Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሜቴክ ነገርና መንግሥታዊ አድርባይነት

የሜቴክ ነገርና መንግሥታዊ አድርባይነት

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ምንም ሆነ ምን “ያለፈው አለፈ“ የሚል አባባል ችግሩን አይገልጸውም፡፡ እጅግ አሳፋሪና እውነትም ቆሻሻ ድርጊት በአገር ላይ መፈጸሙንም መካድ አልተቻለም፡፡ እንኳንስ ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርና ቤተሰቦቻቸውን ሳይቀር በማይወክሉ ጥቂት ስግብግቦች እጅግ ግዙፍ የሚባል የደሃ ሕዝብ ሀብት መመዝበሩን፣ ሕዝቡ መናገርና መጮህ ከጀመረ ዓመታትም ተቆጥሮ ነበር፡፡ እኔም በግሌ በዚህ ጋዜጣ መራር የፀረ ሙስና ትግል እንደሚያስፈልግ የውስጥ አዋቂ መረጃዎችን እያጣቀስኩ ለማቅረብ ሞክሬያለሁ፡፡ ያለፈው ጊዜ ሰሚ ባያገኝም ይህን የሚያሳፍር ሌብነት መንግሥትና ሕግ በያዙት መንገድ አጣርተው ወንጀለኞችን በፍርድ አደባባይ ከማቅረብ ባሻገር፣ የተመዘበረውን የአገር ሀብትም እንደሚያስመልስ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

 ለዛሬ ሐሳቤን እንድገልጽ ያደረገኝ ግን የሌብነቱን ችግር መንግሥታዊው አድርባይነት ምን ያህል ተክኖት እንደዘለቀ በግሌ ከነበረኝ ልምድ አንፃር ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት በወሳኝ አመራር ቦታና በሙያችንም ቁልፍ ቦታ” ላይ ተጎልተን፣ የሚታገሉ ሰዎችን እንኳን ሳናዳምጥ ጥቂት አታላዮችን አምነን በአድርባይነት ያሳለፍነውን ጊዜ ሳስታውስ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ በየብሔራዊ ድርጅቱ ጠንካራ የለውጥ ኃይል ከመምጣቱ በፊት፣ ለሕወሓት የበላይነትም“ ሆነ ለዘራፊው ቡድን ሕገወጥነት አመቺ የሆነ አድርባይነት ያነገሡብን ጥገኞች ሳስብ፣ ባሳለፍኩት ጊዜ ሁሉ በእጅጉ እፀፀታለሁ፡፡ በእውነቱ ከልብ የፖለቲካ ንሰሐ እንድገባ የሚያደርገኝም ይኼው ነው፡፡

 ከዚህ ቀደም ሕዝቡ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ፓርላማውና የተሃድሶው ኢሕአዴግ  ሲታገሉ ቢቆዩም፣ መንግሥት ዘግይቶ ይፋ እንዳደረገው የተወሰኑ የሜቴክ አመራሮች የከፋ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ አገሪቱን ቢሊዮን ዶላሮችን ከማዘረፍ በላይ ሕዝብ በጥቂቶች እንዲበዘበዝ፣ ኢፍትሐዊነት እንዲነግሥ፣ መንግሥትና ሥርዓቱ በሕዝብ እንዲጠሉ አድርገዋል፡፡ በተለይ በሕዝብ ስም ነግደዋል፡፡ በመሠረቱ ግን አሁን ይፋ ለሆነው አስከፊ ውጤት ሁሉ ከላይ እስከ ታች የነበረው የሁላችንም አድርባይነት ዋነኛው መንስዔ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በነበርኩበት ጊዜ ለአዲስ ከተማ አውቶብስ አገልግሎት ድርጅት ሳያምኑበት በጫና በመመደብ፣ በመሬት አሰጣጥ ብልሽት፣ በኢፍትሐዊነት በሚካሄድ ጨረታ፣ ብሎም በሕገወጥ መንገድ ለተደራጁ የጥቃቅን አንቀሳቃሾች ኢፍትሐዊ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ ወዘተ. በተወሰኑ የሜቴክ ኃላፊዎች ቀጥታ የስልክና የመልዕክት ትዕዛዝ ጉዳይ ሲያስፈጽሙ የነበሩ የቀድሞዎቹን  ከንቲባዎች  ጨምሮ፣  ከፍተኛ  የብአዴን አመራሮችና የሕወሓት ካድሬዎች ነበሩ፡፡ እኛም በዝምታና በእሽታ ማለፋችን ሊካድ የማይችል የአደባባይ የመንግሥት ኑዛዜ ሆኗል፡፡ የማይቆጨኝ ግን ከሁለት ዓመት ወዲህ በተካሄደው የተሃድሶ መድረክ ሁሉ፣ ሕዝብ እያነሳ ያለውን በደልና የዘረፋ መረጃ በማጋለጥና ሊያባላን ነው የሚል ጩኸት ሳናሰማ አለማለፋችን ነበር፡፡ በዚያም ጊዜ የማንም የበላይነት የለም፣ ዘረፋም አልተፈጸመም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአገሩ አልታየም ሲሉ ያፍኑ የነበሩት እነኚሁ የበታች አመራሮችና አድርባዮች ነበሩ፡፡

