያንስ ገንዘብ ከፍሎ ያሠራውን ሶፍትዌር ባለቤት ሊሆን እንደሚችል ማንም ጤናማ ሰው የሚስተው ባለመሆኑ ተቀጥሮ የሠራውን ሶፍትዌር ባለቤቱ (ከፍሎ ያሠራው ሆቴል) ሳይፈቅድለት ለሌላ ማስተላፍ ሕጋዊ መሠረት አይኖረውም፡፡ ስለሆነም ባለንብረት ስላልሆነ ራሱ የሌለውን የባለቤትነት መብት ለሌላ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡

ይሁን እንጂ በቅጂና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጁ ላይ እንደተገለጸው ለሶፍትዌር፣ ጥበቃ የሚደረገው ሶፍትዌሩ የተጻፈበት (የፕሮግራሙ ምንጭ ጽሑፍ) ብቻ ነው፡፡ የሶፍትዌር ባለሙያው ንድፉን (ዲዛይኑን/አልጎሪዝሙን) ስለሚያውቀው  እሱን በሌላ የኮምፒውተር መግባቢያ ቋንቋ ጽሑፍ ቢጽፈው ሕጉ ጎደሎ ነው፡፡ ለምሳሌ አስቀድሞ C++ በሚባል የኮምፒውተር ቋንቋ ቢጽፈውና ለሌላ ሆቴል ጃቫ በሚባለው ቢጽፈው ከውጤት አንፃር ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከቅጅ መብት አንፃር ሲታይ ሶፍትዌሩ የተዘጋጀው አንዱ በአማርኛ ቋንቋ ነው ብንል ሌላው በአፋን ኦሮሞ ነው እንደማለት ነው፡፡ የትርጉም ሥራ ነው እንዳይባልም በሕንፃ ዲዛይን ምሳሌ ብንወስደው በተመሳሳይ ዲዛይንና ፕላን አንዱ ግንበኛ ሕንፃውን በብሎኬት ቢገነባውና ሌላው ደግሞ በጡብ ቢሠራው እንደማለት ነው፡፡ በብሎኬት ከተገነባው ሳይሆን ሌላው ግንበኛ የቀዳው ዲዛይኑን አንብቦ ነገር ግን በሌላ ግብዓት መገንባቱ ነው መነሻው፡፡ ዲዛይኑን መቅዳት እስካልተከለከለ ድረስ በጡብ የሠራው በብሎኬት ከገነባው ቀድቷል የሚያሰኝ የሕግ ማዕቀፍ የለንም፡፡ ስለሆነም፣ ሕጉ ክፍተት ስላለበት እዚህም ላይ አሠሪውና ባለሙያው የሚያደርጉት ውል ነው በምትኩ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው፡፡ በሕጉ ሶፍትዌር አሠሪው ሆቴል፣ በመብትነት ዕውቅና የተሰጠው ሶፍትዌሩ የተጻፈበት ወጥ አጻጻፍ በመሆኑ ፋይዳው ዝቅተኛ ነው፡፡

ወደ ሌላ ተያያዥ ጉዳይ እንለፍ፡፡ አንድ የሶፍትዌር መሐንዲስ ለአንድ ቀጣሪ (ድርጅት ወይም ሰው) ሶፍትዌር ለመሥራት ከተቀጠረ ባለሙያው ለቀጣሪው ሙያዊ አገልግሎት እየሰጠ ነው ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ሙያው የሚጠይቀውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ ይጠበቅበታል፡፡ ይሁን እንጂ ሙያው በራሱ በፈጣን ለውጥና ዕድገት ላይ ስለሚገኝ ልክ እንደ ሕክምና፣ ሕግ፣ ሲቪል ምሕንድስና ወዘተ ነጥሮ የወጣ ሙያዊ መለኪያ ስለሌለው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚመሩበት ሕጋዊ ጥበቃና ዕውቅና የተሰጠው የሥነ ምግባር ደንብ፣ ቢያንስ በአገራችን የለም፡፡ 