በሌላ ምሳሌ ለማዳበርም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበርኩበት ጊዜ  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ግምገማ ላይ ተመሥርቶ አንድ ጎበዝ ጋዜጠኛ  በሜቴክ ላይ ጠንከር ያለ ምርመራ ይጀምራል፡፡ ግኝቱም የፕሮጀክት መዘግየት፣ የሀብት ብክነት፣ ለጥቂቶች ያለጨረታ ኮንትራት መስጠት (አሁን ስንሰማ እስከ 37 ቢሊዮን ብር ይደርሳል አሉ!! እግዚኦ ነው)፣ በትልልቅ ኢንዱስትሪዎች የአንድ ብሔር አባላትን በገፍ መሰግሰግ፣ የከተማ አውቶብሶች ከተቀመጠላቸው ጊዜ ባነሰ መበላሸትና የጥራት ችግር፣ የአመራሩ ንፋስ አመጣሽ ረብጣ ሀብት መታየትን፣ ወዘተ. የሚዳስስና ተከታታይ ዘገባ የሚቀርብበት ነበር፡፡

 እኛ ደግሞ፣ “በል ቀጥል በርታ” ስንል ቆየንና የሁለት ከፍተኛ መኮንኖች ስልክ ከቁጣ ጋር እንደ በረዶ ሲወርድብን የኤዲቶሪያል አባላትን ፀጥ አሰኝቶን፣ ጋዜጠኛውም አደብ እንዲይዝ አደረግን፡፡ ለነገሩ በወቅቱ በድርጅቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አማካይነት “ይህ ጉዳይ ቆሞ ሌላ አቅጣጫ ይያዝ” በሚል  ትዕዛዝ የሜቴክን “ስኬት”  እየፈላለግን ጋዜጣውን መሙላት ተያያዝነው፡፡ እንግዲህ ለእነዚህ ሰዎች ማናለብኝነትና በእብሪት ላይ የተሞላ ዘረፋ የሁላችንም አድርባይነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው ለማለት የምወደው ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ሳናውቅ በስህተት ብቻ ሳይሆን፣ እያወቅን በቸልተኝነትና በፍርኃት የለውጡን ጊዜ ጎትተናል፡፡ አገር እንድትጎዳም አድርገናል የሚል ፀፀት ይሰማኛል፡፡  

ሌላው አስተማሪው ነገር ግን የሌብነትና የብልሹ አስተዳደር እናቱም፣ አባቱም፣ አድርባይነት የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ ያለፈውን ሕግና ታሪክ የሚፈርደው ሆኖ፣ አሁን በአዲሱ ለውጥ ወቅትም አምርረን ልንዋጋውና ልንታገለው የሚገባው ይህንኑ በሽታ ሊሆን ይገባል፡፡

 ‹‹አድርባይነት›› የተባለውን ጽንሰ ሐሳብ በግልጽና በጥልቀት በተለያዩ አደረጃጀቶቻችን አማካይነት ልንገነዘበው ይገባል፡፡ በእከክልኝ ልከክልህ፣ በጥቅምና በድርጅት አባልነት ስም እየተሳሳቡ ጥሩ ጥሩውን ውጤት ወደ ራሳቸው እየሳቡና ጥፋት ሲገኝ በሌላው ላይ እያሳበቡ፣ ምንም ሳይሠሩ እየደለቡ እንዲኖሩ መፍቀድ እንደ ማለት ሲሆን፣ ያለፍንበትን አስከፊ ጊዜ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡

አድርባይነት የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ የግል ጥቅምና ዓላማን ለማስቀደም የሚደረግ የፖለቲካ አቋምን ያመለክታል፡፡ ጥቅም የሚያስገኝ እስከሆነ ድረስ ማንኛውንም አቋም ለማራመድ (ለመደገፍ) ቆርጦ መነሳትን፣ ለግምገማም ሆነ ለሕጋዊ ተጠያቂነት ንቀት ማሳየትን፣ የሕዝብን ውክልናና ሥልጣን አሳንሶ ማየትን፣ ዓይንን በጨው አጥቦ ለጥቅም ሲሉ ብቻ የድርጅቱን ራዕይ፣ መመርያና ደንብ፣ የሕዝብን ትዝብትና እምነትን ጭምር ጨፈላልቆ ለመሄድ ያለንን ውስጣዊ የፀባይ (የባህሪ) ዝግጁነት የሚያሳይ ክፉ አመለካከት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዘርና በጎጥ ላይ የተመሠረተው መፈላለግ (እንደ ሌብነት ዋሻ ስለሚያገለግል) በእሳት ላይ ነዳጅ እየሆነ ሲያጋየው ከርሟል፡፡

ይህን ለማለት ያነሳሳኝ ዛሬ ጉዱ የወጣው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ ከላይ እስከ ታች ባለው የኢሕአዴግ አመራር የሚነሳ ሐሜትና ሹክሹክታ ነበር፡፡ ቀዳሚው የተሰጠው ሥራና የተመደበው በጀት በሚሊተሪ አመራር ሊመራ የማይችል መሆኑ፣ መከላከያ በባህሪ ወጪና ገቢው ይፋ ስለማይደረግ ይህ ግዙፍ ተቋም ሲጨመርለትም ያለ ጥርጥር ዘረፋ እንደሚባባስ፣ በውስጡ ያሉ አብዛኞቹ አመራሮችም ነባር ታጋዮችና ከፍተኛ መኮንኖች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ በታሪክ አጋጣሚ የአንድ ብሔር ተወላጆች የሚበዙበት መሆናቸው ግልጽነትና ተጠያቂነትን እንደሚገድብ ሁሉ ይነሳ ነበር፡፡

 ይህን ሁሉ ሥጋት ግን ማረም ሳይችል ‘ቲም ለማ’ እና የለውጥ ኃይሉ እስከሚመጣ ድረስ አድርባይነትና የትግል መላላት አዳፍኖት ይኼ ሁሉ ጥፋት ደረሰ፡፡ ነገሩ የሞኝነትና አጉል በፍረኃት ለራስ የማድላት ውዳቂነት ጉዳይ ሆኖ እንጂ፣ ይህን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ (አቶ ኃይለ ማርያም) ጀምሮ የሚታወቅ ውንብድና፣ ጥቂቶች በሕዝብ ስም እየዘረፉ በሕዝብ ሀብት ሲያላግጡ ዝምታ መንገሡ አገር እንደ መበተን የሚቆጠር አስከፊ ድርጊት ነበር፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ በዚያ መዘዝ በብዙ አገሮች እንደታየው ‹‹የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፣ የአውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጂ›› እያልን እርስ በርስ ከመጨካከንና ከመተራረድ በቀር የሚተርፈን ነገር አይኖርም ነበር፡፡

በመሠረቱ አድርባይነት የሰብዕና ምስክር ነው፡፡ የአመለካከት ችግር ነው፡፡ የሰዎች ሰብዕናና አመለካከት የሚቀረፀው ደግሞ እንደ ወጡበት ቤተሰብና እንደ አደጉበት ማኅበረሰብ ነው፡፡ ሌብነትን ከሚፀየፍ ቤተሰብና ማኅበረሰብ የተገኘ ሰው ሌብነት ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ወይም የመግባት ዕድሉ በጣም ጠባብ ነው፡፡ በበታችነትና በተበደልኩ ስሜት ሲቆጭ ያደገ፣  በስግብግብነትና በአልጠግብ ባይነት የተመረዘ የፈለገውን ያህል ቢምል ቢገዘት ሕዝብ እየበደለ መዝረፍና የራሴ የሚለውን ጥገኛ ከማደለብ አይቦዝንም፡፡ ዛሬም ሆነ ትናንት ብዝበዛ የሚመነጨውም እንዲህ ካለው ወረርሽኝ ነው፡፡