የዳበረ የሥነ ምግባር ደንብ አለመኖሩ ደግሞ የዘርፉ ባለሙያዎች ለደንበኞቻቸው (ቀጣሪዎቻቸው) ሙያው በሚጠይቀው ልክ በጥንቃቄ፣ በትጋት፣ የጥቅም ግጭት ሳይፈጥሩ፣ ምስጢር ጠብቀው ወዘተ ኃላፊነታቸውን ስለመወጣታቸው የሚለኩበት፣ የሚረጋገጥበት ሁኔታ ይጎድለናል፡፡ ይኼ በበኩል የሚያስከትለው ሌላ ጣጣ አለ፡፡

የሶፍትዌር መሐንዲሱ ሠርቶ ያስረከበው የኮምፒውተር ፕሮግራም እንከን ኖሮበት የአሠራውን ድርጅትና ደንበኞቹን ለጉዳት ቢዳርግ አንድም የሙያ ጥፋት በመፈጸሙ፣ አንድም በውሉ መሠረት ግዴታውን ባለመወጣቱ ኃላፊነትን ሊወጣበት ይችላል፡፡ ይሁን የሙያ ጥፋት የሚባል ከሆነ የተጠያቂነቱ መነሻ ከውል የሚመጣ ኃላፊነት ይሆንና ጉዳዩ በፍትሐ ብሔር ሕጉ አንቀጽ 2031 አማካይነት እልባት ሊያገኝ ይችላል፡፡ ስለዚህ በሶፍትዌር ምሕንድስና ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች ማኅበር በመመሥረት ሙያው የሚፈልገውን የሥነ ምግባር ደንብም ማሳደግና ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኼ ለሙያውም፣ ለባለሙያውም፣ ለተገልጋዩም የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡

መካነድር (website) የመሥራት ውል

መካነድር የመሥራት ውልም ሶፍትዌር ከማዘጋጀት ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ነገር ግን መካነድር የራሱ የተለዩ ገጽታዎችና ስላሉት ከባለሙያው የሚጠበቁ ተጨማሪ ኃላፊነት ይኖሩታል፡፡ ስለሆነም በባለሙያውና በአሠሪው መካከል እነዚህን ልዩ ገጽታና ተግባራት ከግምት ውስጥ ያስገባ ውል እንዲደረግ ይጠበቃል፡፡

አሁን ላይ በርካታ የመንግሥት ተቋማት፣ የግል ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች ወዘተ መካነድር አላቸው፡፡ ባለሙያ በመቅጠርም አሠርተዋል፡፡ እያሠሩም ነው፡፡ ጸሐፊው ከጠየቃቸው አሠሪዎችና ባለሙያዎች መረዳት የቻለው ሁለት ዓይነት ስምምነቶች የተለመዱ መሆናቸውን ነው፡፡ የመጀመሪያው በአሠሪውና በባለሙያው ትውውቅና ቀረቤታ ላይ የተመረኮዘ በአመኔታ ብቻ አሠሪው የሆነ መጠን ያለውን ገንዘብ ሊከፍለው ባለሙያው ደግሞ መካነድር ሠርቶ እንደሚሰጠው የሚያደርጉት የቃል ስምምነት ነው፡፡ ዝርዝር ነገር አይኖረውም፡፡

ሁለተኛው ደግሞ በጽሑፍ ውል ያላቸው ናቸው፡፡ ውሎቹ ጠቅለል ያሉ ናቸው፡፡ በጥቅሉ “መካነድር ለማዘጋጀት የተደረገ ውል” በሚል የባለሙያውን ግዴታ በሚመለከት ሠርቶ የማስረከቢያውን ጊዜ ስለአጠቃቀሙ ሥልጠና መስጠትን የመሳሰሉ ጥቂት ግዴታዎችን ብቻ የያዙ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ መካነድር ለመሥራት የሚደረግ ውል ባለሙያው ላይ በርከት ያሉ ግዴታዎችን የሚጥል መሆን አለበት፡፡