በሌላ በኩል ለሌብነት ዋነኛው ማዳበሪያ የሆነው አድርባይነትን ከሚያስፋፉ ባህሪያት አንዱ ስኬታማ የመሆን ጥማት ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ተሽሎ የመገኘት፣ የማሸነፍ፣ በውጤት፣ በዝና፣ በሀብት፣ ወዘተ. በልጦ የመገኘት (‹‹ወንዳታ›› የመባል) ውስጣዊ ፍላጎት ነው፡፡ ይህን ፍላጎት ለማርካት (ከግብ ለማድረስ) ሰውዬው ሥልጣኑንና የተገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም እስከ የትኛውም ጫፍ ድረስ ይጓዛል፡፡ ከድርጅቱ (ከፓርቲው) እና ከሚሠራበት ተቋም መርሆች ጋር ፈጽሞ የማይጣጣሙ ዘዴዎችን (አሠራሮችን) እየተጠቀመና ጉሮሮ ለጉሮሮ እየተናነቀ ይሟሟታል፡፡ ይህ ደግሞ ለአድርባይነት ይዳርገዋል፡፡

ለአድርባይነት ከሚዳርጉ ምክንያቶች ሌላኛው የሰው ልጅ በውስጡ ያለው የሥጋት ተፈጥሮ ነው፡፡ ለትንሹም ለትልቁም መሥጋት ይወዳል፡፡ በሰላም አገር ‹‹ይገመግሙኝ ይሆን? ከደረጃ ዝቅ ያደርጉኝ ይሆን? ይጠረጥሩኝ ይሆን?  ከቤተሰቤ ወደራቀ ቦታ ያዛውሩኝ ይሆን? ያባርሩኝ ይሆን? ዕድገት ይከለክሉኝ ይሆን? እያለ ይጨናነቃል፡፡ ከዚያች ከያዛት ቦታ ቢለቅ ወይም ከዚያ መሥርያ ቤት ቢወጣ ሰማይ የሚደፋበት ይመስለዋል፡፡ በራስ መተማመኑ ብን ብሎ ይጠፋበታል፡፡ ስለዚህ ሕዝብ የጣለበትን አደራና ተቋሙ የሰጠውን ኃላፊነት እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ይጠቅመኛል ብሎ ለሚገምተው አለቃው ሽቁጥቁጥ አሽከር (ባሪያ) ሆኖ ያርፈዋል፡፡

ይህ ጥገኛ፣ ሐሳብ አመንጭነትና ተነሳሽነት የጎደለው አስመሳይ ሌላ ሆኖ ይቀራል፡፡ ለድርጅቱም (ለተቋሙ) ሳይጠቅም ሕዝቡ የጣለበትን አደራ ሳይፈጽም የትውልድ መዛበቻና የዘመን መሳለቂያ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ አድርባይነት የሚያስገኘውን ጥቅም ከፍ አድርጎ የማሰብ አመለካከት ነው፡፡ ድርጅቱ ቢያባርረኝ፣ ሕዝቡ ቢታዘበኝ፣ ሕግ ያለውን ቢለኝ አድርባይ ሆኜ አንድ ዝግ ከዘጋሁ ይካካስልኛል፡፡ የተቀጣሁትን ሁሉ ያህል ብቀጣ በአድርባይነቴ ባገኘሁት ጥቅም እቀጥላለሁ የሚል መሰለብ የሚፈጥረው ነው፡፡ ዛሬ እየተሰማ እንዳለው ወንጀልና በትውልድ ዘንድ መወቀስ ግን ሁሉም ነገር ቢቀር በእጅጉ የተሻለ ነው ባይ ነኝ፡፡  