በአግባቡ ባልተዘጋጀ ውልና ባለሙያው ላይ ግዴታ በመጣል መፈጸም እየተገባው ይህ ሳይሆን በመቅረቱ እንዲሁም ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ባለመሆናቸው የብዙ ድርጅት መካነድሮች ተዘግተዋል፡፡ ከእንደገና ለሌላ ወጭም የተዳረጉ አሉ፡፡  በመሆኑም መካነድር የማዘጋጀት ውልም ቢያንስ የሚከተሉትን ተግባራት ማን እንደሚከናውናቸው የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡ 

መካነድሩ ምን ምን ማካተት (መያዝ) እንዳለበት መወሰን፣ ዲዛይን ማዘጋጀት፣ ልክ እንደንግድ ድርጅት ስም (trade name) ስሙን (domain name) ማስመዝገብ፣ ይዘቱን (ማውጫውን) መወሰን፣ አስፈላጊ የሆነ ሰነዶችን፣ ምስሎችን፣ ቪዲዮና ድምፅ፣ ወዘተ መጫን እንዲሁም የመካነድሩን መረጃዎችን በማስቀመጥ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ በሚያደርግ ድርጅት አማካይነት ለተፈለገው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ (hosting)፣ መካነድሩን መከታተልና ማሻሻልን የመሳሰሉ ጉዳዮች በውል መቋጨት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የመካነድሩን መረጃ በማስቀመጥ ለአገልግሎት ዝግጁ (ሆስት) የሚያደርጉ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሉም፡፡ በውጭ ምንዛሪ በየዓመቱ እየከፈሉ ይህን አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ጋር በመስማማት ይህንን መፈጸምና መከታተል የማን ግዴታ እንደሆነ፣ መካነድሩን ማሻሻል ቢያስፈልግ አስቀድሞ የተዘጋጀበትን ጽሑፍ (source code) ለአሠሪው መስጠትም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህንን የመስጠት ግዴታ የባለሙያው መሆን አለበት፡፡

በአጭሩ መካነድር ማሠራትና የሠራው ባለሙያ እስካለና እስከወደደ ድረስ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችሉ ስምምነቶች ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ካልሆነ ለብዙ ዘመናት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ መካነድሮች ባለሙያው ቢሞት ወይም በማናቸውም ሁኔታ ድርጅቱ የባለሙያውን እገዛ ማግኘት ሳይችል ቢቀር መካነድሩን ማሻሻል ሊያዳግት (ላይችል) ወይም ሊዘጋበት ሁሉ ይችላል፡፡

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም የውሉ ጉዳይ በማድረግ የሚፈጸሙ ውሎችን ፈር የሚያሲዝ ሕግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህና ባለፈው ሳምንት በቀረበው ጽሑፍ ለመዳሰስ የተሞከረው የውሎቹ ውስብስብ በመሆናቸው፣ በመደበኛውና በጥቅል የውል መርሖች ብቻ የሚተዳደር አለመሆኑን የተለያዩ ሁነቶችንና አጨቃጫቂ ሊሆኑ የሚችሉ ጭብጦችን በማንሳት አሳሳቢነቱን ማሳየት ነው፡፡ ምናልባትም ውሎቹን የሶፍትዌር ባለሙያዎቹ ብቻ ሊረዷቸው በሚችሉበት መልኩ በማዘጋጀት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመግዛት (ፈቃድ በማግኘት) የሚጠቀሙ ተዋዋይ ወገኖች ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቅም በሚያስገኝ መልኩ ግንኙነት በመፍጠር ወደ ፊት በኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ቀውስ ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡ 

እንዲህ ዓይነት ችግር ተከስቶ ማስተካከል አዳጋች ከመሆኑ በፊት ቀድሞ ደንብና ሥርዓት ማበጀት የአባት ነው፡፡ የሕግም መኖር አስፈላጊነት ለዚህ ነው፡፡ ካልሆነ በመንግሥትም በተጠቃሚም ላይ፣ በተወሰነ መልኩ ደግሞ በዘርፉ ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰውን ችግር ዳግም ማስተካከል የማንችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለሆንም ጆሮ ያለው ይስማ!

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...