ሌላው የአድርባይነትን ፀባይ ከሚያበረታቱ ነገሮች መካከል መነሳት ያለበት የሰውዬው ወይም የዚያ ቡድን (ሜቴክን መንካት እንደ ፈጣሪ የተፈራበት የአመራሩ ለአገር ደኅንነት የሚጠቅም ሀብት እንደሚያንቀሳቅስና የበላይ አመራሩ ጭምር መሸፈኛ ስለነበረ ነው) የሥልጣን መጠን ነው፡፡ ሥልጣን ሲበዛ ብቻ ሳይሆን ካልተጠነቀቁ ሁሌም በሌብነት ይጋብዛል፡፡ ፍፁማዊ ሥልጣን ደግሞ ለፍፁማዊ ፅፈትና ዓይን ላወጣ አድርባይነት ይዳርጋል፡፡ ሰውዬው ከፍ ያለ ሥልጣን ያለው ከሆነ ተቆጣጣሪ ስለሌለበት፣ ያገኘውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ለግል ጥቅሙ የሚያውልበት ሰፊ ዕድል አለው፡፡

የሌብነት እናት ለሆነው አድርባይነት መኖር በር የሚከፍተው ሌላው አመለካከት ደግሞ ‹‹እኔ ባላደርገው ሌላው ያደርገዋል. . . ስለዚህ ለምን እኔ አላደርገውም?›› የሚለው ነው፡፡ ‹‹ሌላው መጥቶ አጋጣሚውን ለራሱ ጥቅም የሚያውለው ከሆነ፣ እኔስ እጄ ባለው አጋጣሚ ብጠቀም ኃጢያቴ ምኑ ላይ ነው?›› ብሎ ያስባል፡፡ ከዚያም የበላይ አለቆቹን ያያል፡፡ ሁሉም በአድርባይነት በሽታ የተለከፉ ይሆኑበታል፡፡ ያላቸውን ቤት፣ መሬት፣ መኪና፣ ኢንቨስትመንት፣ የአኗኗር ሁኔታ፣ ወዘተ. ሲመለከት እኔስ ከማን አንሳለሁ ይላል፡፡ እንግዲህ ለወደፊቱም ትግሉ እዚህ ላይ ነው፡፡ እንኳንስ ዘረፋና የመንግሥት አመራርነት፣ በንግድም ሆነ በኢንቨስትመንት ስም ሀብት ማጋበስና የሕዝብ ሥልጣን አብረው ሊሄዱ የማይችሉ መሆን አለባቸው፡፡  

 በመሠረቱ አድርባይ በበዛበት ድርጅት ውስጥ ሆኖ “አድርባይ አልሆንም” ማለት ይከብዳል፡፡ ሁሉም አብዶ ጨርቁን በጣለበት አገር ልብስ ለብሶ የሚሄድ ሰው ከተገኘ፣ “ዋናው ዕብድ” የሚባለው እሱ ይሆናል፡፡ ‹‹የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ›› የሚለውም የአድርባዮች መገለጫ ነው፡፡ ሰዎችን አድርባይ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ሌላው ምክንያት የመረጃ፣ የዕውቀትና የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ሰዎቹ በአድርባይ ፀባያቸው የተነሳ በፓርቲና በመንግሥት ሥራ ላይ፣ በሕዝብ ላይ፣ በአገር ላይ፣ በመጨረሻም በራሳቸውና በቤተሰባቸው ሕይወት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ካልተረዱ አድርባይ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

አንዳንዶች በዚህ ረገድ ማግኘት ያለባቸውን መረጃና ግንዛቤ እንዳያገኙ፣ ወይም የተዛባ መረጃ ሆን ተብሎ እንዲያገኙ የሚደረጉበት ሁኔታ መኖሩንም መካድ ግን አይገባም፡፡ ሲጠቃለል የሜቴክ ሲገመት የነበረ የዘረፋ ወንጀል እጅግ ገዝፎ አደባባይ ወጥቷል፡፡ ፍትሕም በሚዛናዊነት ፍርድ እንደሚሰጠው ይጠበቃል፡፡ የመጪው ጊዜ ትልቁ የቤት ሥራ ግን ተመሳሳዩን ወንጀልና ወንጀለኛ እየፈተሹ የሕዝብን ጥቅም ማስከበር፣ አሁን የተጀመረው ለውጥ ደግሞ በአድርባይነትና በበሰበሰ ንቅዘት ተቦርቡሮ አገርን እንዳይገነድስ በፅናትና ሕዝብን በማሳተፍ መታገል ሊሆን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...